
ወጣት ልዩነህ ታምራት ይባላል። ብዙዎች በአነቃቂ ንግግሮቹ ያውቁታል፤ የወጣቶች የአመራር ክህሎት ላይ ሥልጠና ይሰጣል። ‹‹ኢትዮጵያውያን የሀብት ሳይሆን የአመለካከት ችግር ድህነት ውስጥ እንድንቆይ አስገድዶናል›› ብሎ ያምናል። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም ይህንን የመጠቀም የአመለካከት ችግር መኖሩ የሌሎችን ርዳታና ድጋፍ እንድንሻ ሆነናል ይላል። የወጣቶችን አስተሳሰብ በማረቅ ይህንን አሳሪ እምነት ለመቀየር ተነስቷል። የተነቃቃው የኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር (Inspired Development) የሚል ድርጅት መሥርቷል። በመሠረተው ድርጅት ባለራዕይ፣ ስኬታማ፣ ሰላማዊ፣ አብሮነትን የሚያፀናና ጤናማ ወጣት ለመፍጠር ይሠራል።
ወጣት ልዩነህ ከላይ ባነሳናቸው ምክንያቶች የዛሬው «የህይወት ገፀታ» እንግዳ አድርጎታል። የራሱን የሕይወት መንገድ ምሳሌ በማድረግ የኢትዮጵያ ወጣቶች አስተሳሰባቸውን እና ለማንነታቸው ያላቸውን መረዳት ለማስተካከል የሄደበትን ርቀት እንቃኛለን። የግል ሕይወቱን ያሸነፈበት መነሳሳት፣ ለዓላማው ግብ መምታት የከፈላቸው ዋጋዎች ለብዙዎች ተምሳሌት ይሆናል። ከሁሉም በላይ እሱን የመታው እንቅፋት ሌሎችን እንዳያገኝ፤ ካገኘም ከህመሙ በጥበብ የሚሽሩበትን ብልሃትን ርዕቱ በሆኑ አንደበቶቹ ያካፍላል። የዝግጅት ክፍላችንም የእንግዳችንን የሕይወት ምእራፎች እና ስኬቶች በሚከተለው መንገድ አቅርቦላችኋል። መልካም ንባብ!!
የደቡቧ ፈርጥ
ብዙዎች በተፈጥሮ ሀብቷ ተማርከው፤ በተንጣለለው ሐይቋና በጣፋጭ ዓሳዎቿ ተስበው ከሳምንት ሳምንት ወደ ጉያዋ ይገባሉ። ከታቦር ተራራ ጫፍ ሆነው የከተማዋን ውብ መልከዓ ምድር ለመቃኘት ይጓጓሉ። ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ከባሕር ማዶ ጭምር ይከትማሉ። የያኔው ታዳጊ ልዩነህ ታምራት ደግሞ ከሳምንት ሳምንት እንግዶችን በፍቅር ከምታስተናግደው፣ ሰው በሰውነቱ ብቻ አክብራ በምትቀበለው፤ ዓሳ እንደ ጎመን በሚበላባት በተወዳጇ ከተማ በደቡቧ ፈርጥ ሃዋሳ (ኮረም ሰፈር) ነው የተወለደው።
ሃዋሳ ኮረም ሰፈርን ስናሰብ ቀልባችን ድንገት ወደ ኢትዮጵያ ተወዳጅ የእግር ኳስ ይወስደናል። አዳነ ግርማ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ሙሉዓለም በመሳሰሉ የወርቃማ ዘመን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ትዝታችን ይቀሰቀሳል። ታዳጊው ልዩነህ የሕይወት መንገድ ከስፖርቱ ዓለም የራቀ ይምሰል እንጂ በታዳጊነቱ ከእነዚህ ተወዳጅ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ባለውለታዎቻችን ጋር ክቧን ካስ አንቀርቅቦ፣ በኮረም ሜዳዎች ተጫውቶ ነው ያደገው። የትዝታ ጓዳውን ሲበረብር የሽመልስ በቀለ አብዶዎች፤ የአዳነ ግርማ ጎሎች ይቀበሉታል። ትምህርቱን ደግሞ በኢትዮጵያ ትቅደም አሃዱ ብሎ ጀምሯል።
‹‹ሃዋሳ ማደግ ፍቅርን፣ ትብብርን መለማመድ ነው›› ይላል የልጅነት ዘመኑን እያስታወሰ። አብሮነትንና መከባበርን የሚያጠናክሩ ኢትዮጵያዊ እሴቶች የልዩነህን ልጅነት ያጣፈጡ ቅመሞች ናቸው። ዛሬ ለቆመለት መርህ ተገዢ መሆኑ ከልጅነቱ የጨለፋቸው የሃዋሳ በረከቶች ምክንያት ናቸው። በስፖርት፣ በአብሮነት እና በጤናማ አስተሳሰብ የተሞላ ልዩነህ ይፈጠር ዘንድ የሃዋሳ ማህበረሰብ የድርሻቸውን ጡብ ደርድረዋል።
ኢትዮጵያዊነት አፋችን ላይ ብቻ ሳይሆን ልባችን ላይ ነው ያለው፤ ለዚያም ነው ዛሬም ለለውጧ በትጋት የምንሠራው ይላል የዛሬው እንግዳችን። የትናንት ማንነቱ ለዛሬ መሠረት እንደሆነው በልበ ሙሉነት እየተናገረ። በኢትዮጵያ ትቅደም የትምህርት ቆይታው የደረጃ ተማሪ ነበር፤ ልዩ የቀለም ትምህርት ክህሎት ነበረው። ብሩህ አዕምሮ ከታደሉት መሀከል መሆኑ በተለምዶ አጠራር ‹‹ደብል›› ከሚመቱት ተርታ አሰልፎታል።
ችሎታው በሁለተኛ ደረጃና በመሰናዶ ትምህርት ቤትም ቀጥሎ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዝልቆታል። በጊዜው ከቀለም ትምህርት ባሻገር መንፈሳዊ መፅሀፍትን ማንበብ ፊልሞችን መከታተል ያዘወትር ነበር። ይህ ዝንባሌው ሁሉን አቀፍ ምልከታ እንዲኖረው ሕይወትን በተለያየ አቅጣጫ መመልከት እንዲችል እድል ሰጥቶታል። ለስፖርት ያለው ፍቅር ለቀልጣፋነቱ፣ ለንቁና ጤናማነቱ ድርሻ አለው። የእነዚህ ሁሉ ድምር የልዩነህን የሕይወት ልዩነቶች የፈጠሩ ናቸው።
ሌላኛው የሕይወት መልክ
የወጣቶችን አስተሳሰብ በሚያርቁ ሥልጠናዎቹና አነቃቂ ንግግሮቹ የሚታወቀው የወጣት ልዩነህ የልጅነት ሕይወት ፍፁም የሚባል አልነበረም፤ ከሃዋሳ ማህበረሰብ፣ ከኮረም ሰፈር ጠንካራ ሥብእናውን የገነቡ ጡቦችን ያግኝ እንጂ በሌላኛው ገፅ ሊሰብሩት ዳር ዳር ያሉ፣ የልጅነት ገፆቹን ያጠየሙ አስቸጋሪ ወቅቶችን አሳልፏል። ይህኛው ታሪክ ከአባቱ ጋር የነበረውን የደበዘዘ የልጅነት ገፁን ያሳየናል።
አቶ ታምራት ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ከታዳጊ ልጃቸው ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተው ነበር። ከልጆቻቸው መሀል ለእርሱ ፍቅር አልነበራቸውም። አዕምሮው ላልበሰለ ታዳጊ የማይገቡ ቃላቶቹን ተጠቅመው ያስቀይሙት ነበር፤ አለፍ ሲልም ስድቡ ወደ ዱላ ይቀየር ነበር። ይህ ሁኔታ ለታዳጊው ልዩነህ የልጅነት አስከፊው ገፅታው ነው። ጥብቅ ቁጥጥሩን ለመሸሽ፣ ከአባቱ የሚሰነዘርበትን የጥላቻ ቃላት ለመራቅ ሲል በቤት ውስጥ የሚያረቧቸውን ‹‹ከብቶች ለመጠበቅ›› በሚል ሰበብ ከቤት ወጥቶ ይውላል። እግሩ ከደጅ እንደወጣ የሃዋሳ ማህበረሰብ፣ የኮረም ሰፈር ነዋሪዎች በፍቅርና በፈገግታ ይቀበሉታል። ኳስ ሲጫወት ውሎ ከብቶቹን አመሻሽ ይዞ ወደቤት ይገባል።
ይህ ዘዴ ግን ሁሌም አይሠራም ከከብቶቹ መሀል የሰው አጥር ጥሰው የሚገቡ ይኖራሉ። በተከለከሉ ቦታዎች ሲገኙ ይታሰራሉ፤ ያጠፉትን ጥፋት ክሶና ክፍያ ከፍሎ ማስለቀቅ የግድ ነው። ይህ ለልዩነህ ሌላ ፈተና ነው። በዚህ ምክንያት እስከ ድብደባ የሚደርስ ከፍተኛ ቁጣን ከአባቱ ያስተናግዳል። ቁጣና ምት ያስመረረው ታዳጊ ታዲያ ፈጣን አዕምሮውን እና ብልሀቱን ተጠቅሞ አንድ መላ ዘይዶ ነበር። ከብቶቹ ቢታሰሩ የሚያስለቅቅበት አንዳንዴም ከቤት ውጪ ሲውል ምግብ የሚቀምስበት ገንዘብ መሥራት። ለዚህ ደግሞ ሃዋሳ ምቹ ነች። ያገኘውን ተሸክሞ አስፋልት ዳር የሚሠሩ ሥራዎችን ተሯሩጦ ፍላጎቱን መሸፈን ጀመረ።
በጊዜው ከአባቱ በሚደርስበት ጫና የልጅነት አዕምሮው ቢሸበርም የማይበገር ሥብእና እንዲገነባ፣ ዝቅ ብሎ የመስራትን ጥቅም እንዲያውቅ አድርጎታል። በዚህ ሁሉ የቤተሰብ ፈተና ውስጥ ሲያልፍ ግን እናቱ ሁሌም ከጎኑ ነበሩ። የልጃቸውን መገፋት እና ከባለቤታቸው የሚደርስበትን አካላዊ ጥቃት የሚሽር ፍቅርና እንክብካቤን ያሳዩት ነበር። በሚፈጠር ጠብ ከቤት ሲወጣ ሌሊቱን ሙሉ በጎዳናዎች ላይ ይፈልጉት ነበር። የእናቱ ድጋፍ ጫናው የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንዳይከተው፤ ከሕይወት ፈተና ውስጥ አንዱና ቀላሉ እንጂ ማንነቱን የሚያሳጣ አደጋ አድርጎ እንዳይመለከተው ረድቶታል። በሀገር ውስጥና በውጪ መድረኮች ላይ ተጋብዞ የሕይወት ልምዱን ሲያካፍል ይህንን ታሪኩን ሳይናገር አይወርድም። የእናቱን ውለታ የሃዋሳ ማህበረሰብ የማይዘነጉ ትዝታዎች ሥብእናውን ገንብተውታል።
ታዳጊው ልዩነህ ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ የሥራን ጥቅም፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስፈላጊነት የተረዳ ቀልጣፋ ነበር። በሃዋሳ ቤተሰብ መምሪያ ውስጥ በበጎ ፍቃድ ያገለግል ነበር። ህልሙ ትልቅ ነበር። ዛሬ ያሳካቸው እያንዳንዱ የሕይወት ትልሞቹ ያኔ የተወጠኑ ነበሩ። ለጓደኞቹና ወንድሞቹ ‹‹ትልቅ ቦታ እደርሳለሁ፤ ሌሎችን የሚያግዝ ድርጅት እመሠርታለሁ›› በሚል ራዕዩን ሲያጋራቸው ይስቁበትና ያሾፉበት ነበር። እርሱ ግን እያንዳንዱን የሕይወት ቋጠሮ በብልሃት እየፈታ ዛሬ ላይ ደርሷል፤ ለነገም ትናንት ያሰላሰለው ይደርስበት የሚሻው ግዙፍ ህልም አለው።
ህልምን የመፃፍ ጅማሮ
ልዩነህ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፤ በቤተሰብ መምሪያ የበጎ ፈቃደኛ ሆኖ ይሠራል። በወቅቱ ከውጪ የመጡ ነጮች አስተርጓሚ ሆኖ በአንድ ዝግጅት ላይ ተገኘ። ይህ አጋጣሚ ኢንስፓየር (Inspire) ከሚል እንግሊዝኛ ቃል ጋር አስተዋወቀው። ለቃሉ እንግዳ በመሆኑ ትርጉሙን ከተናጋሪዋ ለመረዳት ሞከረ ‹‹ለለውጥ ከውስጥ መነቃቃት እና እራስን ከማነሳሳት›› ጋር እንደሚገናኝ ነገረችው። ከዚህን ጊዜ አንስቶ ‹‹ሰዎችን ለለውጥ ማነሳሳትና ማነቃቃት የኔ ግብ ነው›› ሲል ለራሱ ቃል ገባ።
ወጣቶች ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎችን በበጎ ፍቃደኝነት መሥራቱን ቀጠለ። በክበባት እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ዩኒቨርሲቲ አስከገባበት ጊዜ ድረስ ወጣቶች ራዕይ እንዲኖራቸው፣ ህልማቸውን ለማሳካት የውስጥ ፍላጎት እንዲፈጥሩ ተግባራት ላይ ቀዳሚ ተሳታፊ ሆነ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር አዲስ ምዕራፍ ወደሆነው የሕይወት ገፁ የገባው።
ወጣት ነው፤ የተነቃቃና ራዕይ ያለው። ይህንን ልዩ ስሜት በውስጡ ይዞ ነበር ሻንጣውን ሸክፎ ወደ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገባው። በግቢ የቤተሰብ ‹‹የት ገባህ፤ የት ወጣህ›› የሚል ጥያቄ ቦታ የለውም፤ በነፃነት መብረር ይቻላል። በዩኒቨርሲቲ ብዙ የወጣትነት ጓዝ አለ። ራስን የመግዛት ሃላፊነት፣ ከአቻ ግፊት እና ከትምህርት ጫና ጋር ተያይዞ የሚመጣ ድብርት ሌላም ሌላም አያሌ ሸክሞች ይጠብቁታል። ለእነዚህ ሃላፊነቶች የሚሆን ትከሻን ያዘጋጀ ቢሆንም አንድ ጉዳይ ግን ስሜቱን ይረብሸው ዘንድ የግድ ሆነ።
እግሩ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲን ሲረግጥ ካሰበውና ከሚፈልገው ተቃራኒ የትምህርት ክፍል ተመደበ። ሶሾሎጂ፣ ሶሻል አንይትሮፖሎጂ እና ሳይኮሎጂ የመሳሰሉ የትምህርት ዘርፎችን በልዩነት ይወድ ነበር፤ ለትምህርቶቹ ልዩ ፍላጎት ቢኖረውም ዩኒቨርሲቲው ግን አካውንቲንግና ፋይናንስ መደበው።
በሁኔታው ቅር የተሰኘው ወጣት ልዩነህ በጊዜው የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ወደነበሩት ፕሮፌሰር ዝናቡ ቢሮ አቅንቶ ስለሁኔታው አስረዳቸው። የእርሳቸው ምላሸ ግን ‹‹የምትወደውን ካጣህ የተሰጠህን ውደድ›› የሚል ነበር። ሁኔታው አልተዋጠለትም ። ፍላጎቱን ማሳካት እንደማይችል ሲያውቅ በትምህርቱ እየደበዘዘ ወደሌሎች ጉዳዮች ትኩረቱ እየተሳበ መጣ። ቤተ መፅሀፍት ውስጥ ገብቶ የሊደርሺፕና መንፈሳዊ መፅሀፍትን ያነብብ ጀመር። የመመረቂያ ውጤቱም ዝቅተኛ እንደነበር ያስታውሳል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ልዩነህ ለራሱ የሚሰጠው ግምት ዝቅ ያለ እንደነበር ይናገራል። ይህንን መሰል አጋጣሚን የተጋፈጠበት ምክንያት ደግሞ በግቢ ውስጥ ከሁሉም አካባቢ የሚመጡ ተማሪዎች እና የኑሮ ሁኔታው መዘበራረቅ ነበር። በተለይ በእውቀት፣ በኑሮ ደረጃና በልዩ ልዩ ጉዳዮች ከእርሱ የተሻሉ ተማሪዎች መኖር ‹‹ካሳለፍኩት የሕይወት ማንነት አንፃር በራስ መተማመኔን እያሳነሰብኝ መጣ›› ከሚል ሃሳብ ጋር አላተመው። በዚህ የሥነ ልቦና ትርምስ ውስጥ ጥቂት ጊዜ ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም ይሠራባቸው የነበሩ ወጣቶች ላይ የሚያተኩሩ የማህበራዊ ልማት ሥራዎችም በአንዳንድ ሰዎች ውድቅ ይደረጉበት ነበር። እነዚህ አጋጣሚዎች ተደማምረው የዩኒቨርሲቲ ቆይታውን አክብደውበታል። ‹‹ሰዎች ሃሳብ መጣል ይችላሉ፤ ያንተ ሃሳብ በፅናት ካልቀጠለ ግን እውን አይሆንም›› የሚል የቆየ እምነት ያለው ልዩነህ ጫናውን ተቋቁሞ ህልሙን ከመፃፍ አላገደውም። ክበቦች ላይ በመሳተፍ በሴቶች ጥቃት፣ በፀረ ሙስና እና ሥነ ተዋልዶ ጉዳዮች ላይ በቆይታው ተሳታፊ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በዝቅተኛ ውጤት ተመርቆ ቢወጣም ‹‹መስመሬን እንድቀርፅ አግዞኛል፤ የሕይወቴ ቅርፅ በፈተናዎች ታሽቶ ዋጋ እንዲያገኝ አርጎኛል›› ሲል የከፍታና ዝቅታ ጊዜዎቹን ሳይሸሽግ ይናገራል።
ቅርጫት ውስጥ የተጣለው ማስረጃ
ወጣቱ ልዩነህ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንደወጣ ቤተሰቦቹ ቤት ነበር የገባው። ለዓመታት የለፋበት ትምህርት ጉዞ ‹‹ባለ ዲግሪ›› በሚል ማእረግ መቋጫውን አገኘ። የኮረም ሰፈር ወዳጅ ዘመድ ምርቃቱ ላይ ተገኝቶ ድግሱን አደመቀለት። ለሶስት ወራት በቤት ከተቀመጠ በኋላ ነበር ‹‹ሥራ መፈለግ›› የሚል ግዴታ ውስጥ የገባው። ያን ጊዜ ሌላው የሕይወት ፈተናን የሚጋፈጥበት ምእራፍ ውስጥ ተገኘ።
በአንድ ኮሌጅና የቀድሞው የደቡብ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያቤት ውስጥ አመለከተ። በኮሌጁ ግን ያላሰበው አጋጣሚ ተከሰተ። የሰው ሀብት አስተዳደር የሥራ ማመልከቻ አስገብቶ ወደ መውጫው ሲያመራ የተቀበለችው ሰው ማስረጃዎቹን ወደማይፈለግ የወረቀት ማጠራቀሚያ ውስጥ ስትጨምረው አየ። ‹‹ለምን?›› የሚል ሙግት ውስጥ ሲገባ ከሶስት ነጥብ በታች የሆኑ አመልካቾች እንደማይቀበሉ እንቅጩን ነገረችው።
ወደ ሃላፊው ቀርቦ ‹‹ፈተናውን ልፈተን እድል ስጠኝ›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ተፈቀደለት። ከ17 ሰዎች መካከል ‹‹አካውንቲንግ ፕሪንስፕል አንድ›› የሚል ኮርስ በተግባር ተፈተነ። ለሃላፊው የሰጠውን ቃል ጠብቆ በጥሩ ውጤት አለፈ። ይሁን እንጂ ሥራውን አልተቀበለውም፤ ምክንያቱ ደግሞ በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ካለፉት መካከል አንዱ ስለነበር ነው። ልዩነህ ቅርጫት ውስጥ ልትከተው የነበረውን ሞራሉን ታግሎ አሸነፈ፤ እርሱ ወደሚፈልገው ሥራም ገባ። ሌላ የሕይወት ምእራፍ፤ ሌላ ፈተና።
በዋና ኦዲተር መሥሪያቤ በስፔሻል ኦዲተርነት ለሁለት ዓመት ሠራ። ጊዜውን መለስ ብሎ ሲያስታውስ በደቡብ ክልል ከተሞች ተዟዙሮ የመሥራት እድል ማግኘቱ፣ በመሥሪያቤቱ የነበረው ተደማጭነት እና አዳዲስ ልምዶችን ማካበቱን እንደ በጎ ነገር ይመለከተዋል። ሆኖም የልዩነህ ራዕይ በዚያ የሚቆም አልነበረም። ከልጅነቱ ይመኘው የነበረውን ህልሙን መከተል ይሻል። በዚህ ምክንያት በብዙዎች የሚፈለገውን ሥራ ትቶ ወደ አዲስ አበባ መጣ።
የአባት በረከት የጎበኘው ህልም
አዲስ አበባ ሰፊ ባሕር ነች። ደካሞችን ትውጣለች፤ መዋኘት የቻለ ብቻ በውቂያኖሱ ላይ ይንሳፈፋል። የሕይወት በቀላሉ አልጋ ባልጋ አይሆንም፤ ውድድሩ ከባድ ነው። ልዩነህ በዚህ ውቂያኖስ ውስጥ ነው መልህቁን ለመጣል ጓዙን ሸክፎ የመጣው። ከልጅነቱ የወጠነውን በወጣቶች ማህበራዊ ልማት ላይ የመሥራት ህልሙን እውን ያደርግ ዘንድ ደግሞ ወደዚህ መምጣት ግድ ይለው ነበር።
ጊዜው 2004 ዓ.ም ነበር ፤ሙሉ ለሙሉ አዲስ አበባ የከተመበት ወቅት። የስፔሻል ኦዲተርነት ሥራውን ትቶ በቀጥታ በሴሚናሬ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሜጀሩን በፒያኖ የጀመረበት ጊዜ። የሙዚቃ ተማሪ የመሆን ፍላጎቱ የመነጨው ህብረተሰብ ልማት ላይ አጋዥ የሆኑ አነቃቂ ሙዚቃዎችን (Motivational Songs) ፕሮዲውስ የማድረግ የቆየ ህልሙን እውን ለማድረግ ነበር። እግረ መንገዱን ደግሞ በግቢው የሚሰጠውን የማደሪያ ክፍል መጠቀም ፈልጎ ነበር። ምክንያቱም ለሁለት ዓመታት ካጠራቀመው ደመወዙ ውጪ እራሱን የሚደጉምበት የገቢ ምንጭ አልነበረውም። የተጠራቀመው ደመወዙም ቢሆን ከስድስት ወር ፈቅ አላለም፤ ወዲያው ነበር ያለቀው።
አዲስ አበባ እንደጠበቀው ለልዩነህ ቀላል ፈተናን አልሰጠችውም። ደመወዙን ቅርጥፍ አድርጋ በልታ አልጠረቃችም። ሕይወትን ያሸንፍ ዘንድ ቢኒያም በቀለ ፣ፍቃዱ ጴጤላና ዝናቡ ዮናስ የተባሉ ጓደኞቹ እና በረከት በቀለ የተባለ የሴሚናሬ ዳይሬክተር እገዛ የግድ ብሎት ነበር። እነርሱ አንዳንዴ ምግቡን አንዳንዴም ማደሪያውን እያመቻቹለት አግዘውታል። ከዚህ ጫና ለመላቀቅ እና ውጥኑን ከግብ ለማድረስ የግድ ሥራ ማግኘት ነበረበት። ለዚያም ነበር እስከ 2007 ዓ.ም ከ650 ብር ደመወዝ እስከ ሁለት ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ በተለያዩ ቦታዎች በፒያኖ ተጫዋችነት ተቀጥሮ የሠራው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ልዩነህ ለህልሙ የሚያቀርበውን ተግባር እየፈፀመ ነበር። የመጀመሪያው ርምጃ አዲስ አበባ እንደመጣ ኢንስፓየርድ ኢትዮጵያ የሚል ድርጅት ለማቋቋም ሕጋዊ ፍቃድ ማግኘት ነበር። ከሴሚናሬ ፒያሳ ድረስ በእግሩ እየተመላለሰ ፈቃድ ለማግኘት ሞክሮ በስድስተኛው ወር ተሳክቶለታል። ህልሙን የሚጋሩ፣ ትጋቱ፣ ጽናቱ የሚያነቃቃቸው በራዕይው እውን መሆን እምነት ያላቸው በጎ ፍቃደኞችን ከጎኑ ነበሩ። በሴሚናሬ ቆይታውም ሆነ በመካኒሳ አካባቢ በሃዋሳ የነበረውን የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን (ደም ልገሳ፣ ልብስ የማካፈል፣ ተማሪዎችን ማስጠናት) ማስተባበር አላቆመም ።
አዲስ አበባ በኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ልታሰምጠው ብትታገለውም ተስፋ መቁረጥንና እጅ መስጠትን የማያውቀው ልዩነህ ፈተናዎችን ቀስ በቀስ ማሸነፍ ጀመረ። የሰው እጅ ከማየትና ከመሳቀቅ ያዳኑትን የልፋት ውጤቶቹ ፍሬ ያፈሩ ዘንድ ግን የአባቱ ቡራኬ አስፈልጎት ነበር። ደጋግሞ ስለእናቱ ማውራትና ስለውለታዋ ማመስገን የማይጠግበው ልዩነህ በሕይወቱ ውስጥ አንድ ያልተደፈነ ሽንቁር መኖሩን በወዳጁ አማካኝነት እንዲያስታውስ ሆነ። የአባት ቡራኬና በረከት ምን ያህል ለሕይወት አስፈላጊ እንደሆነ ከመፅሀፍ ቅዱስ እያጣቀሰ መከረው። በመልካም ከማያስታውሳቸው ጊዜያቶች ውስጥ ከአባቱ ጋር የነበረው ግንኙነት አንዱ ቢሆንም የዚህን ጓደኛውን ግሳፄ እንደቀልድ አላየውም። የሕይወት ትግሉ የስኬት መቋጫ ያገኝ ዘንድ የእርሳቸው የቡራኬ እጅ በራሱ ላይ መጫን ነበረበት። ነጭ ሱፍ ገዝቶ ወደ ሃዋሳ አቀና፤ በአባቱ እግር ስር ተደፍቶ ይቅርታን ጠየቀ። እርሳቸውም በፍፁም መፀፀትና ከልብ የመነጨ ፍቅር ‹‹እድሜ ልኬን ስጫወትብህና ስደበድብህና ዋጋ ሳስከፍልህ የኖርኩት እኔ ነኝ፤ ይቅርታ መጠየቅ የነበረብኝ እኔው ነኝ›› በማለት የነካው እዲባረክ፣ ያሰበው እንዲሳካና የልቡ እንዲሞላለት ቡራኬን ሰጥተውት በእርቅ ተቋጨ። ልዩነህ ዛሬ በሕይወት የሌሉት አባቱን ቡራኬ ማግኘቱ የሕይወት መንገዱን እንዳቀናው ያምናል።
ስኬት አደባባይ ላይ
ወጣቶች በራሳቸው፣ በሀገራቸውና በማንነታቸው እንዲተማመኑ፤ ውስጣዊ አቅማቸውን እንዲረዱ የሚያስችል የአስተሳሰብ ለውጥ ሥልጠናዎች ገና ከታዳጊነቱ የመስጠት ልዩ ተሰጥኦና ፍላጎት ነበረው። ይህንን ተቋማዊ ለማድረግ ብዙ ታግሏል፤ ቋሚ ሥራውን ለቆ ለህልሙ ዳር መድረስ ማረፊያ አጥቶ በቤተክርስቲያን ውስጥ አስከማደር ደርሷል። ትግሉና ፅናቱ ግን ከንቱ አልሆነም። ዛሬ በታዳጊነቱ የተለመውን ህልም አሳክቷል።
ኢንስፓየርድ ዴቨሎፕመንት ብዙ ሺህ ወጣቶችን፣ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ አመራሮችን የለውጥ ክህሎትና የውስጥ መነቃቃትን የተመለከቱ ሥልጠናዎችን ይሰጣል። በሀገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ መድረኮች ላይ ተገኝቶ የሕይወት ልምዱን ያካፍላል። ልህቀት ያላቸው መድረኮችን በማዘጋጀት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሀገራቸው ያላትን እምቅ ሀብት፣ ያልተበረዘ ማንነት እና የመሥራት አቅም እንዲረዱ ይሠራል።
‹‹ወጣቶች እንደሚችሉ ስናገር ፈተናዎችን፣ የማለፍ አቅም እንዳላቸው ሳነቃቃና ሳስተምር ከአፌ ሳይሆን ከራሴ የሕይወት ልምድ ነው›› ይላል ልዩነህ፤ ጠጋ ብለው ከሕይወት ልምዱ ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሙት። ትናንት ብዙዎች የናቁትና ሃሳቡን ያጣጣሉት ዛሬ የሃሳቡን እና የምክሩን ጠቃሚነት ተረድተው አጠገቡ ናቸው። ወጣቶችም ራዕይ እንዲኖራቸው ከአሳሪ፣ ከጥገኛ አስተሳሰብ እንዲላቀቁ ፣ ጤናማ እንዲሆኑ ፣ የራሳቸውንም ሆነ የሀገራቸውን ሰላም እንዲጠብቁ ፣ ለፈተናዎች የማይበገሩና እራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ለመምራት የሚያስችል ጥበብ እንዲታደሉ እርሱና የኢንስፓየርድ ዴቨሎፕመንት አባላት ይሠራሉ።
ኢንስፓየርድ ዴቨሎፕመንት ሰዎች ወደ ውስጣቸው መመልከት ከቻሉ፣ ፅናት ካላቸው፣ ለዓላማቸው ተፈፃሚነት ቀላል ስትራቴጂ ከተከተሉ ወደ ስኬታቸው የማይደርሱበት ምንም አይነት ገዳቢ ሃይል የለም ሲል ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያስተምራል። ‹‹ረጂና ተረጂ›› የሚለውን ቃልና ፅንሰ ሃሳብ የማጥፋት ራዕይም አለው። ሰዎች ይህን አስተሳሰብ ከውስጣቸው አጥፍተው ለሥራ የአዕምሮ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ይሠራል። ከተረጂነትና ጥገኝነት ይልቅ የሰው ልጆች ተፈጥሮ የሆነው የበታችና የበላይ የሌበት የማካፈል ልምድና ባህል እንዲፈጠር ኢንስፓየርድ ዴቨሎፕመንት ይሠራል። ለዓላማው ተፈፃሚነት ከመንግሥትና መንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር መድረኮችን በማዘጋጀት አያሌ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
በሃዋሳ ኮረም ሰፈር የተሰነቀው ራዕይ አሁን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ አጋሮችን ይዞ ለወጣቶች የአዕምሮና የአስተሳሰብ ለውጥ እየሠራ ነው። ኦክስፋም እና አክሽን ኤድ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በሀገር ውስጥ ከኤምባሲዎች ጋር፤ ከመንግሥታዊ ተቋም (ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የሲቪል ማህበራቶች ባለሥልጣን እና ሌሎችም) በአጋርነት አብረውት ይሠራሉ። በማህበራዊ ሚዲያ፣ በመገናኛ ብዙሃን ወጣቶችን የሚያነሳሳና ራዕይ እንዲኖራቸው የሚያበረታ ጉዳዮችን በመቅረፅ ያሰራጫል።
ልዩነህ ዛሬ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ሽልማቶች የሚያገኝ ሃሳቦቹ በብዙ ሺዎች በቀላሉ የሚደርስ ወጣት ሆኗል። በዩኒቨርሲቲዎች፣ በሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ልምዶቹን ያካፍላል፤ የአመራር ክህሎት ሥልጠናዎችን ይሰጣል። በደቡብ ኮሪያ ‹‹ሰላም ይቻላል›› በሚል ርእስ ባቀረበው ጥናት የሜዳሊያ አሸናፊ ነው። ሌላው በሳውዝ አሜሪካ አርጀንቲና ውስጥ በባህል በስፖርትና በጥበብ ላይ ባተኮረ መድረክ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳትፏል። በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ የብዙ ባህል፣ ሉዓላዊ ሀገር እና ጀግኖች ወጣቶች ያላት ሀገር እንደሆነች ልምዱን አካፍሏል፤ በዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ በቱርክ ልምዱን አካፍሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሜሪካን ሀገር የተመዘገበ youth in charge የተሰኘ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ባለድርሻ አካላት የሚመክሩበት መድረክ እያዘጋጀ ይገኛል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስገን ጥሩነህ የተገኙበት ‹‹ነፀብራቅ የመሪነት ኮንፍረንስ›› በዚህ ዓመት በኢንስፓየርድ ዴቨሎፕመንት በኩል አዘጋጅቷል።
የልዩነህ ራዕይ
‹‹ዘሩን ብበላው ፍሬ አያፈራም ነበር›› ይላል ልዩነህ፤ ከታዳጊነቱ የሰነቀው ራዕይ እንዲሆን ከመንገድ ላለመቅረት መስዋዕት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ሲናገር። ስንዴ ካልበሰበሰ ፍሬ እንደማያፈራው ሁሉ ሃሳብ እውን እንዲሆን ዋጋ መክፈል እና ጊዜያዊ ፍላጎትን መገደብ እንደሚሻ ከራሱ ልምድ ይናገራል። ለግል ፍላጎቱ፣ ለጊዜያዊ ችግሩ እጅ አለመስጠቱ ዛሬ ኢንስፓየርድ ዴቨሎፕመንት ተቋም ሳይሆን በሃሳብ ደረጃ በእንጥልጥል ይቀር እንደነበር ያምናል። ነገም ሃሳብ በሚንሸራሸርባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሁሉ በመገኘት ሃሳቦቹን ማካፈል ለውጥ የሚያመጡ እይታዎችና ፍልስፍናዎችን ማጋራት የልዩነህ ራዕይ ነው። ቀጣይነት ባለው መልኩ መሰል መድረኮችን በቋሚነት በግሉ ማዘጋጀት ህልም አለው። ኢትዮጵያ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን (በማይስ ቱሪዝም) የማመቻቸት ግብም ይዟል። ስለዚህ ይህንን ዘር መንከባከብ እና ፍሬ እንዲያፈራ መሥዋአት ማድረግ ይፈልጋል።
ልዩነህ ‹‹ጀምሮ መጨረስ እንጂ ጀምሮ ማቆም ለልጆቻችን ምሳሌ አይሆንም›› ይላል። ከዚህ መነሻ ለቀጣይ ትውልድ የሚሆን ተቋማዊ ግንባታ ላይ እንደሚሠራ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበረው ቆይታ ራዕዩን አጋርቶናል። ተተኪ አመራር ማፍራት፣ በጎ ፍቃደኛ፣ የአስተሳሰብ ተውቦህ ያለው መሪ መፍጠር ልዩነህ ዐሻራውን ሊያኖርበት የሚሻውና የመኖር ቁምነገሩ ነው። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም