
የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት፣ እጅግ የተከበረ ሙያ ነው። በዚህ ዘርፍ የተሰማራው ባለሙያም በቂ እውቀት ያለው፣ ሙያውን ፈቅዶና ወዶ የገባበት፣ ለሚያገለግለው ህብረተሰብም እውቀቱን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱን ሳይሰስት የሚሠራ ነው። ከከተማ እስከ ገጠር፣ በጦርነት ቦታ ፣ በወረርሽኝ ወቅት ጭምር ቦታና ሁኔታ ሳይመርጥ ሕይወቱን ሰጥቶ ሙያው የሚጠይቀውን ሃላፊነት በሚገባ የሚወጣ ነው።
ሳይማር ያስተማረውን ማህበረሰብ ዘር፣ እምነትና ቋንቋ ሳይለይ በእኩልነት የሚያገለግል ነው። እስካሁንም ባለው ሁኔታ የጤና ባለሙያው ሙያው ከሚያስገድደውም በተጨማሪነት በሠብዓዊነት ሀገሩንና ሕዝቡን እያገለገለ መሆኑ ለማንም ምስጢር አይደለም።
የጤና ባለሙያ ለሙያውም ሆነ ለባለሙያው ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሙያዊ ሃላፊነቱን በብቃት ይወጣል። ሀገሪቱ የምትከተለውን የጤና ፖሊሲ ውጤታማ በማድረግ ረገድም ሚናው ጉልህ ነው።
የጤና ሚንስቴር ለማኅበረሰቡ ጥራቱን የጠበቀ እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ የኅብረተሰቡን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል። በዚህ ሂደት የጤና ባለሙያው ሙያው በሚጠይቀው መሠረት ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። መንግሥትም ሕዝቡም ይሄንን በሚገባ ይረዳል፤ ሙያውንም ባለሙያውንም በዚህ ረገድ ያከብራል።
ባለሙያውም ይህን ሃላፊነቱን ሲወጣ ሙሉ ለሙሉ መብቱ ተከብሮለት፣ በቂ ክፍያ ተከፍሎት አይደለም። ለሙያው የገባው ቃልኪዳንና መሃላ ፣ ሀገራችን በቂ ክፍያን መክፈል የማትችል ሀገር መሆኗን በሚገባም ተረድቶ ፤ ያሉ ተግዳሮቶችን ሁሉ ተቋቁሞ ነው እያለገለ ያለው። ያም ሆኖ ግን የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ጊዜ የመብትና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ይህን ጥያቄ ለምን አቀረቡ የሚል ማንም አካል የለም፤ ተገቢ ጥያቄ ነው ።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው ልክ ተገቢው ምላሽ መሰጠት እንዳለበት ይታመናል። ሆኖም ግን ጥያቄውን ተከትሎ በአንዳንድ የጤና ተቋማት አካባቢ አድማ በሚመስል መልኩ አንዳንድ ባለሙያዎች ወደሥራቸው አለመግባት፤ ገብተውም ተገቢውን አገልግሎት ያለመስጠት ችግር ታይቷል። ይሄ ሊወገዝ የሚገባው ፣ ከአንድ ጤና ባለሙያ የማይጠበቅ ድርጊት ነው።
የጤና ባለሙያ በየሰኮንዶች በሞትና በሕይወት መካከል ያለችን ሕይወት የሚታደግ ነው። በደም መፍሰስ ሕይወቷን ልታጣ የምታጣጥር እናትን ሕይወት የሚቀጥል ነው። ይህንን ያህል ትልቅ ሃላፊነት ያለበት የጤና ባለሙያ በሥራው ላይ አለማግኘት ምን ያህል ደም የሚፈሳቸውን እናቶች፣ ህጻናት ፣ አረጋውያን … ሕይወት ሊያሳጣ እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም።
ይህንን የሚረዱ ባለሙያዎች ከሥራ ገበታቸው ላይ በመቅረት አድማ ለማድረግ የወሰዱት ርምጃ ከሞራልም ከሕግም አንጻር ተጠያቂ ያደርጋል። በሀገራችን ሕግ መሠረትም አድማ መምታትና ሥራ መቋረጥ ከሌላባቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች አንዱ የጤና አገልግሎት ነው፤ በመሆኑም አብዛኛው የጤና ባለሙያ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደ ወትሮው ሁሉ መደበኛ የጤና አገልግሎቶች ለማኅበረሰቡ ያለምንም መስተጓጎል እየሰጡ ነው።
እነዚህም ባለሙያዎችም ጥያቄ አላቸው፤ ነገር ግን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ጥያቄያቸው እንዲመለስ የሚፈልጉ ፣ ለገቡት ቃል ኪዳን እና መሃላ የሚገዙና ሙያውን የሚያከብሩ ናቸው። በየማህበራዊ ሚዲያው በሚያሰራጨው ወሬ ያልተፈቱ፣ ሀገርና ሕዝብን የሚያከብሩ ናቸው፤ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በተሳሳተ ስሜትና ስሌት ተነሳስተው ሀገርና ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከስህተታቸው ተምረው ወደ መደበኛ ሥራቸው ሊገቡና ማህበረሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል። ልክ እንደ ጤና ባለሙያው ሁሉ ሁሉም የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ በቂ ክፍያ እየተከፈለው አይደለም።
አሁን ሀገራችን እየከፈለች ያለችው ሀገሪቱ መክፈል ከምትችለው አቅም ጋር የተገናዘበ ነው። ያም ሆኖ ግን መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሥራዎችን በመሥራት መሆኑን ደጋግሞ አረጋግጧል።
የጤና ባለሙያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ቀደም ብሎ የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1362 /2017 አጸድቆ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
ስለዚህ የጤና ባለሙያውም ይሄንን በጥሩ ህሊና በመቀበል ወደ መደበኛው ሥራው መሰማራትና ህብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅበታል። አድመኝነት ከሙያ ሥነምግባርና ከሠብዓዊነት አኳያ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲገቡ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ በመቀበል ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም