«የሀገር ልጅ የማር ጠጅ»

ዶክተር ግዛቸው አብደታ ይባላሉ። ሜዲካል ዶክተርና የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ስፔሻሊስት ናቸው። በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የጤና ማበልጸግ ሳይንስ እና የሪሰርች ሜትዶሎጂ መምህር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ዛሬ ላይ ደግሞ በሀገር ደረጃ ከተመረጡ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ ሆነው በ‹‹ ክህሎት ኢትዮጵያ›› ፕሮግራም በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት እየሰለጠኑ ነው። ለሥልጠናው ተመራጭ ያደረጋቸውና ይዘውት የመጡት የፈጠራ ቴክኖሎጂ መጸዳጃ ቤትን ይመለከታል። ይሄ ቴክኖሎጂ በውሃ ግፊት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን መጸዳጃ ቤት አገልግሎት የሚቀይር እንደሆነ ይናገራሉ።

ቴክኖሎጂው ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ የሚጠቅም ፤ ውሃን፤ ሽንትንና ሰገራን በየፈርጁ ለይቶ በአግባቡ የሚያስወግድበትን አሠራር የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳሉ። የሚሠራበትም አግባብ በፋይበር ግላስ ሲሆን፤ ማቴሪያሉ ስለማይበሰብስ፣ ስለማይዝግና የመሸከም አቅሙ ከፍተኛ ስለሆነ ተመራጭ እንዳደረገው ይናገራሉ። ይህ መሆኑ በርካታ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኝ ያክላሉ።

አንዱ ማኅበረሰቡ መጸዳጃ ቤትን ሲሠራ ጉድጓድ ቆፍሮ መሥራትን፤ ፎቅ አካባቢዎች ላይ በአንድ መስመር የሚወርድበትን አኳሄድ የሚያስቀር ነው።

ሁሉም በአንድ አቅጣጫ መውረዱን ማስቀረቱ ያለው ጠቀሜታ አንዱ ክፍል ለሌላ ሥራ ቢፈለግ ጥቅም ላይ ማዋል እንዲቻል ይረዳል። እያንዳንዱን ፍሻሽ በደረቅ፤ በመርዛማና በንጹህ ውሃ መካከል ያለውን ልዩነት መድፈን ደግሞ ለአወጋገድ ጥሩ የሚባል እድሎችን ማምጣቱ ነው። ይህ ማለት ፍሳሾች ተደበላልቀው ሲወጡ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ብክለትን ያስከትላሉ። ለሚፈለገው ዓላማ ለመዋልም አስቸጋሪ ይሆናሉ። ስለዚህም ይህ ቴክኖሎጂ ደረቁን በደረቅ፤ ንጹሁን ውሃ በንጹህ መልኩ እና መርዛማ የሆነውን ሽንት መርዛማ በሆነው መልኩ በመለየት የመጠቀም እድሉን የሚያሰፋ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።

ቴክኖሎጂያቸው አሁን ላይ ተሞክሮም ጠቃሚ መሆኑ በመረጋገጡ የጦር ኃይሎች ሆስፒታልም ከእርሳቸው ጋር ለመሥራት እንደተስማማ ይገልጻሉ።

‹‹ማንኛውም ሃሳብ ወይም ፈጠራ በእውቀትና በክህሎት መደገፍ አለበት። ለዚህ ደግሞ ትምህርትና ሥልጠና የግድ አስፈላጊ ነው። በሌሎች ሙያተኞችም መደገፉ የግድ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ግብ ሳይሆን ድካም ብቻ ነው የሚተርፈው። ለዚህም እኔ አብነት እሆናለሁ። በዚህ የፈጠራ ሥራ ዓመታትን ደክሜያለሁ። ልፋቴ ግን ልፋት ብቻ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ ግን ፍሬውን ለመብላት ተቃርቤያለሁ። ምክንያቱም ሥራዬን በትምህርትና ሥልጠና የሚያግዝልኝ አካል አግኝቻለሁ።›› የሚሉት ዶክተር ግዛቸው፤ ወደ ሥልጠናው ሲገቡ መጀመሪያ በአሉባቸው ችግሮች ዙሪያ የንድፈ ሃሳብ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉን ያስረዳሉ። በተለይም ከእነርሱ ጋር ተዛማጅነት የሌላቸው የሙያ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ መደረጉ በፈጠራቸው ላይ የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።

አንዱና ዋነኛው የኢንጂነሪንጉ ክፍል የሶፍትዌር ሥራና የዲዛይን ትምህርት ከዘርፉ ውጭ የተሰጧቸው የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችና ሥልጠናዎች ሲሆኑ፤ በመቀጠል ወደ ተግባር ትምህርቱ እንዲገቡ ተደርገዋል። በዚህም አንድ ነገር እንደተማሩ ያስረዳሉ። ይህም አንድም የሚወድቅ ሃሳብ እንደሌለ ያዩበት ነው። እርሳቸውና መሰሎቻቸው በዚህ መስመር ውስጥ በመጓዛቸው ሃሳብ በእውቀት እንደሚበለጽግ፤ በክህሎት እንደሚያብብ፤ ከዚያም ለምቶ ራስን ቤተሰብንና ማህበረሰብን ብሎም ሀገርን እንደሚታደግ ማየት አስችሏቸዋል። ከዘመኑ ጋር ዘምኖ ለመራመድ፤ የቀደመውን አሠራር ባሕል፣ ወግ እንዲሁም አካባቢን በሚመጥን መልኩ እያዩ በአዲስ አስተሳሰብ ለመጓዝም እድል እንደሚፈጥር ተመልክተዋል።

‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› ፕሮግራም በተለያየ መልኩ የሚደገፍ ሲሆን፤ በዋናነት የኢፌዴሪ ቴክኒክ ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የሚሠራው ነው። ዋና አላማውም ዜጎችን በትምህርትና ሥልጠና አቅማቸው አጎልብቶ የተሻለ የፈጠራ ሥራን ለሀገር ብሎም ለውጭ ገበያው እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው። በመሆኑም አሁን ላይ ምን ምን ተግባራት እየተከናወነ እንደሆነና ሥራው ምን ድረስ እንደሚዘልቅ በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀዳለ ተክሉን አነጋግረናል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ሃሳብ፤ እውቀትና አቅም ዓለም የመሰከረው ነው። ናሳ ላይ ሳይቀር ኢትዮጵያዊያን ገብተው ብዙ ለውጦችን አምጥተዋል። ኢትዮጵያዊያንን በሀገር ደረጃ ከፍ የማድረጉ ልምድ፤ በፈጠራዎቻቸው፤ በሥራዎቻቸው የመኩራት ሁኔታና የመጠቀም ባሕላችን ግን በእጅጉ የደከመ ነው። ለሀገር ልጅ የሚሰጠው ትኩረት እና የማኅበረሰብ ድጋፍም እንዲሁም የላላ ነው። የውጭ ሀገራትን ብንመለከት ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። ቅድሚያ ለሀገር ምርት ይሰጣሉ። የፈጠራ ሥራቸውን ከፍ አድርገው ያሳያሉ። ለእነርሱ ሁሌም ‹‹ የሀገር ልጅ የማር ጠጅ›› ነው። እኛ ጋር ሲመጣ ግን ተረቱ ብቻ ነው ያለው። በመሆኑም መንግሥት ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። አንዱና ዋነኛው ደግሞ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ዜጎች፤ የፈጠራ ባለሙያዎች ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።

በአንድነት ሥልጠና እየወሰዱ ምጡቁን አዕምሯቸውን ለሀገር እንዲያበረክቱ ማስቻል ነው። ቀደም ሲል በነበረው አሠራር የፈጠራ ባለቤቶች በራሳቸው ጥረት መሥራት አልፈው ሀገር አቀፍ ውድድሮችን ሳይቀር ይሳተፋሉ። ሻገር ሲልም በውድድሮቹ ሲያሸንፉ እዚህ ግባ የማይባል ገንዘብ አለያም የምስክር ወረቀት ተቀብለው ነገሩን ይደመድሙትና ወደ ቀደመ ሥራቸው ይገባሉ። ይህ ደግሞ ሀገሪቱንም ሆነ የፈጠራ ባለቤቶችን በብዙ ሲያደከማቸው ቆይቷል።

ሃሳባቸውን መሬት ላይ ሳያወርዱ፤ ማኅበረሰቡን ሳይጠቅሙና ሌሎችን በአርአያነታቸው ሳያስከትሉ መና አስቀርቷቸዋል። አሁን ግን በቁጭት የሚሠሩበት እድል ተመቻችቶላቸዋል። ሥራው በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜ በተካሄዱ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው ያሸነፉ እንዲሁም የፈጠራ ሃሳብ፣ የቴክኖሎጂ ጥበብና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን በአንድ ቦታ ላይ በማሰባሰብ የፈጠራ ሃሳባቸውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በደንብ አደራጅተው ወደ ተግባር እንዲቀይሩት የሚያደርግበትም እድል ነው።

ከሃሳብ ጥንስሱ እስከ ገበያ አማራጩ ድረስ ድጋፍ የሚደረግበት፤ ሀገራዊ ሃሳቦችን ቅድሚያ የሚሰጥበት እና ለለውጥ የሚያነሳሳ ሲሆን፤ ለዚህም ትምህርትና ሥልጠና ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ተግባር እያከናወነ ስለመሆኑ ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

እንደ ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል ሥራዎች የሚከናወኑት በክረምት ወራት ብቻ እንደነበር የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ ፕሮግራሙ “ሰመር ካምፕ” የሚል ስያሜ እንደነበረው፤ አሁን ላይ ሥልጠናው ወቅትና ጊዜ ሳይገድበው በበጋም፣ በክረምትም የሚሰጥበት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ፕሮግራሙ “ክህሎት ኢትዮጵያ” እንደተሰኘ ያነሳሉ።

በትምህርትና ሥልጠናው የፈጠራ ባለሙያዎች መልካም እድሎችን እንዳገኙበትም ያስረዳሉ። ሥራቸውን በእውቀት፤ በክህሎት እንዲሠሩ፤ ፈጠራቸው ጥራት ያለውና አዋጭነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን፤ ለገበያ የሚያቀርቡበትን ምቹ መደላድል ከመፍጠር ባለፈ ተግባቦታቸውን እንዲያሳድጉ እንዳገዛቸው ጠቅሰውም፤ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በርካቶች የሥራ እድሎችን እንዳገኙ፤ በመደራጀት ጭምር ፋብሪካዎችን እንደከፈቱም ይገልጻሉ።

ወይዘሮ ፀዳለ፤ ‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የሚያፈልቁ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎችን ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ የፈጠራ ሥራቸውን የሚያዳብሩ በተግባር የተደገፈ ሙያዊ ሥልጠና ነው። የሕይወት ክህሎታቸውንና የሀገር ፍቅራቸውን የሚያጎለብቱ ሥልጠናም ነው። የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበትን የመሥሪያ ወርክሾፖችን በስፋት የሚያገኙበትም እድል ነው። እውቀትና ክህሎታቸውን በጋራ የሚያዳብሩበት፤ ሃሳባቸውን ከሃሳብነት ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ነው። እውቀትና ክህሎት ከሚፈተንባቸው ተግባራት መካከል አንዱ ፈጠራዎቹ ሲቀዱ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያለ ማድረግ ነውና ሀገራዊ የማድረግ ጉዳይን እውን የሚያደርጉበት እንደሆነም ያስረዳሉ።

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በሀገር ውስጥ መገጣጠምም ሆነ መጠገን እንዲችሉ እድሉን የሚያገኙበት ነው። በባለፈው ሥልጠና ባገኙት እውቀት 16 የእህል ዓይነቶችን መውቃትና መከካት የሚችል ማሽን መሠራት መቻሉን በማስረጃነት ያነሳሉ።

‹‹በሀገራችን የክህሎት ልማት ሥራ ብዙ የተደከመበት ቢሆንም የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮግራሞችን እስከጀመርንበት እስካለፈው ዓመት ድረስ ተገቢውን ቅርጽ አልያዘም ነበር።›› የሚሉት ወይዘሮ ፀዳለ፤ ሀገራችን ብዙ አዳዲስ ነገር መፍጠር የሚችሉ ዜጎች ያሉባት ብትሆንም በተገቢው መልኩ ደግፎች ተደርጎላቸው የተሻለ ሥራ እንዲያከናውኑ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ነበር። በዚህም መጀመሪያ አካባቢ የልል ክህሎት(soft skill) ሥልጠና በኢንስቲትዩቱ እንዲሰጥ ተደርጓል። ይህ ግን አዋጭነቱ ብዙም ስላልነበረ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ጠንከር ያለና ሀገራዊ ለውጥን የሚያፋጥን ሥልጠናን ወደ መስጠቱ ተገብቷል። በዚህም በርካቶች ውጤታማ ሥራ ሠርተው ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ማበርከት ችለዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ሃሳብ አላቸው፤ መሥራት ይችላሉ፤ መፍጠር ይችላሉ ከሚል እሳቤ በመነሳት ወደ ተግባር የገባው ‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› መርሃ ግብር ከሁሉም ክልሎች፤ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የፈጠራ ባለቤቶችን ያቀፈ ነው። እነዚህ ዜጎች ሥልጠናቸውን የጀመሩት ደግሞ ቴክኖሎጂያቸውን ሊያግዝ በሚችል መልኩ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችንና ሥልጠናዎችን በመውሰድ ነው። ከዚያ በመቀጠል ይዘውት የመጡትን ቴክኖሎጂ የበለጠ ወደሚያጎለብቱበት የተግባር ሥልጠና ገብተዋል። በዚህም አሁን ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙት ሠልጣኞች ብዛት ወደ 147 ደርሷል።

ሥልጠናው በሦስት ተከፍሎ የሚሰጥ ሲሆን፤ የፈጠራ ሥራቸውና የሚፈጀው ጊዜ እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች ታይተው የሚከወን ይሆናል። ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት በመለየት እንደ ፈጠራ ሥራቸው ችግሮቻቸውን እየተሞሉ የሚሄዱበት መሆኑን፤ ችግሮቻቸው በሀገር ውስጥ ትምህርትና ሥልጠና የማይሞላ ሆኖ ከተገኘ የሌሎች ሀገራት ጭምር የሥልጠና እድሎችን አግተው የተሻለውን ለሀገር እንዲያበረክቱ የሚደረግበት ስለመሆኑም ያመላክታሉ። እስካሁን ባለው ሂደትም ብዙዎች ተምረው የተሻሉ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሠሩ ይናገራሉ።

በሀገር ደረጃ እስከ አሁን ባለን ልምድ ሃሳብ አይሸጥም፤ ገበያ የለውም። በሀገሪቱ ላይ ያለውን የቴክኖሎጂ አቅምም ተቀናጅቶ የተሻለ ነገር ሲፈጥር አይታይም። ስለሆነም በ‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› ይህ እውን እንደሚሆን ይታመናል። የሀገሪቱን መልክዓ ምድር፣ አየር ንብረት ወዘተ ያገናዘቡ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችም እንደሚመጡበት ይታሰባል። ይህ እውን እንደሆነ ደግሞ ባለፈው ዓመት መረዳት ይቻላል።

ባለፈው በጀት ዓመት በክረምቱ መርሐ ግብር ከ311 በላይ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የሚያፈልቁ የፈጠራ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነው ከ99 በላይ የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ለሀገር አበርክተዋል። በፕሮቶታይፕ (Pro­totype) ደረጃ የፈጠራ ሥራቸውን ይዘው የመጡትም ቢሆኑ ያሉባቸው ጉድለቶች ታይተውና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ተሞልቶላቸው ወደ ምርት መግባት መቻላቸውን ዳይሬክተሯ ነግረውናል።

ወይዘሮ ፀዳለ በመጨረሻ እንዳሉት፤ በእውቀት፤ በክህሎትና በአቅም የተሻሉ ዜጎችን ማፍራት ከዚህ ሥራ ይጠበቃል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ በማበልፀግ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ መተካትና የሀገሪቱን ወጪ መቀነስም እውን መሆን እንዳለበት ይታመናል። ከዚያም ባሻገር የማህበረሰቡን ሕይወት በማህበራዊም፤ በኢኮኖሚውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ማሻሻል የግድ ነው። ለዚህ ደግሞ የፈጠራ ባለቤቶች ድርሻ የላቀ ሲሆን፤ መንግሥት ቢዝነስ ፕላን ከማዘጋጀት ባለፈ የመሥሪያ ብድር ከልማት ባንክ እንዲያገኙ ያስችላል፤ ራሳቸውን ችለው ቴክኖሎጂዎቹን እያመረቱ ለገበያ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የራሳቸው ድርጅት ከፍተው ማምረት እስኪችሉ ድረስ ድጋፉን ሳያቋርጥ የሚያግዛቸው ይሆናል። የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቹ መሬት ላይ እንዲወርዱ ለማድረግ ከሀገራዊ ትልልቅ ፕሮጀክቶች፤ ከክልሎች ፍላጎት እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ የሚሠራላቸው ሀገራዊ አበርከቷቸው ላቅ ያለ በመሆኑ ነው።

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ከእነርሱ የሚጠበቅ ነገር አለ። አንዱና ዋነኛው ደግሞ ቁርጠኛና ሀገር ወዳድ መሆን ነው። ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንዲሆንላቸው መጠበቅ የለባቸውም። ይልቁንም በችግር ውስጥ አልፈው የጠራ፤ የተሻለና ሀገር በአደረገችላቸው ልክ ለማኅበረሰቡ ጠቀሜታ ያለው ሥራ ማከናወን ነው። ለዚህም ሙሉ አቅማቸውን ማሳየት ይገባቸዋል ሲሉ ይመክራሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You