
ሰውዬውን ገና ስመለከታቸው ነበር ለአዲስ አበባ ምድር እንግዳ መሆናቸውን የተረዳሁት። ክንብንባቸውን አውርደው ሰላምታ ሲሰጡኝ “ያውቁኛል?” አልኳቸው ያልለመድኩት ነገር ሆኖብኝ። “ምነው ጥላዬ? የሥላሴ ባሪያ አይደለህምን? እኛ በሀገራችን በኖርንበት ባሕል ከብቱ፣ አዝመራው፣ ዱር ገደሉን ሳይቀር የእግዜር ሰላምታ እንሰጣለን” አሉ ተደናግጠው።
ሰውነትን በሚያከብረው እሴታችን እጅግ እየኮራሁ እልፍ ስል ከደጀ ሰላም ተቀምጦ እጁ ላይ ያሉ ርጋፊ ሳንቲሞችን እያንቃጨለ ስንኝ ቋጥሮ አንጀት በሚበላ ዜማ ይለምናል።
“እዩት እግሬ ሞቶ፣ እዩት እጄ ሞቶ፤
እለፈልፋለሁ ሆዴ ብቻ ቀርቶ።”
ኪሴን ሳመሳቅል ዝርዝር ብሮችን አግኝቼ እጄን ዘረጋሁለትና ወደፊት ሳዘግም “ሰላም ለአንተ ይሁን!” አለኝ እጅ ነስቶ። አጸፋውን ሳልመልስ ዝም ብየ ስሄድ “የኔ ወንድም ማንነቴን ሳይሆን ምንነቴን አስብ” አለ። የሰው ትንፋሽ የእግዜር ሰላምታ እርቦት። ከድምፁ ቅላጼ ውስጥ ባይተዋርነት አደመጥኩ። ለካስ ገንዘቤን እንጂ እኔነቴን አልነበረም የሰጠሁት። ተመለስኩና “ደህና አደሩ?” አልኩ በአክብሮት ከስሩ እየተቀመጥኩ። እውነትም የጸሎት መሳፈሪያ የተግባቦት መጀመሪያ፣ ትሁታን የአንደበት ፍሬዎቻችን የሆኑ ቃላት ናቸው። ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎቻችንም ኑሯችንም እንዳሳየን ሰላም የነፍስ መራሂት ናትና ለምኖ ለማደርም፣ ዘርቶ ለመቃምም፣ ወልዶ ለመሳምም ሰላም እጅጉን ያስፈልጋል።
እላይ ከሰፈረው መግቢያዬ፣ በእኔ በከተሜውና በባላገሩ ሰው መካከል የነበረውን ልዩነት እንተወውና፣ የሰውዬው ሁኔታ ግን ማኅበረሰባችን ለሰላም ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። በተለይ ቀደም ባሉ አባትና እናቶቻችን ዘንድ ዋጋው በምንም የማይተመን ትልቅ እንደነበር ማሳያ ነው። ሰላምታ የሚወለደው ከሰላም ውስጥ ነውና ለዚህ ቸልታን አያውቅም። “ሰላምታ የእግዜር ነው” እያለ፤ በየእርምጃዎቹ ካገኘው ጋር ሁሉ የመጀመሪያው ትንፋሹ ለሰላምታ ያደረገ፣ የሰላም አምባሳደር ነው። አሁን አሁን ግን ከዚህ መስተጋብር ጋር ያለን ቁርኝት ቀዝቀዝ ብሎ ይታያል። ለሰው ልጆች ሁሉ ፈጣሪ በነጻ የሰጠንን፣ እኩል በነጻነት ልንጠቀምበትና ልንጠብቀው ግድ ይለናል። ሰላማችንን ለማስጠበቅ ስንል ከምናነግበው የጦር መሳሪያ ይልቅ ጥበብ የተሻለ ኃይል አላት። የጥበብንም እምቅ ኃይል በመጠቀም፣ የሀገርን ሰላም በሥነ ጽሁፍ ለመገንባት ይቻለናል።
ጥንትም ሆነ ዛሬ በሀገር ሰላም ግንባታ ውስጥ የሥነ ጽሁፍ ሚና ባያከራክርም፤ ነገር ግን ስለ ሰላም ግድ የሚላቸው ብዕሮች የቱን ያህል ናቸው? የስንቶቹስ ከሀገራዊ ኃላፊነት ጋር ይከትባሉ? በእርግጥ ግድ ብሏቸው ይህን የሚያደርጉ ቢኖሩም፣ ሥነ ጽሁፍን ባለን አቅም ልክ ተጠቅመነዋል ለማለት አያስችልም።
በሥነ ጽሁፍ ታሪክ፣ ከእኛ የኋላ ታሪክ ካላቸው ጋር እንኳን ስንነጻጸር ፋይዳውን በቅጡ አልተረዳነውም። በሥነጽሁፍ ረቂቃዊ ምናብ ደምቆ እንዲነበብ ሃሳብ ጥበብን ሊያዋልድ፣ ሰላምን ሊፈይድ ይገባል። እና ጎበዝ የኔ መታበይ በማይሽር ጸጸት ሕሊናን ከማቆርፈድ በቀር ምን ሊቸረኝ ይችላል? የዘመናችን ፈላስፋ ኑዋም ቾምስኪ “ዓለማችን በማይጠቅም ነገር ጊዜዋን እያባከነች ነው” ይላል። በተፈላሰፈበት መነጽር ውስጥ አጨንቁረው ከተመለከቱ በሥነ ጽሁፍ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ብዕሮችም፣ ከሰላም መንደር ውስጥ በመባከን ላይ ስለመሆናቸው ይታየናል።
ትልቁን ሰላም የዘነጋ ጥበብ ሀገርና ማኅበረሰብን የዘነጋ ያህል ነው። ምክንያቱም ለሀገርና ሕዝብ ሕልውና የሚያስፈልገው የመጀመሪያው መሠረታዊ ነገር ሰላም ነውና።
ይህ የቾምስኪ ተግሳጽ ራስ ማያ መስታወት ቢሆን ጊዜዬን ያባከንኩባቸው፤ ራሴን የሰጠኋቸው የሥነጽሁፍ ሥራዎች ሀገር እንዳንጽ፣ ትውልድ እንድቀርጽ አግዘውኛል። ከቀልቤስ አስታርቀውኛል። የሥነልቦና መረጋጋትንስ አድለውኛል። ፈላስፋው እርግጥ ነው ሥነጽሁፍ ማንነትን መመልከቻ፣ ትውልድን ከትውልድ ማጋመጃ፣ ለክፉ ቀን ማምለጫ፣ ለዘመን ማጌጫ፣ ለዛለ ሞራል መሞርኮዣ፣ ለተራበ መንፈስ መተከዣ ረቂቅ የነፍስ ምግብ ነው።
ሥነ ጽሁፍ ባለው አንድ የማድረግ እምቅ ኃይል፤ ሰማይና ምድር ሲቀደድ የምንሰፋበት፣ ባሕር ከፍለን የምንሻገርበት፣ በሬ ወለደን የምናመክንበት በትራችን ነው። በአብሮነት የጋራ እሴቶቻችን ውስጥም ፍቅርን፣ ፍትህንና እውነትን የምናጸናበት የጥበብ ጉባኤያችን ነው። ስለዚህ እንደ ንስር እይታ የጠለቀ፤ በአርቅቆተ ምናብ የመጠቀ፤ የብዕር ትሩፋት በጥበብ ተሸምኖ በአንባቢ እዝነልቦና ይቋጫል። ነገስታቱ “እረኛ ምናለ?” በማለት ስህተትንም ልክነትንም እንደጠየቁት ሁሉ እኔም ደራሲ ምን አለ? ስል ሥነጽሁፍ ለሀገር ሰላም ግንባታ ያለውን ፋይዳ እፈትሻለሁ። ግድ ብሏቸው በብዕሮቻቸው ስለ ሰላም የከተቧትን ለማንበብ እሻለሁ።
ቤንጃሚን ፍራንክሊን “ኔቨር ዜር ወዝ ኤ ጉድ ዋር ኦር ባድ ፒስ” (የጦርነት ቆንጆ የሰላም አስቀያሚ የለም) ሲል ይገልጸዋል። አባባሉ የሰላምን ረቂቃዊነት የሚያሳይ ነው። ዓለማችን ላይ ለአንዱ ማኅበረሰብ የምን ጊዜም እውነት የሆነ ነገር፣ በሌላው ዘንድ ሀሰት ሆኖ ሊገኝ ይችላል። በተቃራኒው ለአንዱ ሀሰት የሆነው ለሌላኛው እውነት ሊሆን ይችላል። እጅግ ከምንም በላይ ነው የምንለው እውነት እንኳን በሆነ ቦታና ጊዜ ውስጥ የመለዋወጥ ዕድል አለው። ሁለቱን ተቃራኒ የሆኑትን ሰላምንና ጦርነትን ብንመለከት ግን ሁሌም፣ ለሁሉም መልካቸው አንድ ነው። በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚኖር፣ አስተሳሰቡ ካልተንሸዋረረ በስተቀር፤ የሰላም አስቀያሚነትና የጦርነት ቁንጅና አይታየውም። በቤንጃሚን ፍራንክሊን አባባል ውስጥ ያለው ምስል ለሁሉም የማይሻር እውነት ነው።
ከዚህ ቀጥሎ ባለው ቆይታ የምናገኛቸው ሁለት ሰዎችም፣ ከላይ የቤንጃሚንን ሀሳብ የሚጋሩና ሁለቱም በሀገራችን ሥነ ጽሁፍ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ለማኖር የቻሉ ናቸው። እናም የሀገራችን የሥነ ጽሁፍ መልክ፣ በሰላም ግንባታ ላይ ያለውን ፋይዳና እየተጫወተ ባለው ሚና፤ የጋራ ሀሳቦቻቸውን ያነሳሱበታል።
ሥነ ጽሁፍ ሰላምን የመገንባትም ሆነ የተገነባውን የማፍረስ አቅም አለው። “ታዲያ በእኛ ሀገር ሥነ ጽሁፍ ውስጥ የትኛው ገዝፎ ታየ?” የሚለውን መቅድም ጥያቄዬን ያቀረብኩት፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ ነበር። እርሳቸውም ለንባብ ካበቁት “ፈገግታሽን ፍለጋ” ከሚለው መጽሃፋቸው ሃሳብ ጨልፈው መልሳቸውን ያዘግኑኝ ጀመር።
“ጥበብ ፈገግታዋ ሲደበዝዝ ሃገር ታኮርፋለችና ሕዝቦቿ ሰላም ይርቃቸዋል። አብርሃም ሊንከን ሃገር የምትወድቀው ሕዝቦቿ ምን አገባኝ ያሉ ጊዜ ነው” እንዳለው ከጊዜ ወዲህ የእኛ ሥነጽሁፍም በምን አገባኝ ስሜት ተሞልቶ፣ ከወግ ልማዳችን ተፋቶ፤ ልዩነትን የሚያሰፉና ጠብ ጫሪ ሃሳቦችን በመሃበረሰቦች መሃል በመዝራቱ፤ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብራችንን ውጥንቅጡን አወጣው። ይህ ደግሞ ሃገር ተረካቢ ትውልድ እንዳናፈራ ጋሬጣ ሆኖ አላላውስ ብሎናል” ይላሉ አሁናዊ ሥነጽሁፋችን ያለበት ሁኔታ እያሳሰባቸው።
ይህንኑ ጥያቄዬን፤ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት እንዲሁም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሕግ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ደራሲ አበረ አዳሙ ሲመልሱ “ቀድሞ ነገር…” አሉና ትዝብታቸውን እየቀጠሉ “በቢቸና አጋምና ጊዮርጊስ መሪ ጌታ ታየ የሚባሉ ሊቅ የድጓ መምህር ነበሩኝ፤ ይሁን እንጂ በማኅበረሰቡ ዘንድ መጻፍና ማንበብ እንደክፉ ነገር ስለሚታይ ስማቸውን እንኳን አይጽፉም፣ በጣታቸው ነበር የሚፈርሙት። ይህ ፈር የሳተ ብይናችን እያደገ መጥቶ ፊደል ቀርጻ ለዓለም ያሳየችን ሀገር ደካማ የንባብ ባሕል እንዲኖራት አደረገ። በዚህም ምክንያት ለሁሉም ነገር መፍሰሻ ቦይ የሆነው ሥነጽሁፋችን ታመመ። ጣሊያን ለሁለተኛ ወረራ ከመምጣቷ በፊት ተመስገን ገብሬና ወልደገብርኤል አደባባይ ላይ ቆመው፤ ሰላማችን ሊደፈርስ ነው ሀገራችን ልትደፈር ነው” እያሉ ቅድመ ዝግጅት እንድናደርግ ለፍፈው ነበር፣ ሰሚ አላገኙም እንጂ። ጉዳዩ የአስተውሎት ማነስ ካልሆነ በቀር መዓቱም ምህረቱም፣ በረከት መርገሙም ለሥነጽሁፍ የተሰወረ አይደለም። ለዚህም ነው የታሪክ ጠባሳችንን ለመሻር፣ ከዘመን ቁስላችን ለመዳን ሥነጽሁፍ ለሰላም ግንባታ ያለውን ፋይዳ ልብ እንበል ማለቴ” አሉኝ።
የደራሲ አበራ አዳሙ ሀሳብ በዚያ ብቻ አልተቋጨም። ይልቅስ ሥነ ጽሁፍን በሀገር ሰላም መነጽር ውስጥ ባለ እይታቸው “የየጁ ደብተራ ቅኔው ሲጎልበት፣ ቀረርቶ ሞላበት” ነው ነገሩ… ብለው ሃሳባቸውን በእንጥልጥል ተውት። “ምነው?” አልኳቸው ሃሳባቸውን እንዲቀጥሉልኝ መሻቴ አይሎ። ደጅ አላስጠኑኝም ካቆሙበት ቀጠሉ።
ዳግማዊ ኢያሱ ዘ ጎንደር በጥበብ የተሟሸች ሀገራቸውን ለማጽናት የተማረ ማኅበረሰብ ይኖራቸው ዘንድ በቤተመንግሥቱ ዙሪያ ፊደል ለሚቆጥርና ዜማ ለደረሰ እንጀራ፣ ለቅኔ ተማሪ እንጀራ በወጥ ከጠላጋ፤ የመጽሃፍ ተማሪ ደግሞ ከመኳንንቱ እንደ አንዱ ተቆጥሮ ጠጅም እንዲቀዳለት አዘው ነበር። ነገር ግን ሕልማቸው በእንጭጩ ተቀጨና ሊቃውንት አንደበታቸውንም ጥበባቸውንም ለጉመው የበዪ ተመልካች ሆኑ። ከዚህ በኋላ ነበር፡-
“አባቱ ነበር ፈረስ ተንጠልጣይ፤
ልጁ ደረሰ በጩቤ ዘንጣይ”
የሚል ትውልድ የበቀለው። ይሁን እንጂ ሥነጽሁፍ ስለሰላም ለመዘመር ሰንፎ አያውቅምና ይህን ቃላዊ ግጥም
አባቱ ነበር ማሽላ ዘሪ፤
ልጁ ደረሰ ወንዝ አስከባሪ።
በሚል ተክቶ ከጥፋት ይልቅ ልማትን ማስተማር ያስፈልጋል።
ማሊ እንዲህ አይነቱ በጎ እሳቤ በዜጎቿ ልብ ውስጥ እንዲለመልም በቅርቡ ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንጻ ገንብታ ለደራሲያን ማሕበር አስረክባለች። የግብጽማ አይነሳም። በእኛ ሀገርም ጤናማ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር መንግሥት ለድርሰትና ለደራሲ ልቡ ስስ ሊሆን ይገባል። ያለበለዚያ ግን በቀላሉ ሊጠገን የማይችል የትውልድ ስብራት ይገጥመናል።
ሕጻናትን ከስር መሠረቱ ለመኮትኮትና የወጣቱን ሥነምግባር ለማረቅ መፍትሄው በሀገር በቀል እውቀት የተቃኙ የሥነጽሁፍ ሥራዎችን በሥርአተ ትምህርቱ ውስጥ ማካተት ብቻ ሳይሆን፤ መገናኛ ብዙሃንም ሥነጽሁፍ ለሰላም ግንባታ ፋይዳው እንዲጎላ መድረክ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል የሚለውን ረዘም ያለ ትንታኔያቸውን ቋጩት።
አቶ መሳፍንት በበኩላቸው፣ ከዚሁ ሃሳብ ላይ ተመርኩዘው “ከሁሉም ነገር አስቀድሞ አንድ የሥነጽሁፍ ሥራ ሲዘጋጅ ማኅበረሰቡን ምን ያስተምራል፣ ለአንድነትና ለሰላም ግንባታ አበርክቶው ምንድነው ተብሎ መፈተሽ ይኖርበታል። ይህን ቅድመ ሁኔታ የዘነጋን እንደሆነ ከራሱ የተጣላ፤ በሥነልቦና ቀውስ ውስጥ የሚገኝ ትውልድ እናፈራና በገዛ እጃችን የሀገራችንን ውድቀት እናፋጥናለን። ጀርመናውያን ከመለያየት ወደውኅደት የመጡት በጠንካራ የንባብ ባሕላቸው የሥነጽሁፍ ሃብታቸውን ለሰላም ግንባታ በማዋላቸው ነው። ጃፓንም ብትሆን ከመሰረተ ልማቷ በፊት የዜጎቿን አዕምሮ ነው በሀገር በቀል የሥነጽሁፍ ሥራዎች የገነባችው። እኛስ ከእነሱ ተሞክሮ ምን እንማር?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “የትውልዱን የሃሳብ ግርዶሽ ለመግፈፍ ሥነጽሁፍ አይነተኛና ምርጫአልባ ፍትሁን መድሃኒት ነው። በዘመቻ መልክ ሳይሆን በዘላቂነት ልንገለገልበት ያስፈልጋል” ሲሉም አከሉበት።
እርግጥ ነው አብዛኛውን ጊዜ በሥነጽሁፍ የሚቀርበው ይዘት፣ “ጥበብ ለጥበባዊነትና ጥበብ ለተግባራዊነት” በሚል በሀሳባዊ ጎራ ደራሲያኑን የከፈለ ሆኖ ይታያል። ያም ሆነ ይህ በሚነሳው ጭብጥ ግን፤ ለሰላም አጽንኦት ሰጥቶ ወጣቱን ከተወረወረው ቅዝምዝም ማስመለጥ ይኖርበታል። መንግሥትና ሕዝብ በሚያደርጓቸው ትርክትን የማስተካከል ሂደት ውስጥም የሥነ ጽሁፍ አጋዥነት እንደቀላል የሚታይ አይደለም። የሚያቃቅሩ ትርክቶችም በሥነጽሁፍ መልክ ቀርበው ወጣቱን ማናከሳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነውና ጸሀፊያኑም የሚከትቧቸው ጉዳዮች ከሀገራዊ ኃላፊነት ጋር ሊሆን ይገባል። የተሰማ ሁሉ አይነገርም፤ የታሰበም ሁሉ አይጻፍምና ከራስ በላይ የሀገርን ጥቅም በማስቀደም ሥነጽሁፍን ለሰላም ግንባታ ልናውል ይገባል።
ሥነ ጽሁፍ ለሀገር ግንባታ ያለው ሚና ታላቅ መሆኑን ስናነሳ ከትልቅ ምክንያታዊ እሳቤ ጋር መሆን አለበት። ሥነ ጽሁፍ እጅግ ትልቅ ጥበብ ነው። ጥበብ ማለት ደግሞ የማይቻል የሚመስለውንና ከባዱን ነገር በመላ በዘዴ መከወን ማለት ነው። የምንከውነውም በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ነው። የምንፈልገውን የሰዎችን አዕምሮ ለማሸነፍም ሥነ ልቦናዊ የሆነ የስበት ሕግን በመፈጸም ነው። ጥበብ ደግሞ የአዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ስበት ክምችት ናት። የሰው ልጅ አዕምሮ ምክርን እንኳን ቢሆን፤ በደረቁ የመሸከም አቅሙ አናሳ ነው። በቶሎ ያሰለቸዋል። ነጋ ጠባ በደረቁ ሳናዋዛ ስለ ሰላም ብንሰብከው፤ ጥሩ ነገር መሆኑን ቢያውቅም ሳይቆይ ወደ መሰልቸትና ጆሮውን ወደ ማሸሽ ይገባል። ጥበብ ደግሞ የሰዎችን አካል ከመንፈሳቸው ሰቅዞ የመያዝ ስበታዊ ኃይል አላትና ለማስተላለፍ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ሥነ ጽሁፋዊ ጥበብ በተሞላበት መንገድ እስከሆነ ድረስ አለመቀበል አይቻላቸውም።
ኪነ ጥበብ ያለፈውን ከዛሬው ጋር እያስተያየ፣ ነገን አሻግሮ የሚያሳይ ውስጣዊ መነጽር እንጂ ሰባኪ አይደለምና እንደ ሰላም ያለ ጠጠር ያሉ ጉዳዮች በሥነ ጽሁፋዊ ጥበብ፣ በቀላሉ ልናክማቸው እንችላለን። ሕፃናት ልጆች የቱንም ያህል ሊያድናቸው የሚችል መድኃኒት ቢሆን እስከመረራቸው ድረስ ወደ አፋቸው ሊያስገቡት አይወዱም። ሥነ ጽሁፍ ለሀገር ሰላም ግንባታ ስንጠቀም ልክ ጣፍጠው እንደሚቀርቡት ሽሮፕ መድኃኒቶች ማለት ነው። የምንፈልገውን ከሚፈልጉት ነገር ጋር መስጠት ትልቁ የሥነ ጽሁፍ አቅም ነው። ሥነ ጽሁፍን ለሰላም በማዋል ሀገርን ለመገንባት ስናስብም የግዴታ “ሰላም” የምትልን ቃል እያነሳን በመጠቃቀስ ብቻ ላይሆን ይችላል። ስለ አብሮነት፣ ፍቅር፣ መከባበር፣ መቻቻል ወዘተርፈ…ብንጽፍ በእጃዙር ስለ ሰላም ጻፍን ማለት ነው። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መውደቅ በጀመሩበት ቅጽበት ሰላም መደፍረሱ አይቀርም። አንድ ሰላም በሁሉም፣ ለሁሉም ፍቱን መድኃኒት ነው። ሥነ ጽሁፍም መድኃኒቱን መቀመሚያ ጥበብ ነው።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም