የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በኢትዮጵያ ስራ ላይ ከዋለ ከአስራ ሰባት አመታት በላይ አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ፤ አዋጁን አሁን ካለው ነባራዊ የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ጋር በማጣጣም የንግድን ስራና አስተዳደርን ቀልጣፋ ለማድረግ አመቺ አይደለም። በመሆኑም፤ በአንድ በኩል በስራ ላይ ያለውን አዋጅ በጥናት በአዲስ ለመተካት ዝግጅት እየተደረገ ቢሆንም ጥናቱ በአጭር ግዜ ሊደርስ የሚችል ባለመሆኑ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በፍጥነት መስተካከል ያለባቸው ነገሮች በመኖራቸው በቅርቡ ለገቢ አሰባሰቡ ሥራ ከፍተኛ ችግር አስከትለዋል የተባሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ የማሻሻያ አዋጅ ድንጋጌዎች ወጥተው ጸድቀዋል።
የእነዚህ ድንጋጌዎች መውጣት ለግብር ሰብሳቢው ተቋም ብቻ ሳይሆን ለግብር ከፋዩም እፎይታ የሚሰጡ እንደሆነ በማንሳት፤ ነገር ግን መንግስት በተጨማሪ እሴት ታክስና አጠቃላይ በግብር አሰባሰቡ ስርአት ላይ በየወቅቱ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ግብር ከፋዮች ይናገራሉ። የክላውድ ወርልድ ዋይድ ኩባንያ መስራችና ባለቤት የሆኑት አቶ ዳንኤል ዮሀንስ እንደተናገሩት፤ መንግስት የጀመራቸው የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያዎች ለግብር ከፋዩም ሆነ መንግስትን ወክሎ ግብር ለሚሰበስበው አካል ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ከመንግስት ተቋማትና ከልማት ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ግብይት በገዢው ተይዞ የሚከፈልን ታክስ በመቶ ፐርሰንት ቫት ከመያዝ ወደ ሀምሳ በመቶ መደረጉና፤ የተመላሽ ገንዘብ ስርአቱ መስተካከሉ ለብዙዎቻችን ስራችንን በአግባቡ እንዳናካሂድ ያጋጥመን የነበረውን የካፒታል እጥረት ለመቀነስ ይረዳል። እስካሁን በነበረው አሰራር መንግስት እጃችን ላይ ገንዘብ እንዲቀመጥ አይፈልግም የሚል አመለካከት ይፈጠርብን ነበር። አሁን አዋጁ ወደ ተግባር ሲገባ ግን እነዚህ ችግሮች ይቀረፋሉ ብለን እንገምታለን። የታክስ ማሳወቂያ ጊዜ በመራዘሙም ለማሳወቅ በመመላለስ የምናወጣውን ወጪ ብቻ ሳይሆን የሚገጥመንንም ውጣ ውረድ በማስቀረት ለዋናው ስራችን በቂ ጊዜና ትኩረት እንድንሰጥ ያስችለናል።
መንግስት ለእነዚህ ማሻሻያዎች ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ ሌሎቹንም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ለማስቀረት መስራት ይጠበቅበታል። በግብር መሰብሰቢያ ማእከላት በብዛትም በክህሎትም በቂ ሰራተኛ አለ ለማለት አይቻልም። አንዳንዶቹ ቦታዎች በርካታ ተገልጋዮች የሚመጡባቸው ሲሆኑ የተመደበው ሰራተኛ ግን ተመጣጣኝ አይደለም። አዋጁ እነዚህንም ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል። በ1997 ያወጣሁትን ቲን ቁጥር አስመልክቶ መረጃ ለማግኘት በቅርቡ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ስሄድ እንደተመለከትኩት በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለጉዳዮች ቢገኙም አገልግሎቱን ሲሰጡ የነበሩት ግን ሶስት ሰራተኞች ብቻ ነበሩ። ይሄ አንድ ቀን ብቻ የሚያጋጥም አይደለም። በእኔ ስር ስምንት ኩባንያዎች አሉ። በቅርቡም ሶስት ድርጅቶች ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነኝ። የእነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ለማስፈጸም ስሄድ የሚገጥመኝ የዘወትር ተግዳሮት ነው። በመሆኑም፤ መንግስት አሁን እንዳስተካከላቸው አዋጆች ሁሉ የግብር ከፋዩን ችግር እየተከታተለ መቅረፍ ይጠበቅበታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኔትወርክ መጥፋት የሁልጊዜ ማሳበቢያ እየሆነ ነው። በሄድን ቁጥር የሚቀርብልን ኔትወርክ የለም፤ አሊያም መቆራረጥ አለ የሚለው ምላሽ ለተገልጋይ በቂ አይደለም። እንደምክንያትም መቅረብ የለበትም። ይልቁንም፤ ተቋሙ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አማራጭ መንገድ የማዘጋጀት ሃላፊነት አለበት። በተደጋጋሚ የሚነሳውንና በመሰረታዊ ፍላጎቶችና ፍጆታዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣል የለበትም የሚለውንም ሀሳብ መንግስት ማየት አለበት የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ በተለይም በምግብ ነክና ተመሳሳይ ነገሮች ላይ የተቀመጠው የ15% ተጨማሪ እሴት ታክስ መንግስት እንደገና ሊፈትሸው የሚገባ መሆኑን ያሳስባሉ።
በተመሳሳይ የቴ. ዎ አልሙኒየም ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ደበበ በበኩላቸው፤ ማሻሻያው በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩት ትልቅ ፋይዳ አለው ይላሉ። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ፤ በኮንስትራክሽን መስክ ውል ተዋውሎ ቅድሚያ ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ ወደ ዋናው ስራ ከመገባቱ በፊት እቃ የመግዛት፤ አንዳንድ ነገሮችን ለማረጋገጥና መሰል ስራዎችን ለመስራት ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል። በዚህም ምክንያት የተቀበልነው ገንዘብ በአግባቡ አገልግሎት ላይ ሳይውል ተመላሽ የሚደረግበት ጊዜ ይደርስና ለመንግስት ገቢ ለማድረግ እንገደድ ነበር። ይህም ካፒታላችንን ስለሚነካ አጠቃላይ በስራው ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ነበር። ከዚህም በላይ፤ ማሻሻያዎቹ በየወሩ የነበረው ውጣ ውረድ የሚፈጥረውን የጊዜና የገንዘብ ብክነት ይቀርፍልናል ብለን እንገምታለን። ይህም ሆኖ ወረፋ፤ የሲስተምና የኔት ወርክ መቆራረጥ የዘወትር ችግር በመሆኑ፤ በተለይም ወረፋ ለብዙ ድካም እየዳረገን ስለሆነ ፈጣን ሲስተም መዘርጋትና የመክፈያ ቦታና ሰራተኞች በበቂ ሁኔታ መመደብ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ ግብር ሰብሳቢው ተቋም አሰሪውንም፤ ነጋዴውንም ለመቆጣጠር የሚያስችለውን በአንድነት የሚያስተሳስርና የየተቋማቱን የየቀን እንቅስቃሴ የሚመዘግብበት ሲስተም በማዘጋጀት ግዢም፤ ሽያጭም ሲፈጽም መንግስት እያወቀው ሊሆን ይገባል። አንዳንድ ጊዜ እቃ ለመግዛት ስንሄድ ከሻጩ የምንቀበለው ሰነድ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ገቢዎች መስሪያ ቤት ድረስ ሄደን የምንጠይቅበት አጋጣሚ አለ። ወጥ ሲስተም ቢፈጠር ግን እዚያው ሆነን በኦንላይን አረጋግጠን ግዢውን መፈጸም እንችላለን። ይህ አሰራር እግረ መንገዱን መንግስት እያንዳንዱን የንግድ እንቅስቃሴ በማወቅ በግብር መክፈያ ወቅት ብቻ ከሚደረግ የተጨናነቀ ስራ ይድናል። ይህንንም ተከትሎ ከሚፈጠር የጥቅማ ጥቅም መጎዳኘትና ሙስና እንዲቀንስ ይረዳዋል። ይህ አሰራር በተገበያዩም በኩል ምርቶች የት እንደሚገኙ ለማወቅ ስለሚረዳ ተገበያዩን ከውጣ ውረድ፤ መንግስትንም ከተደጋጋሚ ስራ ያድነዋል ይላሉ።
በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማስተዋወቅ ዳይሬክተር ወይዘሮ አባይነሽ አባተ በበኩላቸው፤ አዋጁ ረጅም አመታት ያስቆጠረ እንደመሆኑ በሂደት የሚፈጠሩ ክፍተቶች ይኖራሉ፤ በመሆኑም ሁሉንም በመፈተሽ ማስተካከያ ለማድረግ የተጀመረ ስራ አለ። ይህም ሆኖ የአሁኖቹ ማሻሻያዎች የተደረጉት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሶስቱ ብቻ ተለይተው ነው። ከእነዚህም አንደኛው፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የተጨማሪ እሴት ታክስ የታክስ ማሳወቂያ ጊዜ ለሁሉም ደረጃ ግብር ከፋዮች የሚያስቀምጠው የአንድ ወር የጊዜ ገደብ ነበር። ይህ አሰራር በግብር ከፋዩ በኩል ለታክስ ማሳወቅ የሚያወጣውን ወጪ የሚያንር፤ ለታክስ ሰብሳቢው ተቋምም በየወሩ ገቢ የሚሰበስብባቸውን ሌሎች የቢሮ ስራዎች ለመከወን መጨናነቅ እየፈጠረ መሆኑ ተረጋግጧል። በመሆኑም፤ በማሻሻያው አዋጅ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ማለትም፤ አመታዊ ገቢያቸው ከሰባ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑት በየወሩ እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ሲሆን፤ ከዚያ በታች የሆኑትና ቁጥራቸው ብዙ የሆኑት ግን በየሶስት ወሩ እንዲያሳውቁ የሚፈቅድ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ እንዲሻሻል የተደረገው ደግሞ፤ በገዢው ተይዞ የሚከፈልን ታክስ በተመለከተ ነው። ተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሆነው በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለተመረጡ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች አገልግሎትና እቃ የሚያቀርቡ ተቋማት አሉ። እስካሁን በእነዚህ ተቋማት ግብይት ተከናውኖ ክፍያ በሚፈጸምበት ጊዜ ውክልና የተሰጠው ገዢው መቶ ፐርሰንት የተጨማሪ እሴት ታክሱን ይዞ በማቆየት ለታከስ ሰብሳቢው አካል እንዲከፍል የሚያደረግ ስርአት ነበር። ይሄ ሲሆን ተቋማቱ የግብር ከፋዩን የአገልግሎት፤ አሊያም የእቃ ክፍያ ይሰጡና ለተጨማሪ እሴት ታክሱ ግን ተመጣጣኝ ደረሰኝ ነው የሚሰጡት፤ ግብር ከፋዩም ያንን ደረሰኝ ልክ እንደ ጥሬ ገንዘብ ለታክስ ባለስልጣኑ ያቀርብና ከሚሰበስበው ላይ እንዲካካስለት ይደረግ ነበር።
ይህም ሲሆን በግብር ከፋዮቹ በኩል ተመላሽ ገንዘብ እየበዛ እንዲሄድ በማድረግ የመስሪያ ካፒታላቸውን በመያዝ የመንቀሳቀሻ እጥረት እየፈጠረ በስራቸው ላይ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም፤ በአንድ በኩል የታክስ ባለስልጣኑ ከገቢ መሰብሰብ ጋር የመረጃ አያያዝ ስርአቱን መከተል ስላለበት እንዲቀጥል ሆኖ፤ ነገር ግን መቶ ፐርሰንቱን የተጨማሪ እሴት ታክስ ከመያዝ ይልቅ ግማሹን (ሀምሳ በመቶውን) ለግብር ከፋዩ በመስጠት ሀምሳ በመቶውን ደግሞ ለታክስ ባለስልጣኑ ገቢ እንዲደረግ የሚፈቅድ አዋጅ ነው። ይህም በመደረጉ አገልግሎት አሊያም ሸቀጦችን ከላይ ለተጠቀሱት ተቋማት የሚያቀርቡ ነጋዴዎች የካፒታል እጥረት እንዳይገጥማቸው የሚደግፍ ይሆናል።
ሶስተኛው ማሻሻያ አዋጅ ተመላሽ ገንዘብን በሚመለከት ነው። ከዚህ ቀደም አንድ ግብር ከፋይ በገዛውና በሸጠው መካከል የሚካካስ/ተመላሽ ተጨማሪ እሴት ታክስ በማይኖርበት ጊዜ በህጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ እያቀናነሰ ቆይቶ ተመላሽ ይደረግለታል። ይህንን ለማድረግ እስካሁን በነበረው የተጨማሪ እሴት ታክስ ስርአትና አሰራር ሁሉም የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ጠያቂዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በሙሉ ኦዲት በማድረግ የማረጋገጥ ስራ ይሰራ ነበር። ይሄ አካሄድ በታክስ ሰብሳቢው ተቋም በኩል ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ባለሙያ መድቦ የሚያሰራው ሲሆን፤ ይህም ተደርጎ በውጤቱ ምንም ልዩነት ሳይኖር ግብር ከፋዩ ያቀረበው ትክክለኛ መረጃ ሆኖ ይገኝ ነበር። በመሆኑም በዚህ የማጣራት ሂደት ከፍተኛ የባለሙያ ጉልበትና ጊዜ ይባክናል።
ይህም ሲሆን በግብር ከፋዮች በኩል “የመስሪያ ካፒታላችንን ይይዛል” በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብ ነበር። በትክክልም ተመላሽ ገንዘብ በወቅቱ ሲሰጣቸው ጥሪት ሆኖ ስራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው በመሆኑ ይህን አለማግኘታቸው ወደብድርና ሌሎች የገንዘብ ማግኛ አማራጮች ማማተራቸው አንዱ ችግር እንደነበር ይታወቃል። በመሆኑም፤ በአዲሱ አዋጅ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ማጣራት ስጋትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ተደንግጓል። ይህም ለስጋት መለያ ተብሎ በሚቀመጠው መስፈርት መሰረት፤ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ግብር ከፋዮች የተመላሽ ጥያቄ ሲቀርብ ሙሉ መረጃዎቻቸውን የመፈተሽና የማረጋገጥ ስራ የሚሰራ ሲሆን፤ በአንጻሩ በዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ላይ ያሉት ከሆኑ ግን የሚያቀርቡትን የተመላሽ ጥያቄ ደረሰኝ በማጣራት ብቻ በሚገኘው ውጤት ገንዘባቸውን ወዲያው ተመላሽ ለማድረግ ያስችላል።
የስጋቱን ደረጃ ለመለየትና ስጋቱ እንዴት እንደሚጣልም መመሪያ ተዘጋጅቷል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ መመሪያው ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ሶፍት ዌር ውስጥ መስፈርቶቹ እንዲገቡ ይደረጋል። እዚህ ላይ የሚኖረው የሰዎች ጣልቃ ገብነት ለሶፍት ዌሩ መረጃ ለማስገባት ብቻ ነው። ይሄ ከሆነ በኋላ ሶፍት ዌሩ ራሱ ግብር ከፋዩን ከፍተኛ መካከለኛ ዝቅተኛ ብሎ ያስቀምጠዋል። በዚህ መሰረት ኦዲት የሚደረጉትንም፤ ገንዘቡ ወዲያው ተመላሽ የሚደረግላቸውንም ይለያል። ይሄ የአሰራር ሂደት ለሙስናና ጥቅማ ጥቅም ያለውን ተጋላጭነትም ለመቀነስ የሚረዳ ከመሆኑ ባሻገር በተቋሙ በኩል ያለውን የሰው ሀይል በውጤታማ ስራ ላይ ብቻ በማዋል የጉልበትና የጊዜ ብክነትን ለመታደግ ይረዳል። ባጠቃላይም፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ በሙሉ ተፈትሾ እስከሚከለስ ድረስ የተሻሻሉት አዋጆች በግብር ሰብሳቢውም ሆነ በግብር ከፋዩ በኩል ቀዳሚ የነበሩትን ተግዳሮቶች የሚቀርፉ ናቸው ሲሉ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ