ትናንትን አይቶ፤ ዛሬ ላይ ቆሞ፤ የፊቱን ለመሥራት

ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበሩ የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤቶች በማህበረሰቡ፤ በራሱ በተፈታኝ ተማሪው እና በመምህራን ላይ ድንጋጤን የፈጠረ ነበር ። በትምህርት ጥራት ጉዳዩ የሚመለከተው ሁሉ ቆም ብሎ እንዲያስብ እድል የሰጠ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፖሊሲ ጀምሮ ያሉ ክፍተቶችን ለመፈተሽ ጭምር በር የከፈተ ፣ ለትምህርት ስብራቶች መፍትሄንም ያመላከተ ነበር።

በ2015 ዓ.ም ከተፈተኑት ተማሪዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት ከሦስት በመቶ ያልበለጡ ሲሆኑ፤ በ2016 ዓ.ም ደግሞ ፈተናውን ከወሰዱ 674ሺህ 823 ተፈታኞች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት አምስት ነጥብ አራት በመቶ ብቻ መሆናቸው በወቅቱ ተገልጿል። በ2016 የፈተና ዘመን አንድ ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ እንዳላሳለፉ የታየበት መሆኑና 637 ሺህ 823 ያህል ተማሪዎች መውደቃቸው ሁሉም ሰው በትምህርት ዙሪያ እንዲወያይ ያደረገ ጉዳይ ነው። የትምህርት ስብራቱን ለመጠገንም ከማን ምን ይጠበቃል ? የዘንድሮ ፈተናንስ በውጤታማነት ለመደምደም ትምህርት ቤቶች ምን የተለየ ዝግጅቶችን እያደረጉ ናቸው? የሚለውን ለዛሬ እንቃኛለን።

ቀድሞ መዘጋጀት ለላቀ ውጤት ያበቃልና እንደ ሀገር ለመጪው ፈተና ምን አይነት ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚለውን የፈተናዎች አገልግሎት መረጃን መነሻ አድርገናል። ፈተናው እንደ ሀገር የሚሰጠው እንደ ዓምናው በብሔራዊ ደረጃ በወረቀትና በኦንላይን በመሆኑ በአጠቃላይ የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል የትምህርት ግብዓት ማሟላት፣ የመምህራን አቅም ግንባታ፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና የክፍል ውስጥ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ማሻሻል ላይ ልዩ አቅጣጫ ተቀምጦ ልዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ይላል የፈተናዎች አገልግሎት በማህበራዊ ድረገጹ ያስቀመጣቸው መረጃ ።

ትምህርት ሚኒስቴርም ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትን በተለያየ መድረክ ሲገልጽ ቆይቷል። በዚህም መሠረት ለተወካዮች ምክር ቤት አጠቃላይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በሚመለከት ከፌዴራሉ መንግሥት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ያሉ ተቋማት ለተሻለ የተማሪዎች ውጤት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በተሳካ ሁኔታ፣ ከጥራት ባሻገር በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን እንደሚያስችልም ይታመናል።

የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመቀበል ወደ ትግበራው ከገቡ ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አንዱ ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዝግጅት ምን እንደሚመስል በክልሉ ትምህርት ቢሮ የፈተና ክፍል አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሀሰን ቃሲም ነግረውናል ።

እንደ አቶ ሀሰን ማብራሪያ፤ ትምህርት የአንድ አካል ሥራ ውጤት ብቻ አይደለም። ሁሉም ተረባርቦ የሚሠራው ካልሠራ ደግሞ የሚጠየቅበት፤ ዋጋ የሚከፍልበት የሀገር ጥምረት ውጤት ነው። በዚህም አዲስ የአፈታተን ሥርዓትን ተከትለን ተማሪዎቻችንን ወደ መስመሩ ማስገባት ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ለውጦችም ችግሮችም ተከስተዋል።

ከለውጡ ስንነሳ ተማሪዎች፤ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ከባለፉት ልምዶች በመቅሰም በቁርጠኝነት፤ በራስ መተማመን ውስጥ አልፈው ከኩረጃ የጸዳ ውጤታማ ሥራን እንዲሠሩ ሆነዋል። በተለይም ተማሪዎች ኩረጃን ተጸይፈው፣ ፈተናውን ከሚረብሹ ነገሮች ራሳቸውን ቆጥበው፣ በተረጋጋ እና በራስ መተማመን በተሞላበት ስሜት ፈተናዎችን ወስደው ለተሻለ ውጤት ሲበቁም ተመልክተናል።

መምህራንም ሆኑ የክልል ትምህርት ቢሮዎች እንዲሁም የፈተናዎች አገልግሎት ሥራዎች በሚገባ ታይተውና ጉድለቶቹ ተለይተው እንዲሠራባቸውም እድል አግኝተዋል። በተመሳሳይ ማህበረሰቡም ቢሆን ይህ አይነት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ምን ያህል ተማሪዎችን ማብቃት እንደቻለ የተረዳበትና ለልጆቹ ድጋፍ ማድረግን የጀመረበትን ሁኔታ እንዲያመቻች አስችሎታል፡፡

አቶ ሀሰን እንደሚሉት፤ ከውጤታማነቱ ባልተናነሰ መልኩ በፈተና ሥርዓቱ ውስጥ የታዩ ሀገራዊ ስብራቶችም ነበሩ። ከእነዚህ አብዛኛው አስተማሪ ሆኖ አልፏል። እንደ ክልልም የታየው ይህ ሁኔታ ነው። የፈተናው ውጤት ዝቅ ማለት ከዓመት ወደ ዓመት በቁጭት ለለውጥ የሚሠራበትን ሁኔታ ለመቀየስ አስችሏል። ለዚህም በማሳያነት የሚጠቀሰው የአፈታተን ሥርዓቱ ወደ ሥራ ሲገባ ማለትም በ2014 ዓ.ም የነበረው ውጤትና የ2016 ዓ.ም ውጤትን ማነጻጸር ብቻ በቂ ነው።

በ2014 ዓ.ም በክልሉ ከተፈተኑት ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉት ተማሪዎች ቁጥር 1 ነጥብ 8 በመቶ ሲሆን፤ ከሪሚዲያል ተማሪዎች ጋር ሲደመር 23 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲቀላቀሉ እድል አግኝተዋል። በተመሳሳይ በ2015 ዓ.ም ከተፈተኑት ተማሪዎች ውስጥ ሁለት ነጥብ ሶስት ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል። ይህ ቁጥር ሪሚዲያል ከገቡት ተማሪዎች ጋር ሲደመር 26 በመቶ ነው ። በአምናው የፈተና ውጤት ደግሞ ከ50 በላይ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲዎችን የተቀላቀሉት ቁጥር ወደ ሶስት ነጥብ ስምንት ከፍ ያለ ሲሆን፤ የሪሚዲያል ተማሪዎች ሲጨመሩ 30 በመቶ ያህሉ ማለፍ ችለዋል።

የማለፍ ምጣኔው ከብዛት አንጻር ብቻ ሳይሆን 500 እና ከ500 በላይ በማምጣትም እያደገ የመጣ እንደነበር የጠቆሙት ዳሬክተሩ፤ በቅደም ተከተል 77 ተማሪ ከ100 በላይ ተማሪና 300 ተማሪ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን በከፍተኛ ውጤት እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል። ይህ ግን በ2017 ዓ.ም መደገም እንዳለበት ያምናሉ። ለዚህም እንደ ክልል ጠንከር ያሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ አቶ ሀሰን ማብራሪያ፤ በ2017 ዓ.ም በክልሉ ይፈተናሉ ተብሎ የታሰቡ ተማሪዎች በ1280 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ሲሆኑ፤ ቁጥራቸው 232 ሺህ 620 ነው። በዚህም ከዓምናው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በማለትም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ተግባራቱ ከዝግጅት ምዕራፉ ጀምሮ ያሉት እንቅስቃሴዎች በእቅድና ፕሮግራም የሚመሩ ናቸው ።

ያለፉትን ዓመታት ክፍተትና ጥንካሬ በመለየት ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ እንደ ክፍተት ከተነሱት መካከልም አንዱና ዋነኛው የተለመደውን የምዘና ሥርዓት ቶሎ አቁሞ በአዲሱ የአፈታተን ሥርዓት ውስጥ ገብቶ በአግባቡ መጓዝ አለመቻል እንደሆነ አቶ ሀሰን ይናገራሉ።

የፈተና ሥርዓቱ ከ2014 ዓ.ም በፊት ብሔራዊ ፈተናው ሲሰጥ የፈተና አሰጣጡ ከ50 በላይ ያመጣ በሚል ሳይሆን የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም በማየት ተማሪዎች እንዲገቡ በመደረጉ የተማሪዎች ዝግጅት ትኩረት አግኝቶ እንዲሰራበት አልተደረገም። የሚያልፉትም ዩኒቨርሲቲዎችን ለማሟላት በሚመስል መልኩ ነው። ይህ ደግሞ ዛሬ ላይ የማይጠፋ ጠባሳ አስቀምጦ እንዲያልፍ አድርጎታል ይላሉ።

ሌላው ለተማሪዎች ውጤት ዝቅ ማለት መንስኤ ነው ያሉት ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ተማሪዎችን ብቁ አድርጎ ማውጣት አለመቻል ነው። ተማሪዎች ከክፍል ክፍል ሲሻገሩ ብቃታቸው ተለክቶ፤ ተገቢውን የምዘና ሂደት አልፈውና ለደረጃው የሚመጥን ትምህርት አግኝተው አይደለም። ቁጥር ለመሙላትና የአለፈ የተማሪ ብዛት ከፍተኛ ነው ለመባል በሚያመች መልኩ በመሆኑ ነው። እነዚህ ክፍተቶች ዛሬ ድረስ ተከትለውን ዘልቀዋል። እነርሱን የመፍታት ሥራም እንደ ክልል እየሠራን ነው ሲሉ ነግረውናል።

እንደ አቶ ሀሰን ንግግር፤ ከምዘናው ባሻገር ዐቢይ ምክንያት ነው የሚባለው የመፈጸም አቅም ሁኔታና ክፍተት ነው። በተለይ ከላይኛው እርከን ጀምሮ እስከ ወረዳ ያለው የአስተዳደር ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ ነበር። የትምህርት አሰጣጡ ሁኔታ ሲፈተሽም ችግሮቹ የጎለበቱ ነበር። የተጨማሪ ትምህርትም ሆነ መደበኛ ክፍልን ተከታትሎ የማስተማርና ተማሪዎችን የማገዝ ተግባር በመምህራኑም ሆነ በትምህርት ቤት ማህበረሰቡ በእጅጉ የላላ ነው። ስለዚህም ውጤቱ የሚጠበቀውን ያህል እንዳይሆን አድርጎታል።

በክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተፈተኑት ተማሪዎች ከታችኛው ክፍል የመጡበት ሂደት ፤ የምዘና ሥርዓታቸው ከፍተኛ ክፍተት የታየበት እንደሆነ ገምግሞ በአጭርና ረጅም ጊዜ የሚሰሩ ተግባራትን ለይቷል። በአጭር ጊዜ እሠራለሁ ከአላቸው መካከልም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በሚመለከት የተጠናከረ ሥራ መሥራት የሚለው ሲሆን፤ ይህንን በተመለከተ የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ለሁለት ወር ያህል የክልል ባለሙያዎችና አመራሮች በዞን በመውረድ የ12ኛ ክፍል የትምህርት አሰጣጥን በተመለከተ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይቷል። በዚህም በርካታ ችግሮች ተለይተዋል። ለችግሮቹ መፍትሄ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

ከተሠሩ ሥራዎች መካከልም ከትምህርት ቤት ባሻገር ክልል አቀፍ ፈተናዎችን በመስጠት ተማሪዎቹ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመረዳትና ችግሮቻቸውን ለይቶ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ፈተና መሰጠቱ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ፈተናው ስታንዳርዱን የጠበቀና የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጭምር ያሳተፈ ሲሆን፤ ተማሪዎች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ በሚገባ ይለያል ተብሎ ታምኖበታል። ክፍተታቸውንም እንደ ክልል ለማወቅና እርማት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተስፋ ተጥሎበታል።

እርማቱን በወረዳዎችና ትምህርት ቤቶች ለማከናወን የታቀደ ሲሆን፤ ዓላማውም እያንዳንዱ ትምህርት ቤት፤ መምህራንና ተማሪዎች ያሉባቸውን ክፍተት እንዲለዩ ማድረግ ነው። ከዚያም የፈተናውን ውጤትና የተማሪዎችን ደረጃ በማየትና ለመፍትሄው ለመሥራት ከሳምንት በኋላ ከክልል ጀምሮ ያሉ ባለሙያዎች ወደ ዞንና ወረዳ እንደሚሠማሩና ሁኔታውን እንደሚመለከቱ አቶ ሀሰን ይገልጻሉ።

ይህ የፈተና ውጤት መሠረታዊ የተማሪዎች የአመለካከት ለውጥ ላይ ጭምር ተግባራት እንዲከናወኑ የሚያግዝ መሆኑን ያነሳሉ። ከፈተናው ባሻገር እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማገዝ የሚከናወን የ100 ቀን እቅድ እንዲያቅዱ መወሰኑንም አስረድተዋል። ሀገርአቀፍ ፈተናዎችን በሚመለከት ምን ላይ እንደሚያተኩሩ በመለየት ሁሉም በእኩል ደረጃ የአጠናን ዘዴን እንዲከተሉ ለማድረግም በትምህርት አይነቶች ብቃት ያላቸው መምህራን በመምረጥ በቪዲዮና በድምጽ የተቀረጹ ትምህርቶች ተሰራጭተው እንዲማማሩበት እየተደረገ መሆኑንም አጫውተውናል። ፈተናዎች የሚሰጡት በአብዛኛው በኦላይን ስለሆነም ቴክኖሎጂው ላይ ክፍተት ያለባቸውን ተማሪዎች በመለየትም የተለየ የትምህርት ድጋፍ እንዲደረግም እየተሠራ ስለመሆኑም ነግረውናል።

እንደ አቶ ሀሰን እምነት በአለፉት ዓመታት የተፈተኑ ተማሪዎች ውጤት ማነስ አለያም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውደቅ መንስኤው የምዘና ሥርዓቱ ብቻ አይደለም። ከዚያም የተሻገሩ ችግሮች አሉ። እነዚህም በቀደመው አሠራር እየተገፉ በመምጣታቸውና በቂ እውቀት ሳይጨብጡ ከክፍል ክፍል መዛወራቸው ነው። አሁን ጭምር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው የትምህርት አቀባበላቸውም ሆነ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ተማሪዎች ያጋጥማሉ። እነዚህን ተማሪዎች በተለያየ መልኩ ለማገዝ ቢሞከርም ተወዳዳሪ ለመሆን በእጅጉ ይቸገራሉ። ስለሆነም ይህንን መፍታት የሚቻለው ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ በመሆኑ ክልሉ በዚህ ዙሪያም እየሠራ ይገኛል ።

እንደ ኦሮሚያ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ክፍተት ለመሙላት የአብዛኛው ተማሪ መገኛ የሆኑ ቦታዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን በጥራትና በደረጃ መሥራት ቅድሚያ ተሰጥቶታል። ምክንያቱም ለአርሶአደሩና አርብቶ አደሩ ልጅ በቂ እውቀት የሚያስጨብጡ ትምህርት ቤቶችን መስጠት የትምህርት ጥራቱን ማረጋገጥ ነው ተብሎ ይታመናል። ሌላው ተማሪዎች የማያገኙትን የትምህርት ደረጃ እንዲያገኙ ማስቻል ሲሆን፤ ይህም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት ነው። ለእነዚያ የሚመጥኑ መምህራንን በማሠልጠን ተማሪዎቹ ብቁ ሆነው እንዲገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። አሁን ላይ ከ12 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወደ ተግባር መግባታቸውን አንስተዋል። ይህ እድል ገጠሩ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ከከተማ ተማሪዎች እኩል ለማድረግ ያስችላል ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ሀሰን በመጨረሻ ያነሱት ሃሳብ የውጤቱ መሻሻል የሁሉም በየደረጃው ያሉ አካላትን ርብርብ ይጠይቃል። የትምህርት አመራሩ፣ ወላጆች፣ ተፈታኝ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትልቅ እገዛን ማድረግ ካልቻለ ትምህርቱ በለውጥ ሊታገዝ አይችልም። ስለዚህም የትምህርቱ ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው ካስፈለገ፤ ጥራቱም እንዲረጋገጥ ከታሰበ ዛሬም፣ ነገም ከነገ በስቲያም ብሔራዊ ፈተና ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ላይ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም የትምህርት ዓላማና ግብ ብቃት ያለው ዜጋ መፍጠር ነው። ብቃት ያለው ዜጋ ደግሞ ለሀገር ምሰሶ ነው። ስለዚህ ተማሪዎች በቁርጠኝነት በራሳቸው በመተማመን፣ ኩረጃን ተጸይፈው፣ ፈተናውን ከሚረብሹ ነገሮች ራሳቸውን ቆጥበው በተረጋጋ እና በራስ መተማመን በተሞላበት መንፈስ ፈተናዎችን መውሰድ እንዲችሉ ሁሉም ከአሁን ጀምሮ መሥራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You