የኮሪያ እና የኮንጎ ጀግኖች ሲታወሱ

ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ነች። በተለያዩ አውደ ግንባር የተዋደቁ እና ዳርድንበሯን ሳያስደፍሩ ለዛሬው ትውልድ ያስተላለፉ በርካታ የሀገር ባለውለታዎችን ያፈራች ሀገር ነች። ከዓድዋ እስከ ዶጋሌ ፣ ከማይጨው እስከ ኮሪያ እና ኮንጎ በመዝመት ጀግንነታቸውን በዓለም መድረክ ያስመሰከሩ ስመ ጥር ጀግኖች ከአራቱም ማዕዘናት ይገኛሉ። ከእነዚህ ጀግኖች ውስጥ አንዱ በሁለት አውደ ግንባር ተሰልፈው ሰንደቅ አላማዋን ከፍ ያደረጉት አርበኛ ላቀው ኪዳኔ አንዱ ናቸው።

አርበኛ ላቀው ኪዳኔ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥያቄ መሠረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1951 ወደ ኮሪያ እንዲዘምቱ ጥሪ ካቀረበችላቸው የቃኘው ሻለቃ ጦር ሠራዊት አባላት መካከል አንዱ ናቸው። ወታደር ላቀው ከኮሪያ ዘመቻ መልስ በቀጥታ ባልበረደ ወኔ ወደ ኮንጎ ለመዝመት የበቁ ጀግና ወታደርም ናቸው፡፡

የ87 ዓመቱ ወታደር ላቀው እንደሚያስታውሱት፤ ያኔ ኮሪያ ሲዘምቱ ታላቅ ወንድማቸው ሙሉነህ ላቀውም አብረዋቸው ነበሩ። ስሙ በታላቅና ታናሽነት ይጠራ እንጂ ዕድሜያቸው ብዙም ርቀት አልነበረውም። ኮሪያ ሲዘምቱ ታላቃቸው የ17 እሳቸው ደግሞ የ15 ዓመት ዕድሜ ታዳጊ ልጆች ነበሩ።

ሁለቱም በክቡር ዘበኛ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆዩ ነው የቃኘው ሻለቃ ጦር ሠራዊት አባል በመሆን ሰላም ለማስከበር ወደ ኮሪያ የዘመቱት። እሳቸውና ወንድማቸው በአባታቸው በቤት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ወታደራዊ የሚመስል ሥነሥርዓት እንዲተገብሩ ተደርገው ከማደጋቸውና በአካባቢውም የአባታቸውን ጀግንነት የሚመስል ወኔ ታንፀባርቃላችሁ ከመባላቸው ውጪ ልጆች በመሆናቸው ስለ ውትድርና ሙያ በጥልቀት የሚያውቁት ብዙም ዕውቀት አልነበራቸውም። በተለይ ኮሪያ ሲዘምቱ ስለውጊያ የነበራቸው ዕውቀት ብዙ አልነበረም፡፡

አቶ ላቀው ኮሪያ ከመዝመታቸው በፊት አሁን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ ተብሎ በሚጠራው ፊት ለፊት ባለውና ‹‹ዘበኛ ሰፈር›› እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ውስጥ ቀኑን ሙሉ ኳስ በመጫወት ያሳልፉ እንደነበርም ያወሳሉ። ታድያ አንድ ቀን አባታቸው ከዚሁ ኳስ ሜዳ መጡና ሁለቱንም ወደ ክቡር ዘበኛ ወስደው አስረከቧቸው። ኳስ ጨዋታው በዚሁ ተቋጨ፡፡

ሥራ መቀጠራቸውን ሁሉ ያወቁት ‹‹ይሄን አድርጉ፤ ይሄን አታድርጉ ››የሚል ትዕዛዝ ሲሰጣቸውና ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲነገራቸው ነበር። የወንድማቸውን ለጊዜው እኛ ስንጠይቃቸው ትዝ ባይላቸውም ሥራውን ሲቀጠሩ እሳቸው የሦስተኛ ክፍል ደረጃ የቀለም ትምህርት እንደነበራቸውም ያወሳሉ። እናም ክቡር ዘበኛ በሬዲዮ ኦፕሬተር ሙያ አሠለጠናቸውና እዛው ክቡር ዘበኛ ውስጥ መሥራት ጀመሩ። አሁን ሲያስቡት አባታቸው ወደ ወታደር ቤት የወሰዷቸው ልጆቻቸው የጀግንነት ወኔያቸውን እንዲወርሱላቸው አስበው ሊሆን እንደሚችልም ይገምታሉ፡፡

እንደ ዕድል ሆኖ ወንድማማቾቹ እ.ኤ.አ በ1951 ወደ ኮሪያ ዘመቱ ። የዘመቱት ወታደራዊ ግዳጅ ተብሎ ብቻ ስለተጫነባቸው ብቻ ሳይሆን በሙሉ ፈቃደኝነት ነበር። ወንድማቸውም ሆኑ እሳቸው ለዘመቻው መመልመላቸው ጮቤ እስኪረግጡ አስደስቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በእርግጥ ደቡብ ኮሪያን የመርዳት ተግባሩ የተቀደሰ ነው ባይ ናቸው። ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ ሀገር የማየት አጋጣሚውም በራሱ እንደ ታዳጊ ወጣት የሚፈልጉት ነበር። በዚህ ሁሉ ምክንያት በወኔ ነው የዘመቱት። እንደውም የያኔ ስሜታቸውን አሁን ላይ ሲያስቡት በቀጥታ የአባታቸውን የጀግንነት ወኔ በመውረሳቸው የተፈጠረ ነው ብለው ያምናሉ። ወታደር ላቀው ገና ከኢትዮጵያ ሲነሱ ጀምሮም የነበረውን የዘመቻ ሂደቱን አሁን የሆነ ያህል ያስታውሱታል፡፡

ከአዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ መነሻቸው የነበረው ጃንሜዳ ነበር። እዚህ የመጡት ማክ በሚባል ወታደራዊ መኪና ነው። ከጃንሜዳ ደግሞ በባቡር ወደ ጅቡቲ አመሩ። አሁን የቀናቶቹን ቁጥር ባያስታውሱትም ከጅቡቲ ከ20 ቀናት በላይ ተጉዘው ነበር የኮሪያ ባህር በር ፑዛን የገቡት።

በ15 ዓመታቸው ወደ ኮሪያ ሲያቀኑም እሳቸው የከባድ መሣሪያ ሻምበል ከሆነው አራተኛ ሻምበል ታላቅ ወንድማቸው ደግሞ የደረጃ ጦር ከነበረው ሦስተኛው ሻምበል ጋር ተቀላቅለው ዘመቱ። እሳቸው የነበሩበት የመትረየስ የ100 የሬዲዮ መገናኛ ኦፕሬተሮችን እና 36 ወታደሮችን አቅፎም የያዘ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሰፈር የ100 አለ፤ የመቶ 81 የሚባልም ነበር። ከባድ አዳፍኔ የመቶና በቀጥታ የሚተኩስ መሣሪያ የሚያስተናግድ 75 የሚባልም ነበር። ታድያ የሻምበሉ አዛዥ ሻምበል ፀጋዩ ጣሰው ሲሆኑ፤ የእሳቸው አለቃ ደግሞ መኮንን ወልዴ ይባላሉ። ሁሉንም አጠቃሎ የያዘው ደግሞ የቃኘው ሻለቃ ጦር ይባላል፡፡

ወታደር ላቀው በአጭር በአጭሩ እንዳወጉን የኮሪያ ጉዞ በየዙሩ ነው የተካሄደው። ዙሮቹ እስከ አራት ይደርሳሉ። ታድያ እሳቸውና ታላቅ ወንድማቸው የመጀመሪያው ጦር ከዘመተ ብዙ ዘግይተው ነበር ወደ ዘመቻ የሄዱት። በተለይ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር ወደ ኮሪያ የዘመቱት ኢትዮጵያውያን ብዙ መስዋእትነት የተከፈለበት የጦርነት ውጊያ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ግግር በረዶ ላይ የተቀበሩ ፈንጂዎች ከማምከን ጀምሮ በደፈጣና በሽምቅ ውጊያ በከፍተኛ ወኔ ተሳትፈዋል። ተሰውተዋል፡፡

በሁለተኛው ዙር የተጓዘው ‹ቲቮ› በተሰኘው ከፍተኛ በረዷማ ተራራ ላይ በተደረገው ውጊያ ሁሉ በመሳተፍ የላቀ መስዋእትነት ከፍለዋል። በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙኒስቶች እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች የነበራቸው ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ ሀገር የመሆኗ ምስጢርም ይሄው የሠራዊቱ ብቃትና በወኔ የመሳተፍ ጉዳይ ነው ብለው ያምናሉ። ብዙዎች የሚሰዉት የተሰዉትን ጓዶቻቸውን ተሸክመው ለማዳን ሲሉ እንደነበረና ጀግንነታቸው እዚህ ድረስ የዘለቀ እንደሆነም ያክላሉ።

የሄዱበትን አላማ በኋላ እንደተረዱት ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን በመውረሯ ነው የኢትዮጵያውያኑ እገዛ ያስፈለገው። በአጭሩ ደቡብ ኮሪያን መርዳት ነበር የዘመቻው ዓላማ ፡፡ታድያ በወቅቱ ወንድማቸውና እሳቸው የተለያዩት ኮሪያ ባሕር በር ፑዛን ሲደርሱ ነበር። ታላቃቸው በሽምቅና ደፈጣ ውጊያ ለመሳተፍ በሚያስችለው ቡድን ተቀላቅለው ሲሄዱ፤ እሳቸው በበኩላቸው በፑዛን ለተወሰነ ቀን አረፉና በመገናኛ ሬዲዮ ኦፕሬተር ሙያቸው ወደ ሌላ ቦታ ሄዱና ግዳጃቸውን ለመወጣት በቁ። ግዳጃቸውንም በብቃት በመወጣት የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት አስመስክረው ተመለሱ፡፡

በኮንጎ ዘመቻ የተሳተፉት ደግሞ ከዚህ ከኮሪያ ዘመቻ መልስ ነው። ታላቅ ወንድማቸው ከዓመታት ቆይታ በኋላ ከኮሪያ ዘመቻ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም በኮንጎ ዘመቻ አልተሳተፉም። እሳቸው ኮንጎ የዘመቱት ከኮሪያ ዘመቻ መልስ ራሳቸውን በትምህርት መለወጥ የሚያስችል ተግባር ሲከውኑ ቆይተው ነበር። ከኮሪያ መልስ ተግባረዕድ በመግባት በሬዲዮ ቴክኒሻል ሙያቸው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡

እናም ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ዳግመኛ በኮንጎ ዘመቻ ሊሳተፉ የቻሉት። ወታደር ላቀው ኮንጎ ሲሳተፉም ወኔያቸው አልበረደም። በኮሪያው ዘመቻ፤ ከዘመቻው ቀደም ብሎ የወሰዱት የስምንት ወር ያህል ወታደራዊ ስልጠና ከወታደሩ አባታቸው ከወረሱት የጀግንነት ዕውቀት ጋር ተዳምሮ ለኮንጎው ዘመቻ ወኔ አስታጥቋቸውም ነበር። ይሄኔ ታድያ ወታደር ላቀው በዕድሜም ቢሆን ጎልብተዋል፤ አስተሳሰባቸውም የዚያኑ ያህል ጨምሯል።

ወደ ኮንጎ ዘመቻ ሲሄዱ ከአዲስ አበባ ተነስተው ጅቡቲ ድረስ ዘልቀው ነበር ኮንጎ መድረስ የቻሉት ጉዞውም በመርከብ ነበር። ከመርከብ ወርደው ወደ ኮንጎ ዋና ከተማ ሌዎፓልድቪል መጓዛቸውን ያወሳሉ። ይሄ ከተማ አሁን ኮንጎ ኪንሻንሳ ይባላል፡፡

በኮንጎ ውጊያ ከባድ የሚባል ጦርነት ባይኖርም አልፎ አልፎ የእርስ በእርስ ግጭት የሚቀሰቅሱና ወደ ከባድ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ችግሮች ነበሩ። በአንድ ወቅት በዋና ከተማዋ ግጭት ተቀስቅሶ እሳቸውን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩት ወታደሮች ግጭቱን በመቆጣጠር አብርደው ከተማይቱን ከጥፋት ያዳኑበት ሁኔታም እንደነበረ ያወሳሉ።

ኮንጎ ለዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥሩ አቀባበል ተደርጎለት ለእያንዳንዱ ወታደር ድንኳን ተሰጥቶት ከዓመት በላይ በመልካም ሁኔታ እንደቆየ ይናገራሉ። በኮሪያም ሆነ በኮንጎ ዘመቻዎች እንደታዘቡት ፍራፍሬና አትክልት በደንብ በመኖሩ የሚበላ ነገር ችግር የለም። የተባበሩት መንግሥታት የሚያመጣቸው የታሸጉ ምግቦች በአብዛኛው በተለይ ሥጋ ነክ ነገሮቹ ከኢትዮጵያ አመጋገብ ሥርዓት ውጪ የሆነና ያልተለመደ በመሆኑ ከፓስታና ሩዝ ውጪ አዘውትረው አትክልትና ፍራፍሬ ይመገቡ እንደነበርም ያወሳሉ፡፡

እሳቸው ባያጋጥማቸውም አንዳንድ ባልደረቦቻቸው በእረፍት ጊዜያቸውና በሥራ ምክንያት ኮንጎ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አካባቢዎችን የማየት ዕድሉ ነበራቸው። ወታደር ላቀው የዘመቻ ግዳጃቸውን አጠናቅቀው የተመለሱት ከዛችው ከተመደቡባት ሌዎፓልድቪል ሳይወጡ ነው። ወንድማማቾቹ እነ መንግሥቱን ነዋይና ግርማሜ ነዋይ በአፄ ኃይለስላሴ ላይ የተሳተፈበት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲያደርጉ እሳቸው እዚህች ከተማ ነበሩ። ዜናውንም እዚያው ሆነው ነው የሰሙት። መኮንኖቹ በሙሉ ታዲያ አፄ ኃይለስላሴን የሚቃወሙና የ18 ብር ደመወዝ መሻሻል አለበት የሚል ሃሳብ የሚያራምዱ ነበሩና ይሄን የሰሙ ሰሞን ተደስተው ነበር፡፡

በኮንጎ የተሠማራው የኢትዮጵያ ወታደር ግዳጁን ጨርሶ ሲመለስ የክቡር ዘበኛ ቤት እንደ በፊቱ አልሆነላቸውም። በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ብዙ ሰዎች ተቀይረዋል። ስለዚህ በሬዲዮ ኦፕሬተር ሙያቸው ያገኙትን ዲፕሎማ ይዘው ፕሊፕስ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ካምፓኒ ተቀጠሩ። ከ18 ብር ወደ 1ሺህ 200 ብር ያደገ ለውጥ ማየት በራሱ ለእሳቸው አስደሳች ነበር፡፡በዚህ ላይ የራሳቸው መኪና ተሰጥቷቸው በየሰው ቤት እየዞሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን መጠገን ጀመሩ። እዚህ ካምፓኒም ለ17 ዓመታት ሠርተው ጡረታ ወጡ፡፡በዚሁ መካከል ትዳር መስርተው ለ17 ዓመት ቆይተዋል። በኋላም ሁለት ልጆች መውለዳቸውን አጫውተውናል፡፡

በአጠቃላይ የኮሪያና የኮንጎ ዘማች የሆኑት ወታደር ላቀው ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነት ተናግረው አይጠግቡም። ጥንት በዓድዋ የታየው የኢትዮጵያውን ደፋርነትና ልበ ሙሉነት በኮሪያና በኮንጎ መደገሙን ይናገራሉ። በሁለቱም ጦርነቶች ኢትጵያውያን ጀግኖች መሆናቸውን ማስመስከራቸውን ያወሳሉ፡፡ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ዳር ድንበር ከማስከበራቸውም ባሻገር የተለያዩ ሀገራት ነጻ እንዲወጡ በጀግንነት ተሰልፈዋል፡፡

የዓድዋ ጦርነትን ኢትዮጵያ በአሸናፊነት መወጣቷን ብዙዎች በጥርጣሬ ሲመለከቱት ቆይተው ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያውያን በኮሪያና በኮንጎ በፈጸሙት ገድል የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን እንደሚገባ ዓለም በሙሉ እንዲረዳ እንዳደረጉት ወታደር ላቀው ይናገራሉ። በኮንጎም ሆነ በኮሪያ ጦርነት ከበርካታ ሀገራት የተሳተፉ ወታደሮች ቢኖሩም የኢትዮጵያውያንን ያህል ቆራጥና ልበ ሙሉ እንደሌለም ይመሰክራሉ፡፡

ሆኖም በኮሪያም ሆነ በኮንጎ ለተሳተፉ ጀግኖች ተገቢው ክብር ተሰጥቷል ብለው እንደማያምኑ ወታደር ላቀው ይናገራሉ፡፡እንደውም ተረስተዋል የሚል ቁጭት አላቸው። ለዚህ ደግሞ እሳቸው በሁለቱም ጦርነቶች ገድል ፈጽመው ቢመለሱም ያስታወሳቸው አካል እንደሌለና ኑሯቸውም በድህነት የተሞላ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከሚያገኙት 300 ብር ጡረታና አፍንጮ በር ናይጄሪያ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘውና “የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ” ተብሎ የተሰየመው ማህበር ከሚሰጣቸው መጠነኛ ድጋፍ ውጪ በቂ ገቢ እንደሌላቸው ያስረዳሉ።

ወታደር ላቀው እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት እሳቸው በሕይወት ቢቆዩም አብዛኞቹ የኮሪያም ሆነ የኮንጎ ዘማቾች በሕይወት የሉም ፡፡‹‹ከስድስት ሺህ በላይ የኮሪያ ዘማቾች በሕይወት ያሉት 80 እንኳን አይሞሉም። እነሱም በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት። በተለየ የኮንጎዎቹ ማህበር እንኳን ስለሌላቸው ሕይወታቸውን እንኳን የሚያቆዩበት ዕድል ሳይኖር አስታዋሸ አጥተው በመጠለያና በምግብ እጥረት ይሰቃያሉ። ስለዚህ መላው ኢትዮጵያውያን የእነዚህ ጀግኖች ታሪካዊ አደራ አለበትና ሊያስታውሳቸው ይገባል›› የሚል መልዕክት በማስተላለፍ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You