አዲስ አበባ፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሁለት ዓመታት በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 65 በመቶ ደርሷል፡፡
የግድቡ ግንባታ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ትናንት ውይይት ሲካሄድ የግድቡ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በሳሊኒ ኢምረጂሎ የሚሠራው የግድቡ የሲቪል ሥራ 82 በመቶ ቢከናወንም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሸን ሲከናወን የነበረው የኤሌክትሮመካኒካል ሥራ ገና 25 በመቶ ላይ በመሆኑ ከሁለት ዓመታት በፊት ኃይል ማመንጨት እንደማይጀምር ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 65 በመቶ እንደደረሰና ግንባታውን ለማፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ግንባታው እንደተቋረጠ የሚወራው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸው፣ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ እ.አ.አ በ2022 እንደሚጠናቀቅ ኢንጂነር ክፍሌ አስታውቀዋል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፣ የግድቡን ግንባታ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የግድቡ ግንባታ በታሰበው ፍጥነት ባይጓዝም ግንባታው ለአንድ ቀን እንኳ ተቋርጦ አያውቅም›› ብለዋል፡፡
በግንባታው ላይ የታየው መጓተት በሕዳሴው ግድብ ላይ ብቻ የተከሰተ እንዳልሆነና ሌሎች መሰል ትልልቅ ፕሮጀክቶችንም ያጋጠመ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ለጋራ ጥቅም በግድቡ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ተጨማሪ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ለማካሄድ ተስማምተዋል፡፡ እያንዳንዳችን ሦስት ታዋቂ ባለሙያዎችን በመምረጥ ጥናት እንዲጠና አድርገናል፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳን አዲስ አበባ ላይ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ የግብፅ ተወካይ ደግሞ አገራቸው ላይ ከተወያዩበት በኋላ ለመፈረም ወስነዋል›› ብለዋል፡፡
አንተነህ ቸሬ