ፈጣን መፍትሄ ለፈጣን መንገድ

ፈጣን የክፍያ መንገድ እጅግ ምቹ፣ የትራፊክ መጨናነቅ ፈፅሞ የማይታይበት፣ በተፈለገውና በተፈቀደው የፍጥነት ገደብ አሽከርካሪ ቢጓዝበት መልካም መሆኑን መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከሌላው ዓለም ዘግይታም ቢሆን በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት ወዲህ የፈጣን ክፍያ መንገድን ጣእም በትንሹም ቢሆን ማጣጣም ከጀመረች ሰንብታለች።

ዛሬ ላይ የፈጣን መንገዶችን ምቾት ለመመስከር በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ አይጠይቅም። ለቅምሻም ቢሆን ከአዲስ አበባ አዳማ ወይም ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ ከመቶ ያልበለጠ ኪሎ ሜትር መጓዝ ስለመንገዱ ትንሽም ቢሆን ሃሳብ ለመሰንዘር በቂ ነው።

ታዲያ ይህ መንገድ ምን ምቹ ቢሆን በድንገት አደጋ እንዲከሰት የሚያደርጉ እንቅፋቶችና በርካታ የሕይወትም ሆነ የንብረት ውድመትን የሚያስከትሉ ችግሮች እየተስተዋሉበት እንደሆነ ምስጢር አይደለም። ዘንግተን ካልሆነ በቀር አንድ ሙሉ ሚኒባስ ሰው በዚሁ መንገድ ላይ ወጥቶ የቀረበት ዘግናኝ የትራፊክ አደጋ የሚረሳ አይደለም። የዚህ ፈጣን መንገድ ፍላጎትና ተጠቃሚ በእጅጉ እያደገ ስለመምጣቱ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በየጊዜው ከተጠቃሚዎች ሰበሰብኩት ብሎ ከሚነግረን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መረዳት ይቻላል። ለዚህም ነው መሰል ከአዲስ አበባ ሃዋሳ የሚዘልቅ ተጨማሪ ፈጣን የክፍያ መንገድን ምቾት እንድናጣጥም በቅርቡ ተመርቆልናል። በእርግጥ ይህ መንገድ ገና በመሠራት ላይ ያለ ቢሆንም ከአዲስ አበባ እስከ ባቱ ያለው ብቻ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ክፍት ሆኗል። ይህ እስከ ሃዋሳና ከዚያም አልፎ ረጅም ርቀት አቋርጦ እንደሚዘረጋ የሚነገርለት መንገድ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ እስከሚገኝበት ከተማ ድረስ ለሀገርና ሕዝብ እያበረከተ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ከጥቅሙ ጎን ለጎን እያጎደለ ያለው ነገር ግን እያየን ያላየን አይተንም ያላስተዋልነውን እንድናጤን ይረዳል። በእርግጥ በዚህ መንገድ የሚስተዋሉ ነገሮች ቀደም ብሎ ከተሠራው የአዲስ አበባ አዳማ ፈጣን መንገድ የተለዩ አይደሉም። የተለዩ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር ግን በንብረትና በተለያዩ የዱርና የቤት እንስሳት ላይ የሚከሰቱ አደጋዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ነው። መንገዱን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የመጠቀም ልማዱም በዚሁ መስመር ጎልቶ እየታየ ስለመምጣቱ እግር ጥሎት ወደ ስምጥ ሸለቆዎቹ ከተሞቻችን የተጓዘ አይጠፋውም።

በዚህ የፈጣን መንገድ መስመር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ እንደ ጥይት እየተተኮሱ በሚበሩ ተሽከርካሪዎች ፍጥነት ውስጥ ገብቶ የትኛውም ነብስ ያለው ነገር በራሱም ይሁን በሌሎች ላይ አደጋ እንዳያስከትል የተለመደ የሽቦ አጥር ተሠርቶ ይገኛል። ይህን አጥር እንዲህ ለማለት በማይቻል መልኩ አልፈው የሚገቡ የቤትና የዱር እንስሳት አልፎ አልፎ ሰዎች የአደጋው መንስኤ ናቸው።

ታዲያ ይህ ሁሉ ችግርና አደጋ ሲከሰት ጥፋተኛው ማን ነው? ማነው ተጠያቂው? ሾፌሩ ነው ወይስ ሌላ? ወይስ የክፍያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት?። ጥፋቱን በአንድ ወገን ላይ ብቻ ማላከክ ፍታዊ አያደርግም። ሁሉም ወገን ለዚህ ችግር የራሱ ድርሻ አለው። የፈጣን መንገዱ ውስጥ ሰውም ይሁን እንስሳቶች ድንገት ገብተው አደጋ እንዳይፈጠር የሽቦ አጥር የተሠራ ቢሆንም፣ ይህን አጥር በየቦታው በማፍረስ ወይም ቀዳዳ በማበጀት በየመንገዱ ሰዎችና እንስሳት እንዲሁም ንብረት ላይ ለሚከሰቱ አደጋዎች መቼም እንስሳቱን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። መንገዱ አቋርጦ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ያለው ማህበረሰብ እንዳጠቃላይ የዚህ ችግር መንስኤ ባይሆንም ጥቂት ግለሰቦች በየመንገዱ ጥግ ለከብቶች ግጦሽ ሲሉ የሽቦውን አጥር በማፍረስ ወይም ቀደው እንስሳቱን ወደ መንገዱ ሲያስገቡ ይታያል።

መንገዱ ከክፍያ መንገድ መግቢያ እስከ መውጫ ድረስ እንኳን ሁለት ተቀባባሪና አብሮ ነዋሪ ጎረቤታሞችን የለየ እንደመሆኑ መጠን፣ ሁለቱ ግራና ቀኝ ያሉ ተጎራባች የነባር ቀዬዎቹ ባለቤቶች እንደ ልብ መንገዱን ተሻግረው ቡና ባይጠጡ እንኳን ለችግር መደራረስና መጠያየቅ የሚችሉ አይመስልም። ችግሩ እንግዲህ ቀደም ብሎ የተከሰተ ቢመስልም እንስሳቱ እየገቡ ያሉት ምናልባት መንደርተኞቹ በቀደዱት አጥር፣ ወይም መጠገን ሲገባው ትኩረት ባልተሰጠውና ባልተጠገነው አጥር ዘለው ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፡፡

ጉዳዩ አሳሳቢ የመሆኑን ያህል አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል ቢባል ማጋነን እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ምነው የሀገራችን ትራፊክ ፖሊስ ፈጣን መንገድ መግቢያው ላይ በመሆን በርካታ ሾፌሮችን በጥፋተኝነት ሲቀጡ ይውላሉ፣ ያመሻሉ፡፡ ቅጣቱስ ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ትራፊክ ፖሊስ የመንገዱን አደገኛነት፣ ሊከሰሱና በደንብ መተላለፍ ምክንያት ሊቀጡ የማይችሉ እንስሳትን ችግር ለበላይ ኃላፊዎቻቸው ሳይታክቱ ምን ያህል አመልክተው፣ የውሳኔ ሃሳብስ አሰጥተዋል የሚለውን ለእነሱ እንተወው።

መንገዱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የክፍያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ በመንገዱ የውጭ ግራና ቀኝ በኩል ያለውን የሽቦ አጥር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶት ቢያስጠግን የመፍትሔ አካል ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል ፈጣን የክፍያ መንገዱ ሲሠራ በመንገዱ ግራና ቀኝ በኩል የሚገኙ ነዋሪዎችን እንደ ልብ የማያጠያይቅና የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ፈቺ አለመሆኑ በጥናት ከተረጋገጠ፣ ቢቻል በተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአዲስ አበባ መውጫው ላይ ቃሊቲ አካባቢና ሌሎችም መንገዶች ላይ እንደተሠሩት ድልድዮች ቢሠሩ የመፍትሄ አካል ሊሆን ይችላል፡፡

በፈጣን መንገዱ ላይ ሰዎችንና የተለያዩ የቁም ከብቶችን ማየት እየተለመደ ቢመጣም አንድ ቦታ መቆም አለበት፡፡ እነዚህ እንስሳት በፍጥነት መንገዱ የቀን ተቀን እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጣሪዎች በመሆናቸው፣ የእነዚህ እንስሳትና ተሽከርካሪ ባለቤትና የክፍያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በጋራ ሆነው ወይም በተናጠል ድርሻቸውን ቢወጡ፣ እንደ ቀልድ የሚጠፋውን ሕይወትና ንብረት መታደግ ይችላሉ።

ህሊና ሰብስቤ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You