
በቢጫ የሽፋን ቀለም፣ ከጥቁር የሴት ምስል ጋር ፊቴ ድቅን ካለው መጽሐፍ ጋር ጥቂት ተፋጠጥኩ፡፡ ከመጽሐፉ አናት ላይ “የብሌን አንዳች” የሚል ርዕስ ውስጥ ፈርጠም! ብለው የቆሙት ፊደላት አንዳች ዓይን ይስባሉ፡፡ አንዳንዱም ከወገብ ሰበር! ከአንገት ቀለስ! ብለው ሲታዩ፣ ራሳቸውን ለፎቶ ካሜራው ብልጭታ እያዘጋጁ ነው የሚመስሉት፡፡ አንዱን ከሌላው ያስተሳሰረ የመሃል ቤት እንዳላቸው ያሳብቃሉ። ፊደላቱ አንዳች ነገር ይናገራሉ፡፡ ፊቷን አዙራ በቆመች የብሌን ምስል ውስጥ ዝምታዋ አንዳች ነገር አለው፡፡ በተስፋ ዓለም ውስጥ የተመሳቀለ ህቡህ ሕይወት ይሆን እንዴ…ስልም አሰብኩኝ። ይሁንና ሁሉም የሚያምረው በደራሲው ብዕር ሲነገር ነው ብዬ ተወኩኝ፡፡ ጋዜጠኛው ዋለልኝ አየለ፣ ከስሙ ፊት አንድ ሌላ ማዕረግ ጨምሮ “ደራሲና ጋዜጠኛ ዋለልኝ አየለ” ለመባል የበቃባትን “የብሌን አንዳች” መጽሐፍን ገልጬ፣ እኔም አንዳች ነገር ለማለት አሰብኩ፡፡
ገና መግቢያው ላይ “ሥነ ጽሁፍ እንደ ሕይወት ነው ይባላል” የሚል አንብቤ እንዴት አልኩ? ብዙም ሳልርቅ ምላሹን ከዚያው አገኘሁ፤ “ወጥ የሆነ የጋራ ልኬትና ቀመር የለውም ለማለት ነው” ይላል፡፡ ልክ ነው፤ አንድ ደራሲ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ተደራሲ፣ ብዙ ሺህ አንባቢ…ሁሉም የራሱ እይታ አለው፡፡ እኔም ከአንባቢያን አሊያም ከተደራሲያን እንደ አንዱ ሆኜ ደራሲው ካሰፈረው ላይ ጥቂት ቁና ልስፈር፡፡
240 ገጾች ከበርካታ ርዕስና የታሪክ ጅማቶች ጋር ተጋምደዋል፡፡ ምንስ ጽፎ… ይሆን? ደራሲ ከመጻፉ በፊት ሁሌም በሄደበት መሽጎና አጨንቁሮ የሰው ልጆችን ሕይወት የሚሰልል ሰላይ ነው፡፡ ምርጡ ደራሲ ማለትም ምርጡ ሰላይ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ስለራሳቸው የማያውቁትን ጭምር በውስጣዊ ዓይኖቹ ፈልቅቆ ያወጣል፡፡ የብዙዎችን ሕይወት ከነሚስጥራቸው ያውቃል፡፡ ከማወቅም አልፎ ይፈላሰፍበታል፡፡ ነገርን ነገር ያንሳውና የብሌን አንዳች ገጽ ውስጥ ፍስሐ የተሰኘ አንድ ገጸ ባህሪ ደግሞ “…ከፈጣሪ ቀጥሎ የስጋም የመንፈስም ገመናህን የምታውቅ ሴት ናት፡፡ በዚህ ኮተታም የሐበሻ ባህል ውስጥ ሴት ልጅ ገመና ታውጣ ቢባል የስንቱ ጉድ ይፈላ ነበር” ይላል፡፡ እንግዲህ ሴቷም የወንድ ልጅ ደራሲ መሆኗ ነው፡፡ በእርግጥ ፍስሐም ትክክል ነው፡፡
ወንድ ልጅ ዕድሜ ልኩን አብሮት የኖረውን ባህሪ ሳያስተውል አሊያም ጭራሹን ሳያውቀው ይቆይና ብልህ የሆነችው ሴት በቅጽበት እይታ መንጥራ ታውቅለታለች፡፡ አብረው ሆነው እንኳን እርሱ ላይ ላይዋን በውበቷ ፈዞ፣ እርሷ ውስጥ ውስጡን ማንነቱን ትሰልላለች፡፡ ሁል ጊዜ ባይሆንም ብዙ ጊዜ ግን ሴት ልጅም እንዲህ የወንድ ልጅ ሰላይ ናት፡፡ በዚህ ሃሳብ አምርረን እንዳንከርምበት ሌላኛው ገጽ “በራሱ የማይተማመን፣ ራሱን ችሎ ማሰብና ማገናዘብ የማይችል ሰው የስለላ መጻሕፍትን ካነበበ ፈሪ እና ተጠራጣሪ ይሆናል…” ስለሚል፤ ምክሩን ተውሼ እኔም ላነሳኋቸው ወንዶች፣ ለሴት ልጅ ጥርጣሬ እንዳይገባቸው ልበል፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ ዋለልኝ አየለ “የብሌን አንዳች” ብሎ በሰየማት የበኩር መጽሐፉ ውስጥ ስለምንስ አነሳ? ከማለት የቱን ጉዳይ ይሆን ሳያነሳ የቀረው? ማለቱ ቅርብ መስሎ ይታየኛል፡፡ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ባላዎችን በአራቱም አቅጣጫ ተክሎበታል፡፡ በጓደኝነት፣ በፍቅርና በፍልስፍና ማገር ሦስቱንም በአንድ ያስራቸዋል፡፡ በደረቅ የውሸት ሚስማር የተመታውን፣ በእርጥብ የእውነት ማሠሪያ ይጠፍረዋል፡፡ በብዕር በሚቀልሰው የጥበብ ጎጆ ውስጥ ለንግሥቲቱ ብሌን የሚሆን ዙፋን ከመሃከል ሊሠራላት ይታገላል፡፡ የምስኪኑ ሀብተወልድ ልብም፣ አንድ ጊዜ በፍቅር ሌላ ጊዜ ደግሞ በጦፈ ሙግት ላይ ታች ይላል፡፡ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ካሉ ፍስሐና ደጀኔ ማለት ናቸው፡፡
በዚህች የጥበብ ቤት ቅለሳ ውስጥ ፍስሐ ቋሚውን እንምታ ያለ እንደሆን፤ ደጀኔ የለም ማገሩን ነው የምንመታው ማለቱ አይቀርም፡፡ በጓደኝነት ሕይወት ውስጥ ፍልስፍናም ፍቅርም፣ እውነትና ሀሰትም ለየቅል ግራ ቀኝ መወነጫጨፍ እንዳለ ነው፡፡ ከአራቱ ጓደኛሞች መሃል አንዱ የሆነው ፋሲልም ቢሆን አንዳንዴ በማቃናት ሌላ ጊዜም በመቃናት፣ ወዲህም ወዲያም ሲል እንመለከተዋለን፡፡ የሁሉንም ሕይወት እየሰለለ፣ በደራሲው ብዕር በኩል የሚነግረን፣ ተራኪያችን ሀብተወልድ ነው፡፡
በመጽሐፉ የታሪክ ትረካ ውስጥ እያነበብን የምናደምጣቸው እልፍ ርዕሰ ጉዳዮች ታጭቀውበታል፡፡ ለማንበብና ለመስማት ያብቃን እንጂ ሀብተወልድ እንደሆን አያልቅበትም፡፡ በልቡ የብሌንን ፍቅር አንጠልጥሎ፣ የሚያወራልን አንዳች ብዙ ነገር ነው፡፡ ከሚነግረን አንዱ ገና በመጀመሪያው ታሪኩ “የእንስሳት ብልግና” ይለናል፡፡ “አንዲት ሴት ሁሉንም!” ብሎ ካለ በኋላ ደግሞ “ከጠጠር እና ከወርቅ?” ሲል ያስመርጠናል፡፡ እንደገናም “ልጅ መውለድ ወንጀል?” ሲል ይጠይቀናል፡፡ ሀብተ ወልድ በፍቅር የናወዘባትን፣ ደራሲው በብዕሩ የተከተለባትን፣ ለመጽሐፉም መጠሪያ ያደረጋትን “የብሌን አንዳች” የምትል የፍቅር ሀረግ ከመሃከል ይመዝልናል። “ሥራ ለማግኘት እግሮች ሁሉ ወደ አራት ኪሎ ያመራሉ፡፡ አራት ኪሎ ሄዶ አራት ኪሎ መቅረትም ይኖራል” ያለባትን የአራት ኪሎ ትዝታው እንኳን የአብዛኛዎቻችን ትመስለኛለች፡፡ “የብሄር ግርዶሽ” መቼም ሁላችንም የተጋረድንባት፣ የቀትር ጭጋግ ናት፡፡
እኛም የልባችንን አውርተን አንጀታችንን ለማራስ ስንሻ “በልጅ አመሃኝቶ ይበላል እንኩቶ” እንዲል ነን፡፡ ከመጽሐፏ ውስጥም “በሰካራም በኩል” የምትል የብዕር መልዕክት ትገኛለች፡፡ “የሐበሻ ተወካይ እብድ ወይም ሰካራም ነው፡፡ ‹እውነቱን እኮ ነው!› ይላል አንዳንዱ የልቡ ሲነገርለት፤ ራሱ ግን ደፍሮ አይናገረውም፡፡ …‹እብድ› ብሎ የፈረጃቸው ሰዎች፤ በሚናገሩት የድፍረት እና የግልጽነት ቃል ግን ይደነቃል። ‹ታድለህ› እያለ ሁሉ ይቀናባቸዋል…” ይለናል፡፡ ነገሩ ወለም ዘለም የሌለው እውነታ ነው፡፡ ተራው ተናጋሪ ቀርቶ፣ ደራሲው እንኳን የውስጡን ለመተንፈስ ሲሻ፣ ማስተንፈሻው እብድ አሊያም ሰካራም ነው፡፡ ለዚህም ነው እኮ፣ በፊልምና በመጽሐፉ ሁሉ የእብድና ሰካራም ገጸ ባህሪያት መብዛታቸው። እነርሱ ባይኖሩልን ኖሮ፣ እያንዳንዳችን በማን አመሃኝተን እጃችንን ወደ እንኩቶው እንደምንሰድ እንጃልን…”መጠጥ ለጨዋ መጫወቻ፣ ለባለጌ ግን መምቻ ነው” ይላል ፍስሐ፤ አንዳች በገቡበት “የስካር ሽምግልና” ውስጥ፡፡ ምናልባት “ያልተማረ ሲናገር” ይሆን? እንግዲህ “የጋርዮሽ ምድብ” ውስጥ ያለን እንደሆን ራሳችንን ፈትሸን በስተመጨረሻ “ቅዳሜ እና አራት ኪሎ” አንዱን በአንዱ አንጠልጥለን፣ ያነበብነውን በጥበብ ልቦናችን እንዲያሳድርልን መባረክ ነው። ደራሲው ዋለልኝ አየለ፣ እኚህንና ሌሎች የቀሩትንም ርዕሰ ጉዳዮች እያነሳ፣ ከገጸ ባህሪያቱ ጋር ያነሆልለናል፡፡ በሙግት እያሟገተን፣ በፍልስፍናው እያፈላሰፈን… ከልቡ ላይ ፍቅር ብሌንን እንዳብሳታለን፡፡
ብሌን ግን ማናት? እንደ አንድ አንባቢ የማውቃትም የማላውቃትም ይመስለኛል፡፡ እያነበብኩ እኔም ውስጥ ያለች መስሎኝ እፈልጋትና መልሼ አጣታለሁ፡፡ ብሌን ያለችው በሀብተወልድ ልብ ውስጥ መሆኗን እገነዘባለሁ፡፡ ፍስሐን ያህሉን የፍቅር ማፍያ ባለበት የጓደኝነት ጥምረት ውስጥ፣ ሀብተወልድን መሳይ ምስኪን የፍቅር ረሀብተኛ አለበት፡፡ ሀብተወልድ እንደምን ያለውን ቻይ ልብ እንደያዘ ስንመለከት፤ ለካስ እንዲህም ዓይነት ፍቅር አለ! ብለን መገረማችን አይቀርም፡፡ ሀብተወልድ በብሌን ፍቅር ውስጥ አንዳች ነገር ነው…ብዙ ጊዜ እየተገረምን እናደንቀዋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፤ ምነው ብሌንን አግኝተን ባናገርንለት እስክንል ድረስ እናዝንለታለን፡፡ ድንገት የሆነ ሰዓት ላይ ግን ልክ እንደ ፍስሐ ሁሉ ንድድ! እንልበታለን፡፡ ከማንም በላይ የቅርቡ ሆና ውስጠ ሚስጢሩን ሁላ ሲዘከዝክላት፣ ምን ለጉሞት ነው አንዴ እንኳን ፍቅሩን የማይገልጽላት? በእርግጥ ሀብተወልድ የሚያናድድም ጭምር ነው፡፡ ደግሞ እኮ “ከብሌን ጋር ረዥም ሰዓት እንዞራለን፣ ረዥም ሰዓት እንቀመጣለን፣ ረዥም ሰዓት እንጫወታለን” ይለናል፡፡ ታዲያ ሀብተወልድ የጤናው ነው? ፍስሐስ ቢናደድበት እውነት አይደል?
“እኔ የብሌን ብቻ ነኝ፤ እሷ የማንም ትሁን! አላገባም!” የሚለው ብሌን አንዳችም በማታውቀው ፍቅር ውስጥ ነው፡፡ ከብሌን ጋር እንዲህ ባለው ከተዳፈነ ረመጥ ፍቅር ጋር እየኖረ፣ ከሌላ ሴት ጋር ፍቅር ለመጀመር የሞከረው ብዙ ጊዜ ነው። የቀረባቸው አንዳንዶች ቢወዱትም፣ እሱ ግን ልቡ ያለው መልሶ እያቅበዘበዘ ያመጣዋል፡፡ የሚቀርባቸው የብሌንን ፍቅር ያስረሱኛል እያለ ነው፡፡ ፍቅሩን ለብሌን ቢገልጽላት ደግሞ ኋላ ብትርቀኝስ እያለ በመስጋት ነው፡፡ ብቻ አይገቡ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ እሷን ለእህትነት ሰጥቶ፣ ከሌላኛዋ ጋር አዲስ ህይወት ስለመጀመር ባሰበ ቁጥር ሁሉ “በብሌን ላይ የወሰለትኩ ይመስለኛል” እስከማለት ደርሷል፡፡ ሀብተወልድን እንደፍጥርጥርህ! እንበለውና ደራሲውን ግን አለማድነቅ አንችልም፡፡ እንደ በዛብህ እና ሰብለወንጌል፣ እንደ ፀጋዬ እና ፊያሜታ ጊላይ ያሉ ብዙ ዓይነት ፍቅር ተመልክተናል፤ እንደ ሀብተወልድ ያለውን በአንድ ልብ ውስጥ ብቻ የሚነድ ፍቅር ግን እዚህ መጽሐፍ ውስጥ አየን፡፡ ደራሲ ዋለልኝ አየለ፤ ለብዙዎቻችን እንግዳ መልክ ያለውን ይህን መሳይ ፍቅር ለማሳየት፣ ባልተለመደና ወጣ ባለ መንገድ የሄደበት አካሄድ፣ እጅግ ድንቅ እይታ የምንለው ነው፡፡
የብሌን አንዳች ውስጥ እግር በእግር እየተከተልን እናዝግም ካልን፣ ከመንገድ ላይ መሽቶ እውጭ ማደራችን ነው፡፡ እናም ጠቅለል እያደረግን አንዳች አንኳር ነጠብጣቦችን ማንሳት ይበጀናል፡፡ የደራሲው ብዕር የታሪኮቹ ምሰሶ ሆኖ የተተከለባቸው ሁለት ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎችን እናገኛለን፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው፣ ተራኪው በብሌን ፍቅር ተሳፍሮ የሚጓዝበት መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ይሄው ዋናው ገጸ ሰብ፣ ከባልንጀሮቹ ጋር የሚተምበትና ከግማሽ በላይ የሆነውን የመጽሐፉ ጭብጥና ርዕሰ ጉዳዮች የሚሳለጡበት ነው፡፡ ደራሲው በአንደኛው አውራ ጎዳና ላይ በምናብ አሳፍሮ፣ ከቀለበታማው መስቀለኛ መንገድ ዳር ያደርሰናል፡፡ እንደገና የጉዞ አቅጣጫውን በመቀየር፣ ከሌላ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ይወስደናል፡፡
ታሪኮቹን እጥር ምጥን ባለ መልኩ መቅረባቸው፣ መጽሐፉ አሰልቺነት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ከቃላት አጠቃቀም አንጻር የድርጊትና ገጸ ባህሪያቱን ማንነት የሚመስል ለማድረግ እንደጣረበት ያስታውቃል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ስፍራዎች ላይ ድንገት ብቅ እያሉ፣ ስሜታችንን የሚጎረብጡ አልፎ አልፎ ይከሰታሉ፡፡ የቃላት አጠቃቀም ስንል በጻፍንበት ቋንቋ መራቀቅ ብቻ አይደለም፡፡ የአንባቢውን የስሜት ፍሰት ለመጠበቅ፤ ከድርጊት፣ ከገጸ ባህሪና አሁናዊ ሁኔታ ጋር የቃላት ምርጫና ምጣኔ ማድረግ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በድምሩ ግን የብሌን አንዳች፣ ደራሲውን “እጅህን ቁርጥማት አይንካው!” የምታስብለው ናት፡፡
የገጸ ባህሪያቱ አሳሳልና መቼት…በአንድ የፈጠራ ታሪክ ውስጥ እኚህ ነገሮች፣ የመጽሐፉ ስስ ብልት ማለት ናቸው። እኚህ ካላማሩ ታሪኩ ብቻውን ደረቅ ነገር ይሆናል፡፡ በገጸ ባህሪያቱ መካከል የሚፈጠረው ግጭት ወይንም ሴራ ወሳኝ ህልውና አለው፡፡ የብሌን አንዳች የደራሲው የመጀመሪያ ሥራ እንደመሆኑ የሚያስጨበጭብ ነው፡፡ የገጸ ባህሪያቱ አሳሳል፣ ጠንከር ያለ ማንነትና አይረሴነት የተላበሱ ናቸው። በተለይ “ፍስሐ” የተሰኘው ገጸ ባህሪ ጥልቅ ስሜትን ያዘለና በአንዳች ነገሩ ከአንባቢው ልብ ጋር የሚቆራኝ ዓይነት ነው፡፡ በድርጊትና ፍልስፍናዎቹ ከወደድነው እስከ ጥግ የምንወደው፣ ከጠላነውም እንዲሁ የምንጠላው ገጸ ባህሪ ነው፡፡ ፍስሐ በድርጊቶቹና በአመለካከቱ ከብሌን ጋር ፍጹም ተቃራኒ የሚመስሉ ቢሆንም፣ አንዳንድ ፍልስፍናዎቻቸው ደግሞ ፍጹም ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ፍስሐ ለሀብተወልድ ያወራለትን እውነታ፣ በሌላ ጊዜ ብሌን ስትደግምለት እንመለከታለን፡፡
ነገር ግን በሁለቱ መካከል ያለውን ትልቅ ገደል የምንመለከተው፣ ከባህሎቻችን አንጻር የተቃኙበት መሠረት ለየቅል መሆናቸው ነው፡፡ ብሌን በአለባበሷ ውስጥ እንኳን ስለ ማህበረሰቡ የምትጨነቅ ናት፡፡ የሰው ልጅ ለባህልና ሃይማኖቱ መገዛት አለበት ብላ ታምናለች፡፡ ፍስሐ ደግሞ በተቃራኒው እኚህ ሁለት ነገሮች ነጻነትን የሚጋፉ እስራቶች ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ሁለቱም ግን በእውቀት የተገነቡ አንባቢያን ናቸው፡፡ ዋና ገጸ ባህሪ የሆነውን ሀብተወልድ በእነዚህ ሁለት ገጸ ባህሪያት መሃል ድልድይ የሆነበት መንገድ፣ እውነተኛ ታሪክ ከሆነ “ግሩም!” ብለን እናልፈዋለን። እንደፈጠራ ሥራ እንውሰደው ካልን ግን፤ ደራሲው ዋናው ገጸ ባህሪ እንዳይጎላ ጥቂት ጋርዶታል፡፡ ልቡ ውስጥ ካለው ፍቅር የተነሳ ብሌንን ፍጹም አድርጎ ተቀብሏታል፡፡ ፍስሐን በብዙ ነገሮች የሚሞግተው ቢሆንም በአዋቂነቱ የበላይነቱ ብልጫ እንዲታይበት አድርጎታል፡፡ የብዙ ሃሳቦች መነሻ እሱ በመሆኑም ዋናው ገጸ ባህሪ ፍስሐ እንዲመስለን ያደረጉ አንዳንድ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ አንዳንዴም የሀብተወልድ አቋቋም ልበሙሉነት የጎደለው መስሎ ይታየናል፡፡ ታሪኩ የፈጠራ ሥራ ከሆነ እንደ አማራጭ፤ ብሌንና ፍስሐ በሁለት አውራ ጎዳናዎች ሳይገናኙ ለየቅል ከሚሄዱ ይልቅ፣ በአንድ ሴራ ውስጥ ሲፋጩ ብንመለከት ኖሮ በጣም ውብ ይሆን ነበር፡፡
“የብሌን አንዳች” ረዥም ልቦለድ? አጭር ልቦለድ? ግለታሪካዊ ወግ? ወይንስ ምን እንበለው? በእርግጥ ሁሉም ዓይነት ዘውጎች በጥምረት የሰፈሩበት ይመስላል፡፡ አንዱን ብቻ ነው ለማለትም ይከብዳል፡፡ በረዥም ልቦለድ ውስጥ ከምንም በላይ ደግሞ የታሪክ ፍሰቱ በወጥነት እየተቀጣጠለ የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ አንባቢው የመጀመሪያውን መጨረሻ ለማወቅ ልቡ በጉጉት ቢንጠለጠል የተሟላ ያደርገዋል፡፡ ታሪኮቹ በምዕራፍ ተከፋፍለው፣ እንደ አጭር ልቦለድ በተለያዩ ምዕራፎች ሊሄድ ይችላል፤ ልክ “የብሌን አንዳች” እንደሄደው ሁሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም የታሪክ ሴራዎች ወደ አንድ እየመጡ፣ ወደ መጨረሻው የጡዘት ከፍታ ሊጓዙ ይገባል፡፡
የብሌን አንዳች ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ለመጓዝ የፈለገ ይመስላል፡፡ በየመሃሉ ከሚነግረን የብሌን ፍቅር ባሻገር፣ በቀሪዎቹ ውስጥ የምናገኛቸው ሴራዎች ጣጣቸውን እዚያው በዚያው አዳፍነው፣ ገጸ ባህሪያቱ ብቻ ወደ ቀጣይ ይጓዛሉ። የሚያነሷቸው ሃሳቦች ትልቅና መሳጭ ቢሆኑም፤ እንደ ረዥም ልቦለድ የምንጠብቀው መጨረሻ አይታየንም፡፡ በእርግጥ ይህን ስንል በሀብተወልድና በብሌን መከካል ያለውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ደራሲውም አስቀድሞ ይህንኑ በመረዳቱ ይመስለኛል “ይህ መጽሐፍ ረዥም ልቦለድ ይሁን፣ ወግ ይሁን፣ እውነተኛ ታሪክ ይሁን…ዘውጉን መበየን ቸግሮኛልና ይሆናል ያላችሁትን አድርጉልኝ” ሲል በመግቢያው የሚነግረን፡፡ እኔም ይህንን ነጻነት በመጠቀም ነው፤ እንዳሻኝ መዘባረቄ፡፡ ዘውጉን ግን እኔም ለናንተው ተወኩት፡፡
መጽሐፉን አንብቤ ከጨረስሁ በኋላ፤ ገና ከመክደኔ ያስጓዘንን መንገድ በዓይነ ህሊና ቃኘሁት… እንደ አንድ አንባቢ በዚያች ቅጽበት የተሰማኝ አንድ ነገር ቢኖር፤ በአንዳች ጸጥ ረጭ ባለ የሰላም ውቅያኖስ ተጉዤ ዳርቻው ላይ መድረሴን ነው፡፡ “የብሌን አንዳች”ን ያነበበ ልክ እንደኔው ሁሉ በናፍቆት አሻግሮ ሁለተኛውን መጠባበቁ አይቀርም፡፡ ደራሲውን፤ መዳፍህን ያለምልመው! ብዕርህን ያርዝመው! ብለን እንደገናም እንመርቃለን፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም