በክልሉ ተቋርጦ የቆየውን የጤና መድኅን ዳግም ለመጀመር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በትግራይ ክልል ከተቋረጠ አራት ዓመታት ተኩል የሆነውን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት በዘንድሮው ዓመት ዳግም ለመጀመር እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ኃይለ፤ አሁን ባለው ሁኔታ የጤና መድኅንን በክልሉ ማስጀመር አስገዳጅ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም በጤናው ዘርፍ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ውስብስብ መሆኑንና በርካታ መድኃኒት፣ የሕክምና ግብዓት፣ ለላብራቶሪ የሚያገለግሉ ኬሚካል ሪኤጀንቶችና ብዙ ግብዓት የሚስፈልግ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዶክተር አማኑኤል ገለጻ፤ በክልሉ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ከመቋረጡ በፊት አባል መሆን ከሚችሉት 60 በመቶ ያህል አባል እንደነበሩና በ2013 በጀት ዓመት ያልተካተቱ አካባቢዎችን በማካተት መግባት የሚችሉትን በሙሉ አባል ለማድረግ እቅድ ነበር፡፡ ሆኖም በጦርነቱ መጀመር ምክንያት ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

የጤና መድኅን ለጤና ተቋማት አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፤ ያለፈውን አራት ዓመት ተኩልም በቂ ባይሆንም አጋር ድርጅቶች የሚያመጡትን ድጋፍ በማከፋፈል መታለፉን ገልጸዋል፡፡

በሌሎች ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ ተሸፍኖ በነፃ የሚገቡት ከኤች አይ ቪ ጋር የሚያያዙ የምርመራ ግብዓቶችና መድኃኒቶች፣ የሳምባ፣ የወባ፣ የሕጻናት ክትባት፣ የእርግዝና መከላከያና የምግብ እጥረት ላለባቸው የሚውሉ አልሚ ምግቦች የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በፍጥነት መግባት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሕክምና ተቋማቱ ከመድኃኒት አቅራቢ በዱቤ በመቀበል ኅብረተሰቡን ማገልገላቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል የጤና መድኅን ሥርዓትን መዘርጋት የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የግድ እንደሆነ ዶክተር አማኑኤል ገልፀዋል፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ የኅብረተሰቡን ፈቃደኝነት ለማወቅ ቢሮው ከአጋር አካላትና በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ጥናት አጥንቷል፡፡ በጥናቱ ከጦርነቱ በፊት የጤና መድኅን አባል ከነበሩት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጤና መድኅን አባል መሆን እንደሚፈልጉ ተረጋግጧል፡፡ የጤና መድኅን አባል ካልነበሩት መካከል ደግሞ 79 በመቶ አባል መሆን እንደሚፈልጉ ታውቋል፡፡

‹‹በአማካይ ከ85 በመቶ በላይ ማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አባል መሆን ይፈልጋል›› ያሉት ዶክተር አማኑኤል፤ አብዛኛው ኅብረተሰብ የጤና መድኅን አባል መሆን ቢፈልግም የሚጠበቅበትን መዋጮ መክፈል እንደማይችል በጥናቱ ስለመረጋገጡ ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ አቅም ቢኖረው በቅድሚያ ለምግብ ፍጆታ ያውለው እንደነበር በማንሳት ለማዋጣት እንደማይችል ያሳያል ብለዋል፡፡

ከጦርነቱ በፊት 27 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖርና ይህ ሕዝብ ለጤና ክፍያ ቀርቶ ለምግብም ድጎማ ይፈልግ ነበር ብለዋል። ጦርነቱን ተከትሎ ይህ ቁጥር በእጅጉ እንዳሻቀበ ገልጸዋል።

በክልሉ አብዛኛው ኅብረተሰብ የጤና መድኅን አባል የመሆን ፍላጎት ቢኖረውም የሚከፈለው ብር አለመኖሩ ዋነኛው ችግር ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ ገንዘቡ ከየት ይገኛል የሚለው ጥያቄ ትልቁ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ክልሉ የጤና መድኅን አገልግሎቱን የሚመራና የሚያስተባብር አካል እንደሚያስፈልገው በመታመኑ የበጀት እጥረት ቢኖርበትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ክልሉን በዓመት 19 ሚሊዮን ብር የሚያስወጣና ከክልል እስከ ወረዳ የሚደርስ መዋቅር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለአባላት ምዝገባና መታወቂያ የሚያገለግል የኅትመት ሥራ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ከአባላት መሰብሰብ ያለበትን መዋጮ በመሸፈን እንዲያግዙ በቢሮው የተዘጋጀና በክልሉ ፕሬዚዳንት የተፈረመበት ፕሮፖዛል ለኤምባሲዎችና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ቀርቦ ምላሻቸው እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡ ከግጭት በኋላ የጤና መድኅንን ያስጀመሩ ሀገራት ተሞክሮም የሚያሳየው ለአብዛኛው ሕዝብ መዋጮ ተሸፍኖ በሂደት አብዛኛው ክፍያውን የሚሸፍንበት አካሄድ መከተላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You