
ትውልዷ ሰሜን ሸዋ ይፋትና ጥሙጋ ቀወት ወረዳ ነው። ዕድሜዋ ለሥራ ባይደርስም ሴት ናትና የቤት ውስጥ ሥራዎችን የግድ ተለማምዳለች። በአቅሟ ቤተሰቦቿን በሥራ ታግዛለች። ውሃ ከጉድጓድ አለያም ከምንጭ መቅዳት፤ እንጀራ መጋገር፤ ወጥ መሥራት እንደ መላላክና ከብት ማገድ ሁሌም የሚዘወተሩ ተግባራት ናቸው። ይህ ልምዷ ሰውነቷ ገና ሳይጠና ጠንካራና ብርቱ ሴት አድርጓት። አልችልም የሚል ሃሳብን ከውስጧ የለም። ሥራዎችን ያለ ምንም ዕረፍት ታከናውናለች። በዚያው ልክ ደግሞ እንዳታያቸው ያደረጓትም ነገሮች ነበሩ። አንዱ በልፋቷ ልክ መለወጥን እምብዛም አለማየቷ ነው።
ተምራ ቤተሰቦቿን ዘመናዊ አርሶ አደር ማድረግ አለመቻሏም ዛሬ ድረስ የምትቆጭበት ነው። ለዚህም ደግሞ አዲስ አበባ መምጣቷ ነገሮችን እንዳመ ሰቃቀላቸው ታስታውሳለች። ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሙሉነህ ትናንት ላይ ሆና ስታያት አዲስ አበባ ልዩ ተፈጥሮን፤ ልዩ ማንነትን የምትሰጥ ይመስላታል። በዚህም ገና ስምንት ዓመት ሳይሞላት ጀምሮ አክስቷን ወደ እርሷ ጋር እንድትወስዳት ትጎተጉታታለች። ምክንያቱም አክስቷ ወደ እነርሱ ጋር ስትመጣ የተለየ የአኗኗር ዘይቤን ተከትላ እንደምትኖር ያሳያታል። በአለባበስ፤ በራስ አጠባበቅ፤ ለቤተሰቡ የምታመጣቸው ስጦታዎች ሁሉ ያምሯታል፤ ያንን የማድረግ ፍላጎት ከውስጧ አሳድሮባታል።
አንድ ቀን ይህንን ምኞቷን እውን የምታደርግበትን አጋጣሚ ከአክስቷ ዘንድ አገኘች። አዲስ አበባ ለመሄድም በአቅራቢያቸው መኪና የለምና ወደ መኪናው ለመሄድ ማቄን ጨርቄን ሳትል በበቅሎ ላይ ተፈናጠጠች። ከአንድ ሰዓት ጉዞ በኋላም ሸዋሮቢት ከተማ ላይ ደርሳ ከአክስቷ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጣች።
አዲስ ኑሮ በአዲስ አበባ
ዓለምፀሐይን አክስቷ ከእናቷ እጅ ፈልቅቃ ስታመጣት ከልጆቿ ሳትለይ እንደምታስተምራትና ለወግ ማዕረግ እንደምታበቃት ለራሷ ቃል ገብታለች። በዚህም አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ ጊዜ ሳትፈጅ አካባቢውን በዚያው ትለምደዋለች በሚል ከዘመናዊው ትምህርት ይልቅ የቄስ ትምህርት ቤቱ ይበጃታል ብላ በዚያ እንድትገባ አደረገቻት። ልክ እንደ መዋለ ሕፃናት የሶስት ዓመት ቆይታዋን በዚህ የትምህርት ሥፍራ አሳለፈች። ቶሎ ትምህርት የሚገባት ልጅም ነበረችና ጉብዝናዋን በበቂ ሁኔታ አሳየች።
ዓለምፀሐይ ዘመናዊ ትምህርቱ ስትገባ ከገጠሩ ድባብ ወጥታ የከተማውን የአኗኗር ዘይቤ ለመልመድ በብዙ ተቸግራለች፤ እንደ ከተማው ልጅ ፈጣን መሆን አልቻለችም። አክስቷ የተለያዩ ምክሮችን ትመክራታለች። ቀስ በቀስ ግን ዓለምፀሐይ ነገሮችን ማጤን ጀመረች። ድባቡን ተላምዳውም በትምህርቷ የሚገዳደራት እንዳይኖር አደረገች። እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ የደረጃ ተማሪ በመሆን ያለ ምንም መቆራረጥ ትምህርቷን አስቀጠለች። ከአምስተኛ ክፍል በኋላ ግን እንደፈለገች መማር የማትችልበት ሁኔታ አጋጠማት። ጉብዝናዋ፤ ጥንቁቅነቷና ውበቷ በብዙዎች ዓይን ውስጥ ከተታት። መውጪያ መግቢያ የሚያሳጧት ወንዶች ቁጥር በረከተ። አንድ ቀን ሁለት ቀን እያለች ለወራት እየሸሸች ልታመልጥ ሞከረች። አንድ ቀን የእርሱ መሆን ካልቻለች ሊገላት የሚፈልግ ሰው መኖሩን ስታውቅ ከትምህርት ገበታዋ ላይ በመስኮት ዘላ ለአክስቷ ምንም ሳትላት ጠፋች። ካሳንችስ ላይ ወደምትገኘው ሌላኛዋ አክስቷ ዘንድም ገባች፡፡
እዚህ ከገባች በኋላም ቢሆን ትምህርቷን ለማቋረጥ አልፈለገችም። ለመማር ተመዝግባ ነበር። ነገር ግን አግቢኝ ባዮቹ እዚህም ቢሆን አልራቋትም። እናም ትምህርቷን ትታ በቀጥታ የሙያ ትምህርት ለመማር ጣሊያን ክለብ በሚባል ማሰልጠኛ ውስጥ ገባች። የጣሊያን ምግብ ዝግጅትም ተምራ አጠናቀቀች። ጉብዝና በተፈጥሮ የተቸራት በመሆኗም ሥራ አግኝታ በአንድ ምግብ ቤት በ850 ብር ተቀጠረች። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአክስቷና በመጀመሪያ ባሏ ትውውቅ በሥርዓት እንድታገባ ተደረገች።
ትዳርና ፈተናው
ዓለምፀሐይ ባለቤቷን ባታውቀውም የቤተመ ንግሥት ወታደር መሆኑን ስትሰማ ጥሩ ክብርና ጥበቃ እንደሚያደርግላት ተስፋ አድርጋለች። ሥራ እየሠራች ትዳሯን በአግባቡ እየመራች ወራትን ሲያሳልፉ ጥሩ ሰው መሆኑን አይታለች። ከዓመት ቆይታ በኋላ ግን ምን እንደቀየረው በማታውቀው ሁኔታ ባሕሪው ተለወጠ፤ ተደባዳቢ ሆነ፤ ለእርሷ ያለው ክብርም ቀነሰ። ይህም ጊዜ ያልፋል ብላም ታገሰች። ግን አልሆነም። ትዳሯን ትታ ወጣች፤ በራሷ ቤት ተከራይታ መኖር ጀመረች።
ትዳሯን ትታ መውጣቷ ግን በእጅጉ ፈተናት። ምክንያቱም በወቅቱ ነፍሰጡር እንደሆነች አታውቅም ነበር። ያለ አባት ልጅን ወልዶ ማሳደግ ደግሞ ለእርሷ ዓይነት ሰው ብቻ መኖርን ላለመደ ቀላል አይሆንም። ግን ምንም ዓይነት አማራጭ ስላልነበራት ጥርሷን ነክሳ ፈተናውን ሁሉ ለመጋፈጥ ቆረጠች። ሥራም ሆኖ ደመወዝ ጥሩ ስለነበረ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ሳትቸገር ወራትን አሳለፈች። እስከ መውለጃ ጊዜዋም ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ለነገ መታረሻዋ የሚሆናትን ቅሪት አዘጋጀች። ማንንም ሳትጠራ ራሷን በራሷ አርሳም እናት ናትና ወዲያው ሌላ ሥራ ለመሥራት ቀጣሪዎችን ወደማፈላለጉ ተሰማራች። ሆኖም ልጅ ያለውን ማንም ሊቀበል አይወድምና በቀላሉ ሥራ ልታገኝ አልቻለችም። ስለዚህም ልጇን አዝላ የሰው ቤት ልብስ ማጠብ፤ አሻሮ መቁላት የመሳሰሉ የተመላላሽ ሥራዎችን መሥራት ጀመረች።
ልጅ ወርቁ
ዓለምፀሐይ ስለ መጀመሪያ ልጇ ስታነሳ ብዙ ፈተናዎቿ ከፊቷ ቀድመው ይደቀናሉ። በተለይም እርሱን ለማሳደግ የከፈለችውን ዋጋ በምንም የሚተካ አይደለም። ግን ደግሞ አትቆጭበትም። ምክንያቱም በእርሱ የምትሻውን ሁሉ እያሳካች ነው። ለአብነት ደጋግማ ለመማር ብትሞክርም እርሱን ትታ ማድረግ በምንም መልኩ ሊሳካት አልቻለምና ትምህርቷን ትተዋለች። የዩኒቨርሲቲ መግባት ህልሟንም አሳልፋ ለልጇ ሰጥታለች። በተለይም ከትምህርቷ ጋር ተያይዞ የማታ ትምህርት ለመማር በቆረጠችበት ወቅት በተደጋጋሚ እየገጠማት ያለው ነገር በምንም ተዓምር ልጆቼን ትቼ እንድትል አድርጓታል። ቀን ስትለፋ ውላ ማታ ወደ ትምህርት ቤት ታቀናለች። ከዚያ መልስም ከልጆቿ ጋር ደስተኛ ሕይወትን ትመራለች። ይህ አካሂድ ለመጀመሪያ ጊዜ የበኩር ልጇን በሠራተኛዋ ችልተኝነት ሊያሳጣት ነበር። ይህም ልጇን አምና የሰጠቻት ሠራተኛ እያስገደደች ልጁን ወተት ስትግተው ትን ብሎት ሊሞት ተቃርቦ ደረሰች። መፍትሔው ሆስፒታል መውሰድ ነውና ነፍስ የሌለው የሚመስለውን ልጇን ይዛ ከነፈች። ለነብሴ ያለ ሰው አግኝታም በመኪና ሆስፒታል አደረሳት። በብዙ ድካምና ሕክምና ልጇን ከሞት ታደገች። ከዚያ በኋላ ሠራተኛ አምና ልጆቿን ትታ መውጣትን እርም አለች። ትምህርቷንም ይማርላት ዘንድ ለእርሱ ሰጠች። የበኩር ልጇም አላሳፈራትም። ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ህልሟን ለማሳካት እየታተረ ነው፡፡
ሁለተኛው ገጠመኝ ደግሞ እንደለመደችው ትምህርቷን ለመከታተል ወደ ትምህርት ቤት አመራች። ከትምህርት ቤት ስትመለስ ግን ያየችውን ማመን አቃታት። ልጆቿ በጣም ፈርተዋል፤ ቤቱ ተመነቃቅሯል፤ አንዳንድ ወሳኝ የምትላቸውም እቃዎች የሉም። ግራ ገብቷት ስትጠይቃቸው ሌባ ቤት ውስጥ ገብቶ ሙሉ እቃውን ዘርፎ ልጆቹን አስፈራርቶ መውጣቱን ተረዳች። የልጆቿን ፍርሃት ስታስበውም ‹‹ለማን ብዬ ነው የምኖረው፤ የምማረውስ›› በማለት ትምህርቷን እርግፍ አድርጋ ተወችው።
ዓለምፀሐይ ስለ በኩር ልጇ አስተዳደግ ስታነሳ ‹‹ልጄ ትምህርቴም፤ ወርቄም፤ ልብሴም፤ ምሳዬም ነው። ሥሠራ ማግኘት ሳልችል ስቀር እርሱን ለማሳደግ ያለኝን ወርቅ እና ልብሴን ሸጬ ደስተኛ የሚሆንበትን እድል ሰጥቼዋለሁ። የሰው ፊት እየፈጀኝ መሥራት ያለብኝን ሁሉ ከአቅም በላይ እየሠራሁ ነገው ብሩህ እንዲሆን ለፍቻለሁ። አባት ያገኛል በሚልም ሌላ ትዳር እስከ መያዝና ተጨማሪ ፈተና በራሴ ላይ እስከ ማምጣት ደርሻለሁ። በርግጥ ፈተናው ወርቅ የሆኑ ልጆችን ስላፈራሁበት አልቆጭበትም። ሴት ልጅ ጠንካራ ናት፤ በራሷ ምንም የማድረግ ኃይል አላት የሚለውንም ተምሬበታለሁ። በሆነው ነገር አልናደድም። ልጆችን በምንም ልገዛቸው እንደማንችል እናቶች አባወራም መሆን እንደምንችል በእነርሱ አይቼዋለሁና ሁሌም ደስተኛ ነኝ። አሁንም እኔን ይራበኝ፤ ይጥማኝ እንጂ እነርሱ በምንም እንዲከፉብኝ አልፈልግም። ለዚህም ዘወትር የቻልሁትን እየሠራሁ የወደዱትን ማድረግ አልቦዝንም›› ትላለች።
ችግር ምላጭ ያስውጣል
ሙሉ ቀኗን በቅጠል ለቀማ አሳልፋ፤ ልጇን እንኮኮ በማለት ቅጠሉን አዝላ ገበያ ላይ የምትሸጠው በዝቅተኛ ዋጋ ነበር። ሆኖም የልጆቿ ሆድ ጦሙን ማደር የለበትምና ዘወትር በሌሊት ተነስታ የሚያስፈራውን የኮተቤ ጫካ አቆራርጣ በመሄድ ቅጠሉን ትለቅማለች። በዚህ ሥራዋ የገጠማትን ነገር መቼውንም አትረሳውም። ከቅጠል ለቀማው እርም ብላ የቀረችውም በዚህ ምክንያት ነበር። ትንሹን ልጇን ይዛ ወደ ጫካው የምትሄደው እዚያው ጫካ ውስጥ አረፍ አድርጋት ሳትርቅ እየተከታተለቻት ለቀማዋን በምታከናውንበት ወቅት ድንገት ጅብ መጥቶ ሊበላት የነበረውን አጋጣሚ ስታስታውስ ይዘገንናታል። በወቅቱ አከራይዋ ባትደርስላት ኖሮም ልጇ የጅብ እራት ትሆን ነበር። ግን ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› ሆነና ነገሩ ልጇ ተረፈችላት። ከዚያን በኋላ ልጇን አዝላ የምትሠራውን ሥራ መርጣ የሰው ቤት ተመላላሽ ሠራተኛ ሆነች። ልብስ ማጠቡን፤ አሻሮ መቁላቱንና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወኑን የገቢ ምንጯ አደረገች።
ይህም ብዙ ለእርሷ ዓይነት ወጣት የሚሆን ተግባር አይደለምና በግሏ ለመሥራት እቅድ አወጣች። ከቤቷ ሳትወጣ የምትሠራውን ሥራ አስባ አገኘችም። ይህም እንጀራ እየጋገሩ ለሌሎች ማስረከብ ነበር። ከዚያ በተጨማሪ በምግብ ሙያ የሰለጠነች በመሆኑ ለሚረከቧት ሰዎች ምን ምን ዓይነት ሥራዎችን እንደምታከናውን በመንገር ሰዎችን እንዲያመጡላት ራሷን አስተዋወቀች። እድሏ ቀና እና ብዙዎች ሥራ ያሠሩዋት ጀመር። ዛሬ ድረስም በትዕዛዝ ጠላና ምግብ ታዘጋጃለች። ዳቦ ለሚፈልግም ትደፋለች።
ዓለምፀሐይ አንድ ሥራ ብቻ መሥራት አይመ ቻትም። ጉልበት እስካለኝ ድረስ ለምን እሰንፋለሁ የሚል አቋም አላት። ስለዚህም ከምግብ ዝግጅቱ ባሻገር መንግሥት በሰጣቸው መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ታመርታለች። ከቤቷ አልፋ የገቢ ምንጯን እያሰፋች ትገኛለች። በተጨማሪነትም በቤቷ በጎችን የማደለብ ሥራ ትሠራለች። ዶሮም ታረባለች።
የዓለም ፀሐይ የሥራ ምርጫ ዘርፈ ብዙ ነው። አርሶ አደር፤ የምግብ ባለሙያ ብቻ ሳትሆን ወጌሻም ነች። የብዙዎችን አካል መልሳለች። የዚህ ሙያ ባለቤት ያደረጓት አያቷ ናቸው። ልጅ እያለች እርሳቸውን ተከትላ ውልቃት፤ ስብራት፤ ሕፃናት ላይ በብዛት የሚከሰት የቡኣ መውረድ፤ ስር መዞር… የመሳሰሉ ችግሮችን በእጇ አክማለች። ልምዱን ፈጥና በመያዟና ለብዙዎች ተስፋ በመሆኗ ደግሞ አያቷ ሳይቀሩ የመሰከሩላት ነች። ሲጠሯትም ‹‹ዳባሽ›› እያሉ እንደነበር ታስታውሳለች።
ዳባሽ ዛሬ ላይ ብዙዎችን ዳብሳ መፍትሔ ሆናቸዋለች። በዚህም ዶክተሮች ሳይቀሩ ከእጇ በረከት ተቋድሰዋልና የወጌሻነት ተግባሯን ስታከናውን ችግር እንዳይገጥማት በማሰብ ዘወትር ጓንት፤ ማስክና መሰል የሕክምና ቁሳቁሶችን ያበረክቱላታል። አንዳንዶች ደግሞ የልምድ ሐኪም እንዳትሆን ማድረግ ስላለባት ነገር ምክራቸውን ይለግሷታል። ከሕክምና ውጭ ያሉ ሰዎች ደግሞ አልባሳትን እንደ ልዩ ስጦታ ይለግሷታል።
እርሷ ዘንድ የሚመጡ ሰዎች ብዙም ቢሆኑም የምታስተናግድበት በቂ ሥልጠና አለመውሰዷ፤ ለሕክምና የሚሆን በቂ ቁሳቁስ አለማግኘቷና በቂ የሆነ ክፍል አለመኖሩ በእጅጉ ያስጨንቃታል። በተለይም የቤት ጉዳይ አይደለም ለወጌሻነት ሥራዋ ለራሷም የጠበበ መሆኑ ብዙዎችን ማገዝ እንዳትችል ስለስገደዷት በጣም ታዝናለች። በዚህ አጋጣሚም የሚያግዛት ሰው ብታገኝ ደስ እንደሚላት ትናገራለች። አግዙኝ ማለቷ ያላትን ለማካፈል ካላት ጉጉት አንጻር መሆኑንም አበክራ ታስረዳለች።
ዓለምፀሐይ ‹‹ረሃብ የራስን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የምንመለከትበትን ዓይን የሚገልጥ ነው›› የሚል አቋም አላት። እርሷ ባትራብ ኖሮ ሌሎችን ማየት እንደማትጀምር ታወሳለች። ትናንት እርሷ በችግር ውስጥ በማለፏ በማህበሯ በኩል የተቸገሩትን ታበላለች። ዘወትር ደግሞ በዓላት ላይ ለነደያን ትሰጣለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ በወረዳ ደረጃ የሴቶችና ሕፃናት ክፍልን ታግዛለች። እንዴት ከተባለ ወረዳው እውቅና ሰጥቷት በወረዳው ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑና ችግር ላይ ያሉ ሴቶችን በማንሳሳት መጀመሪያ በራሷ ቤት የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት ወደ ማገገሚያ እንዲገቡ ነገሮችን ታመቻቻለች።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም