ከዓድዋ ድል በመማር ለቀጣይ ድል ራስን ማብቃት

ኢትዮጵያውያን የዛሬ 129 ዓመት ሊደበዝዝና ሊሻር የማይችል ነጻነታቸውንና ሉአላዊነታቸውን ያስጠበቀ ደማቅ ታሪክ ዓድዋ ላይ አስመዝግበዋል። ሀገራቸውን ቅኝ ሊገዛ የመጣውን የጣሊያን ሠራዊት ድል በማድረግ የተቀዳጁት ይህ ድል የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበትና በደማቁ የተጻፈ ታሪክ ነው።

በበርካታ ኢትዮጵያውያን የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው የተጎናጸፉት የዓድዋ ድል ሁልጊዜም የማይረሳና ምስክር የማይሻው ኃያል የኢትዮጵያውያን ገድል ሆኖ ሲጠበቅና ሲዘከር ይኖራል።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ነፃነቷንና ክብሯን በማስጠበቅ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ቀንዲል እንዲሁም የቅኝ ገዢዎችን ፍላጎት ከንቱ በማስቀረት፣ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር መሆን የቻለችበት ነው። ድሉ በቅኝ ግዛት የነበሩ አፍሪካውያንንና ጥቁር ሕዝቦችንም ለበለጠ ትግል ያነሳሳም በመባል ይታወቃል።

ከዚህ ታላቅ ድል ብዙ ትምህርት መቅሰም እንደሚቻል በተደጋጋሚ ይገለጻል፤ ለመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል ከፈጸሙት ተጋድሎ ምን ተምሯል? የተማረውንስ በምን መልኩ እየተገበረ ነው? ምንስ መማርና መተግበር አለበት?

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን እንደሚሉት፤ የዓድዋ ድል ቀደምት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ሕልም ያከሸፉበትና አንጸባራቂ ድል ያስመዘገቡበት ነው፣ ትልቅና ለአፍሪካም ነጸብራቅ ነው።

ትውልዱ ከዓድዋ ድል ሊማራቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተነግረው አያልቁም፤ የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ፋና ወጊ ስለሆነው የዓድዋ ድል ብዙ ልናውቅና ብዙም ልንናገርለትና ልንማርበት ይገባል ሲሉም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያስገንዝባሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳስታወቁት፤ ከድሉ የምንማረው የመጀመሪያው ጽናት ነው። የዓድዋ ድል ጥቁር ሕዝቦች በዓድዋ ላይ ባደረጉት ተጋድሎና በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘ ድል እንደመሆኑ ከዓድዋ ድል በጽናት፣ ለሉዓላዊነትና ለነጻነት የመታገልን አስፈላጊነት መማር ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ታልፎ የተገኘው ፍሬም ምን ያህል ጣፋጭ እንደሆነም መረዳት ይገባል።

ሌላኛው ትውልዱ ከዓድዋ መማር የሚገባው የአንድነትን ፋይዳ ነው። ምክንያቱም አንድነት ከዓድዋ በላይ በምንም ሊገለጽ አይችልም። የዓድዋ ዘመቻ በመላው ሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ካያሉበት በአንድነት ‹‹ሆ›› ብለው መዝመታቸው በጣሊያን ጦር ላይ ድል እንዲጎናጸፉ አድርጓቸዋል ሲሉም ጠቅሰው፤ በዚያ የተጋድሎ ወቅት አንድነታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ መታየቱን ያመለክታሉ።

የዓድዋ ድል አንድነትን ብቻ ሳይሆን አብሮነትንና ጽናትንም በደንብ አድርጎ እንደሚያንጸባርቅ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያውያንን ለነጻነት ሟችነት በሚገባ የሚያሳይ ታሪካዊ ድል መሆኑን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ጠቅሰው፤ ትውልዱ ይህን መገንዘብ እንዳለበት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ለሀገር የተከፈለውን መስዋዕትነት መማርም እንደሚቻል ያመላክታሉ። ዓድዋ የትውልድ ቅብብሎሽ እንደመሆኑ የያን ጊዜው ትውልድ ያደረገው ተጋድሎና የከፈለው መስዋዕትነት ለዚህ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻሉ።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ትውልዱ ለሀገር ሲባል ከተከፈለው መስዋዕትነት ትልቅ ትምህርት ያገኛል፤ እያገኘም ነው። ይህ ትውልድ ያገኘውን ትምህርት ለራሱ ብቻ የሚኖረው ሳይሆን ለመጪው ትውልድ እንዲኖርበት የተሻለ ነገር በማድረግ ሀገር እንዲለውጥና እንዲገነባ ትልቅ ትምህርት መወሰድ ይገባል። ድሉ ከጽናት ባሻገር ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት ነው።

የዓድዋ ድል የነጻነት ምልክትም ነው። ስለነጻነት በሰፊው መማር የሚቻልበት ነው። ቅኝ ገዥዎችን አሻፈረኝ በማለት በተከፈለ መስዋዕትነት የተገኘ ድል ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ለመላ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አርማ ሆኖ የሚያገለግል ነው። የዓድዋ ድል ያስተላለፋቸውን ሰፋፊ መልዕክቶች ከያዙ ከእነዚህ አንኳር ነጥቦች ብዙ እንማራለን ሲሉም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያውያን የዓድዋን ድል በተለያየ መንገድ ሲያዩትና ሲገልጹት ቆይተዋል ፤አንዳንዶች ድሉን የኛ ትግል ውጤት ነው ሲሉ መደመጣቸውንም ይጠቅሳሉ። ‹‹ድሉ ትልቅና ለአፍሪካና መላ ጥቁር ሕዝቦችም ያገለገለ ሆኖ ሳለ ወደ ውስጥ ስንመለከት ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እርስ በእርሳችን የኔ ነው፤ የኔ ነው እያልን ስንወዛገብ ቆይተናል›› ይላሉ።

‹‹በአንዳንድ ጉዳዮች ተለያይተን የምንናቆረውን ወደ ጎን ትተን ዓድዋ የሁላችንም አሰባሳቢ እና አቃፊያችን መሆኑን ለዚህ ትውልድ በደንብ ማሳየት አለብን፤ ያንንም ለማስቀጠልም ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል›› ብለዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በዚህ ዘመን ደግሞ ዓድዋ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ብሎም አፍሪካውያንን የሚወክል በመሆኑ ድሉ ሲከበርም በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በተለያዩ አመለካከቶችና በፖለቲካ ልዩነቶች መከፋፈል ሳይኖር የዓድዋ ድል የሁላችንም መሆኑን ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲከበር እየተደረገ ነው። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምም ይህን በሚያንጸባርቅ መልኩ ተገንብቷል፣ ሙዚየሙ ድሉን ሁላችንም በጋራ እንድናከብር ያስችላል።

ስለዓድዋ ድል በሚጠበቀው ልክ ተሠርቷል ማለት ባይቻልም እነዚህን የመሳሰሉ ማሳያዎች መኖራቸው በቀጣይ የተሻለ እንድንሠራ ያደርገናል ነው ያሉት።

ድሉን አንድ ትልቅ አሰባሳቢ ቅርስ ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን፤ የዓድዋ ድል የአሰባሳቢ ትርክትነት በተለይ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትምህርት ነው፤ ይህ ደግሞ ከዚህ ትውልድ ያገኘነው ማሳያ ነው ብለን ማንሳት እንችላለን ሲሉም ያብራራሉ።

ስለዓድዋ ብዙ ነገሮች ይቀሩናል፤ ዓድዋ ላይ የተከፈለውን መስዋዕትነት ያህል እየኖረን አይደለም የሚሉት መሐመድ (ዶክተር)፤ በቀጣይ ደግሞ ትውልድ ደግሞ በልካችን እንድንኖረው ዓድዋ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ አሁን የተሠሩ ሥራዎችን መሠረት አድርጎ ተጨማሪ ሥራዎችን እየሠራን ሰፋፊ ድሎች ማስመዝገብ አለብን ሲሉም ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያውያን ለጥቁር ሕዝቦች ጥሩ ማሰባሰቢያ ሊሆን የሚችል ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይሄኛው ትውልድ ከዓድዋ የወሰደውን ትምህርት በተግባር እየተረጎመ የተጀማመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው ያመላክታሉ። መጪው ትውልድ ደግሞ ከድሉ በሰፊው ተምሮ የቀሩትን እየሠራ ለቀጣዩ ትውልድ እያስተላለፈ ቅብብሎሽን ጠብቆ መጓዝ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳብራሩት፤ የዓድዋ ድል በቀላሉ አልተገኘም፤ በቀደምት አባቶች የሕይወት መስዋዕትነት የተገኘ እንደመሆኑ ትውልዱ ለዓድዋ የሚገባውን ክብር ሊሰጥ ይገባል፤ ክብር መስጠት ሲባል በዓድዋ ዙሪያ ጥናትና ምርምሮች በሚገባው ልክ ተሠርተዋል ወይ? ያሉ ጥናትና ምርምሮች ምን ያህል በቂ ናቸው? ምንያህል ያሳለፍንበትን ታሪካዊ ዳራ በደንብ ሊያሳዩን የሚችሉ ናቸው? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ የታሪክ ባለሙያዎች፣ የአርት፣ የሥነጽሁፍ ባለሙያዎች እና የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባለሙያዎች የሚገባውን ያህል እያደረጉ እንደሆነ ያመላክታሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ እነዚህ ባለሙያዎች ጥናትና ምርምር ከማድረግ ባሻገር ማሳተምና ጽሑፎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነባቢ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን በዓድዋ ድል ላይ ያለው እውቀት ሊያድግ፣ አስተሳሰብ እየሰፋና ሁሉም ሊማር የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

በዓድዋ ድል ላይ የሚገባውን ጥናትና ምርምር አድርጎ ማሳተምና ተተኪው ትውልድ እንዲማርበት ማድረግ ትልቁ ሥራ ሊሆን ይገባል። የዓድዋ ድል የጦር ሜዳ ትግል ውጤትም፤ ስኬትም ነው።

አሁን ባለንበት ዘመን ኢትዮጵያ የምትፈልገው የጦርነት ድል ብቻ አይደለም፤ የኢኮኖሚ ድል ነው ሲሉም አስገንዝበዋል። ይህ ዘመን በኢኮኖሚ በጣም የተጎዳ ማህበረሰብ ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢኮኖሚው ረገድ በርትቶና ጠንክሮ በመሥራት ውጤት ማምጣት ከአሁኑ ትውልድ ይጠበቃል ይላሉ።

ትውልዱ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ በትጋት ሰርቶ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መቀየር አለበት ሲሉም አስገንዝበው፣ በዓድዋ በትጥቅ ትግል የተገኘውን ድል በኢኮኖሚያዊ እድገትና ሽግግር ማሳየት ከትውልዱ ይጠበቃል ብለዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ የኢኮኖሚ እድገት ሲመጣ የፖለቲካ ውህደት፣ ስምምነቶችና መግባባቶች ደግሞ በሂደት ይመጣሉ፤ በፖለቲካ ሂደቶች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ለመቅረፍ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል። ድሉ ወታደራዊ ድል ቢሆንም ድሉን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲዊ ድሎችን ለማግኘት በሰፊው መሥራት ከዚህ ትውልድ ይጠበቃሉ።

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው ዶክተር ረታ ግርማ መላ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለነጻነታቸው መጠበቅ መስዋዕትነት ከከፈሉበት የዓድዋ ድል ብዙ መማር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያውያን ጠላትን ድል በመምታት ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ሲሉ ያሳዩት ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ አንድነትና የከፈሉት መስዋዕትነት ብዙ እንደሚያስተምሩ ያመላክታሉ።

በዓድዋ ጦርነት መላ ኢትዮጵያውን ስንቅ ከማቀበል ጀምሮ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ድሉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን ያመላክታሉ። ኢትዮጵያውያን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የተጎናጸፉት ይህ ድል ኢትዮጵያውያንን ብቻ የጠቀመ አለመሆኑንም አስታውቀዋል።

በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ የነበሩ መላ ጥቁር ሕዝቦች ለነጻነታቸው አጥብቀው እንዲታገሉ አቅም የፈጠረላቸው፣ ትልቅ የሞራል ስንቅ የሆናቸው ታላቅ ድል መሆኑንም አስታውቀዋል። የዓድዋ ድል ለፓን አፍሪካ ንቅናቄ ትልቅ ኃያልና ሞራል እንደሆነም ይገልጻሉ።

በተለይ የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል የሚማረው ሰፊ ትምህርት እንዳለ የሚናገሩት ረታ (ዶ/ር)፤ ራስን ለወገንና ለሀገር መስጠትን በተግባር የሚማርበት ነው ይላሉ። አባቶችና እናቶች ለሀገራቸው ለልጅ ልጆቻቸው ብለው ራሳቸውን ሰጥተው መስዋዕትነት ከፍለው ሀገር እንዳቆዩና ነጻነትን እንዳስጠበቁ የምናይበት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ አሁን የሚታዩ አንዳንድ ችግሮችንም እኛም በዚያው ልክ ተነስተን መፍታት እንዳለብን እንደሚያስተምርም ጠቁመዋል። ችግሮች ተወሳስበው የሀገር እድገት ወደኋላ እንዳይጎቱት፣ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው፣ በንግግር፣ በምክክር፣ በዘመነ የፖለቲካ አሰራር ፣ ሰላምን በማስፈንና በጋራ ሀገራዊ ጥቅም ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

‹‹በተለያዩ ሥርዓቶች የተፈጠሩ ተጽዕኖዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የሀገራችንን እጣ ፈንታ የምንወስነው እኛ ነን። እጣ ፈንታችን አንድ ላይ የተሳሰረ ነው፤ ያለምንም መለያየትና መከፋፈል ለጋራ ጥቅም ተግተን መሥራት አለብን። ሁሉም ነገር የሚካሄደው ሀገር ስትኖር ነው። በሰላም ወጥተን ሠርተን የምንመለሰው ሰላም ሲኖር ነውና፤ ለሀገር ሰላም ሁላችንም ልንሠራ ይገባል ›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሰላም ሲባል ደግሞ የጦርነት መኖር ወይም አለመኖር አይደለም የሚሉት ረታ (ዶ/ር)፤ አሠራሮችን ማዘመን ፣ ሥርዓትን ማስጠበቅና ተቋማት ሥርዓትን ተከትለው እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። ሀገራዊ ስሜት ሊኖር እንደሚያስፈልግ፣ ለግል ጥቅም ሳይሆን ለሀገር ጥቅም መቆም እና የሕዝብ ወገንተኛነት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህ ረገድ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ጠንክሮ ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከዓድዋ በኋላ የመጡ ትውልዶች የዓድዋን ድል በተለያዩ መንገዶች ለመድገም መሞከራቸውንም ጠቅሰዋል። ለአርባ ዓመታት ተዘጋጅቶ ፋሽስት ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን መውረሩን አስታውሰው፣ የያኔው ትውልድ ደግሞ ይህን ወረራ በዓድዋ ወኔ በመቀልበስ በድጋሚ ለሉዓላዊነቱ ቀናኢ መሆኑን አሳይቷል ሲሉ አመልክተዋል።

ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመት በወረረበት ወቅት አርበኞች በዱር በገደል ሆነው እረፍት በመንሳት ብዙ ትግል ማድረጋቸውን ገልጸዋል። እንደገናም በሶማሊያም እንዲሁ ሁለት ጊዜ(በ1956 እና በ1969) ሀገር የመድፈር ሙከራዎች ተደርገው እንደነበር አስታውሰው፣ ኢትዮጵያውን ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ማስጠበቃቸውን ጠቅሰዋል።

አሁን ድረስ እየተሠሩ ያሉ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ፣ ሀገር የማሳደግ፣ የማዘመን ጥረቶች ማሳያዎች መሆናቸውንም ያመላክታሉ። ለዓድዋ ድል መታሰቢያ መሥራት እንደ ትልቅ ነገር ሊወሰድ የሚችል መሆኑንም ይገልጻሉ።

ጥረቶቹ የሚበረታቱ ሆኖ ሳለ የተሠራው ሥራ ግን በዓድዋ ልክ ሠርተናል ብለን የምንኩራራበት አይደለም ያሉት ረታ/ዶክተር/፣ ወደፊት መሠራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች እንዳሉም ይጠቁማሉ። ሀገሪቷ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ሁሉንም እያሰባሰበች ያለች ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ጠንካራ ተቋማት መገንባት እና ሕዝብንና ሀገርን በኃላፊነት ማገልገል ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዓድዋ ድል ትልቅ ድል በመሆኑ በወታደራዊ አካዳሚዎች ታሪኩ ይጠቀሳል ሲሉ ገልጸዋል። ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ፤ የአሜሪካ ወታደራዊ አካዳሚ እስካሁን የዓድዋን ድል አስመልክቶ እንደሚያስተምር ጠቅሰዋል። በዚህም ኢትዮጵያውያን እንዴት በምን ስትራቴጂና ቴክኒክ አሸነፉ የሚለው በትምህርቱ እንደሚዳደሰስም ተናግረዋል።

‹‹እኛም የተሠሩ ሥራዎችን እያበረታታን በዚያ ደረጃ ሀገራችንን ከፍ አድርገን መሥራት አለብን፤ ዓድዋ በፈጠረው መንፈስና ስሜት በአንድነትና በእኩልነት በሀገራዊ ስሜት ሀገር ለማሳደግና ሕዝብን ለማገልገል፣ ሁላችንም ባለንበት የሥራ ዘርፍ በቅንነት፣ በታማኝነት መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ›› ብለዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የዓድዋ ድል ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ታሪክ የያዘ ድል በመሆኑ ትውልዱን በዚህ ላይ በሚገባ መቅረጽ ይገባል። ይህም ስለ ድሉ ብዙ ማስተማርን ይጠይቃል። የዓድዋ ድል በተለያየ ደረጃ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካትቶ ትውልዱ እንዲማርበትና በድል መንፈስ ለሀገሩ እንዲሠራ ማድረግ ያስፈልጋል።

ጠንካራ ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት እንዲኖሩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትም ይጠቅማል። ዘመናዊ የፖለቲካ አካሄዶች እንዲኖሩ በሰላም መታገልን መለማመድ እንደሚያስፈልግ፣ ለሰላም መወያየት፣ መከራከር፣ መደራደር በሰላማዊ ሁኔታ የሀገሪቷን ፖለቲካ ማሳደግና ዲሞክራሲን ማስፋፋትና ሀገር ማሻገር ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You