የኮንፈረንስ ቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በአግባቡ ለመጠቀም!

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ምቹ ሀገር ሆናለች። ይህንንም ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ካስተናገደቻቸው በርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች፣ በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ከተካሄዱት በርካታ ግዙፍ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች መረዳት ይቻላል።

ይሄ እንዲሆን ያስቻሉት ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ እነዚህን ጉባዔዎችና ተመሳሳይ መድረኮች ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች በሀገሪቱ በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸውን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። አስቀድሞም እንደ አፍሪካ ኅብረት ኢሲኤ ያሉ ግዙፍ መሰብሰቢያዎች በሀገሪቱ እንዳሉ ይታወቃል፤ በቅርቡ ደግሞ በአንድ ጊዜ ብዙ ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ ሌሎች የስብሰባ አዳራሾች ያሏቸው እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ አዲሱ የንግድ ባንክ ህንጻ፣ ሳይንስ ሙዚየም እና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ያሉ ማዕከላትን አሰናድታለች።

በሆቴል አገልግሎት በኩልም በርካታ አልጋዎች ያሏቸው ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ስካይላይትን የመሳሰሉ በርካታ ባለኮከብ ሆቴሎች አሏት። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ያህል በአፍሪካም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆነ አየር መንገድ ባለቤት መሆኗም ሌላው ለኮንፈረንስ የሚያፈልግ ወሳኝ መሠረተ ልማት ነው።

ከጸጥታ አኳያም እንዲሁ የተሳታፊዎችን ደህንነት ምንም አይነት ጥያቄ ውስጥ ያላስገቡ በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎች በብዛት የማስተናገድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ልምድና ብቃቱ አላት።

መዲናዋ አዲስ አበባ እያካሄደች ያለችውን የኮሪደር ልማት ተከትሎ በመሠረተ ልማት፣ በከተማዋ ገጽታ ላይ እየታየ የመጣው ጉልህ ለውጥም እንዲሁ ለኮንፈረንስ ማዕከልነቷ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ግብዓት መሆኑ ተመስክሮለታል።

በእርግጥም ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባዔዎችን፣ ኢግዚቢሽኖችንና የመሳሰሉትን በማዘጋጀት በኩል ትልቅ አቅም ተፈጥሯል፤ ይህ አቅም ሀገሪቱ ከዚህም የተሻገረ ሌላ አቅም እንድትፈጥር አርጓታል። ለኮንፈረንስ ማስተናገድ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ሀገሪቱም መዲናዋ አዲስ አበባም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ እንዲሆኑ አስችለዋል።

ለኮንፈረንስ ማስተናገጃነት የሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች ለኮንፈረስ ቱሪዝምም እጅግ ወሳኝ ናቸው። ሀገሪቱ በእነዚህ ላይ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ሌሎች ወሳኝ ግብዓቶች የሆኑትን የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ዘና የሚሉባቸው ሥፍራዎችን፣ ጉብኝት ማድረግ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎችም መፍጠር መቻሏ ደግሞ ለኮንፈረስ ቱሪዝም ይበልጥ ምቹ እንድትሆን አድርጓል።

በኮሪደር ልማቱ የጉባዔ ተሳታፊዎች ካረፉባቸው ሆቴሎች ወይም ከስብሰባ አዳራሾቻቸው ብዙ ርቀት በእግር በመጓዝ ራሳቸውን ዘና ሊያደርጉ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ሙዚየሞችን ያካተቱ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ያሉ ግዙፍ አዳራሾች መኖራቸውም ለኮንፈረንስ ቱሪዝሙ ትልቅ ፋይዳ አለው። ይህም የጉባዔ ተሳታፊዎች ከጉባዔው ጎን ለጎን ሙዚየሞችን መጎብኘት ያስችላል። በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ለቱሪስት መስህብ ሊውሉ የሚችሉ ተቋማትን መድረስና መጎብኘትን ቀላል እንዲሆን አድርገዋል።

በተለይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎችን እያስተናገደ ያለበት ሁኔታ ሀገሪቱ በኮንፈረንስ ማእከልነት የፈጠረቻቸው ምቹ ሁኔታዎች ለኮንፈረንስ ቱሪዝምም ይበልጥ መጎልበት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ያመላክታል፤ የተለያዩ አዳራሾችን ማካተቱ፣ ሙዚየሙ ፣ አካባቢው የለማበት ሁኔታ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ ሥፍራ እንዲኖረው ያደርጋል።

በቅርቡ ደግሞ በአይነቱ ልዩ የሆነ ሌላ ግዙፍ የኮፈረንስ ማእከል ይፋ አድርጋለች። ይህ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽስን ማዕከል በመባል የሚጠራው ግዙፍ ተቋም ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ብዙ ሺህ ሰዎችን በአንዴ ማስተናገድ የሚችሉ በርካታ አዳራሾችን፣ ሌሎች በርካታ አዳራሾችን፣ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ኢግዚቢሽንና ባዛሮችን ማካሄድ የሚያስችሉ ስፍራዎችን እና ሰፊ አረንጓዴ ስፍራዎችን ወዘተ እንዲያካትት ተደርጎ በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ማዕከል ነው። ማዕከሉ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ አዲስ የመንገድ ግንባታ እየተካሄደለትም ይገኛል።

የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ሀገሪቱን ወይም ከተሞቿን መጎብኘት ሊፈልጉ ይችላሉ፤ ሀገሪቱም ያሏትን መስህቦች ለማስጎብኘት ትፈልጋለች፤ አንዳንድ ኮንፈረንሶች ደግሞ የጉብኝት ፓኬጅ ጭምር እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።

ለእዚህ ደግሞ ለኮንፈረንስና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ሲባል የተፈጠሩ መሠረተ ልማቶችን በማስጎብኘት ሀገሪቱ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ መሥራት ያገባል። አስጎብኚዎችና ከኮንፈረንስ አዘጋጆች በዚህ በኩል ብዙ ይጠበቅባቸዋል። የቱሪስት መስህቦችን ማስተዋወቅና መሸጥ ላይ በልዩ ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል። አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና የቀድሞዎቹንም በሚገባ ማስተዋወቅ እንዲሁም ከኮንፈረንሶቹ ጋር እንዲያያዙ ማድረግ ላይ በስፋት መሥራት ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ ነው!

አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You