ትራምፕ ከፑቲን ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጌያለሁ አሉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሀገራቸው በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ባቀረበችው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ያደረጉትን ውይይት “ጥሩ እና ውጤታማ” ሲሉ አደነቁ። ይህ የሆነው ፑቲን እና የአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በሞስኮ ከተገናኙ በኋላ፣ ጽሕፈት ቤታቸው በሰላም ሂደቱ ላይ የአሜሪካን “ግራ ቀኙን ያየ እና ተስፋ የተሞላበት” ሃሳብ እንደሚደግፉ ካስታወቀ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።

ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ውይይቱ “ይህ አሰቃቂ እና ደም አፋሳሽ ጦርነት በመጨረሻ እንዲያበቃ የሚያደርግ በጣም ጥሩ ዕድል ነው” ብለዋል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ግን ፑቲንን ጦርነቱን ለመቀጠል ንግግሮችን ለማጓተት ሞክረዋል ሲሉ ተናግረው ነበር።

ሰር ኬር ስታርመር በበኩላቸው የሩሲያው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ሀሳቦችን በማንሳት “ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ” ሊፈቀድላቸው እንደማይችል ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዩክሬን በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት የተቀበለች ሲሆን፣ ሩሲያ ግን እስካሁን አልተስማማችም። ሐሙስ ዕለት ፑቲን የተኩስ አቁም ሃሳብ “ትክክል ነው፤ እኛም እንደግፋለን…ግን ልዩነቶች አሉ” ካሉ በኋላ በርካታ ጠንካራ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል። በዚህ በፕሬዚዳንቱ ቅድመ ሁኔታ የተበሳጩት ዘለንስኪ “ሸፍጥ የተሞላበት” በሚል ኮንነዋቸዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዓርብ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ተከታታይ ጽሑፍ ላይ ትችታቸውን በመቀጠል “ፑቲን ከዚህ ጦርነት መውጣት አይፈልግም፤ ምክንያቱም ያ ባዶውን ያስቀረዋል። “ለዚህም ነው ገና ከጅምሩ፣ የተኩስ አቁም ከመደረጉ በፊት እንኳ እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና ተቀባይነት የሌላቸው ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ዲፕሎማሲውን ለማበላሸት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ያለው” ብለዋል።

ፑቲን ሁሉንም አካላት “ማለቂያ ወደሌለው ውይይቶች ይጎትታል… ወታደሮቹ ዜጎቻችንን እየገደሉ ቀናትን፣ ሳምንታትን እና ወራትን በከንቱ ንግግሮች ያባክናል” ሲሉ ጽፈዋል። “ፑቲን ያቀረቡት እያንዳንዱ ቅድመ ሁኔታ ማንኛውንም ዲፕሎማሲ ለመግታት የሚደረግ ሙከራ ብቻ ነው። ሩሲያ የምትሠራው በዚህ መንገድ ነው። እናም ደግሞ ስለዚህ ጉዳይ አስቀድመን አስጠንቅቀናል።”

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር የትራምፕን የተኩስ አቁም ሃሳብ ክሬምሊን “ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቱ” ፑቲን “ለሰላም ግድ እንደሌለው” ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “ሩሲያ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ከመጣች የተኩስ አቁም ስምምነቱ የምር እና ለዘላቂ ሰላም መሆኑን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆን አለብን” ብለዋል ።

“ይህ ካልሆነ ግን ጦርነቱ እንዲያበቃ በሩሲያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር እያንዳንዱን ብሎን ማጠባበቅ አለብን። “ቅዳሜ ሰር ኬር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በለንደን በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ የቀረበውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተወያይቶ ከስምምነት ለመድረስ ከ25 መሪዎች ጋር የቪዲዮ ስብሰባ ያደርጋሉ።

በዚህ ስብሰባ ላይ ሰር ኬር “የፈቃደኞች ጥምረት” ሲሉ የሚጠሩት የአውሮፓውያኑ ሀሳብ፣ አሜሪካ ያቀረበችው የተኩስ አቁም ሥራ ላይ ከዋለ የወደፊት የሩሲያ ጥቃትን ለመከላከል ይሠራል የሚለው ላይ እንደሚወያዩ ተሰምቷል። ዘለንስኪ ዓርብ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “በሩሲያ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሁሉ፣ በተለይም ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሊያግዙ የሚችሉ ጠንካራ እርምጃዎችን ቢወስዱ መልካም ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

“ፑቲን በጦር ሜዳ ላይ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ … ስለተጎዱት” እንዲሁም “ኢኮኖሚው ስላለበት ትክክለኛ ቁመና እየዋሸ ነው” ፑቲን “ዲፕሎማሲው እንዳይሳካ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን በዋይት ሐውስ እምነት ሁለቱ ወገኖች “በፍፁም ለሰላም የዚህ ያህል ቅርብ ሆነው አያውቁም። “የዋይት ሐውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት ሐሙስ ዕለት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በሞስኮ በፑቲን እና በዊትኮፍ መካከል የተደረገው ውይይት “አመርቂ ነበር” ብለዋል።

ትራምፕ “በፑቲን እና ሩሲያውያን ላይ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉ ግፊት አድርገዋል” ብላለች። ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፋቸው ላይም ፑቲን በሩሲያ ወታደሮች የተከበቡትን የዩክሬን ወታደሮች ሕይወት እንዲታደጉ የጠየቁ ሲሆን፣ ያ ባይሆን ግን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያልታየ “አሰቃቂ እልቂት” ይሆናል ነው ያሉት።

ይህ የፕሬዚዳንቱ አስተያየት የተሰማው ሩሲያ ባለፈው ዓመት በዩክሬን የተያዘውን ግዛቷን ለማስመለስ ጥረቷን አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት፣ በኩርስክ የሚገኙት የዩክሬን ወታደሮች “መነጠላቸውን” እና ለቅቀው ለመውጣት እየሞከሩ መሆኑን ፑቲን ሐሙስ ዕለት ከገለጹ በኋላ ነው። ነገር ግን ዓርብ እለት የዩክሬን የጦር ኃይሎች ጄኔራል ባልደረባ ወታደሮቻቸው ተከብበዋል መባሉን “ውሸት እና ፈጠራ” ሲሉ አስተባብለዋል።

በመግለጫቸው የዩክሬን ወታደሮች አካባቢውን ለቅቀው ወደ ተሻለ የመከላከያ ስፍራ” ውጤታማ በሆነ መልኩ መሰባሰባቸውን” እና የማጥቃት ርምጃው መቀጠሉን ገልፀዋል። “በእኛ ክፍል የመከበብ ስጋት የለም” ማለታቸውን በማስታወስ ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You