
በኢትዮጵያ ሴቶች ለዘመናት የተፈጸሙባቸው ጫናዎች ከትምህርት፣ ከአመራርነትና ከመሳሰሉት ርቀው እንዲኖሩ አርገዋቸዋል:: በዚህ የተነሳም የወንዶችን ያህል በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሰፊ ተሳትፎና ጉልህ ሚና ሳይጫወቱ ኖረዋል:: በእዚህም ለራሳቸውም፤ ለሕዝብና ለሀገር ማበርከት ያለባቸውን እንዳያበረክቱ ተደርገዋል::
ይሁንና እነዚህን ጫናዎች በመቋቋም በቤተሰብ በመንግሥትና በመሳሰሉት አካላት የተፈጠሩላቸውን መልካም እድሎች በሚገባ በመጠቀም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመሠማራት የወንዶችን ያህል ባይሆንም ለሀገር አኩሪ ተግባር የፈጸሙ፣ የሀገርን ስም በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር ያስጠሩ ሴቶች ጥቂት እንዳልሆኑም ይታወቃል::
ለወንዶችና በወንዶች ብቻ ተከልለው በቆዩ የምርምርና የሳይንስ ዘርፎች ነጥረው ወጥተው በሀገር ብቻም ሳይሆን በዓለምም ጭምር እውቅና ያገኙ ሴቶችን ኢትዮጵያ ማፍራት ችላለች::
በዓለም ለ114ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ በዛሬው እለት እያከበርን ያለነውን የዓለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግም በሳይንስና ምርምር ዘርፍ ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካበረከቱና እያበረከቱ ካሉት ሴት ተመራማሪዎች መካከል የመጀመሪያዋን የዘርፉን ብቸኛዋን ሴት መሪ ተማራማሪ እንግዳ አድርገን ይዘን አቅርበናቸዋል::
እንግዳችን ይጋርዱ ሙላቱ ዶ/ር ይባላሉ፤ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ የቀርከሃ ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ ከማስተዋወቅ ጀምሮ ምርታማነትን የሚያሳድጉ በርካታ የምርምር ውጤቶችን በማበርከት ይታወቃሉ:: በተለያዩ ክልሎች በመዟዟርም የቀርከሃ እውቀትና ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግና በርካታ የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን በመሥራት ከፍተኛ የሚባል ለውጥ ማስመዝገብ የቻሉ ሴት ተመራማሪ ናቸው::
ይጋርዱ ዶ/ር ተወልደው ያደጉት በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሐገር አነብሴ ሳርምድር ወረዳ ግትም አቦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚሁ ቀበሌ በሚገኘው ዝምብቲት ቁስቋም ትምህርት ቤት እንዲሁም የመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመርጡ ለማርያም አብርሐ ወአጽብሐ እና ሞጣ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ውጤት በማለፍ በሐረማያ ግብርና ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በደን ሳይንስ አጠናቀዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደያዙ በቀጥታ ወደ ትዳር የገቡት ይርገዱ ዶ/ር፣ ኑሯቸውን የትዳር አጋራቸው ከሚኖሩበት አዲስ አበባ 512 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰሜን ወሎ አደረጉ::
እዚያም ሳሉ ከአማራ ግብርና ኢንስቲትዩት ማዕከላት አንዱ በሆነው የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል በመቀጠር በተማሩበት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን በታታሪነት አገልግለዋል:: በዚህም ከጀማሪ ተመራማሪነት እስከ ረዳት ተመራማሪ ደረጃ መድረስ የቻሉ ሲሆን፣ በማዕከሉ በቆዩባቸው ዘጠኝ ዓመታት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከስዊድን ግብርና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ (SLU) በምርት ሰጪ ደን ማምረት (Production Forestry) ሠርተዋል::
ይጋርዱ ዶ/ር በስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ቆይታቸው ሁለገብ ጥቅም ያላቸውን የዛፍ ዝርያዎች ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ያደረጉት የመረጣ ምርምር እና ቅድመ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ሥራ በዘመናቸው ካስገኟቸው ጉልህ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል። በቁሳዊ እድገቱ ቀይ ባሕር ዛፍን በሶስት እጥፍ የሚበልጠው ግማርዳ ግራር (Acacia polyacantha) ‘ስሪንቃው’ እየተባለ የሚጠራውን ዝርያ በሐርቡ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎች በማስፋፋት ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸውም ይገለጻል።
እንግዳችን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ልጆቻቸውን እያሳደጉ ባሉበት ወቅት አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በተባባሪ ተመራማሪነት ደረጃ ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ። በኢንስቲትዩቱ ከተቀጠሩበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እንጨት ያልሆኑ የደን ውጤቶች በተለይም ቀርከሐ ምርምር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል::
በኋላም የሚሠሩበት ክፍል ራሱን ችሎ የኢትዮጵያ አካባቢና ደን ኢንስቲትዩት ተብሎ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከመውጣቱ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር በደን ልማት ሲከናወን በቆየው ሀገራዊ ጥረት የመሪ ተመራማሪዋ ሚና ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለም ይጠቀሳል::
በተለይም በደን ላይ ለዓመታት ባደረጉት ሰፊ የምርምር ሥራ በምርምር ዘርፍ ከፍተኛ የሚባለውን የመሪ ተመራማሪነት ደረጃ ማግኘት ችለዋል:: በዘርፉ በርካታ ትምህርታዊና ጥልቀት ያላቸውን የምርምር ፅሁፎችን ለሀገር ያበረከቱ ሲሆን አሁንም ድረስ በማማከር ሥራ ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ::
ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆንም ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ በዚህም ከፍተኛ እውቅና ተችሯቸዋል:: ይጋርዱንና ዶ/ር ቀርከሐን መለየት እስከሚያስቸግር ድረስ በሥነ-ሕይወቱ፣ አያያዙ፣ ልማቱ እና አጠቃቀሙ ላይ ምርምር በማድረግ ከ40 በላይ ሳይንሳዊ ህትመቶችን አበርክተዋል። የኢትዮጵያ ደን ልማት በምርምሩ ዘርፍ የመሪ ተመራማሪ ደረጃ እድገት ከጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሰጥቷቸዋል::
“መሪ ተመራማሪ” በምርምር ተቋማት የሚሰጥ የመጨረሻው ከፍተኛው የደረጃ እድገት ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎች “ፕሮፌሰር” የሚባለው ደረጃ ነው። ይህ ዕድገት በኢትዮጵያ ደን ልማት ለአራተኛ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ሥርዓት ውስጥ እስካሁን ለሴት ተመራማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን ይጋርዱን ዶ/ር የዘርፉ የመጀመሪያዋ ሴት መሪ ተመራማሪ ያደርጋቸዋል::
ይጋርዱ ዶ/ር ተወልደው ባደጉበት አካባቢም ሆነ ወቅቱ ትምህርት እምብዛም የተስፋፋበት ቦታ ስላልነበር በርትተው በመማርና ወደ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የአስተማራቸውን ቤተሰብና ማህበረሰብ የማገዝ ትልቅ ህልም እንደነበራቸው ይገልጻሉ:: በተለይም ከፍተኛ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን በህክምናው ዘርፍ ወሳኝ ሚና መጫወት የዘወትር መሻታቸው እንደነበረም ይጠቅሳሉ::
ሆኖም በደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከተመደቡም በኋላ በተለይ ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት በሚያስችል ደረጃ በትጋት አጥንተዋል:: ለዚህ ህልማቸው መሳካት ደግሞ በግላቸው ያለምንም መታከት ያደረጉት ከነበረው ጥናት ጎን ለጎን የታላቅ እህትና ወንድሞቻቸው ድጋፍ ወሳኝ ሚና እንደነበረውም ያስታውሳሉ::
‹‹በእኔ ዘመን በአካባቢያችን ብዙ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም ነበር፤ ሴት ብትማርም የትም አደርስም የሚል ኋላቀር እሳቤ ስለነበር በጣም ጥቂት ሴቶችን ነበር ቤተሰብ አምኖ ወደ ትምህርት ቤት ይልካቸው የነበረው›› ይላሉ:: ማህበረሰቡ ለሴቶች በነበረው ግንዛቤ፣ ሴቶችም ራሳቸው ለራሳቸው በነበራቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን የተነሳ ሁኔታዎች በጣም ፈታኝ እንደነበሩም ያነሳሉ:: ይህ በመሆኑ ማህበረሰቡ የሚጠብቀውን ማድረግ ያስፈልግ ስለነበር ሴቶች እንደ ወንዶቹ ሁሉ ያሰቡበት እንዳይደርሱ ትልቅ ጫና ይፈጥርባቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ:: እነዚህን ጫናዎች ተቋቁሞ መሥራትና ውጤት ማስመዝገብ የብዙዎቹ የአካባቢው ሴቶች ፈተና እንደነበር ይገልጻሉ::
በተለይም ትምህርት ቤቶች በአካባቢያቸው ባለመኖራቸው ሴት ልጆችን ለትምህርት የሚልክ ቤተሰብ በጣት የሚቆጠር እንደነበር ይጋርዱ ዶ/ር ያስታውሳሉ:: ‹‹በተለይም መለስተኛ ደረጃ ሳለሁ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ ቤተሰብ እሄድ ስለነበር የቤተሰቡ ናፍቆት ከፍተኛ ፈተና ነበር›› ይላሉ::
ሁለተኛ ደረጃ ከደረሱ በኋላም ለወራት ከቤተሰብ ርቀው የሚኖሩ በመሆናቸው ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ በእጅጉ የመንፈስ ጥንካሬን ይሹ እንደነበረም ይናገራሉ:: ሴትነታቸውን የሚፈታተኑ ጉዳዮችን መቋቋም አቅቷቸው ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ተማሪዎችም እንደነበሩ ያመለክታሉ::
እሳቸው ግን የቤተሰቦቻቸው ያልተቋረጠ ድጋፍና ተግሳፅ አቅም እንደሆናቸውና የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በፅናት ለማለፍና የወደፊቱን አርቀው ለማሰብ እንዳገዛቸውም ያስረዳሉ:: ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ያገኙት ተሞክሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገቡም በኋላ ለአካባቢውም ሆነ ለዩቨርሲቲው ማህበረሰብ አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በትዕግስት ለማለፍ ያገዛቸው መሆኑን ያነሳሉ::
በሌላ በኩል በሚማሩበት የትምህርት ዘርፍ ወንዶች መብዛታቸው ከእነሱ እኩል ለመራመድ እና ብርቱ ተወዳዳሪ ለመሆን ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀማቸውን ያመለክታሉ:: ‹‹ምንም ነገር ሳያታልለኝ ፤ ራሴን ቆጥቤና በማስተዋል በመንቀሳቀሴ ከፍተኛ ውጤት እያመጣሁ ነው ያጠናቀቅሁት›› ይላሉ::
መሪ ተመራማሪዋ እንደሚሉት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ ዓለም በገቡበት የአማራ ግብርና ምርምር ተቋም ከአዲስ አበባ 512 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው ነበር:: በሌላ በኩል ባለቤታቸው ኑሯቸው አዲስ አበባ ስለነበር ከሥራው ጎን ለጎን እየተመላለሱ ቤተሰብን ማስተዳደር ሌላው የሕይወታቸው ፈታኙ ክፍል ነበር:: በተለይ ደግሞ የመጀመሪያ ልጃቸውን ወልደው ስለነበር በርቀት ሆኖ ልጅን ማሳደግና መከታተል እንደማንኛውም እናት አስጨናቂ ጊዜ እንደነበር አይዘነጉትም::
ይጋርዱ ዶ/ር ቤተሰብ ከማስተዳደሩ ጎን ለጎን የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩም ማርገዛቸው ሌላው በፅናት ማለፍ የሚጠይቅበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ሆኖም የትዳር አጋራቸው ጠንካራ ድጋፍ ስለነበር ቤተሰባቸውንም ሆነ ሥራና ትምህርታቸውን በብቃት እንዲወጡት ያስቻላቸውም መሆኑን ይመሰክራሉ::
‹‹እንደ አንዲት ሴት፣ እንደ አንዲት እናት፣ እንደማንኛውም ሠራተኛ ከወንዶቹ እኩል ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያጋጥሙኝን ሁሉ በፅናት ማለፍ የግድ ብሎኝ ነበር፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁሉ ግን የባለቤቴ ድጋፍ አልተለየኝም ነበር›› በማለት ይገልፃሉ:: ‹‹በመሠረቱ በርቀት ሆኜ ለመሥራት የወሰንኩት ከባለቤቴ ጋር ተመካክረንና አምነንበት ስለነበር የሚያጋጥሙን ችግሮችንም እንዲሁ በመተጋገዝ ለማለፍ ጥረት እናደርግ ነበር›› ይላሉ::
‹‹በተለይ የሁለተኛ ዲግሪዬን የመመረቂያ ፅሁፍ በምሠራበት ወቅት የአምስት ወር ነፍሰጡር ስለነበርኩኝ፤ በተጨማሪም ሥራ ላይ ረጅም ጊዜ መሥራቱ በጣም ከባድ ነበር፤ በተጨማሪም የቤተሰብ ናፍቆቱ በራሱ የሚፈጥረው ጫና ነበር›› ሲሉ ይናገራሉ:: ሆኖም ሳይሰለቹና ለስንፍና እጅ ሳይሰጡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ ችለዋል::
ስሪንቃ በሚገኘው የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በነበሩበት ወቅት በርካታ የምርምር ውጤቶችን ያበረከቱ ሲሆን፣ በተለይ በቴክሎጂ ቅድመ መስፋፋት ሥራ ላይ ከፍተኛ እምርታ እንዲመጣ ያደረጉ መሆናቸው ይጠቀሳል:: ከእነዚህም ውስጥ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በሚሠሩበት ጊዜ የመመረቂያ ጥናታቸውን ቻይና ድረስ በመሄድ የቀርከሃ ልማትና ቴክኖሎጂን በስፋት በማየትና ምርምር በማድረጋቸው ያ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመጣና እንዲላመድ በማድረግ ሂደት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል::
የመሪ ተመራማሪነትን ማዕረግ ዘንድሮ ባገኙበት ወቅት በግብርና ሥርዓት ውስጥ ብቸኛዋ ሴት መሆናቸውን ሲያውቁ መገረማቸውን ያልሸሸጉት ይጋርዱ ዶ/ር፤ ይህ ሊሆን የቻለው በዘርፉ አቅም ያላቸው ሴቶች ባለመኖራቸው ሳይሆን እድሉን ባለማግኘታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ::
ሴቶችን ማብቃት የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበው፤ በተለይም ትላልቅ የሃላፊነት ቦታዎችን እንዲመሩ እድሉ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባም ያመለክታሉ:: ለዚህ ደግሞ ሴቶች ከቤት ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤትና ሥራ ቦታ ድረስ ያሉባቸውን ተፅዕኖ ተቋቁመው በማለፍ ያላቸውን እውቀትና አቅም ለሀገር ጥቅም እንዲያውሉ ማድረግ ቀዳሚ ሥራ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ::
‹‹ሴቷ ልክ እንደወንዱ ሁሉ ትላልቅ የሃላፊነት ቦታዎች ቢሰጧት በተሻለ ሁኔታ ስኬታማ መሆን ትችላለች›› የሚሉት ይጋርዱ ዶ/ር፣ ለዚህም ደግሞ የሴቷ ቁርጠኝነት፤ ግብ ጥሎ መንቀሳቀስና ለዓላማ ፅኑ መሆን ወሳኝነት እንዳለው ይናገራሉ:: በተለይ በሳይንስና ምርምር ሥራዎች ላይ ያሉ ሴቶች አቅማቸውን አውጥተው በመጠቀም ለራሳቸውም ሆነ ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም