
ለውጥ መሻቶችን እውን ለማድረግ በግለሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በሀገር ደረጃ የሚፈጠር መነቃቃት ነው። ስኬታማ መሆን የሚቻለውም መሻቶችን ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ እሳቤ እና በሁለንተናዊ መልኩ ከትናንቶች መፋታትን የሚጠይቅ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው።
በተለይም በአንድ ሀገር የሚከናወን የለውጥ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንዲሆን ከለውጥ መሻቶች በስተጀርባ ያሉ ገፊ ምክንያቶችን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል። ለነዚህ ምክንያቶች ታማኝ መሆን፣ ለችግሮች መፍትሔያቸውን በማፈላለግ ሂደት ውስጥም ከትናንት አብዝቶ መማርን እና ትናንቶችን ላለመድገም ከራስ ጋር መስማማትን የሚጠይቅ ነው።
ለውጥ በራሱ ከትናንቶች ለመውጣት ዛሬን በአዲስ እይታ የማየት እና ነገዎችን ብሩህ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፤ እራሱን የለውጥ ኃይል አድርጎ የሚያስብ የትኛውም ኃይል በሰከነ መንፈስ ከታሪክ መማር ይጠበቅበታል፤ የለውጥ ትርክቶቹም ትናንትን በአግባቡ የቃኙ እና ዛሬን ያስተዋሉ ሊሆኑ ይገባል።
የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት የሆኑ ሀገራት፤ በረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪካቸው ውስጥ ያሉ የከፍታ እና የዝቅታ የታሪክ ምዕራፎቻቸውን ለውጥ ሊፈጥር ከሚችለው ሞቅታ ውጪ ሆነው በሰከነ መንፈስ እና በተረጋጋ አዕምሮ ሊመለከቷቸው ይገባል። ይህን ማድረግ ተመሳሳይ ታሪክን በመድገም አዙሪት ውስጥ እንዳይገቡ ያስችላቸዋል።
አንደኛ ዓይነት ከትናንት የከፍታ ታሪክ ትርክት ቁጭት በየዘመኑ ለለውጥ የተነሳሳ ትውልድ በሚኖርባቸው ሀገራት፤ ለውጡን ስኬታማ አድርጎ የማኅበረሰቡን መሻት ተጨባጭ ለማድረግ ለታሪክ አብዝቶ ታማኝ መሆን፤ ታሪክን በራሱ ዓውድ ለዛሬ የለውጥ ጉዞ መማሪያ አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል።
ታሪክ የአንድ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሂደት ማሳያ መስታወት ነው። ከየት ተነስቶ ምን ያህል ተግዳሮቶችን ተሻግሮ አሁን ላይ እንደሚገኝ ከማሳየት ባለፈ፣ የአሁናዊ ማኅበረሰባዊ መሻቶች ታሪካዊ ዳራ ምን እንደሆነ አመላካች ነው። እንደ ማኅበረሰብ ከትናንት የተለወጠ ማንነት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም ወሳኝ አቅም ነው።
በለውጥ ወቅት የሚነሱ የለውጥ እሳቤዎች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ተግዳሮቶች በተሻለ መንገድ፣ ያለ ብዙ ያልተገባ ዋጋ ለመሻገር፤ ከታሪክ ጋር የተያያዙ ግራ መጋባቶችን እና ብዥታዎችን ማጥራት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ከታሪክ ጋር በተቃርኖ በመቆም የትኛውንም የሕዝብ ፍላጎት ለዘለቄታው ተጨባጭ ማድረግ አይቻልም።
ይህ ችግር እንደሀገር በተለያዩ ወቅቶች አጋጥሞናል። በተለይም ከሃምሳዎቹ ጀምሮ በሀገሪቱ የተስተዋሉ የለውጥ ክስተቶች፣ ሀገርን እንደሀገር ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ፣ የሕዝቡን የለውጥ መሻቶች እውን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። የትውልዶችን ተስፋ ከመናጠቅ ባለፈ የለውጥ ቁጭቶችን ተጨባጭ ማድረግ አልቻሉም።
በነዚህ ሰባት አስርተ ዓመታት ራሳቸውን የለውጥ ኃይል አድርገው ያሰለፉ ኃይሎች፣ ረጅሙን ጊዜያቸውን፣ በልዩነት ፍረጃ ውስጥ ሆነው፣ ልዩነቶችን በኃይል ለማስወገድ ያልተገባ ርቀት የሄዱበት ነው። በዚህ ሂደትም የሕዝቡ የለውጥ መንፈስ በግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎት ተጠልፎ የታየበት ሁኔታ ተስተውሏል።
ግለኝነት እና ቡድንተኝነት የፈጠረው አደጋም የሀገርን ሕልውን ስጋት ውስጥ መክተት የሚያስችል ግዝፈት ያገኘባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። በነዚህ ወቅቶች ዳተኝነት፣ ደንታ ቢስነት፣ በሕዝብ የለውጥ መሻት መቆመር፣ ከሁሉም በላይ ባንዳነት በስፋት ተስተውሏል። ከዚህም አልፎ ታሪክን የፖለቲካ ሸቀጥ ለማድረግ ረጅም ርቀት ተሄዷል።
ከሀገር እና ከሕዝብ መሻቶች ጋር ሁሌም በተቃርኖ ከሚቆሙ፣ ለዚህም ያላቸውን አቅም ሁሉ በየዘመኑ ሳይቆጥቡ ከሚንቀሳቀሱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ሳይቀር መርሕ አልባ ኅብረት ፈጥረው የቆሙ ኃይሎች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። ይህንን ሀገራዊ እርግማን ዛሬ ላይ መሻገር ካልቻልን ነገም ይኖራሉ። ሊያስከፍሉን የሚችሉትም ያልተገባ ዋጋ ከትናንት የከፋ ስለመሆን ለማሰብ የሚከብድ አይደለም።
የሕዝባችን የትናንት ሆነ የዛሬ፤ የነገም መሻት ሰላም እና ከዚህ ሰላም የሚመነጭ ልማት ነው፤ እድገት እና ብልፅግና ነው። የታሪካዊ ጠላቶቻችን የትኛውም እንቅስቃሴ ደግሞ የሕዝባችን ሰላም እና ከሰላሙ የሚመነጨውን ዘላቂ ልማት ማደናቀፍ ነው። እነዚህን ሁለት ፍላጎቶች አስታርቆ መሄድ አይቻልም። ማስኬድ ይቻላል ብሎ ማመን ባንዳነት ነው ።
የዚህ አይነቱ ክስተት በቀደመው ሀገራዊ ታሪካችን ሲከሰት የቆየ፤ አሁን ላለንበት ተጨባጭ እውነታ ያለው አበርክቶም ቀልሎ የሚታይ አይደለም ። ይህ ትውልድ እንደ ትውልድ በጀመረው የለውጥ መነሳሳት ላይ ላለፉት ሰባት ዓመታት የፈጠረው ሀገራዊ መንገጫገጭም ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሎናል ።
ይህን አይነቱን ከትናንት ያለመማር የባንዳነት የጥፋት ጉዞ መላው ሕዝባችን ሊታገሰው የሚገባ፤ አሁናዊ በሆነው የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ተዘግቶ ማለፍ ያለበት ሀገራዊ ፈተና ነው። አስተሳሰቡ ሆነ አስተሳሰቡ የሚያስከፍለው ያልተገባ ዋጋ ለሚቀጥለው ትውልድ የቤት ሥራ ሆኖ መቀጠል የለበትም። የትኛውም የተቃውሞ ሃሳብ ሆነ ከሀሳቡ የሚመነጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሀገር እና ሕዝብን አሳልፎ ለጠላት ፈቃድ የሚሰጥ ሊሆን አይገባም!
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም