
– እስካሁን 53 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ናቸው
አዲስ አበባ፡– የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለችግኝ ተከላ የሚውል 42 ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡እስካሁን ድረስ 53 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ በዘንድሮ ዓመት በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን ለመትከል የዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡በእዚህም የመሬትና የችግኝ ማፍላት ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቁመው፤ 42 ሺህ ሄክታር መሬት ዝግጁ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ 75 ሚሊዮን ችግኞችን ለማፍላት ታቅዶ፤ እስካሁን ድረስ 53 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ማፍላት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አሁንም የችግኝ ማፍላት ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ በቀሪዎቹ የመትከያ ጊዜው እስኪደርስ ድረስ ቀሪዎቹን ችግኞች ለማሟላት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ እንደ ቀርከሃ ፣ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ብርቱካን፣ ቡና ፣ወይራና የመሳሰሉት ለምግብነትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ ችግኞች ለመትከል ዝግጁ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በ42ሺህ ሄክታር መሬት የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ የተሠራበት መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የችግኞች ማፍላትና ሌሎች አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተከላ ወቅቱ እስኪደርስ ድረስ እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡
በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል የሚሉት ኃላፊው፤ ከእዚሁ ጎን ለጎን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መትከል እንዲችል ቦታዎች ተመርጠው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
አብዛኛው ለችግኝ መፍላት ሥራው እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ እንዲሁም አብዛኛው የተከላ ቦታዎች መረጃ በጂፕኤስ መወሰዱን አመላክተዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ችግኞች አብዛኛውን ለምግብነት እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውሉ መሆናቸው ኅብረተሰቡ በሚገባ እያወቀውና እየተረዳው መምጣቱን የሚገልጹት ኃላፊው፤ ይህም ኅብረተሰቡ ለችግኞቹ የሚያደርገው የእንክብካቤ ሥራ እያደገ እንዲመጣ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
አምና በተመሳሳይ ወቅት የተተከሉት ችግኞች የእንክብካቤና የጥበቃ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊው፤ የችግኞቹ የጽድቀት መጠን 80 በመቶ ያህል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በባለፈው ዓመት በተከላ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች ተሞክሮ በመውሰድ በዘንድሮም እንዳይደገም ለማረም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ ከተከላ ጋር ተያይዞ ከወዲሁ ግንዛቤ ለመስጠት እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ዘግይተው የሚተከሉ ችግኞች የዝናብ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ሳይጸድቁ እንደሚሞቱ የሚገልጹት አቶ ባባክር ፤ ክልሉ መሬቱ ጠንከር ያለና ሞቃታማ ስለሆነ ችግሩን ለመፍታት ችግኞችን ቀደም ብሎ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም