የኢንስቲትዩቱ መቋቋም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርትና የኦዲት ደረጃዎች ለመተግበር ያስችላል

አዲስ አበባ፤- የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርትና የኦዲት ደረጃዎች ለመተግበር እንደሚያስችል ተገለጸ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንስቲትዩቱን ማቋቋሚያ አዋጅ ትናንት ባፀደቀበት ወቅት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሂሳብ ሙያንና ባለሙያውን አቅም በማሳደግ የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ተቋም የለም። በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርትና የኦዲት ደረጃዎችን በሚፈለገው ደረጃ ለመተግበር ሳይቻል ቆይቷል።

የኢንስቲትዩቱ መቋቋም የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎችን በማፍራት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርትና የኦዲት ደረጃዎችን በኢትዮጵያ ለመተግበር የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመው፤ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎችን በስፋት ማውጣት ጥራት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘረጋ፤ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በተጨማሪ ሀገሪቱ ብቁና በቂ የሂሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችላት ከመሆኑ በላይ በባለሙያ እጥረት እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት በመዘርጋት የሀገሪቱን የገቢ አቅም ለማሳደግ ይረዳልም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አምስት መቶ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሰርተፍኬት ለማግኘት በውጭ ምንዛሪ እየከፈሉ በተለያዩ ሀገራት እየሠለጠኑ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያ የፈረመችው በአጀንዳ 2063 የአፍሪካ አሕጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስር ስምምነት ለመተግበር ወሳኝ ነው። ኢንስቲትዩቱ ተቋቁሞ በቂ የተመሰከረላቸው ባለሙያዎች ማፍራት ካልቻለ ከውጭ ማስመጣት የግድ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅትም ጥቂት የማይባሉ የሂሳብ ባለሙያዎች በከፍተኛ ክፍያ ከሌሎች ሀገራት እየመጡ ይሠራሉ። የኢንስቲትዩቱ መቋቋም ሀገሪቱ ለዓለም አቀፍ የሂሳብ ባለሙያዎች የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረትም ይጠቅማል። ከዚህም ባለፈ ዓለም አቀፍ እውቀት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማፍራት ወደ ሌሎች ሀገራት እየሄዱ እንዲሠሩ የሚያስችል ይሆናል ።

የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች በኬንያ 45 ሺህ፤ ዩጋንዳ 4 ሺህ፤ ታንዛንያ 5 ሺህ፤ ናይጄሪያ 60ሺህ ሩዋንዳ 6 ሺህ ያላቸው ሲሆን፤ እስካሁን በኢትዮጵያ 500 የሂሳብ ባለሙያዎች ትምህርት ላይ ሲሆኑ 250 ብቻ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 19ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ትናንት አፅድቋል።

የኢንስቲትዩቱ መቋቋም የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የተሟላ፣ ግልጽ እና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት መዘርጋት ያስችላል ተብሏል።

የሒሳብ ሙያን አንድ ርምጃ ወደፊት የሚወስድና ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች ታሳቢ ያደረገ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የሒሳብ ባለሙያ ማፍራት እንደሚያስችልም ተገልጿል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You