ለፈተና ያልተበገረ የሰባት ዓመታት ውጤታማ የለውጥ መንገድ !

የሕዝብ ጥያቄ የበረታበት፤ የለውጥ ኃይል በፓርቲ ውስጥ ያቆጠቆጠበት፤ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የሕዝቡን ስሜት በመረዳት፣ የውስጥ ፓርቲ የለውጥ ኃይሉን አዝማሚያም የተረዱበት ነበርናም የለውጡ አካል ለመሆን በሚል ከሥራ ኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ዜና ያሰሙበት፤ በኋላም ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ራሱን በጥልቅ ተሐድሶ ተመልክቶ የአመራር ለውጥ ለማድረግ የተገደደበት፤ እና ለውጥ የተወለደበት ሰባተኛ ዓመት ላይ እንገኛለን።

እነዚህ ሰባት ዓመታት ደግሞ የለውጥ ማግስት ዓመታት እንደመሆናቸው ከሕዝብም፣ ከመንግሥትም የበዙ ፍላጎቶች የታዩባቸው፤ የበዙ የቤት ሥራዎችም የነበሩባቸው፤ የበዙ ፈተናዎችም የተስተናገዱባቸው፤ ከዚህ ሁሉ ግን ፈተናን ወደ ዕድል እየቀየረ የሚሄድ የለውጥ አመራር የተገለጠባቸው እና የለውጥ ማግስት ዓመታት ጉዞውም ፈተናዎችን እያሸነፈ በውጤት ታጅቦ መዝለቅ የቻለባቸው ነበሩ።

የለውጡ የመጀመሪያ ወራትና ዓመታት ትልቁ ፈተና የሕዝቡን ስሜት በየፈርጁ ተገንዝቦ ማስተናገድ ነበር። ምክንያቱም ታፍኖ የቆየ የሕዝብ ስሜት በለውጡ ማግስት ባገኘው ነፃነት ገንፍሎ ወጥቷል። አደባባዮች፣ ሰፈሮችና መንደሮች ሁሉ በሕዝብ ሰልፍና መፈክር የተሞሉበት፤ ይሄንን ተከትሎም ጥቂት ኃይሎች አጋጣሚውን ላልተገባ አጀንዳ ማራመጃነት ሊጠቀሙ የሞከሩበት ነበር።

በሂደት ግን አካሄዱን መግራት፤ ሕዝቡም ስሜቱን እንዲቆጣጠር የሚያደርጉ ሁሉን አቀፍ መድረኮች በሁሉም አካባቢዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ተካሄደ። እናም ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ አደባባይ በሰልፍ ከሚውል የለውጥ ሂደቱን በሚያግዙ የልማት፣ የሰላምና ሌሎች ዓውዶች ላይ ቢውል የተሻለ መሆኑን ማስገንዘብ እና ሕዝቡን የለውጡ ዋና አጋር ማድረግ ተቻለ።

በተለያየ ምክንያት በተለይም በፖለቲካ አመለካከትና አካሄድ ምክንያት የተሰደዱ፣ የታሰሩ፣ ጫካ የገቡ ኃይሎች ለሰላማዊ ትግል ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና ከእስርም እንዲፈቱ የተደረገበት አግባብም ቀላል የማይባል ፈተና ነበረው። ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል በጥበብና ብስለት የተመራ እንደመሆኑ እነዚህን አካላት (ሁሉንም ባይባልም) የለውጡ አቅም አድርጎ መጠቀም ተችሏል።

በኋላም የለውጡን መንገድ ተቀላቅለው መራመድ የተቸገሩ ኃይሎች እንደ ሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር አጥብቀው ሠሩ። ሁለት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ100 የላቁ ግጭቶች በተለያዩ ስፍራዎች እንዲከሰቱ አደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የግድያ ሙከራ ከማድረግ አንስቶ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙን ብሎም የወቅቱን የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በመግደልና በማስገደልም ወደለየለት ጦርነት እንዲገባ ብዙ ሠሩ።

ከዚህ አለፍ ሲልም በሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት በመፈጸም፣ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የጦር ዓውድ እንዲሆን አደረጉ። ይሄ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ቢሆንም፤ በመንግሥት በኩል በነበረው በሳል አመራር ሂደቱን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፤ ብዙዎችም የጦርነትን አስከፊነት በመገንዘብ የሰላም መንገድን እንዲመርጡ ማድረግም ተችሏል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይዞት የመጣው ፈተናም፤ እንደ ሀገር የፈጠራ አቅማችንን እንድንፈትሽ ያስገደደም ነበር። በዚህም ብዙ ወጣቶች ወደ ፈጠራ በመግባት ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ብዙ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እንዲታዩ አድርጓል። ከዚህም በላይ የኮሮናም ሆነ የጦርነቱ ወቅት ጉዞ በአንድ ነገር ላይ ከመቸከል ይልቅ ዘርፈ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚገባ በመገንዘብ፣ በምግብ ራስን ለመቻል በተደረገው ጥረት አሁን ላይ በግብርናው ዘርፍ ለታየው ውጤት መሠረት ተጥሏል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሕዝብ አቅምን አስተባብሮ የተሠራው ሥራም ዘርፈ ብዙ ስኬት የተመዘገበበት ነው። የገበታ ፕሮጀክቶች፤ የኮሪዶር ልማት ሥራዎች፤ የአካባቢ ጥበቃና የወንዞች ዳርቻ ልማት ሥራዎች፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ የወጪና ገቢ ምርቶችን ለማመጣጠን የተከናወኑ ተግባራት፤ የዲፕሎማሲው ዘርፍ አዲስ የስኬት ጎዳና፤ የመከላከያ እና ደኅንነት ተቋማት ላይ የተሠራው ሥራ እና አሁናዊ ቁመናን የመሳሰሉ ውጤቶች የእነዚሁ ሰባት ዓመታት ስኬቶች ናቸው።

እነዚህ ሁሉ ስኬቶች ታዲያ በተመቻቸ መንገድ የተገኙ አይደሉም። ይልቁንም ከባዶ ካዝና በመነሳት፣ በታሪክ ታይቶ ወደማይታወቅ የመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችት የተደረሰ ነው። ከስንዴ ልመናና ሸመታ ተነስቶ፣ በስንዴ ራስን ወደመቻልና አልፎም ወደመሸጥ፣ ከፍ ሲልም ከአፍሪካ ቀዳሚ የስንዴ አምራች ወደመሆን የተሸጋገረ ነው። በኤክስፖርት ገቢ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል።

ከፓርቲ ተልዕኮ ፈጻሚነት የዴሞክራሲ ተቋማት ወደ ነፃ ተቋምነት የተደረገ ሽግግር፤ ከፓርቲ ሕልውና ጠበቃነት ወደ ሀገርና ሕዝብ ደጀንነት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፈጣሪነት የተስፈነጠሩ የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማትን ወደመሥራት የተወነጨፈ የለውጥ ጉዞ ነው።

ይሄ ጉዞ በጦርነት፣ በድርቅ፣ በወረርሽን፣ በጎርፍ፣ በውጪ ኃይሎች ጫና እና ሌሎችም ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመለወጥ የተገኘ ነው። ዛሬም ፈተናዎቹም አሉ፤ የለውጡ ኃይሉም አለ፤ እናም ፈተናው ወደ ዕድል እየተለወጠ የላቀ ውጤት መመዝገቡ ይቀጥላል። ምክንያቱም፣ ለውጡ ከሕዝብ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ነውና!

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You