
በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል፤ ስለ ኢትዮጵያ ጥበብና ስልጣኔም አበርክቶው ይጠቀሳል፤ በሰሜኑ መስመር ለሚመጡ ሁነትና ክስተቶች የመሸጋገሪያ መድረክም ሆኖ ከትናንት እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡ የለውጥና አብዮቶች ጓዳም ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል፤ የትግራይ ሕዝብና ክልል፡፡
የትግራይ ሕዝብ በተለይ ላለፉት ሃምሳ እና ስልሳ ዓመታት፤ የተለያዩ ጥያቄዎችን በሚያነሱ ኃይሎች መዳፍ ተይዞ ጊዜውን በጦርነት፣ ትውልዱን ለእልቂት የዳረገ የዓለም ሕዝብ ነው፡፡ ስለ ልማት፣ ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ አብሮነት፣ ስለ ብልፅግናና ሌሎችም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ አጀንዳዎቹ ሲል በዘመናት ሂደት ለከፈለው ዋጋም የሚገባውን ሳያገኝ ለጥቂት ቡድኖች ፍላጎት ተገዢ እንዲሆን እየተገደደ ይገኛል፡፡
ስለ ዴሞክራሲ ታግሎ ዛሬም ዴሞክራሲ ከስም የዘለለ ያልተገለጠለት፣ ስለ ሰላም ዋጋ ከፍሎ ዛሬም የሰላም አየር እንዳያገኝ ለተደጋጋሚ ጦርነት እየተገፋ ያለ፣ ስለ ልማትና ብልፅግና ልጆቹን ገብሮ ዛሬም የልማት ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ ለተጨማሪ መስዋዕትነት ልጆቹን እንዲሰጥ የሚገደድ ሕዝብ ሆኗል፡፡
በእዚህ ረገድ ከ2010ሩ ለውጥ ማግስት የተፈጠረው ከፍ ያለ የሀገራዊ ሪፎርም ሂደት ውስጥ መራመድ ያቃታቸው ሰዎች የተከተሉት ያልተገባ መንገድና የፈጠሩት ችግር፤ ክልሉን በተለይም ሰሜን ኢትዮጵያን ለግጭትና ጦርነት ዳርጎት ቆይቷል፡፡ ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው በዚህ ጦርነትም የሕይወት እና የአካል እንዲሁም ከፍ ያለ የንብረት ጉዳት መድረሱ የሚታወቅ ነው፡፡
ይሄን ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ደግሞ፣ በመንግሥት በኩል ከፍ ያለ የሰላም አማራጮችን በመንደፍና ለእዚሁ እውን መሆን ሳይታክት በመሥራት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲፈጸም እና ለሰሜን ኢትዮጵያ መረጋጋት ትልቅ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የትግራይ ክልልን ጨምሮ አጎራባች ክልሎች ፊታቸውን ወደ ሰላምና ልማት እንዲመልሱ እድል ሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬም በክልሉ ያሉ ኃይሎች በተለያየ መልክና ሁኔታ ውስጥ በመጓዝ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲርቅ፤ ውጥረት እንዲነግስ፤ የሕዝቡም የልማትና የመልካም አስተዳደር እንዳይመለስ አካባቢው በጦርነት እሳቤ እንዲጠመድ የሚያደርጉ ተግባራትና እንቅስቃሴዎች እየታዩ ይገኛል፡፡
ይሄ ደግሞ ዘመናትን ዋጋ ሲከፍል፤ ሁለትና ሦስት ትውልዶችን በሕዝብ ጥያቄ ስም ሲገብር፤ አያሌ ወጣቶች እንዲሰደዱ፣ ሕጻናት ያለ አሳዳጊ፣ አረጋውያንን ያለ ጧሪ የማስቀረት መንገድ ነው፡፡ ሕዝቡ ሰላም ሲፈልግ የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንዲገባ፣ ልማት ሲጠይቅ ወደ ጦርነት እንዲያመራ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያነሳ አፈናና ጭቆና እንዲጫንበት የማድረግ ጉዞም ነው፡፡
ዛሬ ላይ የክልሉን ብሎም የአጎራባች ክልሎችን፣ አልፎም ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ችግር እንዲሆን የታሰበውን ጦርነት፣ በሰላም ቋጭቶ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ለተፈጻሚነቱ እየተሠራ እና ውጤትም እየታየ ባለበት በዚህ ሰዓት፤ ስምምነቱን በማይመጥን መልኩ ክልሉን ሰላምና ልማት እንዲርቀው ለማድረግ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችም የክልሉን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ያልተገነዘቡ፤ ይልቁንም ለራስ ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ሕዝቡን መጠቀሚያ የማድረግ አካሄዶች ናቸው፡፡
ምክንያቱም፣ ዛሬ ላይ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና ልማት እንጂ ጦርነት አይደለም፡፡ የትግራይ ወጣቶች የሚሹት የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆንን እንጂ ጠብመንጃ አንግቶ እርስ በርስ መዋጋትን አይደለም፡፡ የትግራይ እናቶች የሚሹት የልጆቻቸውን ብሩህ ነገ ማበጀትን እንጂ ቂምና በቀልን ማውረስ አይደለም፡፡ አረጋውያኑ ስለ ሀገር ሲሉ አካላቸውን የገበሩ አካል ጉዳተኞች፣ ሕጻናቱ እና ሌሎችም የሚሹት እንደ ሀገር የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ተቋዳሽ መሆን ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ግን ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ጥቅምና ፍላጎትን መነሻ አድርገው የሚታዩ ያልተገቡ አካሄዶች የትግራይ ሕዝብ ፍላጎትም፣ ሃሳብም አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በወጣቶች የጦርነት ይብቃ፣ ሰላምና ልማት እውን ይሁን ድምጽ እየተሰማ ያለው፡፡ ለእዚህም ነው የትግራይ ሕዝብ ስለ ሰላም መነጋገርና መግባባትን፣ ስለ ልማት በጋራ መቆምን የሁሉም ነገር ማሰሪያ መሆኑን ደጋግሞ ሲናገር የሚደመጠው።በመሆኑም በክልሉ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ከግለሰባዊ እና ቡድናዊ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ፤ ለትግራይ ሕዝብ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ብልፅግና ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም