
– እልፍነሽ ሙለታ (ዶ/ር) በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት ከፍተኛ ተመራማሪ
ጥቂት ሴቶች ብቻ የሚቀላቀሉትን የትምህርት መስክ ምርጫዋ ያደረገችው ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነው:: ቁጥር ነክ ትምህርት ዕጣ ክፍሏ በመሆኑም ዝንባሌዋ ወደ ተፈጥሮ ሳይንሱ ነው:: ይሁንና የአስረኛን ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዳ ውጤት በመጣ ጊዜ በአንድ የትምህርት ዓይነት ያልጠበቀችው ውጤት ተከሰተ፤ ይህም የትምህርት ዓይነት አጥብቃ ትወደው የነበረ ቢሆንም የደከመችለትን ከቁብ ባለመቁጠሩ አስኮረፋት፤ የዛሬው የሴቶች ቀን ልዩ ዕትም እንግዳችንን እልፍነሽ ሙለታ (ዶ/ር)::
እልፍነሽ (ዶ/ር) በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተቋም በከፍተኛ ተመራማሪነት በማገልገል ላይ ትገኛለች:: አዲስ ዘመንም በዓለም ለ114ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተመራማሪዋ ጋር ቆይታ አድርጓል::
ትውልድና እድገቷ
የልዩ ዕትሙ እንግዳችን፤ ትውልዷ ኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በቾ ወረዳ፣ ቆቦ የምትባል ቀበሌ ውስጥ ነው:: ቤተሰቦቿ መምህራን ናቸው፤ ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን የተከታተለችው ቤተሰቦቿ በሚሠሩበት ቶሌ ወረዳ፣ አቤቤ በምትባል ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው ትምህርት ቤት ነው::
የትናንትናዋ እልፍነሽ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመማር ገና እምብዛም ባልፈረጠሙ እግሮቿ በየቀኑ የሶስት ሰዓት መንገድ መጓዝ ግድ ይላት ነበር:: ወደ ስምንተኛ ክፍል ስትዛወር ግን በየቀኑ ለሶስት ሰዓት ያህል ያመላልሳት ከነበረው የእግር ጉዞ አረፈች::
የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን በቾ ወረዳ፣ ቱሉ ቦሎ ከተማ የተማረች ሲሆን፣ እንዲሁም ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍልም እዛው ቶሉ ቦሎ ከተማ ኅብረት ፍሬ በሚባል ትምህርት ቤት ተከታተለች:: የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል የመሰናዶ ትምህርቷን ለመማር ግን ቱሉ ቦሎ ከተማን ለቅቃ ወደ ሰበታ በመሄድ ተማረች::
የፊዚክስ ትምህርትና ኩርፊያዋ
ሁሌም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ትኩረቷን ይስባል:: አጥብቃም ትወደዋለች:: የአስረኛ ክፍል ለፈተና እስከቀረበችበት ጊዜ ድረስ በተለይ ፊዚክስ በጣም የምትወደው የትምህርት ዓይነት ነበር:: ከፊዚክስ ትምህርት ፍቅሯ የተነሳ ከራሷ ክፍል አልፋ ሌላው ክፍል ገብታ እንድትማርም ትደረግ ነበር:: የፊዚክስ መምህሯም ይህን ጠንቅቀው ያውቁ ነበርና በምታደርገው ሁሉ ድጋፍ ከመስጠት አይቆጠቡም ነበር::
ለፊዚክስ ትምህርት ያላት ፍቅር ሳይቀዘቅዝ የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈተነች:: ውጤት በመጣ ጊዜ ግን ያ በምትወደው ፊዚክስ የመጣው ውጤት ግን አስደነገጣት፤ ያየችውንም ውጤት ማመን አቃታት:: ውጤቱ ‹‹ሲ›› ነበር:: እንደዚያ እንዳልወደደችውና እንዳልተከታተለችው ሁሉ የፊዚክስ ትምህርት ውጤቷን ባየች ጊዜ ትምህርቱን አኮረፈችው::
‹‹ትዝ የሚለኝ ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ ለአንድ ሴሚስተር ብቻ ከክፍሌ 2ኛ መውጣቴ ነው:: ከዚያ ውጭ ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የአንደኝነትን ደረጃ ለማንም አሳልፌ ሰጥቼ አላውቅም›› የምትለዋ እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ በእነዚያ ሁሉ ጊዜያት ቁጥር ያለባቸውን የትምህርት ዓይነቶች አጥብቃ የምትሻ መሆኗን ታወጋለች::
የፊዚክስ ትምህርትን አጥብቃ ትወድ እንደነበር ሁሉ፤ የሕግ ትምህርትን ደግሞ አጥብቃ ትፈራዋለች፤ ምክንያቷ ደግሞ ሕግ ከሰው ጋር የሚያጣላ ነገር ያለው ስለሚመስላት፤ ከሰው ጋር መጣላትን አትፈልግም:: ስለዚህ ምርጫዋ ቁጥር ያለው የትምህርት ዓይነት በመሆኑ ቅድሚያውን የሰጠችው ለኢኮኖሚክስ ሆነ::
ኢኮኖሚክስን ይበልጥ እንድትወድ ያደረጓት ደግሞ የኢኮኖሚክስ መምህሯ ናቸው:: እርሷ እንደምትለው በርግጥ ኢኮኖሚክስ የሚወደድም የትምህርት ዓይነት ነው::
የከፍተኛ ተቋም ትምህርቷ
የመጀመሪያ ዲግሪዋን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተከታተለች ሲሆን፣ የተመረቀችው በኢኮኖሚክስ ነው:: ጥቂት እንደቆየች ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅላ በሪጂናል ኤንድ ሎካል ዲቨሎፕመንት ስተዲስ (Reginal and local development studies) ለመመረቅ በቃች:: የዛሬዋ ተመራማሪ እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ ሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛ ለአንድ ዓመት ብቻ ከቆየች በኋላ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ ተቀጥራ መሥራት ጀመረች:: በዩኒቨርሲቲውም የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን አስተምራለች፣ በኋላ ላይ ግን የተማረችው ኢኮኖሚክስ በመሆኑ ወደ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ገብታ ኢኮኖሚክስን ማስተማር ጀመረች::
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተቀጠረችው በ2005 ዓ.ም ክረምት ላይ ነው ፣ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ክፍለ ትምህርት በመምህርነት ስታገለግል ቆየች:: ብዙም ሳትቆይ በ2010 ዓ.ም ላይ በዚያው በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የመማር እድል በማግኘቷ በዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ (Development Economics) መማር ጀመረች:: በ2016 ዓ.ም በማጠናቋም በቀጥታ የተቀጠረችው አሁን በተመራማሪነት እያገለገለችበት ባለው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተቋም ነው::
ሴት በተፈጥሮዋ ኢኮኖሚስት ናት
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ ሴት ባትማርም ኢኮኖሚስት ናት ትላለች:: ምክንያቱም እናቶቻችን ቁጠባን የሚያውቁት ስለተማሩ አይደለም:: የቁጠባን ሳይንስ ከእናቶቻችን መረዳት እንችላለን፤ ይህንንም በአንድ ቀላል ምሳሌ ስታስረዳ ፤ እናቶች እንጀራ ጋግረው ካበቁ በኋላ መጨረሻ ላይ የሚቀረውን አልቅልቀው አይደፉትም፤ ከዚያ ይልቅ ለእርሾነት ያስቀምጡታል:: መጀመሪያውኑ ከሊጡ ቆንጠር አድርገው ለእርሾ በሚል ማስቀመጥ እንደሚቻል ሳያጤኑ ቀርተው አይደለም::
ነገር ግን የመጨረሻዋ ልቅላቂ የምትመስለው ሙጣጭ ነገር የሆነች በጣም ጥቂት እህል ብጤ ስላላት በቀጣይ ለእርሾነት ያስቀምጧታል እንጂ አለቅልቀው እንደዋዛ አይደፏትም:: ለቀጣዩ እንጀራ ጋገራ በእርሾነት እንድታገለግላቸው የሚያስቀምጧት እርሷኑ ነው ትላለች::
እርሷ እንደምትገልጸው ከሆነ፤ ሴቶች በሁሉም ነገር በሚያስብል ደረጃ ጥንቁቆች ናቸው:: ሴት ልጅ በተፈጥሮዋ አባካኝ አይደለችም:: በብዙ መንገድ ሲጤን ሴቶች ብዙ ነገሮችን በቁጠባ የሚይዙ ናቸው:: ቁጠባ ሲባል ብርን ብቻ ማስቀመጥ ማለት አይደለም፤ ቁጠባ ሲባል የጊዜም ጭምር ነው::
ለምሳሌ ሴት ልጅ፣ በአንድ በኩል ሥራውን በተገቢው መንገድ እየተወጣች በተመሳሳይ ደግሞ በቤት ውስጥ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት ለመወጣት ልጆች በማሳደጉም ሆነ ቤተሰቧን በመንከባከቡ ረገድ ጊዜዋን አብቃቅታ በቁጠባ ትጠቀማለች:: ይህ በተፈጥሮ የተቸራት ጸጋዋ እንደሆነ ትናገራለች ::
የሴቷ ድርሻ – በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እና ኢትዮጵያ ያለፈችበትን መንገድ አብሮ እንዳለፈ ሰው ኢትዮጵያ ስትደሰት እኛም ሴቶች ደስ ይለናል ትላለች:: ኢትዮጵያን ሲከፋት እኛንም ይከፋናል ስትል የውስጧን ታወጋለች::
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደርሶ ማየት የምትፈልገው ሁሉም የሀገሯ ዜጋ ሳይራብና ሳይጠማ ውሎ ሲያድር ነው:: ከዚህ ጎን ለጎን ማየት የሚያስደስታት በሚያድገው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሁሉም በፍትሃዊነት ተጠቃሚ መሆን ሲችል ነው:: በጥቅሉ ምኞቷ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ያላትን ኢትዮጵያን ማየት ነው::
ያንን የተረጋጋ የሀገሬን ኢኮኖሚ ለማየት ደግሞ የእኛ የሴቶች ሚና የላቀ ነው ትላለች:: ጠንካራና ጽኑ እምነት ያላቸው ሴቶች ያሉበት ሀገር ብዙ ነገሩ ስኬታማ እና የጸና ነው:: ምክንያቱም ሁሉም ነገር ላይ የሴቶች ተሳትፎ ካለበት ስኬታማ መሆን ቀላል እንደሆነ ታምናለች:: እኛ ሴቶች ያደገችን ሀገር ማየት የምንፈልግ ከሆነ፤ ረሃብተኛ የሌለባትን ሀገር መመልከት የምንሻ ከሆነ ወንዶች ብቻ ያንን ሊያሳኩት አይችሉምና እንበርታ በማለት ታስገነዝባለች::
በአንድ እጅ ማንም አጨብጭቦ ተሰምቶ አያውቅም፤ ሺ ጊዜ የፈረጠመ እጅ ቢኖረውም ዝም ብሎ ከመወዝወዝ ባሻገር የጭብጨባ ድምጽ ማሰማት አይችልም:: በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ የሴቶች ቁጥር አለ ተብሎ ይነገራል:: ስለዚህ አብሮ በመሥራት ኢትዮጵያን ለማሳደግ ይህን ሀብት መጠቀም መቻል አለብን:: እኛ ሴቶች ጠንካሮች፤ ደግሞም ቁርጠኞች ነን:: ስለዚህ ሴቶችን በሚገባቸው መንገድ ሁሉ ማሳተፍ ከቻልን እና መንግሥትም የሴቶችን አቅም ከተጠቀመበት ወደ አስቀመጥነው ርዕይ የማንደርስበት አንዳች ምክንያት የለም ትላለች::
ሴት እና ምርምር
እየሠራች ያለችበት ተቋም በብዙ ትኩረትን የሚሻ እንደሆነ ትገልጻለች:: ተቋሙ የመንግሥት እይታ ያለበት ነው:: ለዚህ በምክንያትነት የምታስቀምጠው በምትሠራበት ተቋም የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች እንደ ጠቀሜታቸው ታይተው የፖሊሲ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው:: በዚያው ልክ ተረድታ የሚጠበቅባትን ለማድረግ እውቀቷን ሳትሰስት በማገልገል ላይ ትገኛለች::
እርሷ እንደምትለው፤ ሴትነት ጠንካራ የተባሉ ሥራዎችንም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት አይገድብም:: በርግጥ ሴት ልጅ ላይ ከሥራዋ በተጨማሪ በቤት አካባቢ ሌላ ሸክም መኖሩ የሚታወቅ ነው:: ሴት ልጅ ቤቷ ስትገባ እናትነቱ ስላለ ለልጆቿ የሚጠበቅባትን ማድረግ ግድ ይላታል፤ ሚስት በመሆኗም ደግሞ የቤቱ ራስ ለሆነው ባለቤቷም በተመሳሳይ የምትሰጠው ጊዜ ይኖራልና ቤቷ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠብቋት ይታወቃል::
ከእናትነት እና ከሚስትነት በተጨማሪ ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች አሉ የምትለው እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ እንደ አንድ የማኅበረሰቡ አካል በዚያም ተሳትፎ ማድረግ የሚጠበቅ ነው ትላለች:: እንዲያም ሆኖ በሥራዋ በተጣለባት አደራ ልክ ትኩረት ሰጥታ በትጋት ትሠራለች::
ባለችበት የሥራ ዘርፍ ሀገሯን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ ናት:: እንደ እርሷ አባባል በተሠማራችበት ዘርፍ ሚናዋ ዜሮ ነጥብ 0001 በመቶ እንኳ ብትሆንም ያንን አበርክታ ማለፍን ትሻለች:: ያንን ለማሳካትም ወትሮም ቢሆን በመምህርነት ሙያ ላይ እያለችም ሆነ አሁን በምርምሩ ዘርፍ በተሰማራችበት በቁርጠኝነት ትሠራለች::
በአሁኑ ጊዜ እየሠራች ያለችው የምርምር መስክ ላይ ይሁን እንጂ ምርምር ሥራ ላይ ብቻ አልተወሰነችም:: ጊዜያዊ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡ ለአብነት ያህል እንደ አጭር የፖሊሲ መግለጫ መሰል ሥራዎችንም ሳታቋርጥ ጽፋ ለሚመለከተው ታቀርባለች:: በዚያ አጭር የፖሊሲ መግለጫ ላይ ምናልባት የሚጠቀሙ ሴክተሮች እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይኖራሉ፤ ያንን ለመጻፍ ጊዜ አትመርጥም፤ ቤት ስትገባ ተደራራቢ ሥራዎች እንዳሏት ብታውቅም፤ ለነገ ማሳደርን አትሻም::
ለምሳሌ በዚህ ዓመት በኢኮኖሚው ዘርፍ በርካታ አዳዲስ ለውጦች የታዩበትና ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም የገባችበት ነው ትላለች:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ አዳዲስ ነገሮች የሚታዩበት ጊዜ ነው:: እሱም ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚው ጋር ተያይዞ በዓለም ላይም በርካታ ለውጦች እየተፈጠሩ መሆናቸውንም ታስረዳለች::
ከዚህ የተነሳ ሀገራችንን ጨምሮ ገና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሚታይ ስጋት መኖሩም አይቀሬ ነው:: ታዲያ እነዚህን ለውጦች በዕለት ተዕለት ተግባሯ በሚያጋጥማት ጊዜ ጣቷን ከኮምፒውተሯ ኪቦርድ ጋር ማነካካት ግድ ይላታል፤ ትጽፋለች፤ አትታክትም:: የጉዳዩ ባለቤት እንደ መሆኗ ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮችን አይታ አታልፋቸውም፤ ኢትዮጵያን ይጠቅማታል ብላ በምታስበው ነገር ላይ ሁሉ የራሷን አበርክቶ ከማስቀመጥ ቦዝና አታውቅም::
የምትጽፈው ሁለት ገጽ አሊያም ሶስት ገጽ ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ነገር ቁም ነገሩ ነው:: ይህ የፖሊሲ አጭር መግለጫ ጽሑፍ በእርሷ ተቋም አገላለጽ (policy briefing) ይባላል:: ስለዚህ ይህን ከማድረግ ተቆጥባ አታውቅም:: በዚህ ዓመት ከመስከረም ወር ጀምሮ እስከ የካቲት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ አምስት የፖሊሲ አጭር መግለጫ ጽፋለች:: እሱን የምትጽፈው በቋሚነት የምትሠራው የምርምር ሥራዋ ሳይስተጓጎል ነው::
ቁርጠኝነቱ እስካለ ድረስ ይህን ማድረግ ይቻላል ትላለች፤ ሴት ስለሆንኩ ወይም እናት ስለሆንኩ የራሱ የሆነ የሥራ ጫና ቢኖርም ከወንድ የሚያሳንሰኝ ነገር ግን የለም ትላለች:: ሴትነት ከምንም ዓይነት ሥራ የሚያስተጓጉል አይደለም:: እኔ ለየትኛውም የሥራ ዓይነት መሽመድመድ ይሉት ነገር አይነካካኝም ስትል ቁርጠኝነቷን ታስረዳለች::
እንደ እርሷ አባባል ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ነን የሚለውን አባባል ማሳየት ያለባቸው በመናገር ሳይሆን በሥራ ነው:: እንደ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አንድ ተመራማሪ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚሠራው የምርምር ሥራ ሁለት ነው:: ይህን የሚያደርገው ተመራማሪው ፕሮፖዛል ቀርጾ እና አቅርቦ ከሚመለከተው አካል አስተያየት ተቀብሎ ከጸደቀ በኋላ መረጃዎችን በመሰብሰብ ይሠራል::
ስለዚህ እርሷም የተቋሙ ሠራተኛ እንደ መሆኗ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠበቅባት የነበረውን የምርምር ሥራ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሳታስተጓጉል አስገብታለች:: ይህን ስታደርግ ሴትነት አልጎተታትም:: ወደኋላም አላስቀራትም:: ሁለተኛውን የምርምር ሥራ ለመቀጠል ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ፕሮፖዛል በመቅረጽ ላይ ትገኛለች:: እሱም ቢሆን ከቀነ ገደቡ ሳይተላለፍ የሚገባ እና ይሁንታን የሚያገኝ እንደሚሆንም ባለሙሉ ተስፋ ናት::
በዚህ መሃል ለፖሊሲ የሚሆን አጭር መግለጫ በየተወሰነ ጊዜ በመጻፍ ለቅርብ አለቃዋ የምታስረክበዋ የዛሬ እንግዳችን፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ብዙ ጉዳዮች አሉ ትላለች:: ለአብነትም በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም ምን ላይ እንደሚገኝ እና ሀገሪቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ለመረዳት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ. ኤም.ኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ያደረጓቸውን ቆይታና በኋላም ሁኔታውን አይተው የሰጡት ግብረ መልስ እንደነበር የሚታወስ ነው::
ታዲያ በወቅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ስለኢትዮጵያ ያሉት ነገር ምንድን ነው? እንድምታውስ እንዴት ይገለጻል? ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶችስ የሚጠበቀው ምንድን ነው? ከግለሰብስ የሚጠበቀው ምንድን ነው? የሚለውን ነገር ለመጻፍ ሞክሬያለሁ ትላለች::
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ እንደሚታቀው የአሜሪካ መንግሥት ዋነኛው ዓለም አቀፍ የርዳታ ተቋም የሆነው ዩ.ኤስ.ኤይድ በተለያየ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል:: ይሁንና አዲስ ተመራጩ ፕሬዚዳንት፣ አሜሪካ በዚህ ተቋም አማካይነት ስታደርግ የነበረውን ድጋፍ እስከ መዘጋት እንደምትደርስ መናገራቸው ይታወቃል::
ታዲያ ከእርሳቸው ትዕዛዝ በኋላ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ የሰብዓዊ ርዳታ ፕሮግራም የሚቋረጥ ከሆነ እንደ ኢትዮጵያ በእኛ ላይ ሊደርስ የሚችለው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? እኛስ ያንን የሚቋረጠውን ድጋፍ በምን እንተካው? መፍጠር የሚገባን ስልት ምን መሆን አለበት? በተለይ ዲያስፖራዎች በዚህ ጉዳይ እንዴት መሳተፍ ይኖርባቸዋል? በሚል ጉዳይ ወደ አምስት አጭር የፖሊሲ መግለጫዎችን ጽፋለች::
እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ እንደምትለው፤ ሴት በመሆናችን ብቻ ከወንዶች እኩል እንዳንሳተፍ ምንም የሚያግደን ነገር አይኖርም:: የሥራ ጫናው አለ፤ ይሁንና ያንን ያለብንን የሥራ ጫና ማስተካከል እንደሚቻል በልበ ሙሉነት ትናገራለች ::
ነገር ግን ሴቶችን ጨምሮ የብዙዎቹ አመለካከት ከባድ እና ጠንካራ ናቸው ተብለው የተፈረጁ ሥራዎች የሚተውት ለወንዶች ብቻ ነው:: በጣም አነስተኛ እና ዝቅተኛ ናቸው በሚባሉት የሥራ ዓይነቶች ላይ ደግሞ ሴቶችን የማስቀመጡ ነገር አለ፤ ይህ ግን በፍጹም ተገቢ አይደለም ባይ ነች::
ምንም እንኳ የሥራ ትንሽና ትልቅ ብሎ መፈረጁ ተገቢ ባይሆንም ሴት እነዚያ በብዙዎች አዕምሮ ከባድ ናቸው አሊያም ጠንካራ ናቸው በሚል የተፈረጁ ሥራዎችን ሴትም ከወንዶች ባልተናነሰ ሁኔታ ማከናወን ትችላለች:: ሴቷ ይህን ማድረግ የምትችለው ግን ጠንክራ በመሥራት እንጂ በንግግር ደረጃ “እኔ ከወንድ እኩል ነኝ” በሚል አይደለም፤ ሰርቶ በማሳየት ግን እንደሚቻል ትልቅ እምነት አላት::
እኔ የማምነው ሰርቼ በማሳየት ነው የምትለዋ ተመራማሪ እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ በማኅበረሰቡ ተፈርጆ ለወንዶች የተሰጠ ጠንካራ ሥራ ነው የተባለውን ሴቷ አሳምራ ትሠራዋለች፤ ይህን በተግባር ማሳየት እንደሚቻልም ትናገራለች:: ደግሞም ትላለች “እኔ ከወንዶች እኩል ተወዳድሬ በመሥራት ማሳየትን እሻለሁ እንጂ አንሼ መታየትን እና ድጋፍ እንዲሰጠኝ አልፈልግም” ስትልም ታብራራለች:: በርግጥም በተቋሟት ውስጥም እያከናወነች ያለው ሥራ አባባሏን የሚደግፍ ነው::
የምርምር ሥራ እና ቤተሰብ
የምታልፋቸውና የምትሻገራቸው ፈተናዎች ባህሪ የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል:: ልጆቿ ጊዜዋን ይፈልጋሉ:: በተመሳሳይ ራሱን የቻለ ተቋም ነውና ትዳሯም ጊዜ ይፈልጋል:: ከዚህ የተነሳ ለሥራዋም ሆነ ለቤተሰቧ የየራሳቸውን ጊዜ መድባ መንቀሳቀስ ሙከራ ታደርጋለች:: በመሆኑም ልክ ከሥራ መልስ ወደቤቷ እንደደረሰች እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ከመሥሪያ ቤት ተከትሏት የሚመጣን ሥራ በፍጹም አትነካም::
ምሽት አራት ሰዓት እስከሚደርስ ድረስ ልጆቿ ውሏቸው ምን ይመስል እንደነበር ትጠይቃለች፤ ከእነርሱ ጋርም እንደ እናት እና ልጅ ጊዜ ታሳልፋለች፤ የትምህርት ቤት ቆይታቸውን ትገመግማለች:: በጥቅሉ ከልጆቿ ጋር ትወያያለች::
ከልጆቿ ጋር የመወያየቷ ዋና ምክንያት ትውልድን ኮትኩቶ የማሳደግ ኃላፊነት ስላለባት እንደሆነ ትጠቅሳለች:: በተለይም ወላጆቿ ከልጆቻቸው ጋር በለጋ እድሜያቸው በአግባቡ ማሳለፍ ካልቻሉ ውሎ አድሮ ብዙ ነገር ይታጣል ትላለች:: ከዚያም አልፎ እናት እና ልጅ እንደማይተዋወቅ ሰው ሁሉ ባዕድ መስለው ሊተያዩ ይችላሉ ስትል ታመለክታለች:: ትዳርም እንዲሁ ነው፤ የራሱ የሆነ ጊዜ ይፈልጋል::
ለዚህም ነው በየቀኑ እስከ ምሽት አራት ሰዓት ያለውን ጊዜ ለቤተሰቧ የምትሰጠው:: ልጆቿ ሲተኙ እርሷ ግን በየዕለቱም ባይሆን ብዙ ጊዜ ሥራዋን ትቀጥላለች:: የቱንም ያህል ምሽቷን በሥራ ብታሳልፍም ጠዋት ላይ ለመነሳት አትቸገርም፤ ጠዋት በቤት ውስጥ በሥራ በኩል ድጋፍ ለምትሰጣት ልጅ ብቻ የልጆቿን ምግብ እንድትሰራ አትተውም:: እርሷም አብራ ትንጎዳጎዳለች:: ምግቡን ከሠራች በኋላም በየምሳ እቃቸው አድርጋ ትሸኛቸዋለች:: ይህ ከልምድ የመጣ ትጋቷ ነው::
እንግዳችን እልፍነሽ (ዶ/ር)፣ በቤቷ ውስጥ ያለውን ሥራ መልክ አስይዛ እና ልጆቿን ወደ ትምህርት ቤት ሸኝታ ቢሮ ከገባች በኋላ ግን ትኩረቷን ሁሉ የምታደርገው ሥራዋ ላይ ነው:: በአብዛኛው የተመራማሪዎች ሥራ የጥሞና ጊዜ እንደሚፈልገው ሁሉ እርሷም በቢሮዋ ሆና ያንኑ ታከናውናለች:: እርሷ እንደምትለው ከሆነ፤ ሌላ የተለየ ምክንያት ከሌላት በስተቀር ቢሮ ከገባች አትወጣም:: የምታባክነው ምንም ዓይነት ሽርፍራፊ ደቂቃ የላትም::
ይህ ዓይነቱን ልምድ ያመጣችው ከተማሪነቷ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ታስረዳለች:: በተለይም የመጀመሪያ ዲግሪዋን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተማረች ባለችበት ጊዜ ቅጽል ስም እንዳወጡላት ታስታውሳለች:: የወጣላት ቅጽል ስም ትሪያንግል (ሶስት ማዕዘን) የሚል ሲሆን፣ ውሎዋ ከ“ዶርም-ክፍል-ካፌ” ስለማያልፍ የተሰጣት ስያሜ ነው:: የምታባክነው ጊዜ የለም፤ በተማሪነቷ ግድ ካልሆነ በስተቀር ክፍል አለመግባት ብሎ ነገር በእርሷ ዘንድ የሚታሰብ አይደለም::
ዛሬም ቢሆን እርሱ ባሕሪዋ አልተለያትም፤ ከሥራ ገበታዋ ያለ በቂ ምክንያት በምንም ምክንያት አትቀርም:: ቤት ስትገባ ሰዓቱ የቤተሰቧ እንደሆነ ሁሉ ወደ ሥራ ገበታዋ ስትመጣ ደግሞ ሰዓቱ የሀገሯ ጉዳይ ሥራ ነው:: በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ፈተናዎች የሉም ማለት አይደለም ትላለች::
የማይረሳው ገጠመኝ
በሴትነት እልፍ ሲልም በሕይወት ዘመኗ አንድ የማትረሳው ገጠመኝ አላት:: የሁለተኛ ዲግሪዋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማረች ባለችበት ወቅት ነፍሰ ጡር ነበረች:: የመጀመሪያ እርግዝና ስለነበርም ወልዶ ለመሳም ጉጉቱ አለ:: በወቅቱ መኖሪያዋ ሰበታ፣ የምትማረው በመመላለስ ነበር:: ይሁንና የመውለጃዋ ጊዜ እየተቃረበ በመጣ ጊዜ መመላለሱ እየከበዳት መጣ:: ስለዚህ የነበራት አማራጭ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅርብ በተባለ ቦታ ተከራይቶ መማር ነው::
ለተማሪ የሚሆን ቤት የሚገኘው የት ይሆን? የሚለውን ለማወቅ ዞር ዞር ተብሎ ሲጠየቅ ጥሩ የሚሆነው ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው ተባለ:: ቤት ፈልጎ የማግኘቱን የቤት ሥራ የትዳር አጋሯ ወስዶ በተባለው አካባቢ ያገኛል፤ ቤቱን እንዳየም ብዙ ሳያቅማማ ቀብድ ይከፍላል:: ቤቱን የተከራየሁት ለባለቤቴ ነው፤ ለጊዜው ልጅ የለንም፤ ነገር ግን ከእርሷ ጋር የምትኖር አንዲት ልጅ አለች የሚለውን በአጭሩ ያሳውቃል::
በነጋታውም እቃ እንደሚያስገባ ይስማማል:: ትምህርቷን በመማር ላይ ላለችው ባለቤቱ የተከራየውን ቤት ለማሳየት ከክፍል እስክትወጣ መጠበቅ ነበረበትና በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ አካባቢ ቆይቶ ከክፍል እንደወጣች ይዟት ወደተከራየላት ቤት ለመድረስ ተጣደፈ::
እንግዳችን እልፍነሽ (ዶ/ር) እና ባለቤቷ ወደ ስፍራው ደርሰው ግቢ ውስጥ እንደገቡ የቤቱ ባለቤት (አከራያቸው) የቤታቸው በረንዳ ላይ ቆመው ነበርና ወደ ውስጥ ከዘለቁት ባልና ሚስት ጋር ፊት ለፊት ተያዩ፤ በተለይም ትኩረታቸው እልፍነሽ (ዶ/ር) ላይ ነበርና የመውለጃዋ ጊዜ የተቃረበ መሆኑን ከሆዷ መግፋት የተነሳ ተረዱ::
ይህን እንዳስተዋሉም፤ ከሰዓታት በፊት ቀብድ ሰጥቷቸው ቤቱን የተከራየው ባለቤቷን ጠሩት:: እርሱ ወደተከራየው ቤት እያቀና ነበርና ወደዚያ ሳይደረስ ከርምጃው በሚገታ ዓይነት ድምጸት “ወንድሜ!” ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰሙት:: “አቤት!” ባላቸው ቅጽበትም፤ “ብርህን ተቀበለኝ” አሉት:: ችግሩ ምንድን ነው? ብሎ በጠየቀ ጊዜ፤ “ቤቱ የለመደው ላጤን ነው” የሚል አጭር ምላሽ ብቻ ሰጡት::
በዚህን ጊዜ እንደ አንድ የመጀመሪያ እርግዝና ያውም ለመውለድ እንደተቃረበች ሴት የሚሰማ ስሜት ቢኖርም፤ እስኪ ሌሎች ዘንድ ሔደን እንሞክር አላለችም:: ወዲያው አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰች:: ትምህርቷንም ማቋረጥ አላሰበችም:: እስከምትወልድ ድረስ ግን ካለችበት ሰበታ በመመላለስ ለመማር ቆረጠች፤ አደረገችውም:: ይህ እኔን የገጠመኝ ፈተና ለሌሎች ሴቶች ትምህርት ነው ትላለች::
የወደፊት ህልሟ
ወደፊት ብሆን ብዬ የማስበው አንዲት የተሳካላት ኢትዮጵያዊት ሴት መሆን ነው:: የተሳካላት ሴት ስል ግን ሀብታም ሴት መሆን ማለት አይደለም:: የተሳካላት ኢትዮጵያዊት ሴት መሆንን እሻለሁ ማለት በያዝኩት ሙያ፤ የተዋጣላት ባለሙያ መሆን ነው::
ሀገሬ ለብዙ ዓመታት በእኔ ላይ ኢንቨስት አድርጋለች የሚል አስተሳሰብ አለኝ:: ምክንያቱም ከአንደኛ ክፍል እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ስማር ከሁለት አስርት ዓመት በላይ ሀገር እኔ ላይ ሀብቷን እንዳፈሰሰች ይሰማኛል፤ እኔም ለሀገሬ የሆነች አንድ ጠብ የማደርገው ነገር እንዲኖረኝ ጽኑ ፍላጎቴ ነው:: ይህ ሕልሜ ነው ትላለች::
ምናልባትም እኔ ሳልፍ ልጆቼ በኩራት መናገር የሚችሉትን ነገር ለሀገሬ ማበርከት እሻለሁ የሚለው ቁርጠኝነቱ አላት:: ሀብት ቢከማች በአንድ ሌሊት ሊጠፋ የሚችል ነገር ነው፤ ነገር ግን ለትውልድ የሚሻገር ነገር ማድረግን እንደምትናፍቅ ትናገራለች::
መልዕክት
ለሴቶች የማስተላልፈው መልዕክት “ሴቶች ይችላሉ፤ ችለውም አሳይተዋል” የሚለውን ነው:: ሴቶች ያለን ደግሞ ልዩ የሆነ ተሰጥኦ ነው:: በተፈጥሯችን የተቸርነው ልዩ ተፈጥሮ ያልኩት ለምሳሌ ሴት ልጅ ልሥራ ካለች በአንድ ጊዜ ከአንድ ነገር በላይ ተግባራትን ማከናወን መቻሏ ነው::
ለምሳሌ የቤት ውስጥ ሥራ እየሠራች፣ አንደኛው ልጇ የሚጠይቃትን ጥያቄ በተግባር ምላሽ እየሰጠች በተመሳሳይ የሌላኛዋን ልጇን ጥያቄ ተቀብላ በምትኩ ምላሽ መስጠት ትችላለች:: በዚህ ዓይነት ውስጥ ግን ወንዶችን አስቀምጦ ያንን ሥራ ተወጡት ቢባሉ ሊያሳኩት አይችሉም የሚል መረዳት አለኝ:: ይህ ለሴት ልጅ የተቸራት ስጦታዋ ነው ትላለች::
ስለዚህ ሴቶች አትችሉም የሚል ትርክት ሲሰነዘርብን ባለመቀበል እንስማማ:: መቻላችንን ደግሞ በተግባር ለማሳየት እንጣር:: ሴት ከሆነች አትችልም የሚል ነገር በተደጋጋሚ የምንሰማ ከሆነ ውሸት ሲደጋገም እውነት ለመሆን እንደሚዳዳው ሁሉ እኛም “አዎ! አልችልም፤ ምክንያቱም ሴት ነኝ፤ ምን ይደረጋል በቃ!” ወደሚለው ነገር እንዳንሔድ “እንችላለን” የሚለውን የሚያጀግነውን ቃል በመያዝ በመሥራት እናሳይ እላለሁ:: የሴቶች እኩልነት የሚለውን አባባል በተግባር እንደግፍና እናጽናው ባይ ነኝ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም