አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያና በኤርትራ መካካል ሰላም በመስፈኑና ስጋት በመወገዱ ድንበር አካባቢ የነበረውን የተወሰነውን የመከላከያ ሠራዊት ወደ ሌሎች የ ኢትዮጵያ ክፍሎች የማንቀሳቀስ ሥራ እያከናወነ መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በመከላከያ እየተከናወነ ያለው መልሶ የማደራጀት /የሪፎርም/ ሥራ የሠራዊቱን በላቀ ብቃት ግዳጅ የመወጣት አቅም የሚጠናክርና ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ የሚያገለግልበት ሁኔታ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡
የልዩ ዘመቻዎች ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሞላ ኃይለማርያም የመከላከያ አዲስ አደረጃጀትን አስመልክቶ ትናንት ከሌሎች የመከላከያ ከፍተኛ አዛዦች ጋር በመከላከያ ሚኒስቴር በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ በኤርትራ በኩል የነበረው ስጋት በመወገዱ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረውን ሠራዊት የተወሰነውን የሜጋ ፕሮጀክቶችን ደህንነትና የሕብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ፣ የክልሎችን የጸጥታ ኃይል አቅም ለማጠናከር ሲባል ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የማንቀሳቀስ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
እንደ ሌተናል ጄነራል ሞላ ገለጻ፤ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍሎች ማዛወር መጀመሩ ሠራዊቱ ሙሉ ለሙሉ ከባድሜና ሌሎች አካባቢዎች ወጥቷል ማለት አይደለም፡፡
በሚኒስቴሩ እየተሠራ ያለው አዲስ አደረጃጀት መከላከያ ዕጩ መኮንኖችን ከዩኒቨርሲቲ እንዲመለመል ዕድል እንደሚሰጥ የተናገሩት ሌተናል ጄነራል ሞላ፤ ሰራዊቱ ለህገ መንግሥቱ ተገዥ ሆኖ የህዝብ አለኝታነቱ የሚጠናክርበትና የብሄር ብሄረሰቦች ተዋፅዖ የተመጣጠነ እንዲሆን ማስቻሉን አመልክተዋል፡፡
የሰሜን ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ጌታቸው ጉዲና በበኩላቸው በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆምና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሠራዊቱ ከተለያዩ የጸጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በችግሩ ተዋናዮች ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አሳስበዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ተላብሶ የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም ሳይታክት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ዘውዱ በላይ፤ ሠራዊቱ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«ወደ ቤተ መንግሥት የሚገባው በምርጫ ብቻ ነው» ያሉት ሜጀር ጄነራሉ፤ በተለይ በመስከረም 30ቀን 2011ዓ.ም መሳሪያ ታጥቀው ወደ ቤተ መንግሥት የሄዱት የመካላከያ አባላት ተግባር ከሠራዊቱ ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ በመሆኑ ከድርጊቱ ፈጻሚዎች መካከል 66ቱ ላይ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሰጥ ፤ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ አስተዳዳራዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
ጌትነት ምህረቴ