
ዘመን የየራሱን በጎነት ይዞ እንደሚመጣ ሁሉ ለማኅበረሰብ ነውር የሆኑ እውነታዎችን የአደባባይ የማንነት ትርክት አድርጎ የሚመጣበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በተለይም በለውጥ ወቅት የሚፈጠሩ አለመስከኖችን እና ግራ መጋባቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ግለሰቦች እና ቡድኖች ለፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ከማኅበረሰቡ እሴቶች ፍፁም የተቃረኑ ነውሮችን የአደባባይ የድፍረት ትርክት አድርገው ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ነው።
ይህ አይነቱ የነውር መንገድ፤ መንገዱን ለመረጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አሁናዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያ አቅም መፍጠር የሚያስችል ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ቢታመንም፤ ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ለማንም ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ አይደለም። በታሪክ እና በትውልድ ፊት ተጠያቂነትን እና መቅለልን ከማስከተል ያለፈ ፋይዳም አይኖረውም።
ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ እና ለነፃነት ከሁሉም በላይ ለሀገራቸው ካላቸው ቀናዒነት አኳያ፤ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢገኙ ሀገራቸውን አሳልፈው የመስጠት የታሪክ ጥላሸት የለባቸውም፤ ከጠላት ጎን ከመሰለፍ ሕይወትን በሚጠይቅ የተጋድሎ መስክ ላይ በክብር መሞትን የሚሹ፤ ይህንንም ለትውልዶች የማንነት ግንባታ ዋነኛ እሴት አድርገው የሚወስዱ ናቸው።
በዚህ ዘመናትን በተሻገረ የማንነት ግንባታ ውስጥ ብዙዎች ከምንም በላይ ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ክብር መስዋዕት ሆነዋል። ከዚህ በተቃራኒም በክፉ ቀናት በሀገር እና በሕዝብ ላይ በአደባባይ ክህደት የፈጸሙ፤ ለግል እና ለቡድን መሻታቸው የሀገር እና የሕዝብን ክብር አሳልፈው ለጠላት የሰጡ፤ ለጠላት ያደሩ ባንዳዎች ተፈጥረው አልፈዋል፤ ዛሬም አሉ።
በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ እነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች የቱንም ያህል ለጠላት ፍላጎት ያደሩ ባንዳዎች ቢሆኑም፤ ሕዝባችን ለሀገሩ ካለው ቀናዒነት አኳያ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ከማድረግ ባለፈ፤ ሀገሩን እና ነፃነቱን ሊነጥቁት አልቻሉም። የአስተሳሰብ ነውራቸውም ለዘመናት የተጠበቀውን ሕዝቡ ስለ ሀገሩ እና ነፃነት ያለውን ቀናዒነት አላደበዘዘውም።
ይህ የአስተሳሰብ ነውር ዛሬም በመላው ሕዝባችን የሚወገዝ ነው። ሕዝባችን እንደ ሕዝብ የሚጠየፈው ክፉ ልምምድ ነው። ወደፊትም ቢሆን ሕዝባችን በሀገሩ ካለው ተስፋ እና ተስፋዎቹ ከፈጠሩት ብሩህ ነገዎች አኳያ እየተወገዘ የሚቀጥል ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። እንደሀገር የመጣንባቸው የረጅም ዘመናት ተሞክሯችንም ይህንኑ ተጨባጭ እውነታ የሚያሳዩ ናቸው።
ይህም ሆኖ ዛሬም ሕዝባችን በብዙ ተስፋ፤ ብዙ ዋጋ ከፍሎ አምጦ በወለደው ለውጥ ማግስት በዚህ ነውር አስተሳሰብ ራሳቸውን በአደባባይ የገለጹ ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንዶች ለግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎታቸው ለውጡን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም፤ ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን በሥልጣን እና ሥልጣን የፈጠረላቸውን ያልተገባ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል በዚህ የአስተሳሰብ ነውር/ባንዳነት በድፍረት አደባባዮችን ሞልተው ታይተዋል።
ለግለሰባዊ እና ለቡድናዊ ፍላጎታቸው ስኬት “ከየትኛውም አካል ጋር” ለመሥራት ዝግጁነታቸው ሲገልጡ ተሰምቷል፤ አንዳንዶች ከዝግጁነት አልፈው በተጨባጭ፤ ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ሳይቀር ኅብረት አድርገው፤ የጠላትን ዘመን ተሻጋሪ የጥፋት ሃሳቦችን ተሸክመው፤ ሀገርን እና እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ያልተገባ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል።
ይህ የአስተሳሰብ ነውር የለውጥ ወቅት ፋሽን ይመስል፤ በየለውጥ ዘመኑ የተለያየ ግጥም እና ዜማ እየወጣለት የአደባባይ የድፍረት ቋንቋ ሆኗል። የማኅበረሰባችን የለውጥ እሳቤዎች መሬት ወርደው የለውጥ ፍሬ እንዳይሆኑ ትልቅ ፈተና ከሆነም ውሎ አድሯል። የጥፋት ፖለቲካ እርሻ ከሆነም ሰነባብቷል።
ይህ በየጎጡ የሚሰማው “ከየትኛውም አካል ጋር አብረን እንሠራለን” የሚል የሀገር እና የሕዝብን ፍላጎት አሳልፎ ለጠላት የመስጠት የባንዳነት አባዜ፤ ትናንት ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን፤ በቀጣይም ሊያስከፍለን የሚችለው ያልተገባ ዋጋ ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይሆንም።
ይህ እውነታ ሊታየው እና ሊሰማው የማይችለው በባንዳነት የጥፋት አስተሳሰብ የተገራ ብቻ ነው። ለእርሱ ሀገር እና ሕዝብ ማለት የፍላጎቱ መነገጃ ሸቀጥ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ዘንድ ያልተገባ ዋጋ መክፈል የሚባል ነገር የለም፤ ለፍላጎቱ ስኬት የማንንም መስዋዕትነት ይፈልጋል። የፍላጎት ስኬቱም የሚለካው በሌሎች የመስዋዕትነት መጠን ነው።
መንግሥት በአንድ የታሪክ ወቅት የሚመጣ እና የሚሄድ ክስተት ነው። ሀገር ግን ከመንግሥት በላይ ትርክት እና ህላዌ ያላት፤ በተንሰላሰሉ የለውጥ እሳቤዎች ዘመናትን እየዋጀች የምትቀጥል፤ የዜጎች ዕጣ ፈንታ፤ ብሩህ ተስፋ ነገዎች አልፋ እና ኦሜጋ ናት። ይህንን በአግባቡ መረዳት እና መታረም “ከየትኛውም አካል ጋር አብረን እንሠራለን” የሚሉ አካላት አሁናዊ የቤት ሥራ ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም