ኢንሳ የወጣቶችን ታለንት ለማበልፀግ የሚሰጠውን ሥልጠና ወደ ክልሎች ሊያስፋፋ ነው

አዲስ አበባ፡- የወጣቶችን ታለንት ለማበልፀግ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ይሰጥ የነበረው ሥልጠና በቀጣይ ወደ ክልሎች ሊያስፋፋ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የኢንፎርሜሽን አሹራንስ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ሃኒባል ለማ ለኢፕድ እንዳስታወቁት፤ ኢንሳ የወጣቶችን ታለንት ለማበልፀግ በሳመር ካምፕ የሚሰጠው ሥልጠና በሚቀጥለው ክረምት ወደ ክልሎች ሊያስፋፋ ነው፡፡

እስከ አሁን ሥልጠናው የሚሰጠው ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ሥልጠናውን ተደራሽ ለማድረግ በየክልሉ ሥልጠናውን የወሰዱ አቅም እንዲያጎለብቱ እቅድ መያዙን አመላክተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 300 ያህል ወጣቶች በሳመር ካምፕ ፕሮግራም ተካተው ሥልጠናውን በመከታተል ተመርቀዋል ያሉት አቶ ሃኒባል፤ በዚህም የሠልጣኞችን ቁጥር ከ60 ወደ 300 ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሃኒባል ገለጻ፤ ይህም ለብዙ ወጣቶች ዕድል ለመፍጠር እና በሀገር አቀፍ  ደረጃ ያለውን አቅም ለማወቅ ያግዛል፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናውን ለመውሰድ ፍላጎት ኖሯቸው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ መምጣት ለማይችሉት እንዲሁም ተቋሙ በአንድ ቦታ ማስተናገድ ያልቻላቸውን እንዲያስተናግድ ዕድል የሚከፍት ነው፡፡

ወጣቶች በሥልጠናው በንድፈ ሃሳብ ይዘው የመጡትን በተግባር በመደገፍ ኢንዱስትሪው ላይ እንዲሠሩና በዘርፉ የተሻለ የሰው ኃይል እንዲፈጠር እያገዘ እንደሚገኝ አቶ ሃኒባል ጠቁመዋል፡፡

ሥልጠናዎቹ በማታ፣ በቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በሳመር ካምፕ የሚሰጡ ናቸው ያሉት አቶ ሃኒባል፤ የሳይበር ጥቃትን በመከላከልና የሀገርን ደኅንነት በማረጋገጥ በተጨማሪ በቀጣይ በዘርፉ አቅም ያላቸው ሰዎች ለማፍራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሃኒባል ገለጻ፤ ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪው እያደገ በመጣ ቁጥር ከሳይበር ደኅንነት ጋር የሚነሱ ስጋቶች እያደጉ መሄዳቸው አይቀሬ ነው፤ እንደሀገር ይህንን ጥቃት መቋቋም የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ ነው፡፡

ከፍላጎት ባለፈ እምቅ አቅም እንዳላቸው የሚጠቁሙ ጉዳዮች፣ የሳይበር ደኅንነት ችግሮች የመፍታት አቅም እና ለመፍታት የሚጓዙበት ርቀት፣ የጀመሯቸው ፕሮጀክቶች እንዲሁም የሳይኮ ሜትሪ ፈተናዎች መውሰድ ለሥልጠናው ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ሃኒባል፤ ታለንት ያላቸው ወጣቶች አምጥቶ ማሠልጠን ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም የሳመር ካምፑ በመደበኛ ደረጃ ማሠልጠን ከተጀመረ ሦስተኛ ዙር መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥልጠናው ብቻ ሳይሆን ከሥልጠናው በኋላም ወጣቶቹ የሀገር ሀብት የሚሆኑበትና ታላላቅ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ከሳይበር ጥቃት የሚጠብቁበት መንገድ ተዘርግቶ እየተሠራ ነው፡፡

ዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ያለበት በመሆኑ ለግል ሴክተሩ ክፍት የማድረግ፣ ዩኒቨርስቲዎች የሳይበር ደኅንነት ከሥልጠና ባለፈ በመደበኛ ኮርስ እንዲሰጡ እንዲሁም ይህንንም ሊደግፍ የሚችል የሕግና ሌሎች የአሠራር ሥርዓቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በቴክኖሎጂው ላይ የመሥራት ፍላጎት ያላቸው እና እራሳቸውን ያበቁ እንዲሁም የተለያዩ ታለንት ያላቸውን ወጣቶች ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ በማሳተፍና በመመልመል አሠልጥኖ እያስመረቀ እንደሚገኝ የሚታወስ ነው።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You