ዘለንስኪ ሀገራቸው በቀጣይ ከአሜሪካ ጋር ውጤታማ ውይይት እንደምታደርግ ተናገሩ

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ በመጪው ሳምንት በሳውዲ ዓረቢያ ሀገራቸው ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር ልታደርገው ያቀደችውን ውይይት ‹ትርጉም ያለው› እንደሚሆን ተስፋ መሰነቃቸው ተገለጸ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሳውዲ ዓረቢያ ቢገኙም በውይይቱ የማይሳተፉ እንደሆነ ሲታወቅ ሀገራቸው ዩክሬን አስቸኳይ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በትጋት እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በበኩላቸው የአሜሪካ የእርቅ ቡድን የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ መወያየት ይፈልጋል ያሉ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ትራምፕ ከአቻቸው ዘለንስኪ ጋር ፍሬ ያለው ውይይት አለማድረጋቸው እና ትራምፕ ዘለንስኪ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ዝግጁ አይደለም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በመሪዎቹ መካከል የተፈጠረውን የዲፕሎማሲ ቀውስ ተከትሎ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ታደርገው የነበረውን ወታደራዊ ርዳታ እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ ማቆሟ ይታወሳል፡፡ ዘለንስኪ ውይይቱ በዛ መንገድ መቋጨቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው ሀገራቸው ከፍተኛ የጦር መሣሪያ አቅራቢ ከሆነችው አሜሪካ ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ እንደምትፈልግና በዚህ መሠረት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ሐሙስ ዕለት ትራምፕ የይቅርታ እና የምስጋና ደብዳቤ ከአቻቸው ዘለንስኪ እንደደረሳቸው ዊትኮፍ የተናገሩ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ አክለውም ‹ከዩክሬናውያን ጋር ወደትክክለኛው መንገድ እንደምንመጣ እና ሁሉም ነገር በመልካም እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን› ሲሉ ዊት ኮፍ አክለዋል፡፡

ዘለንስኪ አሜሪካ ከማንኛውም የሰላም ድርድር በፊት ስምምነት ውስጥ እንዲገቡ ከፍተኛ ጫና ስታደርግባቸው የቆየች ሲሆን እሳቸው በበኩላቸው ለሀገራቸው ጥብቅ የፀጥታ ዋስትና እንደቅድመ ሁኔታ የሚያነሱት ሆኗል፡፡ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሦስት ዓመታትን በዘለቀ ጦርነት ከተከፈለ የሕይወት መስዋዕትነትና የንብረት መውደም በተጨማሪ ሩሲያ

ዘለንስኪ ሀገራቸው በቀጣይ ከአሜሪካ ጋር ውጤታማ ውይይት እንደምታደርግ ተናገሩ የዩክሬንን ሃያ በመቶ ግዛት መቆጣጠሯ ተነግሯል፡፡

ዘለንስኪ የመከላከያ ወጪን የመጨመር እቅዶች በፀደቁበት የአውሮፓ ኅብረት የመሪዎች የብራስልስ ቀውስ ጉባኤ ላይ ከተገኙ በኋላ በሳውዲ ዓረቢያ ስለሚደረገው የአሜሪካ እና ዩክሬን ውይይት በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ተከታታይ ጽሑፎችን አስፍረዋል፡፡ ‹‹የዩክሬን እና የአሜሪካ ቡድኖች ሥራቸውን ቀጥለዋል፣ እናም በሚቀጥለው ሳምንት ትርጉም ያለው ውይይት እንደሚኖረን ተስፋ አደርጋለሁ›› በማለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው ታውቋል፡፡

ዘለንስኪ በማከልም ‹‹ዩክሬን ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ ለሰላም ያላትን መሻት አሳይታለች፡፡ ጦርነቱ እየሄደ ያለው በሩሲያ እምቢተኝነት ብቻ ነው›› ያሉ ሲሆን ሞስኮ ጦርነቱን እንድታቆም መላው የዓለም ሕዝብ የበለጠ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአየር እና በባሕር የሚደረግ የተኩስ፣ በሰው እና በሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ያቀረቡትን የእርቅ እቅድም በአበረታችነቱ ጠቅሰውታል፡፡

ሩሲያ የፈረንሳይ መንግሥት ላቀረበው የሰላም እቅድ እስከ አሁን አስተያየት ያልሰጠች መሆኑ ሲገልጹ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሐሙስ እለት ‹‹ሀገራችን የምትፈልገው ሰላም በዘላቂነት መረጋጋት የሚሰጣት ነው›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ በተጨማሪም ‹‹የሌሎች የሆነ ምንም ነገር አንፈልግም ነገር ግን የእኛ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አሳልፈን አንሰጥም›› በማለት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

ሩሲያ የዩክሬንን ደቡባዊ ክሪሚያ ግዛት በአውሮፓውያኑ 2014 የጠቀለለች ሲሆን ሌሎች ሙሉ በሙሉ ያልተቆጣጠረቻቸውን አራት የዩክሬን ግዛቶች የራሴ ግዛቶች ናቸው የሚል ጥያቄን በማንሳት ላይ ትገኛለች፡፡ ሦስት ዓመታትን የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት ጦርነት የትራምፕን ወደሥልጣን መምጣት ተከትሎ የሦስተኛ ወገን አሸማጋይ ቡድን እንደገባበት ይታወቃል፡፡ መረጃውን ከቢቢሲ አግኝተናል፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You