ደላሎችም አርሶ አደሮችን አታልለዋል
አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ባደረገው ማጣራት የ85 ማዕድን ኢንቨስትመንት ፈቃዶችን መሰረዙን አስታወቀ፡፡ የማዕድን ሀብት ያለው መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች በደላሎች መታለላቸውም ተጠቁሟል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ይርዳው ነጋሽ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት ለመለየትና የዘርፉን አሠራር ከህገ ወጥነት የተላቀቀ እንዲሆን በወሰዳቸው ዕርምጃዎች በ500 ፈቃዶች ላይ ምርመራ አድርጎ ባልተገባ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የ85 ኩባንያዎችን ፈቃድ ሰርዟል፡፡
እንደ ኢንጂነር ይርዳው ገለጻ፣ ከተሰረዙ ፈቃዶች መካከልባለቤት የሌላቸው ወይም የማይታወቅ፣ ፈቃዱን የወሰደው አካል በአገር ውስጥ የሌለ፣ በውክልና ስም ፈቃዱ በደላላ እጅ ያለ፣ በሼር ድርሻ ስም በአንድ በመቶ ድርሻ አርሶአደሩን በማታለል ጉዳይ አስፈጻሚ ያደረጉ፣ የመሬት ካሳ ከአምስት ዓመት በኋላ እንከፍላለን በማለትና አርሶአደሩን በማታለል ካሳው ተከፍሎኛል ብሎ እንዲፈርም ያደረጉና ገመናቸው የተጋለጠ፤ ባላቸው ኃይልና አቅም በመጠቀም ያለአግባብ ፈቃድ የወሰዱ፤ መሬት በኪራይ ስም ሸጠው የሄዱ ይገኙበታል፡፡
ዘርፉ ትልቅ ኪራይ ሰብሳቢነት ያለበት መሆኑም ታይቷል ያሉት ኢንጂነር ይርዳው፤ የዚህ አንዱ ምንጭ በየደረጃው የሚሰጥ ፈቃድ ሲሆን፤ ዘርፉ ለደላላ የተጋለጠ መሆኑም ትልቅ ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ደላሎች በተለይ ማዕድን ያለው መሬት ያላቸው አርሶደሮችን እየለዩ ማሽን ካለው ጋር በማገናኘት፣ ሂደቱን መንግሥት እንዳይቆጣጠረውና መገኘት ያለበት አገራዊ ገቢም እንዳይገኝ አድርገዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተር፤ በኦሮሚያ የፊንፊኔ ልዩ ዞን ብቻ ከ400 በላይ የድንጋይ መፍጫ ክሬሸር ቢኖርም፤ በተለይ ምሥራቅ ሸዋ ባሉ አካባቢዎች እያከናወኑ ባለው የሽያጭ ደረሰኝ ማወናበድ ተግባር መንግሥት እነዚህን ክሬሸሮች እየተቆጣጠረ አለመሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ይህ የማዕድን ህገ ወጥነት ደግሞ ከአዘዋዋሪዎችና ከጸጥታ ኃይሎች ጀምሮ የበርካታ አካላት እጅ ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ ኮትሮባንዱን እያስፋፋው ይገኛል ብለዋል፡፡ በተለይ በጉጂ ዞን ያሉት ሰባ ቦሩ፣ ኦዶ ሻኪሶ እና ሃጋ ዋዩ ወረዳዎች በወርቅና ኤሜራልድ የበለጸጉ እንደመሆናቸው፤ ኮትሮባንዲስቶች አዲስ አበባ ሆነው በደላሎቻቸው አማካኝነት ማዕድኖቹን እየገዙ ወደ ቻይናና ህንድ በሕገ ወጥ መንገድ እየላኩ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ባለስልጣኑ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ጥቁር ገበያን ለማጥፋት የሚያስችሉ ውይይቶች ከባለድርሻዎች ጋር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ እየተደረገ ባለው ክትትልም በትናንትናው ዕለት በጉጂ ዞን አንድ ግለሰብ ከአንድ ኪሎ ግራም ወርቅ ጋር መያዙንና ሁለት ሱቆችም መዘጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በዋናነት የፈቃድ አሠራር ስርዓቱን ማጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
ወንድወሰን ሽመልስ