አገልግሎቱ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የአካል ድጋፍ ህክምና ሰጠ

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የተለያዩ የአካል ድጋፍ ህክምና መስጠቱን በጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ገለጸ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ታሪኩ ታደሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አገልግሎቱ የአካል ድጋፍ መሣሪያዎችን ማምረት፣ የአካል ድጋፍ መሣሪያ ለሚያስፈልጋቸው እና በሱስ ለተጎዱ ሰዎች ህክምና መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል፡፡

እስካሁን ድረስም በቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የታገዘ ህክምና ለ50 ሺህ ሰዎች መስጠት መቻሉን አመልክተው፤ በአማካኝ በዓመት ለአንድ ሺህ 600 ዜጎች የሱስ ማገገሚያ ህክምና እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አገልግሎቱ ተኝተው ለሚታከሙ ህመምተኞች ከአራት መቶ በላይ አልጋዎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

ይህን ህክምና ያገኙት ከሱስ እና ከአዕምሮ ህክምና ውጭ የአካል ድጋፍ ፈላጊዎች መሆናቸውን አመልክተው፤ የተፈጥሮ፣ ሰው ሠራሽ አደጋ እና በእድሜ ምክንያት የሰውነት አካላቸው በመጉደሉ ምክንያት የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውን መከወን ያቃታቸው፤ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ያስቻለ የህክምና አገልግሎት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ከአጋዥ የድጋፍ ህክምናዎች መካከልም ህጻናት ተወልደው መቀመጥ ወይም መራመድ የማይችሉ ፤ አንዳንድ ጊዜ እግራቸው አጭር ሆኖ የተወለዱ ህጻናትን ማገዝ፣ ከእግር፣ ከወገብ እና ከሌሎች አካላት ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ችግሮች የዌልቸርና ሰው ሠራሽ አካል ድጋፍና ህክምና እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ታሪኩ እንደተናገሩት፤ እክካሁን ድረስ የተሰጠው ህክምና በአዲስ አበባ ከተማ በተገነባው ማእከል ብቻ ነው፡፡ በቀጣይ አገልግሎቱ ቅርንጫፎችን የማስፋፋት እቅድ አለው፡፡

ሌላው ህክምና እንኳን ቢቀር ፤ ሱስ ብቻ አዲስ አበባ በሚገኘው ማዕከል ብቻ ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል በመላ ሀገሪቱ አገልግሎቱን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡

በድጋፍ ቴክኖሎጂ በኩል ኢትዮጵያ እራሷን መቻል አለባት፡፡ ከዊልቸር ጋር ተያይዞ በብዛት ማምረት እና የበለጠ ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም፤ በዊልቸር እና ሌሎች አጋዥ መሣሪያዎችን በሀገር ደረጃ ከማምረት አንጻር ጥሩ መሠረት ተይዟል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአጋዥ ጆሮ ማዳመጫ እና በሌሎች የቴክኖሎጂዎች መሣሪያዎች ላይ የጅማሮ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ይህንንም በቀጣይ ጊዜያት ለማሳካት በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ታሪኩ እንዳነሱት፤ በዘርፉ ከዚህ በፊት ትኩረት ተሰጥቶ አልተሠራም፡፡ ከውጭም ቢሆን እውቀቱን እና ቴክኖሎጂውን ማምጣት እንደ ተጨማሪ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ውጪ የተቋማት አለመገንባት እና የገንዘብ እጥረትም እንደ ተግዳሮት የሚነሳ ነው፡፡

በዘርፉ እንደ ሀገር ዝግጁነት ስላልነበረ ሰውን የማሠልጠን ሥራ አለመሠራቱን በመግለጽ፤ ሰዎችን ማሠልጠን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን እያመረተ የሚያክም መሆኑ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለየት ያደርገዋል ያሉት ዶክተር ታሪኩ ፤ በእድሜም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን በቴክኖሎጂ የማገዝ ሥራም ለወደፊቱ የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You