የቱሪስት ፍሰቱን በአዳዲስ አማራጮች የማሳደጉ ጥረት የሚበረታታ ነው!

የዓለም ቱሪዝም ድርጅትን መረጃ ዋቢ ያደረገው በቅርቡ የወጣ መረጃ እንዳመለከተው፤ ኢትዮጵያ በቱሪስቶች ፍሰት መጨመር ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሀገር ውስጥም የውጭ ቱሪስቶችም ቁጥር እየጨመረ ስለመምጣቱ ከክልሎች የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሀገሪቱ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ ቅርሶችን በማደስ፣ በዩኔስኮ መመዝገብ ያለባቸውንም በማስመዝገብ በአጠቃላይ ለቱሪዝም ሀብቶች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ በኩል ብዙ ርቀት የተጓዘች እንደመሆኗ የተመዘገበው አፈጻጸም የሚገባት ነው። ተሠርቶ የመጣ ለውጥም ነው።

ሀገሪቱ አስቀድሞም በውጭም በሀገር ውስጥም ቱሪስቶች ለመጎብኘት ከበቂ በላይ አቅም አላት። የአያሌ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ባሕል ሀብቶች ባለቤት ናት፤ ከእነዚህም መካከል 12 የሚዳሰሱና አራት የማይዳሰሱ ቅርሶቿ በዩኔስኮ ተመዝግበውላታል። ከእነዚህ መካከል ጥቂት የማይባሉት በዩኔስኮ የተመዘገቡት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ተጨማሪ አቅሞች ተፈጥረውላታል፤ በገበታ ለሸገርና ለሀገር ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ መናፈሻ ፓርኮች፣ ሪዞርቶች ተገንብተዋል። እድሳታቸው የተጠናቀቀ ቤተመንግሥቶችና በኮሪዶር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ናቸው።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ሌላው የሀገሪቱ የቱሪዝም አቅም ሆኖ መጥቷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው የቆየው ይህ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ገና ከጀምሩ ውጤታማ መሆን እያስቻለ ነው። በእዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 19 ዓለም አቀፍ ሁነቶች የተስተናገዱ ሲሆን፤ ዘንድሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ66 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ተስተናግደዋል። በእዚህ ውስጥ የሚፈጠረው የቱሪዝም ዘርፉ እንቅስቃሴ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።

በዘርፉ የመጣው ለውጥ የእዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው። ለእዚህም የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ይፋ ያደረገው ደረጃም ሆነ በዘርፉ በክልሎችም ሆነ እንደ ሀገር እየታየ ያለው እድገት በችሮታ የመጣ አይደለም። ብዙ ተደክሞና ተሠርቶ የተገኘ ነው።

ለውጡ ከፍተኛ ቢሆንም በዘርፉ ካለው አቅም እንዲሁም ከተካሄደው ልማት አኳያ ሲታይ ከእዚህም በላይ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ለእዚህ ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተለመደው መንገድ ወጣ ባለ መልኩ ዘርፉ ላይ ለመሥራት እያከናወናቸው ያሉ ተግባሮች ትልቅ አቅም መሆን ይችላሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት በአማካይ የሚያጓጉዛቸውን ከ12 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ለእዚህ ዓላማ ታጭተዋል። እነዚህ መንገደኞች እንደቆይታቸው አዲስ አበባን ወይም ሀገሪቱን ሊጎበኙ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ለመፍጠር ታስቦ አየር መንገዱ የቱሪዝም ሚኒስቴርና ኢሚግሬሽን በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት አድርገዋል።

የትራንዚት መንገደኞች ሌላ አውሮፕላን እስከሚመጣ ድረስ ከተማዋንና ሀገሪቱን እንዲጎበኙ ማድረግ መቻል ከአየር መንገዱ መንገደኞች ብዛት አንጻር የቱሪስት ፍሰቱን መጨመር እንዲሁም ከቱሪስቶቹ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪም ማሳደግ ይቻላል።

ለእዚህ ትልቅ ሃሳብ ተፈጻሚነት የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ መረባረብ ይኖርባቸዋል። ሥራው ሙያዊ በሆነ መንገድ መከናወንም የሚኖርበት እንደመሆኑ እንደ አስጎብኚ ድርጅቶችና ከመሳሰሉት አብሮ መሥራት ይገባል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የክልል የሚመለከታቸው አካላትን፣ ሙዚየሞችን፣ ፓርኮችን ፣ ወዘተ ያሳተፈ መሆን ይኖርበታል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተለመደው የቱሪስት ምርት ጎን ለጎን አዳዲስ ምርቶችን ይዞ ለመቅረብ ባለው ቁርጠኝነት ሰሞኑን ደግሞ በዩኔስኮ ጂኦፓርኮችና ጂኦቱሪዝም ሀገሪቱ ከቱሪዝም ሀብቶቿ በሚገባ መጠቀም በሚያስችላት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም ተሞክሮ መቅሰም ያስቻለ ሰፊ መድረክ አካሂዷል።

ይህም ትልቅ ርምጃ ነው። ሀገሪቱ በርካታ ጥብቅ ፓርኮች፣ መልክዓ-ምድሮች፣ ወዘተ ያሏት እንደመሆኗ ከእዚህ በሚገባት መልኩ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ አሁንም ይበልጥ በቁጭት መሥራት እንዳለባት በመገንዘብ በእዚህ ላይ ለመሥራት መታሰቡ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ ያለው ቁርጠኝነት ሌላ ማሳያ ይሆናል።

በተለመደው መንገድ በተጠናከረ መልኩ መሥራቱ እንዳለ ሆኖ አዳዲስ የቱሪዝም ምርቶችን ይዞ በመምጣት ከዘርፉ የበለጠ ለመሆን በተጀመሩ ጥረቶች ተግባራዊነት መረባረብ ደግሞ ሌላው ሥራ ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You