የአመራርነት ብቃትን ማሳያዋ እንስት

ሴቶች ተፈጥሮ በሰጣቸው ስስና አዛኝ ልብ ልጆቻቸውን ከማንም በላይ ይንከባከባሉ፤ ችግሮችን በብልሃትና በዘዴ መሻገርንም ይችላሉ። ብዙዎች ይህን ተሰጥዖዋቸውን እያዩ የቤት ውስጥ ኃላፊነትን ብቻ ለመሸከም የተፈጠሩ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሴቶች ከቤት ወጣ ብለው እንደማንኛውም ሰው አመራር እየሰጡ ውጤት ያስመዘገቡባቸውን በርካታ ታሪኮች መጥቀስ ይቻላል።

በዓድዋው ድል የእቴጌ ጣይቱ ሚና ምን እንደነበር፤ ጣሊያን ዳግም ኢትዮጵያን ሲወር በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ተጋድሎ የስመጥሯ ሸዋ ረገድ ገድሌ አስተዋፅዖ ምን እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል።

በዚህ ባለንበት ዘመንም በተሰማሩበት ሥራ ሁሉ በአካባቢያቸው፣ በሀገራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያገኙ ሴቶች በርካቶች ናቸው። በበጎ አድራጎት ሥራቸው ከአበበች ጎበና እስከ ማዘር ትሬዛ፤ በስፖርት ከደራርቱ ቱሉ እስከ ፓውላ ራድክሊፍት፤ በአመራር ሰጪነት ከሚያ ሞትሊን እስከ አንጌላ መርክል ያሉትን ጠቅሰን አንዘልቃቸውም። በዚህ ጽሑፍም የኦ ፕሮዲዩስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስለሆነችው ስለወይዘሮ ማርታ በላይ የምንላችሁ ይኖራል።

ማርታ የተወለደችው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷንም በሕይወት ብርሃን ትምህርት ቤት ተምራለች። ቤተሰቦቿ የሕይወት መንገድ መርቷቸው ወደ አሜሪካ ሲሄዱ እርሷም አብራ በመሄድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በዚያው በአሜሪካ አጠናቃለች።

የመጀመሪያ ዲግሪዋንም በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን በአትላንታ ቴክኒካል ኤንድ ግሬስል ዩኒቨርሲቲ አግኝታለች። በጆርጂያ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ደግሞ በሳይበር ሴኩሪቲ ኤንድ ዳታ ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛለች። አሁን ላይ ባለትዳር፣ የሁለት ልጆች እናት እና የፒኤች ዲ ተማሪ ነች።

አሜሪካን በምትኖር ጊዜም ትምህርቷን ትከታተል የነበረው ‹‹ሳይንስ ባይ ቱሞሮ›› በሚባል ኩባንያ ውስጥ ከኅትመት እና ማስታወቂያ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት ነበር። አሜሪካ በነበረችበት ወቅት ወደ ሀገር ቤት (ኢትዮጵያ) ተመልሳ ሀገሯን የማገልገል ጉጉት እንደነበራት ትናገራለች።

በ2013 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ሥራዎችን የመሥራት ዕድል አገኘች። በዚህም የሜልባ ዘመናዊ ማተሚያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ሆነች። ማተሚያ ቤቱን እያስተዳደረች ጎን ለጎንም የኦሮሚያ ክልል የልማት ድርጅቶችን በየዘርፋቸው ከፋፍሎ ለማደራጀት እና ለማስተዳደር እንቅስቃሴ ጀመረች። በዚህም የኦ ፕሮዲዩስ ግሩፕ ተፈጠረ፤ የግሩፑም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆና ተመረጠች።

የኦ ፕሮዲዩሲንግ ግሩፕ በስሩ የሜልባ ማተሚያ ቤት፤ ኬና መጠጦች፤ ኦሮሚያ ስቲል ግሩፕ፤ ኢፋልኮ እንጨት ፋብሪካ እና ጋራጅን የያዘ ትልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው።

ማርታ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ የራሷን ሥራ ከመሥራትም ባሻገር ክልሉን የማገዝ እቅድ እንደነበራት ትናገራለች። ይሁንና እንደዚህ አይነት ኃላፊነት ተሸክማ ግዙፍ ድርጅት የመምራት ብቃት ይኖረኛል ብላ አልገመተችም። ውጭ ሀገር ኖራ እንደመምጣቷ የባሕል ልዩነት ይፈትነኛል የሚል ስጋትም አድሮባታል። አሁን ግን በአመራሮች፣ በባለቤቷና በብዙ ሰዎች ርዳታ ያለምንም ችግር ሥራዋን ለማከናወን በቅታለች።

ማርታ ከመወሰኗ በፊት የምትፈራ፤ ወስና ሥራ ከጀመረች በኋላ ግን ተግታ በመሥራት የውሳኔዋን ትክክለኛነት ለማሳየት የምትጥር ነች፤ በዚህም ተሳክቶላታል።

እንደማርታ ገለጻ፤ የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ሰፊ ሕዝብ ነው፤ ፍላጎቶቹም ብዙ ናቸው። እንደ አመራር ይህን የሕዝብ ፍላጎት ለማርካት ከእርሷ ብዙ እንደሚጠበቅ ገልጻ፤ በምትሠራቸው ሥራዎችም ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሆነ ታስረዳለች።

ሜልባ ማተሚያ ቤት ተመርቆ ወደ ሥራ እንደገባ ትኩረቱ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ነበር። በኢትዮጵያም ፕሪንቲንግ (ኅትመት) ላይ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ባለመኖሩ እና ያሉትም በልምድ የሚሠሩ በመሆናቸው የተማረ የሰው ኃይል ለማግኘት ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች። ነገር ግን ከ2014 ዓ.ም መጋቢት ጀምሮ የማሻሻያ ሥራዎችን በመሥራት ከፕሮጀክት ወደ ኦፕሬሽን በመግባት ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

የተማሪዎች የትምህርት መጽሐፍትን እና መጽሔቶችን በማሳተም በተለይም ለትምህርት ዘርፉ ትልቅ እገዛ ማድረግ ተችሏል። ተቋሙም ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ 33 ሚሊዮን መጽሐፍት ለማተም ውል ገብቶ 88 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱንም ትናገራለች።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ፤ ለኅትመት ግብዓት የሚሆኑ ወረቀቶች ከውጭ የሚገቡ ናቸው። የመሣሪያዎች መለዋወጫ ከውጭ የሚገባ ነው። ተቋሙ ምንም እንኳን በእድሜ ልጅ ቢሆንም፤ የትምህርት ሥርዓት ለውጡን ተከትሎ በርካታ ሥራዎች ወደ ተቋሙ እንዲመጡ ግድ ብሏል፤ ተቋሙ ባደረገው የሥራ ማሻሻያና በአመራሮች ቁርጠኝነት መጽሐፍቱን በወቅቱ አትሞ ለተገልጋዮች እንዲደርሱ ማድረግ ተችሏል።

የማተሚያ ድርጅቱ ለምሥራቅ አፍሪካ የሚበቃ አቅም አለው ያለችው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በቀጣይም ውስጣዊ ችግሮቹን ቀርፎ ውጫዊ ተግዳሮቶቹን ተጋፍጦ በሙሉ አቅሙ በመሥራት የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ትናገራለች።

የመንግሥት የልማት ድርጅት ዓላማዎችም በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ፤ የገበያ ክፍተትን መሙላትና ማረጋጋት፤ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ገቢ እና ሀብት መፍጠር ነው። በዚህ ረገድ ተቋሙ ብዙ ርቀት እንደሄደ ሥራ አስፈጻሚዋ ትገልጻለች። ሆኖም ግን አሁንም በሙሉ አቅሙ እየሠራ አይደለም፤ ለዚህም የበላይ አመራሮች መፍትሔ በማፈላለግ ላይ መሆናቸውንም ትናገራለች።

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሰላምታ መጽሔትን ጨምሮ ትላልቅ ሥራ እየሠራን ነው። በቀጣይም ወደ ፓኬጂንግ ሥራ ለመግባት ታቅዷል። እስከ ጅቡቲ እና ኬንያ በመሄድ ገበያ የማፈላለግ ሥራ ይሠራል፤ በዚህም የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማምጣት ታቅዷል›› ትላለች።

አሁንም ተቋሙ ከብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት እና ከቻምበር የግል ማተሚያ ቤት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ጠቅሳለች። ተቋማቱ በብዛት የኅትመት ግብዓት ሲኖራቸው ለሜልባ የሚሸጡበት ሁኔታ እንዳለና በሌሎች ጉዳዮችም በትብብር እንደሚሠሩ ታስረዳለች።

የኦ ፕሮዲዩሲንግ ግሩፕም እንደ አንድ ግሩፕ መሥራት ከጀመረ አንስቶ ለውጥ አምጥቷል ትላለች ወይዘሮ ማርታ። ወደ አንድ መምጣቱም ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም፤ ለቁጥጥር እና ለምርታማነት አስተዋፅዖ አለው። አመራሮች ብቁ እንዲሆኑ፤ በቅርበት ሁኔታውን ለመከታተል፤ ድርጅቶቹም በምርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ እና ስትራቴጂክ የሆኑ ጉዳዮች ለአመራሩ እንዲተው አድርጓል።

አሁን ላይም ሜልባ በቀን እስከ 120ሺህ ኅትመቶችን አጠናቆ ያስረክባል ይህንንም ወደ 250ሺህ ለማድረስ ይሠራል። 488 ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፤ የሀብት መጠኑም እስከ 9 ቢሊዮን ብር የሚገመት ነው፤

ወይዘሮ ማርታ ሜልባን ማስተዳደር ከጀመረች አንስቶ ማተሚያ ቤቱ አፈጻጸሙንም ገቢውንም እያሳደገ መገኘቱ የአመራር ብቃቷን እንድንመለከት አድርጎናል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You