
– ከስምሪት መስመር ውጪ የመጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል
አዳማ፡- የአዳማ ከተማን የትራንስፖርት ፍሰት የተሳለጠ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች ማስገኘታቸውን የአዳማ ከተማ ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ከስምሪት መስመር ውጪ የመጫንና ከታሪፍ በላይ ማስከፈል በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱንም አመልክቷል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያ ሹሚ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ የከተማዋን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሰላማዊና ዘመናዊ በማድረግ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተውባቸዋል፡፡
ኤጀንሲው ግንዛቤ በመፍጠር፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችን በመተግበር እና ሕጋዊ ርምጃ በመውሰድ የሠራቸው ሥራዎች የትራፊክ አደጋዎች እንዲቀንሱ፣ የመንገዶች መጨናነቅ እንዳይከሰት እና የከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተረጋጋ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል፡፡
እንደ አቶ መኩሪያ ገለጻ፤ የትራንስፖርት ፍሰቱን ሥርዓት ለማስያዝ ታክሲዎች፣ ባጃጆች ሌሎች ተሽከርካሪዎች በማኅበራት ተደራጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ቦሎ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች ቦሎ እንዲኖራቸው፤ እንዲሁም ቦሎ ኖሯቸው የማኅበር አባል ያልሆኑት ደግሞ የማኅበር አባል እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ከተመደቡበት የስምሪት መስመር ውጪ በሚሠሩ፣ ትርፍ በሚጭኑና ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የእርምት ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በእዚህም ሕጋዊ ያልነበሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት የከተማዋን የትራንስፖርት ፍሰት ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል፡፡
ኤጀንሲው ከትራፊክ ፖሊሶች፣ ከተቆጣጣሪዎች፣ ከማኅበራትና ከተሽከርካሪ ባለንብረቶች ጋር በጋራ በመቀናጀት ካለፈው ወር አጋማሽ ወዲህ በሠራቸው የቁጥጥር ሥራዎች የሕግ ጥሰት ከፈፀሙ 674 ባጃጆች መካከል 379 ያህሉ ሕጋዊ ሆነዋል፡፡ በርካታ አሽከርካሪዎች ደግሞ ኤጀንሲው ርምጃ ከመውሰዱ በፊት ሕጋዊ ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ቦሎ ወስደዋል፤ሕጋዊ ሆነዋል፡፡ 295 የሚሆኑት ደግሞ ሕጋዊ ለመሆን በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእዚህም 17 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የከተማዋን የትራንስፖርት ፍሰት ከአንድ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ሆኖ በመከታተል የሚታዩ ጉድለቶችን ለማረም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ የሕግ ጥሰት የፈፀሙ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያቸውን በቴሌ ብር አማካኝነት እንዲከፍሉ በማድረግ ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋት ተችሏል፡፡
ኤጀንሲው ያከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገባቸውን የጠቆሙት አቶ መኩሪያ፤ ከሦስት ሳምንታት በፊት በቀን በአማካይ ከ17 እስከ 23 የስርቆት አቤቱታዎች ለኤጀንሲው ይቀርቡ እንደነበርና አሁን ግን መሰል አቤቱታዎች እየቀረቡ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም ከስምሪት መስመር ውጪ የመጫን እና ከታሪፍ በላይ የማስከፈል ክፍተቶች በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሱም አቶ መኩሪያ ገልጸዋል፡፡
የዘርፉን ባለድርሻ አካላት አቅም ለማሳደግ ከኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ እና ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ኤጀንሲው የከተማዋን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዘመናዊ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን እና ሕጋዊ አሠራሮችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተያዘው ሀገራዊ እቅድ አዳማ ‹ስማርት ሲቲ› የመሆን ግብ አስቀምጣ እየሠራች እንደሆነች የተናገሩት አቶ መኩሪያ፤ የ‹ስማርት ሲቲ›ን እቅድ ለማሳካት በዋናነት ትኩረት ከሚፈልጉት ዘርፎች መካከል አንዱ የትራንስፖርት ዘርፍ በመሆኑ፤ ኤጀንሲው የከተማዋን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዘመናዊ በማድረግ የ‹ስማርት ሲቲ› እቅዱ እንዲሳካ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም