‹‹ስታርት አፕ ›› ቀጣዩ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሶሶ – አቶ ሰላም ይሁን አደፍርስ

– አቶ ሰላም ይሁን አደፍርስ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ‹‹ስታርት አፕ›› ልማት ዋና ሥራ አስፈፃሚ

ትዮጵያ ከዘመኑት እኩል ዘምና ከፍ ያለች ሀገር እንድትሆን የቴክኖሎጂ ፋይዳ ከምንለው በላይ ትልቅ ነው። ካደጉት ሀገራት እኩል ለመራመድም ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድሏን እያሰፋች ትገኛለች። በሁሉም መስክ ማለትም የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለመሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ ራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መመራት ተገቢ ነው።

የቴክኖሎጂ አቅም ማደግም በሀገር ውስጥ አገልግሎትን ከማሻሻል አንስቶ በውጭ ሀገራት ለሚገኙ በዚህ ዘርፍ ያሉ የቴክኖሎጂ ፍላጎቶችን ለማሟላት የራሱን አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው‹‹ስታርት አፕ››

አሁን ላይ ሀገሪቱ ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ማሳያው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ‹‹ስታርት አፕ›› ከዋና ሥራዎቹ አንዱ አድርጎ በመያዝ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሠማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ‹‹ስታርት አፖች›› የማበረታታትና የመደገፍ ሥራ ይሠራል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ‹‹ስታርት አፕ›› ልማት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰላም ይሁን አደፍርስ እንደሚሉት ይህ ዘርፍ ካደገ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋና ምሶሶ ሊሆን ይችላል።

አቶ ሰላም ይሁን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ከመከላከያ ኢንጂሪንግ ኮሌጅ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲስተም ኤንድ ኮንትሮል ኢንጂነሪንግ ከለንደን ሲቲ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

አቶ ሰላም ይሁን በቴክኖሎጂና ተያያዥ ዘርፎች ከአስር ዓመታት በላይ ልምድ አካብተዋል። አሁን ደግሞ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ‹‹ስታርት አፕ ›› ልማት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ለሀገር የሚሰጠውን ገፀ በረከት እየመሩ ይገኛሉ።

ከአቶ ሰላም ይሁን ጋር ‹‹ስታርት አፕ›› ምንነት አንስተን መንግሥት በዚህ ዘርፍ እያከናወነ ያለውን ተግባር አብራርተውልናል፤ መልካም ቆይታ።

አዲስ ዘመን፡- ‹‹ስታርት አፕ›› ምንድነው?

አቶ ሰላም ይሁን፡- ‹‹ስታርት አፕ›› ማለት ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ እና ፈጠራ የሆነ የገበያ መዋቅርን የሚለውጥ ወይም ተጨማሪ ካፒታልና ድጋፍ ሲያገኝ ሊያድግ የሚችል፤ በምርት የማምረት ሂደት ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ሃሳብን ተግባራዊ የሚያደርግ ኢንተርፕነረር ወይም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ማለት ነው።

‹‹ስታርት አፕ›› የምንለው ሃሳብ በውጭ ሀገራት ሲሠራበት የቆየና ለእኛ ሀገር አዲስ የሆነ ጉዳይ ነው። ‹‹ስታርት አፕ›› የፈጠራ ሃሳብ ሆኖ የበለጠ የዲጂታሉን ዓለም የሚጠቀም ሥራው በፍጥነት አድጎ ትልልቅ ካፒታሎችን የሚያመጣ የፈጠራ ሃሳብ ነው። በዓለማችን ያሉ በዲጂታል ዓለም ላይ የመጡ ለውጦችን የመሩት ‹‹ስታርት አፕ ›› ናቸው።

እንደ ፌስቡክ፤ እስካይፒ፤ ቲውተርና ሌሎች ኩባንያዎች ትልልቅ የዲጂታል ንግድ የሚከናወንባቸው ፕላት ፎርሞች በ‹‹ስታርት አፕ›› እየተመሩ ነው።

በመሠረታዊነት ስታርት አፖች የሚባሉት ፈጣን አዳጊ የሆኑ የፈጠራ ዓይነታቸው ከተለመደው ወጣ ያለ ራዲካል የሆነ ለውጥ የሚያመጡ ከፍተኛ ሪስክ ያለባቸው ግን ደግሞ አዳዲስ ገበያዎችን የሚያመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ናቸው።

‹‹ስታርት አፕ›› በራሱ መለመድ ያለበት ቃል ነው። በየሀገሩ ትርጓሜ ሳይሰጠው በቃሉ እየተጠቀሙበት ነው ያሉት። ልክ ሬዲዮን የሀገራችን ቋንቋ አካል የሆነውን ያህል ‹‹ስታርት አፕ›› በዓለም አቀፍ ደረጃ መግባቢያ ሆኗል። በአዋጁም ላይ ‹‹ስታርት አፕ ›› ስም እንዲሆን ተወስኗል።

አዲስ ዘመን፡- ‹‹ስታርት አፕ›› ከጥቃቅንና አነስተኛ ወይም ከኢንተርፕረነር በምን ይለያል?

አቶ ሰላም ይሁን፡- ‹‹ስታርት አፕ›› ሰው በታየው ልክ ነው የሚተረጉመው። አውዱ እየታየ መተርጎም አለበት። አዳዲስ ቢዝነስ የጀመሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች እንጂ ‹‹ስታርት አፕሮች›› አይባሉም። ሥራ ፈጣሪ ወይም ኢንተርፕረነር የተለያዩ ዓይነት ቢዝነሶች ፈጣሪዎች ኢንተርፕረነር ይባላሉ።

ስታርትአፕ የሚባለው የሥራ ፈጠራ አቅምንና አዲስ ነገር የማግኘት ወይም የኢኖቬሽን አቅምን አንድ ላይ ያደረገ ነው። ኢንተርፕረነሩ ላይ አቅም የሚፈጥር አዲስ ፈጠራ ነው፤ ንግድ አይደለም ሌላ አዲስ የቢዝነሰ ሃሳብ ነው።

‹‹ስታርት አፕ›› እንደ ሌሎች ቢዝነሶች መድረሻው ተገምቶ የሚጀመር አይደለም። ‹‹ስታርት አፕ›› ላይ የሚመጣው ነገር አይገመትም። አዲስ ሃሳብን ይዞ አዲስ ገበያ ውስጥ ሲገባ ከተለመደው ውጭ የሆነ አዲስ ባሕል የሚፈጥር መድረሻው የማይታመን ትርፍ ወይም ኪሳራ ሊሆን የሚችል ማለት ነው።

ለምሳሌ ራይድ ሲመጣ ላዳ ወይም ባስና ታክሲ ባለበት ከተማ ውስጥ ልክ እንደ አሜሪካው ኡበር ዓይነት በቴክኖሎጂ የሚመራ ትራንስፖርት የሚል ሃሳብ ሲመጣ መጨረሻው አይገመትም ነበር። አሁን ግን ገበያው ውስጥ የራሱን የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው። ‹‹ስታርት አፕ›› ማዕከሉ ቴክኖሎጂና አዳዲስ ፈጠራን በማጠቃለል የያዘ አዲስ የቢዝነስ ሃሳብ ነው።

‹‹ስታርት አፕ›› ፈጠራንና ቴክኖሎጂን አጣምሮ የያዘ ዋናው መገለጫው በፍጥነት የማደግ በአንድ ዓመት በሁለት ዓመት በጣም የሚያድግ ነው። ለምሳሌ ያነሳነው ራይድ በፍጥነት አድጎ ለበርካታ ሾፌሮች የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ ቴክኖሎጂው ብዙ ሰው ደርሶ በብዛት ገንዘብ ማስገኘት የሚችል ዓይነት የሥራ ፈጠራ ነው።

‹‹ስታርት አፕ›› ከሃሳብ ተነስቶ እስከ ትልልቅ ካምፓኒ የሚደርስ በዚያ መካከል ግን ምቹ ሁኔታ አግኝቶ እንዲያድግ ሥራ የሚጠይቅ አዲስ ባሕል ነው።

አዲስ ዘመን፡- ‹‹ስታርት አፕ›› እንደ ሀገር ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለፃል?

አቶ ሰላም ይሁን፡- ‹‹ስታርት አፕ›› እንዲፈጠር የ‹‹ስታርት አፕ›› ኢኮሲስተም መፈጠር አለበት። ኢኮ ሲስተም ማለት ሥራውን የሚመራ የተሳሰረ የተናበበ ሥርዓት ይፈልጋል። ከመንግሥት አካላት ጀምሮ ገንዘብ አቅራቢዎች፤ ፈጠራውን የሚሠሩት ባለ ሀብቶች የካፒታል ማርኬት ለከፍተኛ ደረጃ መናኸሪያ ይሆናሉ። አሁን ላይ በኢኮ ሲስተሙ ፈጣሪዎቹ ፈጠራውን የሚያሳደጉ አካላት እንደ ዩኒቨርሲቲ ያሉ በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉና መንግሥት አብረው የሚሠሩበት የፈጠራ ዘርፍ ነው።

ይሄን ኢኮ ሲስተም በደረጃ ስናየው በአዲስ አበባ ደረጃ ከጎረቤት ኬንያ ጋር ሲታይ የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይህ ደረጃ ገና የእንቅስቃሴ ደረጃ ላይ ነን ማለት ነው። መንግሥት ገና የሕግ መዋቅር እየሠራና ሌሎች ነገሮችን እያየ ይገኛል።

እኛ ካለንበት ደረጃ ቀጣዩ ግሎባል ስቴጅ ይባላል። ግሎባል እስቴጁ ላይ ለመድረስ ከእንግሊዝ ሀገር ከመጡ አጋዦች ጋር አንድ የኢኮሲሰተም ፕላት ፎርም ተመርቋል። በዚህ ፕላት ፎርም ላይ ከአራት መቶ በላይ ሃሳብ ያላቸው ‹‹ስታርት አፖች ›› ተመዝግበዋል።

ኢኮ ሲስተሙ ውስጥ የተፈጠሩት ‹‹ስታርት አፖች›› ቁጥር ማወቅ ይቻላል። እስካሁን በውስጥ ዳታ ቤዝ የተመዘገቡትና የተለያዩ ጥናቶች ተጠንቶ እንደተገኘው ‹‹ስታርት አፕ›› የሚመስሉ ታይተዋል። የ‹‹ስታርት አፕ›› ደረጃዎች ኤርሊ ስቴጅ፤ ፕሪ ሲድ፤ ሲድና ግሮዝ አስኬል አያለ ነው የሚሄደው። ‹‹ስታርት አፖቹ›› በዚህ ሂደት ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ ተብለው የታሰቡት ከአንድ ሺ በላይ አሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ አራት መቶ ዘጠና ሰባት አካባቢ ናቸው። ተጨማሪ ጥናት ግን ይፈልጋል። ሌሎች አንደ ራይድ፤ ጋሪ ሎጀስቲክስ የመሳሰሉት ከፍ ብለው ገቢ ማግኘት ጀምረዋል።

በርካቶች በጤና በትራንስፖርት በጉዳይ አስፈፃሚነት በትምህርት የተለያዩ ‹‹ስታርት አፖች›› አሉ። አግሪ ቴክ፤ ፊን ቴንክ ላይ ያሉ በርካታ ‹‹ስታርት አፖች›› አሉ።

አዲስ ዘመን፡- ዘርፉ ከፍ ብሎ እንዲታይ እና ውጤታማ እንዲሆን በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ሰላም ይሁን፡- መንግሥት እንደሚታወቀው ፖሊስ፤ የመተደዳሪያ ማሕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ ነው የሚሠራው። መንግሥት መደላድል መፍጠር ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው። መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ ትኩረት ሰጥተውበት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

‹‹ስታርት አፕ›› ማነው የሚለውንም ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ በግልፅ አስቀምጠውታል። ‹‹ስታርት አፑ›› በደፈናው ሥራ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ዛሬ የጀመረው ሥራ ሂደቱ ቢሊዮኖችን ሊያስገኝ የሚችል የፈጠራ ዓይነት ነው።

ከትርጓሜውም በላይ ኃላፊነት ወስዶ መሪ መሆን፤ እያንዳንዱ ‹‹ስታርት አፕ›› የሚፈልገውን እንዲያገኝ ያመቻቻል። ‹‹ስታርት አፖች›› ትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተገኝተው አቅማቸውንም እንዲያጎለብቱ መንግሥት እየሠራ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ በአራት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ‹‹ስታርት አፕ›› ሊሠራበት የሚችልበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። አይሲቲ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች ቴክኖሎጂ በማሳደግ ‹‹ስታርት አፖች›› ምቹ ሁኔታ እንዲኖራቸው እየተሠራ ይገኛል።

ከዚህም ባሻገር አዋጅ አውጥቶ በሥርዓት የሚመራ የቢዝነስ አካባቢ እንዲሆን እየተሠራ ነው። ‹‹ስታርት አፑን›› የተመለከተ መመሪያም ወጥቶ ለመጽደቅ እየተጠባበቀ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ዘርፉን የተመለከቱ አዋጅና ሕግ ከማውጣት ባሻገር ለ‹‹ስታርት አፖች›› ምን የተለየ ድጋፍ ያደርጋል?

አቶ ሰላም ይሁን፡- መንግሥት ለ‹‹ስታርት አፖች›› ድጋፍ የሚያደርገው ‹‹ስታርት አፖቹ ›› ስለሚያሳዝኑት አይደለም። ሃሳባቸው ዋጋ ይኖረዋል ተብሎ ስለሚገመት ነው። ‹‹ስታርት አፕ›› የያዘውን የሃሳብ ጥራትን ከመገመት ጀምሮ የያዘው ሃሳብ በምን እንደሚገመት ዋጋ እስከ መስጠት ከዚያም ሃሳባቸው አድጎ መሬት እንዲይዝ የኢንቨስትመንት አማራጮች በማሳየት ትልቅ ቢዝነስ እንዲፈጠር የማድረግ ሂደት ውስጥ ብዙ ተዋናዮች ናቸው ያሉት።

ይህ ቢዝነስ አዲስ ባሕል በሕግ ካልሆነ በምንም ሊመራ አይችልም። ለምሳሌ አንድ ‹‹ስታርት አፕ›› ሥራ ለመጀመር ሲያስብ ለሃሳቡ መሞከሪያ የሚሆን ገንዘብ አያገኝም፡፡ ለሃሳቡ ቢሳካም ባይሳካም ድጋፍ የሚያደርግ አካል አልነበረም፡፡ አሁን ግን ጅምሮች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የሕዝብን ገንዘብ አንስቶ ሰጥቶ ሞክረህ ወድቀህም ቢሆን ና ማለት ይከብዳል። ስለዚህ ይሄንን በተለያዩ ፈንዶች በመስጠት መደገፍ የመንግሥት ሥራ ነው።

ለአዲስ ሃሳብ ፈንድ ማድረግ የማይችል ሀገር ስለፈጠራ ማሰብ ያስቸግረዋል። ስለዚህ አዳዲስ ሃሳቦች ከመሬት ተነስተው ይሠራሉ አያሠሩም የሚለውን ለማየት ኢንቨስተሮች አይፈልጉም። እነሱ ትርፍ ሊያመጣ የሚችል ጉዳይ ላይ ብቻ ነው እጃቸውን ማስገባት የሚፈልጉት። ሆኖም አሁን በተፈጠረው እድል ‹‹ስታርት አፖች›› ቀርበው ሃሳባቸው ተወዳድሮ ፈንድ የሚያገኙበት አሠራር እየተመቻቸ ነው።

መጀመሪያ ‹‹ስታርት አፖች›› ናቸው አይደሉም የሚለው ይለያል። ‹‹ስታርት አፖቹም›› ‹‹ስታርት አፕ›› ስለመሆናቸው መለያ ያገኛሉ። ከተለያዩ የግል ተቋማት ጋር የሚቀናጅ ሃሳብን ከመሬት የሚያነሳ አሠራርም ተዘርግቷል። ይህ እንዲኖርም በአዋጁ ተካቷል።

ሌላው ሃሳባቸው የሚጠቅም ነገር ግን በቂ አቅም የሌላቸው ‹‹ስታርት አፖች›› ቀጣይ ነገራቸው እንዴት ይቀጥላል የሚለውም ታይቷል። ሃሳቡ ለሀገር የሚጠቅም ሆኖ ኢንቨስተሮች ካልወደዱት መንግሥት የራሱን አማራጭ ይወስዳል። ይህ ማለት ካፒታል ማርኬት ዓይነት ተቋማት ፈንድ በማድረግ መንግሥት ኢንቨስትመንት ውስጥ ገብቶ ያንን ሃሳብ ወደ ተግባር ይቀይረዋል ማለት ነው።

ሶስተኛው አንድ ገንዘብ ለማግኘት ኮላተራል የሚጠየቅበትን አሠራር ሌላ የጋራንቲ አሠራር በመዘረጋት ኮላተራልን የማስቀረት ሁኔታም ይመቻቻል። ምናልባት ያ ገንዘብ ባይመለስ እንኳን የጋራንት አሠራር የሚሸፈንበት አሠራርም በመንግሥት ተመቻችቷል።

መንግሥት ለ‹‹ስታርት አፖች›› የሚሆኑ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሚፈለገው ርቀት በሙሉ ሄዶ እንዲመለስ የሚደረግበት አሠራር ዘርግቷል።

አዲስ ዘመን፡- የዘርፉ ዋና ፈተናዎች ምንድናቸው?

አቶ ሰላም ይሁን፡- የዘርፉ ፈተና ዋናው ግንዛቤ አለመኖር ነው። ዘርፉ በደንብ ካልታወቀ በተለመዱ አሠራሮች የመዋጥ ስጋት አለበት። ይህ ዘርፍ በራሱ የሚያመጣው ነገር ታይቶ ስለማይታወቅ ውጤቱም የማይገመት ይሆናል። በዚህ ምክንያት አዲሱን ነገር የመሞከር ፍርሃት አለ። በዚህ ግንዛቤ አናሳ በሆነበት ጉዳይ ላይም ነባሩን ሕግ ከአዲሱ እሳቤ ጋር አብረው የማጣጣም ተግዳሮት አለው።

የማኅበረሰብ ግንዛቤ አለመኖሩ አዳዲስ ሃሳብ የሚመጣ እንደማይጠቅም ይወሰዳል። በዛ ላይ ሥራው እንደልቡ እንዳይሄድ ኢኮሲስተሙ ምቹ አለመሆኑ፤ የፈንድና የተለያዩ መገልገያዎች እጥረት በዘርፉ ላይ ባለቤት መብዛት በራሱ ፈተና ነው።

ከምርት ጥራቱም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ኳሊቲ ያላቸው ‹‹ስታርት አፖች›› መጥፋት አለ። ‹‹ስታርት አፖች›› እንዲያብቡ በጣም ጠንካራ የሆኑ ተማሪዎች ጠንካራ የሆኑ ፈጣሪዎች አስፈላጊ ናቸው። ከኖርማል ቢዝነሱ የተለየ መሆኑን በራሱ ተግዳሮት ነው። ዘርፉ አዲስ በመሆኑ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች አሉት።

አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ሀገራት ከተለያዩ ‹‹ስታርት አፖች ››ተነስተው ትልልቅ ኩባንያ የፈጠሩ ግለሰቦች አሉ። ይህ ነገር በሀገራችን እውን ሲሆን አይታይም ለምን?

አቶ ሰላም ይሁን፡– ትልልቅ ሆነው ለማየት ምቹ መደላድል መፈጠር አለበት። እንዲያውም በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ምንም ዓይነት ኢኮ ሲስተም ሳይመቻች እንዴት ጠንካራ ‹‹ስታርት አፖች›› ኖሩ ብለን መደነቅ ነው ያለብን። ራይድ፤ ፈረስ፤ የተለያዩ ፊን ቴክ ላይ የሚሠሩ ‹‹ስታርት አፖች›› መጥተዋል መደነቅ አለባቸው።

እነ ጋሪ በስፋት ሎጀስቲክ ላይ የሚሠሩ ጠንካራ ‹‹ስታርት አፖች›› ናቸው። እንዲያውም ሳይታሰብ አዲሱ ባሕል እየተለመደ ነው። ቴሌ ብርም የ‹‹ስታርት አፕ›› ሃሳብ። በርካታ ገንዘብ በውስጡ እየሄደ ነው። ብዙ ‹‹ስታርት አፖች›› ከስር ተነስተው ኢኮሲስተሙን ባይቀይሩት መንግሥትም አይመለከተውም ነበር።

‹‹ስታርት አፖች›› አንድ ሃሳብ አንስቶ ውጤት ላይ እስኪደርስ የተለያዩ ደረጃዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። አንድ ሃሳብ ከመነሻው ጀምሮ ሁለት ዓመት ቢፈጅ ኢንቨስትመንቱ የሚፈጀው ተደምሮ ዓለም አቀፍ እስኪሆን በሀገራችን በስምንት ዓመት ውስጥ ውጤታማ ከሆነ ተሳካ ማለት ነው።

ካምፓኒው ገበያው ላይ ከዋለ በኋላ ስንት ቢሊየን ያስገባል ተብሎ ለገበያ ይቀርባል። ይህ ደግሞ የእድገት መተማመኛ ነው። ሀገራችን አንድ ሁለት ‹‹ስታርት አፕ›› በአስር ዓመት ብታሳካ ሌሎቹ ይቀየራሉ።

የተቀሩት የሀገር ውስጥ ገበያውን እየቀየሩ ይሄዳሉ። ውድድር ያለበት ኢኮ ሲሰተም ይኖራል። የሀገር ውስጡንም የውጪውንም ገበያ የተሻለ ለማድረግ ‹‹ስታርት አፕ›› ጠቃሚ ነው። ‹‹ስታርት አፕ›› ኳሊቲ ያለው ቢዝነስ ቴክኖሎጂን የተደገፈ አቅም ለማንሳት ጠቃሚ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የሀገራችንን ‹‹ስታርት አፕ›› ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር አቀናጅተው ቢነግሩን?

አቶ ሰላም ይሁን፡- የ‹‹ስታርት አፖችን›› እድገት ለማወቅ በኢኮ ሲስተሙ ዋጋቸው ነው የሚለካው። ለምሳሌ በአፍሪካ ‹‹የስታርት አፕ›› ደረጃ ላይ ቶፕ አራቶቹ ኬንያ፤ ናይጄሪያ፤ ደቡብ አፍሪካና ግብፅ ናቸው። ኢኮ ሲስተም የሚተመነው ምን ያህል የውጭ ኢንቨስተሮች አሉ የሚለው ነው። ቬንቸር ካፒታል ኢንቨስተሮች መጥተው ኢንቨስት የሚያደርጉት ገንዘብ ያስገኛል። ይህ ቬንቸር ካፒታል ኢንቨስተሮች የመንግሥትንም ሆነ የሌሎች በቢዝነሱ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን ገንዘብ ይይዙና የእኛ ከፍተኛ ጥቅም የሚያመጡ ሃሳቦችን ይዘው ወደ ገበያው የሚያወጡ ናቸው። በሀገራችን እንዲህ ያለ ኢኮሲስተም ገና እየጀመረ ነው።

ኬንያ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፤ ሌሎቹም ከዛ በላይ ናቸው። እስካሁን ከምሥራቅ አፍሪካ ኬንያ አድጋለች። እነሱ የተሳካላቸው ቀድሞም ኢኮሲስተማቸው ዓለም አቀፋዊ ስለነበር ነው።

የኛ ሲታይ በደንብም አልተጠናም 100 ሚሊየን ዶላር አካባቢ ነው እስካሁን። አቅሙ በጣም ገና ነው፡፡ አቅም ቢኖርም የኢኮሲስተሙ ዋጋ ግን እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። በእኛ ሀገር ብዙ ሥራ ይጠይቃል። አንዴ ከተጀመረ ግን ውጤታማ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል።

አዲስ ዘመን፡- ‹‹ስታርት አፖች›› በማህበር ተደራጅተው የሚሠሩበት፤ ከእናንተ ጋርስ በቅርበት የሚገናኙበት አሠራር ካለ ቢገልፁልን?

አቶ ሰላም ይሁን፡- አሁን ላይ መረጃዎችን ነው የምናሰባስበው። ብዙዎቹም ከኛ ጋር የሚሠሩ ናቸው። አሁን እየሠራን ያለነው ‹‹የስታርት አፖች›› ኮሚኒቲ ነው። ጠንካራ የሆነ እርስ በእርሱ መመጋገብ የሚችል ዓይነት ኮሚኒቲ እየሠራን ነው። የተሰበሰቡ ‹‹ስታርት አፖችንም›› ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ነው። አሁን ‹‹ስታርት አፕ›› ኢትዮጵያ የሚል ብራንድ ፖርታል አዘጋጅተናል። እዚያ ውስጥ የመንግሥት የግል የተለያዩ አካላት እንዲኖሩ መደረግ አለበት።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

አቶ ሰላም ይሁን፡- የስታርት አፕ ትልቁ ፈተና ከሙከራ ወደ ገበያ ለመግባት የፋይናንስ አቅም ውስኑነት ነው፡፡ በጋራ ጥረት እና ተናብቦ በመሥራት የፋይናንስ ውስንነቱን ተሻግረው ዕሴት የሚፈጥሩ አቅሞች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ይህ ኢኮ ሲስተም ነገን አይቶ የሚሠራበት ነው። በዚህ አስተሳሰብ ደግሞ ነገሮች እንዲታዩ ቢሳሳትም እንኳን እንዲታይ መፍቀድ አንዱ ወሳኝ ጉዳይ ነው።

አዲስ ነገሮች ሲሞከሩ ከመከልከል ይልቅ በተለያየ መንገድ በማበረታታት ከሙከራ ወደ ችግር ፈቺ ፈጠራ ማሸጋገር ያስፈልጋል። አዳዲስ ሂደቶችን በመሞከር ጅምሮችን ማስቀጠልና ማጎልበት ተገቢ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በአንባቢያን ስም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ሰላም ይሁን፡– እኔም ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ፡፡

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You