የዓድዋው የግጥም ምትሐት

ዓድዋ ሲወሳ የማይነሳ ስንኝ የለም:: በእናት ሀገር ጀንበር፣ በጦሩ አውድማ ሰላቶው ለመቃብር… በእሳት ለበሱ መድፍ ጎራዴ ዘምቶ፣ በስድስት ሰዓታት ውስጥ አፈር ከድሜ መብላቱ ምትሐት እንጂ ምን ሊሉት! ሳተናው አርበኛ በጠላት ሬሳ ላይ ቆሞ ይሸልላል! ይፎክራል! ቀረርቶውን በዜማ እየቀዳ፣ ለፍትሐት ቢሆነው፤ በቁም ሬሳው ላይ አርከፈከፈው::

የአያት ቅድመ አያቶቻችንን፣ የሐበሻውን ጀብዱ፤ ቢረሳ ቢረሳ እንደምን ለጠላት ይረሳ? ሲነሳ ሲነሳ እኛስ እንደምን ግጥሞቹን ልንረሳ? አቤት ግጥም! አቤት ምትሐት! አጋሚዶውን ከአፈር ደባልቆ፣ ስንቱ አርበኛ የጥቁር ብራቅ ምትሐተኛ ተባለበት:: እምዬ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ ይናገሩ! ባልቻ አባ ሳፎ፣ ራስ መኮንን ይመስክር! ራስ መንገሻና ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ ሚካኤልና ተክለ ሃይማኖትም ሌሎችም…ሌሎችም ቢኖሩና ቢናገሩት፣ ከአርበኛው ፊት ተቀምጠን ብንሰማው፣ ምትሐቱስ እንኳን ያኔ አሁንም ባነቃን ነበር:: የግጥም መድፍ አቁመው፣ ከስንኙ አፈሙዝ ውስጥ በሚወነጨፍ ቃላት አንድ በአንድ ጠላትን ረመረሙት!

ፊታውራሪ ደጃዝማቹ ፊት ፊት እየቀደመ፣ ሳተናው አርበኛ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እየገሰገሰ፣ ዓድዋን ለተዓምር ሲያደርገው፤ እነኚህ ሁሉ እጃቸው ላይ ምን ነበር? ከጎራዴና ከጦር ጋሻ፣ ይተኩስ አይተኩስ ውሉ ካለየለት የዛገ ጠመንጃ በቀር አንዳች የረባ ነገር አልያዙም ነበር::

ጦር ታጥቀው ሳይሆን የጥበብ ወኔ ታጥነው ነበር፤ እንዲያ በልበሙሉነት ለዘመናዊ የጦር መሣሪያ ደረት ሰጥተው “ብከዳሽ ቀኜ ይክዳኝ!” እያሉ ለእናት ሀገር መዋደቃቸው:: ከላይ ላለው የጦር መሪ፣ ከታች ላለውም አርበኛ፤ የነበራቸው አንድ አልሞ ተኳሽ ጥበብ ብቻ ነበር:: ከጥበብም ግጥም ነበር:: በግጥሙም፤ ሽለላና ፉከራ፣ ቀረርቶና የአዝማሪው ስንኞች ናቸው:: ግጥም ይገጠማል፤ የአርበኛው ወኔ እንደ አውሎ ንፋስ ሆ! ብሎ ይነሳል::

‹እስቲ በል አንድ ስንኝ አውርድማ!› እያሉ ከላይ እንደ አሞራ የሚያንዣብበውን የጠላት አውሮፕላን መሬት አውርደው አመድ ያደርጉታል:: ‹ከሽለላው! ድገምለት ከፉከራው!› እየተባባሉ፣ የቃላት መድፍ አስወንጭፈው የጦር ምሽጉን በእሳት ሰደድ ዶግ ዓመድ ያደርጉታል:: …ዓድዋ ላይ ምትሐቱማ ብዙ ነበር:: ድንብርብሩ የወጣ ሰላቶው ሁላ፤ ኧረ ምን ጉድ ነው! ከምድር ሳይሆን ከሰማይ ነው እያለ፣ መውጫ መግቢያው የጠፋው በምንስ ሆነና:: እንዲያውም ሰላቶው ምን አለ፤ “ከፊታቸው መድፍ እየተንጣጣ…እነርሱ በሬሳ ላይ ቆመው የሚሸልሉ ምን ዓይነት ፍጥረት ናቸው…”

“አሻፈረኝ! እምቢ አሻፈረኝ!

ሞትም አልፈራ ናና ሞክረኝ!”

ይላል፤ አርበኛው መድፍ ፊት ቆሞ፣ መድፈኛውን እያፈዘዘ:: ትርዒት የመሰለው ሞኝ ፈረንጅ፣ አፉን ከፍቶ ጀግናውን እንደ እብድ ሲመለከት፤ እሳት ክንዱን አቅምሶት አረፈው:: የታጠቀውን እንጂ፣ የታጠቁትን አልተመለከተም ነበር:: በዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስካፍንጫው ታጥቆ ደረቱን ሲነፋ፣ በትንሽ መርፌ ተርኩሰው እንደፊኛ ሊያፈነዱት እንደሚችሉ አልገባውም:: በታንክና በመድፍ መምታትን እንጂ፤ በሽለላና ፉከራው ውስጥ ስላለው የግጥም ምትሐት ከቶም አልጠረጠረ:: “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እንዳሉም መንጥረውት አረፈ::

ዓድዋ ላይ ግጥም፤ ወኔ ብቻ ነበር? ሲሸልሉና ሲፎክሩ፣ ፍርሃት እንዳያርዳቸው ብቻ? በጭራሽ አይደለም:: ሁለቱም እንደ አንደኛው ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከዚያም በላይ የሆነ ነገር አለ:: ይህም፤ ሳይንስም ሆነ ሌላ ማንም ያልደረሰበት፣ የኛ አባቶች ብቻ የሚያውቁበት ምትሐት ነው:: “ምትሐት” ሲባል ለአንዳንዶቻችን እንደ ሰይጣናዊ ያለ አስማት መስሎ ቢታየንም፤ ግን አይደለም::

ምትሐት ማለት ከሰው ልጆች ተፈጥሮ በላይ የሚመስለውን ነገር፣ በአንዳች ጥበባዊ ኃይል መከወን ማለት ነው:: በፈጣሪው አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ፣ ምድርን ሊቆጣጠር የሚችልበት ኃይል የተሰጠው ነው:: ክፉ አሊያም ጥሩ የሚያስብለው አጠቃቀማችን እንጂ ያንን ኃይል መጠቀማችን አይደለም:: ሊጠቀምበት የፈለገው መንገድ ለመጥፎ ሆነ እንጂ፤ ለሰይጣን እንኳን አስቀድሞ በአምላኩ የተሰጠው ኃይል ነበር::

ለዓድዋው የግጥም ምትሐት፣ እውነትም ቢሆንልኝ መላምት፤ ግጥም ለአርበኛው በስንኝ የተቋጠሩ ማጀገኛ ቃላት ብቻ አይመስለኝም:: በቃላት ውስጥ አንዳች መለኮታዊ የሆነ ኃይል እንዳለው ማሳያ፤ ሰማይና ምድር የተፈጠሩት በቃል ነው:: የአባቶች ጥበብ በሆነው ጠልሰም ውስጥ ቃላት አሉበት:: እንዳልነው ለክፉ ተግባርና ምግባር አዋሉት እንጂ ‹ድግምት› የምንለው ነገር የቃላት ድግግሞሽ ነው:: ታዲያ ቃላት እንኳንስ በግጥም ያህሉ ውስጥ ይቅርና በሌላውም ተፈጥሯዊ ኃይል አላቸው:: እንግዲህ ስለዚህ ኃይል ተረድቶ፣ የዘመናዊ ጦር የማይቋቋመውን ጥበብ ለዓለም ለማሳየት የኛን አባቶች መሆንን ይጠይቃል::

የዓድዋው ምትሐተኞች እነማን ነበሩ…የዓድዋ የጥቁር አምባር፣ የሐበሻ ጀብዱ ያለ ግጥም ያለ ስንኝ አልተቋጨም:: የአርበኛው የሚፋጅ ክንድ ነበልባሉ ከግጥም ነው:: ልቡ በቃላት እንደ ክብሪት ተለኩሶ፣ በእሳት ረመጥ አደባየው! ከላይ ከታች አተራምሶ:: ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ጠመንጃውን ያጎረሰው መች የጥይት ቀለህ ብቻ ሆነና፤ ቢመዝ ከአፎቱ የግጥም ስንኝ ነው:: ግጥሙ ቤት በመታ ቁጥር ሁሉ፣ ጠመንጃውም አነጣጥሮ፣ ጎራዴውም አየር ቀዝፎ፣ ጦሩም በጠላት ግንባር ይሰተራል:: የሰላቶው ጦር ምድር ርቆት ይረፈረፋል::

“የዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፤

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው::”

እያለ የአርበኛው የኋላ ደጀን፣ ይህን መሳይ ስንኝ መዞ ጀግናውን ሰው ምትሐተኛ አደረገው:: የፊቱ ሳተና ፊታውራሪ ገበየሁም፣ ጠላትን ዶግ አመድ ለማድረግ ከፊት ገሰገሰ:: የድሉን ምትሐት በዓይኑ በብረቱ ያየም፤

“ያ ጎራው ገበየሁ!

አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፤

ለምሳም ሳይደርሱ ቁርስ አደረጋቸው!!” አለና አወደሰው::

ፊታውራሪው ገበየሁ ጠላት ፊት ቆሞ ስንቱን ከረፈረፈው በኋላ፤ ደረቱን ለመድፍ ሰጥቶ ከፊት ለፊት ተመታ:: ይሄኔ ነበር እንግዲህ፤

“ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ!”

የተባለለት ወፍ ከሰማይ ጣይ ብቅ ማለቱ:: በዓድዋ ላይ ያልተገጠመለትም ሆነ ያልገጠመ ባይኖርም፣ ያነሳነውን የአንዱን ገበየሁ እንደሁሉም እንየው::

በጦር አውድማው አርበኞች ሲፎክሩና ሲሸልሉ፣ ከአዝማሪው አዝማች ጋር ሁሉ ቀረርቶውንም ሲነፉ፣ በሁሉም ውስጥ ግጥም አለበት:: በግጥም ውስጥ ከተፈጥሮ በላይ የሆነና ተፈጥሮ ሲገልጡ ነበር:: በዓድዋ  የድል ማግሥት የግጥም ስንኝ እንደ ችቦ በርቶ ሲንቦገቦግ ነበር::

“ዳኘው በዲሞቶር በለው በለው ሲል፤

የቃኘው መኮንን

ደጀኑን አፍርሶ ጦር ሲያደላድል፤

ባልቻ በመትረየስ ነጥሎ ሲጥል፤

ተክለሃይማኖት ንጉሥ በለው ግፋ ሲል፤

እቴጌ ጣይቱ ዳዊቷን ዘርግታ ስምዐኒ ስትል፤

ለቆሰለው ጀግና ውሃ ስታድል፤

እንዲህ ተሠርቶ ነው የዓድዋ ድል::” በማለት፤ የአንድነት አሰላለፋቸውን የሚነግረን ግጥም በደማቁ ሰፈረ:: ይህ ግጥም ራሱን የቻለ አንድ ታሪክ ነው::

የዓድዋን ሰሞን በሥነ ግጥም ስንቃኘው፣ በግሌ ሽው የሚልብኝ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ ግጥምን የጥበብ ቋንቋቸው አድርገው፣ በቅኔ ከዚህም ከዚያም ጋር ሲግባቡ በነበረበት ዘመን ላይ፣ ልክ እንደ አሁኑ ቀለሜ የበዛበት ቢሆን ኖሮ፤  ማኅበረሰባዊ ጥበባት በምን ያህል የዓለም ከፍታ ይገኙ ነበር? ምላሹ፤ በልዝቡ ማንም ሊገምተው የሚችል ነው::

አሁን ላይ በመጽሐፍትም ሆነ በቃል የምናውቃቸው የቀድሞ ግጥሞች፤ ከመጥፋት ድነው በኖህ መርከብ ላይ እንደተገኙት ናቸው:: ሲዘንብ የነበረው የጥበብ ዝናብ ምድሩን ሁሉ ባሕር አድርጎ፣ አሁን የምንመከተው ኩሬውን ነው:: ከዓድዋ በፊትም ሆነ በዓድዋ ሰሞን፣ ሙሉ ለሙሉ እስኪባል ድረስ ማኅበረሰባችን ውስጥ ብዕር አይታወቅም:: ግን ደግሞ፤ አንዱም ሳይማር ሁሉም ገጣሚና ባለቅኔ ነው::

ዛሬ ላይ ስንኝ ለመቋጠር ወረቀትና ብዕር ይዘን ስናምጥ የምንውል ቢሆንም፤ ያኔ ግን እንደተራ ንግግር ድንገት ከአፋቸው አፈትልኮ የሚወጣ ነበር:: ቤተክርስቲያንና ቤተ መንግሥት አካባቢ ካልሆነ በስተቀር፣ ግጥሞቹን የመከተብ ሀሳብም ሆነ የተመቸ ነገር የለም:: በጊዜው ሰሚው የተገረመባቸውን ‹እገሌ እንዲህ አለ› እየተባለ በቃል ሲወራረስ፣ አንዳንዱም በየመንገዱ እየተንጠባጠበ የተረፉትን ነው ዛሬ የምናገኛቸው::

እንጂማ እንደሚገጠመውና እንደተገጠመው ቢሆን ኖሮማ አንድ ግዙፍ መርከብ የማይችላቸው መጻሕፍት ይወጡ ነበር:: አሁን የምናውቃቸው ስለ ዓድዋና በዓድዋ የተባሉ ግጥሞችም፤ በጊዜው ከተነገረው አንጻር ምናልባትም ሁሉም አምልጠውናል ብንል ነው የሚቀለው:: ምክንያቱም አሁን ያሉት ድንገት በቃል ለመያዝ የበቁት ብቻ ናቸው::

ሥነ ግጥም የውስጣዊ ኃይል፣ የምትሐት ቀመር ብቻ አይደለም:: ግጥም ስሜትን መግለጫ ቀለም ብቻ አይደለም:: ግጥም ቦታና ሁኔታን፣ ጊዜና ድርጊትን፣ ማንነትንና ምንነትን የሚናገር ትልቅ የታሪክ ማኅደር ነው:: ከትውልድ ትውልድ የሚቀባበሉት ወርቃማ መዝገብ ነው:: ዓድዋን በሚያህል የመላው ጥቁር ሰንደቅ ውስጥ ግጥሞቻችን ሁሉን ተናጋሪ ቀለም ይዘው ተቀምጠውበታል::

የእነዚህ ግጥሞች ቀለም መደብዘዝም ሆነ መበላሸት፣ ቃል በቃል እየተኩ የነበረውን ባልነበረው መተካት፤ የዓድዋን ታሪክ እንደማጥፋት ነው:: ይህንን ተረድተን የምንጠነቀቅላቸው ስንቶች ነን? በተለይ እንደ ማኅበራዊ ሚዲያ ባሉ ልቅነት በሚጎላባቸው መንደሮች ውስጥ ያልተገቡ ስንኞችን የምናስተውልባቸው አጋጣሚዎች ቀላል አይደሉም:: መጀመሪያ በነበረው ላይ የራሳችንን ቆርጠን ስንቀጠልበት ይታያል::

የራሳችን የሆኑ ስንኞችን መፍጠር መልካም ሆኖ ሳለ፤ ከቀደመው ጋር መበወዙ ታሪካዊነቱን ብቻ ሳይሆን ታሪክንም ያዛባል:: በዓድዋ ተራሮች ላይ ያልታየ እንጂ ያልሆነ ምንም የለም:: ያልተጻፈ እንጂ ያልተገጠመ አንዳችም የለም:: ምትሐተኛውን ነው እንጂ ምትሐቱንስ ምኑንም አላየን::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You