
ትምህርትና ጊዜ በብርቱ ቁርኝት አላቸው:: አጥብቀውም የሰላምና ፀጥታ መስፈንን ይሻሉ:: እነዚህ ነገሮች ምሉዕ ካልሆኑ ግን ሀገሪቱን በማኅበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊም ሆነ በፖለቲካዊ መስክ ይፈትኗታል:: በዚህ ውስጥም ተማሪዎች የመማር ዕድላቸውን በብዙ መልኩ እንዲያጡ ይሆናሉ:: በከባድ ተፅዕኖ ውስጥም ይወድቃሉ:: በመሆኑም ለሰላምና ፀጥታ መስፈን ትልቁን ተሳትፎ ማድረግ የሚገባቸው ከወላጆች ባሻገር ትምህርት ቤቶችና የትምህርቱ ማኅበረሰብ ናቸው::
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና አማካሪ አቶ ኤፍሬም ተሰማ በዚህና መሰል የትምህርት ጉዳይ ላይ ቢሮው እየሠራ ያለውን ተግባር ዘርዘር አድርገው ይናገራሉ:: ሥራውም «ትምህርት ለትውልድ» በሚለው ንቅናቄ ላይ ተመሥርቶ ስለመሠራቱ ያነሳሉ::
ትምህርት የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት መሠረት እንደሆነ ይታወቃል:: ይህንን ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ደግሞ ተማሪዎች ከፀጥታ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ችግሮች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ፤ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እና ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ በርካታ አሠራሮችን መዘርጋት የግድ ይላል:: ስለሆነም በክልል ደረጃ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው::
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አንዱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ያለው የድጋፍና ክትትል ሱፐርቪዢን ሥራው ነው:: ሥራው በዞን፤ በወረዳና ትምህርት ቤቶች ላይ ተመሥርቶ ይከናወናል:: ቢሆንም በዋናነት ማዕከል የተደረገው የትምህርት ቤቶችን ተግባርና እንቅስቃሴን በማየት ነው:: የሚመራው በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሲሆን፤ ለእያንዳንዱ የገዥው ፓርቲ አባል አመራር አንዳንድ ትምህርት ቤት ተሰጥቶ ትምህርትና ትምህርትን በተመለከተ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ይቆጣጠራል:: ውጤታማ ሥራ እንዲሠራም ድጋፍ ያደርጋል::
እነዚህ ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ የሚያቅዷቸው እቅዶች ላይ ተንተርሰው የተከናወነውና ያልተከናወነው በምን ምክንያት እንደሆነም ይለያል:: አመራሮቹ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ከአንድ እስከ ሁለት ቀን ባለ ቆይታቸው ያልታቀደ ዕቅድ ካለ በመከታተል እንዲታቀድ ያደርጋሉ::
በክትትል ሥራው እንደ ክልል ብዙ ለመማር ማስተማሩ እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን ነቅሶ ማረም እንደተቻለ የገለጹት ኃላፈው፤ በዚህ ክትትል ምንም የፀጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤቱ አመራር ሙሉ ቀን ማስተማር ሲገባው ግማሽ ቀን የሚያስተምርበት ሁኔታ ታይቷል:: ለአብነት በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ቀን ማስተማር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እያለ ትምህርት ሲሰጥ የነበረው ለግማሽ ቀን ብቻ ነበር:: በዚህም ይሄን ትምህርት ቤት የመከታተልና የመደገፍ ኃላፊነት የተሰጠው አመራር በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሙሉ ቀን እንዲሰጥ አድርጓል:: በተጨማሪም ሌሎች ውሃ የሌላቸው ትምህርት ቤቶች ውሃ እንዲያስገቡ፤ መምህራን እጥረት ያለባቸው መምህራን እንዲቀጠርላቸው፤ መጽሐፍት ችግር ያለባቸው መጽሐፍት እንዲቀርብላቸውና በፈረቃ የሚያስተምሩም ሙሉ ቀን እንዲያስተምሩ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም አንስተዋል::
በክትትል ሥራው አንድ ሰው በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ከአንድ እስከ ሁለት ቀን ቆይቶ መምህሩ የሚያስተምርበትን እቅድ እንዴት ያወጣል፤ እየተጠቀመበት ነው ወይ ለይስሙላ ነው የሚያዘጋጀው የሚለው ተፈትሿል:: በዚያ ክፍል ውስጥ የተመዘገበው ስንት ተማሪ ነው፤ ክትትሉስ ምን ይመስላል፤ ተማሪው ለመማር ምን ያህል ፍላጎት አለው፤ የደብተር አያያዙ ምን ይመስላል፤ መምህሩ የተማሪውን ደብተር ያያል ወይ ፤ የቤት ሥራ ሰጥቶ ያርማል ወይ የሚሉና መሰል በክፍል ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች እንዲሁም የተማሪ መጽሐፍት ጥምርታ በሙሉም እንደሚቃኝም አብራርተዋል::
ከመጽሐፍት አንጻር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የታተሙ አዳዲስ መጽሐፍቶችን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ የማተሚያ ድርጅቶች አቅም ውስንነት መኖሩ፤ በሚፈለገው ጊዜ አሳትመው ማድረስ ያልቻሉት መኖራቸው መጽሐፍቱ ፈጥነው ለተማሪ መድረስ አልቻሉም:: በተጨማሪም ወረዳዎች ላይ በስቶር የማስቀመጥ ሁኔታዎች መታየት፤ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተረፈውን መጽሐፍት ራሳቸው ጋር መያዝ፤ ተማሪው መጽሐፍቱን ወስዶ እቤት ማስቀመጥና ትምህርት ቤት ይዞ አለመምጣት በችግርነት የሚነሱ ናቸው:: ከዚህ አንጻርም አመራሩ ይሄንን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል::
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የታተመ አምስት ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍ በተጨማሪ በተለያየ መንገድ ያልተሰራጨው መጽሐፍት ወደተፈለገው ትምህርት ቤት እንዲደርስ ማድረግ ነው ሌላው በአመራሩ የተሠራው:: በተጨማሪም ቢሮው መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ስድስት ሚሊዮን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍት በማሳተሙ ሁኔታው በመጠኑም ቢሆን ተፈቷልና ተማሪዎች እቤት ያስቀመጡትን መጽሐፍት ይዘው መምጣት እንዳለባቸውም አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ ሥራ መገባቱን ያስረዳሉ::
የተማሪዎችና የመምህራን ዲሲፕሊን ጉዳዮችም በቼክ ሊስት ውስጥ እንደ ዋና ጉዳይ ተይዞ ትምህርት ቤት በመውረድ እየተሠራበት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ በሕጉ መሠረት ሥራቸውን ያላከናወኑ መምህራን፤ የትምህርት ቤት አስተዳደሮች፤ አመራሮች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ብሎም ከኃላፊነታቸው እንደተነሱም ያወሳሉ::
በክትትሉ መሠረት በክልሉ ከደረጃ በታች የነበሩ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች ስለመከናወናቸውም ያነሱት:: ከዚህ አንፃር ባሳለፍነው የ2016 ዓ.ም ክረምት የ2ሺ948 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ዕቅድ ስለመያያዙም ያስታውሳሉ:: በ2017 አጋማሽ የትምህርት ዘመን ድረስም ከእቅዱ በላይ 3ሺ304 የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አጥራቸው፤ ግንባታቸው እንዲሠራ ተደርጓል:: የተማሪዎች መቀመጫም ተሟልቷል:: የተሰባበሩ በሮችና መስኮቶች ተጠግነዋል:: ሳቢ፤ ማራኪና ምቹ እንዲሆኑም ተሠርቷልም ብለዋል::
በፀጥታ ችግር የወደሙትን ለመተካትና ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ ከ20ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንም አውስተዋል:: በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደተገነቡ ጠቅሰው፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ብቻ 5ሺ የተገነቡ መሆኑንም አንስተዋል::
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ባለፈው ክረምት 1 ሺህ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እስከ ሁለተኛ ሩብ ዓመት 700 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተሠርተው ወደ አገልግሎት ገብተዋል:: ተማሪውን ውጤታማ ከማድረግ አንፃርም የመምህራኑ ምቾትና ጥቅም መጠበቅ ስለሚያስፈልግ በዚህ ዓመት ክረምት ላይ የመምህራን መኖሪያ ቤት ከእቅዱ በላይ 10ሺህ 56 ተገንብተው ለመምህራኑ ተረክበዋል:: ብዙ ሥራ የሚሠራበትና መረጃ የሚሰበሰብበት ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ከመሆኑም አንጻር ወጣት ተማሪዎች ይሄን እንዲለማመዱ ከማድረግ አኳያም በግማሽ ዓመቱ እንደ ቢሮ በሁሉም ወረዳዎች ውስጥ 361 ዲጂታል ፓርክ ለመገንባት ታቅዶ ከእቅዱ 72 በመቶ ተከናውኗል::
ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከአካባቢ ፀጥታ መጓደል ጋር ተያይዞ በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ተቋማት የደረሰውን ጉዳት እና ጉዳቱን ለማካካስ እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስቀጠል ስለተከናወነው ሥራም አንስተዋል:: እሳቸው እንዳሉትም፤ በኦሮሚያ ክልል በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች ካለው አለመረጋጋትና ከፀጥታ መጓደል ጋር ተያይዞ ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተዋል:: ከተዘጉት በተጨማሪ በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችም ነበሩ:: የፀጥታ ችግር ባለባቸው የክልሉ ዞኖች ከነበሩት ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 296ቱ በከፊል ተጎድተዋል:: ከእነዚህ ውስጥ 74ቱ የሁለተኛ ደረጃ ሲሆኑ፤ 1ሺህ 222 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው::
በተጨማሪም ከዚሁ ፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ 344 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል:: ከወደሙት መካከል 23ቱ ሁለተኛ ደረጃ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን አንስተው፤ በአጠቃላይ የፀጥታ ችግር ባለባቸው የክልሉ ዞኖች ከነበሩት ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 640 ትምህርት ቤቶች ከፀጥታ ጋር ተያይዞ በአካባቢያቸው በነበረው ችግር ጉዳት ስለደረሰባቸው ከመማር ማስተማሩ ሂደት ተስተጓጉለው ቆይተዋል:: እስከ ባለፈው 2016 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ድረስም 400 ያህሉ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደነበርም ያስረዳሉ:: በተጎዱትና በተዘጉት ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን እንደተገደዱ ይገልጻሉ::
አቶ ኤፍሬም እንዳሉት፤ ወላጅ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይልክ፤ በላከባቸው አካባቢዎችም በብርቱ እንዲጨነቅና እንዲረበሽ ሲያደርግ የነበረ የክልሉ የፀጥታ ችግር ጉዳይ አሁን ላይ ቀስ በቀስ በብርቱ እየተሻሻለ መምጣቱንም ሳያነሱ አላለፉም:: በ2017 ዓ.ም ትምህርት ዘመን የፀጥታው ጉዳይ እየተሻሻለ በመምጣቱ አብዛኞቹ በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ተማሪዎችን በመቀበል እያስተማሩ ስለመገኘታቸውም አውስተዋል::
ከ2012 እስከ 2016 ተዘግተው ከነበሩ 400 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፀጥታው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ በ2017 ትምህርት ዘመን ስድስት ወራት 200 ያህሉ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ተማሪዎችን በመቀበል እያስተማሩ ለመገኘት ስለመብቃታቸውም ይናገራሉ::
እንዲህም ሆኖ በፀጥታ ችግር ተዘግተው ከነበሩት 400 ትምህርት ቤቶች ቀሪዎቹ 200 ትምህርት ቤቶች አሁንም የአካባቢያቸው የፀጥታ ሁኔታ ባለመሻሻሉ ለመከፈት አለመቻላቸውን ያነሳሉ::
በ200 ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ሩቅም ቢሆን በአጎራባች አካባቢዎች ሄደው የሚማሩበት ሁኔታ መመቻቸቱን ይጠቅሳሉ:: በአጠቃላይ በክልሉ ከ2012 ዓ.ም በፊት በነዚህ የፀጥታ ችግር ባለባቸው ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ከ600 ሺ በላይ ተማሪዎች በዚሁ መልኩና አዲስ በተገነቡ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ መደረጉንም ያስረዳሉ አቶ ኤፍሬም::
ይሄም ሆኖ አሁንም ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ባልተከፈቱት 200 ትምህርት ቤቶች፤ ምን አልባትም ጉዳት ደርሶባቸው በነበሩ ትምህርት ቤቶች ይማሩ ከነበሩ ተማሪዎች አንዳንዶቹ ባለመመቻቸት ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለው ሊቀሩ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ::
በአጠቃላይ አዲስ ከተጨመሩት ጋር በኦሮሚያ ክልል አሁን ላይ 17 ሺ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ:: በዚህ ውስጥ ዘጠኝ ሚሊዮን ተማሪዎች እየተማሩ ነው:: እንደዚሁም 1ሺ 369 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። በዚህም 1ነጥብ 1ሚሊዮን ተማሪዎች እየተማሩ ነው:: እንደ ክልል በ2017 ትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች አጠቃላይ ብዛትም 11 ነጥብ 98 ሚሊዮን ነው ይላሉ:: ከነዚህ ተማሪዎች ውስጥ 4ሚሊዮኑ የቅድመ አንደኛ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው::
«ዘንድሮ የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀድናቸው ተማሪዎች ቁጥር ዘጠኝ ሚሊዮን ነበር» ሲሉ የሚያስታውሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በተለያዩ ምክንያቶች አራት ሚሊዮኑን ተማሪዎች ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግ ስለመቻሉም ያስረዳሉ::
በስተመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፤ ዘንድሮ ለ12ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተና እንዲሁም ለስድስተኛ እና ለስምንተኛ ሚኒስትሪ ፈተና ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው:: ዝግጅቱ በክልሉ ያሉትን 41 ልዩና አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚማሩትን ተማሪዎች ያጠቃልላል:: ለአብነትም አዳሪ ትምህርት ቤቶች 851 ተማሪዎችን፤ ልዩ ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው 1 ሺ 89 ተማሪዎች ያስፈትናሉ:: ምዝገባ በኦን ላይ ተካሄዷል:: በተለይ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተና ከአሮጌው እና ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብዓቶች እንደሚመጣ ተገንዝበው እነዚሁ ላይ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው:: ሞዴል ፈተናዎችን በመሥራትም መለማመድ አለባቸው:: የሁለተኛው ትምህርት ዘመን የክትትል መርሐ ግብር ተጀምሯል:: አመራሩ ወደ ትምህርት ቤቶች ወርዷል:: ክትትሉ የ12ኛ ሀገር አቀፍ ፈተና እንዲሁም ስድስትና እና ስምንተኛ ክፍል ላይ ያለውን ዝግጅት ይፈትሽና ይቃኛል ሲሉ ያስረዳሉ::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም