
ኢትዮጵያ በዕድገት ወደ ኋላ ከቀረችባቸው ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛው ለባለሙያዎች ተገቢውን ክብር መስጠት አለመቻሏ መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ ቀደም ካለው ጊዜ አንስቶ የእጅ ባለሙያዎችን ከማክበር ይልቅ ቀጥቃጭ፣አንጥረኛ፣ አፈር ገፊ፣ መጫኛ ነካሽ ወዘተ እየተባለ ክህሎት ያላቸው ሰዎች እንዲሸማቀቁ እና እንዲገለሉ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ለባለሙያ የተሰጠው ቦታ ዝቅተኛ መሆኑም ፈጠራ እንዳይስፋፋ እና ክህሎቶች እንዳያድጉ ከማድረጉም በተጨማሪ ሀገር ከባለሙያዎች ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታጣ አድርጓታል፡፡ ይህ ደግሞ የግብርና ሥራ ለዘመናት በኋላ ቀር አስተራረስ ዘዴ እንዲቀጥል እና የጎጆ ኢንዱስትሪም እንዳይስፋፋ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሆኖም ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ ስንመለከት የእድገታቸው ዋነኛ ምስጢር ባለ ክህሎቶችን ማክበር መቻላቸው ነው፡፡ ዛሬ ታላቅ ሀገር መሆን የቻሉትም ትናንት ክህሎት ያላቸው ዜጎቻቸውን ማክበር እና መጠቀም በመቻላቸው ነው፡፡
ይህንኑ በመረዳትም መንግሥት ለቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ የተለየ ትኩረት በመስጠት ዘርፉ ለዘመናት ሲያጋጥሙት ከቆዩ ችግሮች ለማላቀቅ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የተዛባውን አመለካከት ከማስተካከል ጎን ለጎን በተለያዩ አካባቢዎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማስፋፋት ዜጎች በስፋት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዋነኛ ዓላማ በሀገሪቷ ብቁ፣ ተነሳሽነትና የፈጠራ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በመፍጠር ዕድገትና ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው፡፡ ዘርፉ ጊዜው የሚፈልገውን የሰለጠነ ሰው ኃይል ለገበያ በማቅረብና ፈጠራንም በማበረታታት የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡
ቴክኒክና ሙያ ዜጎች በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረውም ሆነ በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን መቀየር የሚችሉበትን ሙያ የሚያስታጥቅ ከመሆኑ ባሻገር ኢንዱስትሪዎች ባልተቋረጠ መልኩ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል እንዲያገኙም የሚያስችል ነው፡፡ የስልጠና ዘርፉ የሚያፈራው የሰው ኃይል ከኢንዱስትሪው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለውና የሀገርንም የኢኮኖሚ አቅጣጫ የመወሰን አቅም ያለው ነው፡፡
ሆኖም በኢትዮጵያ በነበረው ሁኔታ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ በቂ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ በበቂ ሁኔታ ዘርፉን ለመደገፍ ተነሳሽነት ያልነበረው ከመሆኑም ባሻገር ከዘርፉ ተመርቀው የሚወጡትም ተገቢው ዕውቅናና ክብር የሚሰጣቸው አልነበሩም፡፡ በዚህም ምክንያት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ለሀገር ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ ማበርከት ተስኖት ቆይቷል፡፡
ከለውጡ ወዲህ ግን መንግሥት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን በማቋቋምና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማዕከላትን በማስፋፋት ለኢኮኖሚው ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በማድረግ ላይ ይገኛል፡ ፡ ሙያ ተቋማት ሲከፈቱ የአካባቢያቸውን ጸጋና ገበያ ማዕከል አድርገው እንዲከፈቱ በማድረግ፤ የተሻሻሉ ስልጠናዎች እንዲሰጡ በማድረግ እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ዘርፉ በሀገር ልማት ውስጥ ተፈላጊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም የተቋማቱን አቅም በማጠናከር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ጭምር በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲተኩ የማበረታታትና የመደገፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ዘርፉ ባገኘው ድጋፍም ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ምርታማነት እንዲያድግ፣ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር ብሎም በአመለካከቱም ሆነ በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል የማቅረብ ሚናውን ለማሳደግ ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ አጋዥ መሆን ጀምሯል፡፡ በተለይም የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት የሆነውን ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና ፈጠራን በማበረታታት ረገድ ዘርፉ የተጫወተው ሚና ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እየሰለጠኑ የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ወጣቶች ክህሎቶቻቸውን በማቀናጀት ኢትዮጵያን ለማነጽ ትልቅ አቅም የሚሆኑ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የብልፅግና ጎዳና የማይተካ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ለዘርፉም ሆነ ለባለሙያዎች የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም