
በ1966 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ኢትዮጵያ የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም። ይህንን ሁኔታ አንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ታላቋን ሱማሊያ የመመስረት ቅዥት ውስጥ የገባው የሱማሊያ መንግሥት ሀሳቡን እውን የሚያርግ መስሎት ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል።
ወትሮም ውጫዊ ጠላት ሲመጣባቸው ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አንድ በመሆን የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን የዓድዋውን ተሞክሯቸውን ለምስራቁ ጦርነት ተጠቅመውታል።
በወቅቱ የነበረው መንግሥት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ ከ300ሺ በላይ ሀገር ወዳድ ሚኒሻዎች በአጭር ግዜ አሰልጥኖ ወደ ግንባር በማሰማራት ወረራውን ቀልብሷል። ወርሃ የካቲት በ23ተኛው ቀን 1889ዓ.ም በዓድዋ የተበሰረው ዓለም አቀፍ ድል በወርሃ የካቲት በ26ተኛው ቀን በ1969 ተደግሟል።
ነገር ግን ግርግር …. ይመቻል እንደሚሉም በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ሽኩቻ ወይም እስከ ትጥቅ ትግል የደረሰ ግጭት ስለነበር አንዳንድ ከመንግሥት ጋር ተቃርኖ የፖለቲካ ፍላጎት የነበራቸው ፓርቲዎች ለሱማሊያ ድጋፍ ሰተዋል። በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች በቀይ ሽብር እና በነጭ ሽብር አራማጆች በርካታ ሰዎች ይገደሉ ነበር። ሱማሊያም የተጠቀመችው ይህንን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን አለመረጋጋት ነው።
ታዲያ ሽንፈት የማያውቃት እና ድል ታሪኳ የሆነችው ኢትዮጵያ ክፍተቱን ተጠቅሞ ሊወራት የመጣውን የዚያድ ባሬን ጦር አሽመድምዳ ጥላ ድንበሯንም በደም አጥራለች። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ዛሬ እለቱ የድል ነውና ድሉን ከባለድሎቹ አንደበት ለማድመጥ ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ አናግሮ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ በ1956 የታንክ መቶ አለቃ ሆነው ሱማሊያን ተዋግተዋል። በ1969 የታንክ ሺ አለቃ ሆነው በባቢሌ ግንባር ሀረር እና ባቢሌን ሊይዝ ከነበረው ከሱማሊያ መንግሥት ጋር ተዋግተዋል። በውጊያውም ግንባራቸው ቆስሎ ወደ ሃንጋሪ ሄደው እንዲታከሙ ተደርጓል። የነበረውንም ጦርነት እንዲህ ያስታውሳሉ።
አዲስ ዘመን ፡- በወቅቱ የነበረው የሱማሊያ መስፋፋት ምን አይነት መልክ ነበረው?
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡– ሱማሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከረችው አንድ ግዜ ብቻ አይደለም። በመጀመሪያ 1953 ቀጥሎም ከሶስት አመታት በኋላ በ1956 እና በ1961 ዓ.ም ወረራ ፈጽማለች። ሞሀመድ ዚያድ ባሬ በአደባባይ “ታላቋ ሶማሊያ” የሚል ቅዥት ይዛ የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩበትን መሬት በሙሉ በሀይል ለመጠቅለል ሞክሯል፡፡
ለዚህም በወቅቱ በርዕዮተ አለም አንድ ከሆነው ከሶቭየት ህብረት መንግሥት መጠነ ሰፊ የሠራዊት ግንባታና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ተደርጎለት ነበር ። ጉዳዩ በሶማሊያ በኩል ታስቦበት እና ታቅዶበት የተደረገ ነው። በዚህም በ1969 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ 300 ኪ.ሜ ፤በደቡብ ምስራቅ ደግሞ 700 ኪ.ሜ ዘልቆ ወረራ ፈጽሟል ። መላው ህዝብ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጎ ወረራውን መቀልበስ ተችሏል። ድሉ ሀገር እና ህዝብን ከፍ ያለ የተጋድሎ መስዋዕትነት ያስከፈለ ነው ።
አዲስ ዘመን ፡- እርሶ በወቅቱ እንደነበሩ አዋጊ መኮንን ምን አይነት ትዝታ አሎት?
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡- በእርግጥ ጦርነት እልቂት ያለበት በመሆኑ ምንም በጎ ትዝታ አይኖረውም። ሀገራት ያላቸውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማድረግ ሲችሉ ጦርነትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው ተገቢ አይደለም ። የሶማሊያ መንግሥት ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ በአፍሪካ ህብረት በኩል ማድረግ ይችል ነበር ፤ያንን ግን እንደ አማራጭ አልወሰደውም ። የአፍሪካ ህብረትን ቻርተር በሚቃወም መንገድ ወደ ወረራ መግባትን መርጧል፡፡
እኔ በ1956 የታንክ መቶ አለቃ ሆኜ ተዋግቻለሁ። በ1969 የታንክ ሺ አለቃ ሆኜ በባቢሌ ግንባር ሀረር እና ባቢሌ እንዳይያዝ ከጓዶች ጋር መስዋዕትነት ከፍያለሁ። በዚያ ግዜም ነበረ ግንባሬ ቆስሎ ወደ ሃንጋሪ ከ15 ጓዶች ጋር ለህክምና የሄድነው። በወቅቱ የተደረገውም ውጊያ ፈጽሞ አላስፈላጊ ነበር።
የሱማሌ መንግሥት አምስት ኮከብ አድርጎ የቅዥት ህልሙን ለማስፈጸም ያካሄደው የእብሪት ጦርነት ነው። ውጊያው የተደረገው በተለምዶ እንደሚባለው በካራማራ ብቻ አይደለም። በሙስታሂል፤ በጎዴ፤ በዋርዴር፤ በአዋሬ፤ በቀብሪደሀርና በደገሃቡር በሚባሉ በተለያዩ ግንባሮች የተለያዩ ብዙ መስዋዕትነትን የጠየቁ ውጌያዎች ተደርገዋል። የካራ ማራን ድል የተለየ የሚያደርገው ስትራቴጂክ በመሆኑ ነው።
ጦርነት አውዳሚ ነው። ከእኔ ጋር ወደ ሀንጋሪ ከሄዱ የጦር ጉዳተኞች ውስጥ አይናቸው የጠፋ ሁለት እግራቸው የተቆረጡ ነበሩ። የኔ ቀላል ጉዳት ስለነበረ ተርፌአለሁ። ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ ያላገቡ ወጣቶች ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በጦርነቱ የአየር ኃይሉ የተጋድሎ ታሪክ ምን ይመስላል?
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡- አየር ኃይሉ በወቅቱ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ተጋድሎም አድርጓል። በዓለም ታሪክም አምስት አውሮፕላን የጣለ ጀግና የጦር ኃይል ተዋጊ አላውቅም። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ግዜ የራሺያ አብራሪ ሶስት አውሮፕላን መጣሉን አውቃለሁ። ለገሰ ተፈራ ግን በወቅቱ አምስት የጦር አውሮፕላን ጥሏል።
ለገሰ ተፈራ በሱማሊያ መንግሥት አምስት አውሮፕላን ጥሎ ከተያዘ በኋላ ለ11 አመት ታስሯል። በመጨረሻም በምርኮኛ ልውውጥ ግዜ ሲመለስ አንድ አይኑን አጥቶ ነበር። ከሌተንል ኮነሬልነትም ወደ ብርጋዴር ጀነራልነት እንዲያድግ እና ከፍተኛ የጀግና ሜዳሊያ እንዲሸለምም የደርግ መንግሥት አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የክተት አዋጅ ሲታወጅ ወደ ውትድርና የገቡ ሰዎች ስሜት ምን ይመስል ነበር?
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡- በወቅቱ የነበረው የደርግ መንግሥት በመሀል ከተማ ሳይቀር ቀይ ሽብር የታወጀበት በሰሜኑ በኩል ከባድ ጦርነት የነበረበት ነበረ። የክተት አዋጅ ሲታወጅም ታጠቅ የገባው 300ሺ ወታደር እንደነበር ይነገራል። በወቅቱም የመንግሥት ሠራተኛ፤ ገበሬ እና በልዩ ልዩ የሥራ መስክ የነበሩ ዜጎች ሀገር ተወራለች ሲባል ለዘመቻ ከተዋል ፡፡
ሕዝቡ ለነጻነቱ ካለው ክብር እና ለነጻነቱ ካለው ቀናኢ ነት የተነሳ የመንግሥትን የክተት ጥሪ የተቀበለው በተደፈርኩ ስሜት እና በታላቅ የሀገር ፍቅር መነሳሳት ነው ።ሕዝቡ ለክተት አዋጁ የሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ለተገኘው አንጸባራቂ ድል ትልቁ አቅም የሆነ ነው ።
አብዛኛው ተዋጊ ሀይል ታጠቅ ገብቶ ለግዳጅ ሲወጣ ዝርዝር የሆነ ወታደራዊ ስልጠና ያገኘ አልነበረም ። የሀገር ፍቅር ስሜት እና የአልደፈርም ባይነት መነቃቃት በጦርነቱ አንጸባራቂ ለትውልዶች የሚተርፍ ድል እንድንቀዳጅ አድርጎናል ።
በወቅቱም ኢህአፓ ጭቁን ጭቁንን አይወጋም ይሉ ነበር። የተለያዩ ወረቀቶችንም እየበተኑ ይገድሉ ነበር። ብዙ ውስጣዊ ችግሮችም ነበሩ። የሀገር ጉዳይ እና የፖለቲካ ጉዳይን የለዩ የሀገር ፍቅር ስሜት ያደረባቸው ወታደሮች ግን ለሀገራቸው ድንበር ተዋድቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትውልዱ ከካራማራ ምን ይማር?
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡- ትውልዱ ከካራማራ ብዙ የሚማረው ነገር አለ ።አንደኛው መከፋፈል ለውጪ ጥቃት በር እንደሚከፍት። ከዚህ በመነሳት ችግሮችን በአግባቡ በውይይት መፍታት ባህልን ማዳበር አለበት ።ከዚህ ውጪ የሀገር ህልውና አደጋ ውስጥ ሲወድቅ የልዩነት ትርክቶችን ትቶ ለሀገር መቆምን ሊማር ይገባል ። ድልም የመስዋዕትነት ፍሬ መሆኑን በአግባቡ በማስተዋል ሁሌም ለሀገራዊ ድል እራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ይህንን እውነት በማስተማር በሀገር ጉዳይ የነቃ ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል ።
አዲስ ዘመን ፡- ጀግኖች መከበር ባለባቸው ልክ ተከብረዋል ብለው ያምናሉ? እንዲከበሩስ ምን መደረግ አለበት?
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡– ለአብነት የብርጋዴር ጀነራል ለገሰ ተፈራ ጉዳይን ብናነሳ በሱማሊያ መንግሥት አምስት አውሮፕላን ጥሎ ከዚም ለ11 አመት ታስሮ አይኑን አጥቷል። በኋላም በአሜሪካን ሀገር ሞቶ ወደ ሀገሩ ሲመጣ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያ እንዲቀበር ገንዘብ ተከፍሏል። ቤተክርስቲያኑ የጀግና መቀበሪያ ነው። ይህ መሆን አልነበረበትም ለሀገሩ ባለውለታ ነበር።
ጀግኖችን ለማበረታታት ይሄ ነው የሚባል ወጪን ላይጠይቅ ይችላል። መልካም ፍቃደኝነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ለምሳሌ ጉና ላይ ሶስት ፓይለቶች ሶስት አውሮፕላን አቃጥለዋል ግን ምንም አይነት እውቅና አላገኙም። ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬም ታንክ ማርኳል ነገር ግን በከንቲባዋ የተሰጠው ቤት ውስጥ ሳይኖርበት ነው ሞት የቀደመው። አሁንም የቅርብ ግዜ ትውስታችን በነበረው ውጊያ ላይ አንዲት ሴት ወታደር ኮሎኔል ማርካለች እንዲህ አይነት ጀግናም የአደባባይ ክብር ይገባታል፡፡
የመገናኛ ብዙኃኑም እንዲሁ ጀግናዎችን ማክበር እና እንዲከበሩም ማስተዋወቅ አለባቸው። ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ ሀገሬን ኢትዮጵያ ወገኔን ብለው የተዋደቁ እና እውነተኛ ተጋድሎን ያደረጉ ዜጎች ክብር እና እንክብካቤ ሊሰጣቸው ይገባል። መንግሥት ብዙ ሀላፊነቶች ያሉበት ቢሆንም የጀግኖችን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህንንም በማድረግ አዳዲስ ጀግኖችን መፍጠር ይቻላል። ቀድሞ ለነበሩት ጀግኖቻችን ክብር እና እንክብካቤ ስናሳይ እኔ ባልፍም ለቤተሰቦቼና ለልጆቼ ህዝቡ አለ በማለት አዳዲስ ጀግኖችን እናበረታታለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ
ብርጋዴር ጀነራል ዋሲሁን፡- ሀገራችን አሁንም ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት እንዳላት ይታወቃል ይህንንም ማጠናከር ያስፈልጋል። በሀገር እና በድንበር ጉዳይ መቀለድ አያስፈልግም። ያለ ሀገር ምንም መሆን አይቻልም። ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም