
በአንድ ዓላማ በፅናት ድል የተጎናፀፉት የኢትዮጵያ ባለውለታዎች በዓል ዛሬ ይከበራል። ይህ የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አርበኞችን የሚዘክረው በዓል ከጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጋር ላይለያይ በፅኑ ተጋምዷል። 84ኛው የድል በዓል ዛሬ ሚያዚያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም መከበሩን ምክንያት በማድረግ፤ የአርበኞች በዓል በምን መልኩ ሲከበር ቆየ? አርበኞች በአንድ ዓላማ ለሀገራቸው ነፃነት ተዋግተው ተሳክቶላቸዋል። ይህንን አንድነት እና የዓላማ ፅናት የውስጥ ሠላምን ለማረጋገጥ መጠቀም የሚቻለው እንዴት ነው? በሚሉ እና በሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎች ዙሪያ ከጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጋር የነበረንን ቆይታ እነሆ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡- የአርበኞች በዓል በምን መልኩ ሲከበር ቆየ?
ልጅ ዳንኤል:- በዓሉ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ በደማቅ መልኩ ሲከበር ነበር። ከ14ቱም ጠቅላይ ግዛት ትልልቅ አርበኞች ንጉሠ ነገሥቱ፣ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተው ያከብሩት ነበር። እኔም በበዓሉ ስሳተፍ ነበር። ሆኖም በአንድ ዘመን እጅግ በላቀ መልኩ ሲከበር የነበረው ይህ የድል በዓል፤ መንግሥት ሲለወጥ የአከባበር ሁኔታው ተቀየረ።
መልኩ የተለወጠበት አንደኛው ምክንያት በጊዜው የነበሩ ደጅ አዝማቾችም ሆኑ ፊት አውራሪዎች፤ ባላምባራስም ሆኑ ነጋድራሶች፣ ሁሉንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የእርሳቸው የግል ተጠሪዎቻቸው ወይም አሽከሮቻቸው አድርጎ በማየት ፊውዳል በሚለው ቃል እንዲጠሉ በመደረጉ ነው። ጊዜው የአብዮቱ ዘመን በመሆኑ የትኛውም ሰው እንደሚያውቀው ብዙ ሰዎች አርበኞች ሳይቀሩ ተገድለዋል። ግማሹ ሲታሰር፤ ገሚሱ በሕመም ሞተ፤ አንዳንዱ ‹‹ዘራፍ›› ብሎ ጫካ ገባ። የቀሩት የጤና ችግር እና የዕድሜ መግፋት አንድ ላይ አዳከማቸው፤ ተመናመኑ። ይህን ተከትሎ በብዙ ግርማ ሞገስ እና በልዩ ሁኔታ በደመቀ መልኩ ይከበር የነበረው በዓል ቀርቶ እንዲሁ ቀኑ ይታለፍ ጀመረ። ይህ ሁሉ የሆነው ንጉሣዊ ሥርዓቱ ስለተገረሰሰ ነው።
ለጊዜው ያዘነም ሆነ የተደሰተ ነበር። ነገር ግን ደስ ያላቸው ስህተት እንደነበር የተረዱት ቆይተው ነው። ሆኖም የተሰበረ ብርጭቆ መጠገን አይችልም። የወቅቱ መንግሥት ከቆይታ በኋላ የአርበኞች ማህበር ከሕብረተሰቡ ጋር ያለውን ትስስር በመረዳቱ በዓሎችን ለማክበር መሰናዳት ጀመረ። በእርግጥ ለይስሙላ አበባ ተቀምጦ ሊሆን ይችላል። ‹‹በዓሉ ነፃነታችንን የተቀበልንበት ሳይሆን፤ እኛ ራሳችን ዋጋ ከፍለን ነፃነት ያገኘንበት የአሸናፊነት በዓል ነው።›› ብሎ ሕብረተሰቡን አሰባስቦ የማክበር ሂደት ምናልባትም ለሰባት ዓመታት አካባቢ ተቋርጦ ነበር። በዛ በሞቅታ ይከበር የነበረው በዓል ለአንድ ዓመትም ቢሆን መቋረጡ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ተማሪ አንድ ዓመት አቋርጦ እንደገና ወደ ትምህርት ቤት ሲገባ እንደሚኖረው ልዩነት የበዓል አከባበሩ ሰፊ ልዩነት ታየበት።
አዲስ ዘመን፡- አርበኞቹ ነፃ ያወጡት ኢትዮጵያውያንን ነው። ለምን የአርበኞች በዓል ከንጉሡ ጋር ተሳሰረ? ይህንን እንዴት መረዳት አቃታቸው?
ልጅ ዳንኤል:– ሳይረዱት ቀርተው አይደለም። የወቅቱ መንግሥት የፖለቲካ ሪዮተ ዓለም ከንጉሡ የተለየ ነበር። ስለዚህ በፊት የነበረውን በተመለከተ ማሰብም ሆነ ማውራት አይቻልም ነበር። ያለፈውን ሁሉ እርግፍ አድርጎ መተው እንደግዴታ ተቆጠረ። ስለቀደመው የተናገረ በሙሉ የመንግሥት ጠላት ነው ሲባል ሁሉም ፈራ። ምክንያቱም ሰው ሃይል ሲበዛ ይፈራል። የእኛ ሀገር ሰው ደግሞ ጭምት ነው። ጎንበስ ብሎ ያሳልፋል። አንድም ያልተከበረው በሰዎች ፍራቻ ነው። ሆኖም ሙሉ ለሙሉ አልተቋረጠም ሲንከባለል ቆየ።
የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ በነበረበት ዘመን፤ በተመሳሳይ መልኩ የተወሰነ ንቅናቄ ነበር። መንግሥት በዓሉ ከሕብረተሰቡ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባቱ፤ ራሱ ይፈልገው ስለነበር፤ በኋላ ከአርበኞች ማህበር በደርግ የተወረሰው ንብረት እስከ መመለስ ደረሰ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ነፃነቱን የስከበረበት በዓል በተወሰነ መልኩ እንዲከበር ሲደረግ ቆየ።
የድሮ አባት አርበኞች ብዙዎቹ በደርግ ጊዜ በማለቃቸው፤ ያሉት ደግሞ በጣም ሽማግሌ እና አሮጊት ከመሆናቸው በተጨማሪ የድሮውን ታሪክ የሚያከብሩ ብቻ ስለነበሩ በእርግጥ የኢህአዴግ መንግሥት እንደደርግ መንግሥት በአርበኞቹ ችግር ይፈጠራል የሚል ፍርሃት አልነበረበትም። እኛም መንግሥት በዓሉ ይከበር በሚል ጠለቅ ብሎ ጥያቄ ባያቀርብም እየገባን ራሳችን ጥያቄ እያቀረብን በዓሉን እያከበርን ቆየን። ስለዚህ ከሞላ ጎደል በዓሎቹ መከበር ጀመሩ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው መንግሥት ለአርበኞች ያለውን ምልከታ እና እየተከበረ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ምን ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል፡- አሁን ያለው መንግሥት ደግሞ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች ማህበርን እና ታሪኩን ያከብራል። በዛ ምክንያት በየዓመቱ የተወሰነ ድጎማ ለአርበኞች ፈቀደ። በዓሎቻችን በነሥርዓት እንዲከበሩ አደረገ። አሁን በምንሄድበት እና በምንጠራበት ቦታ ክብርና ሞገስ እያገኘን ነው። ጀርባችን ላይ ካባ ስለተደረገልን ተሰሚነት እያገኘን ነው።
አሁን ይህንን በዓል የምናከብረው ወጥተን ሰንደቅዓላማ ይዘን ሙዚቃ ከፍተን ለመዝፈን አይደለም። ታሪኩ ሁልጊዜ መታወስ ስላለበት ነው። ታሪክ የሌለው ሕብረተሰብ በምንም ዓይነት ሊኖር አይችልም። ያንን ልናፀባርቅ የምንችለው በዓላቱን በማክበር እና በማስከበር ነው። ስለዚህ በዓላቱ በመንግሥትም መከበር አለባቸው። ለምሳሌ ዓድዋ ቢነሳ፤ በዓሉ ጠፍቶ ነበር። ኢትዮጵያን የሚጠሉ እና መረበሽ የሚፈልጉ፤ የአፄ ምኒሊክን ስም ለማጠልሸት ምን ያህል እንደሠሩ ይታወቃል። መንግሥት እና ሕገመንግሥት እንደሌለ በማስመሰል በጥብጠው ለሌላ የውጪ መንግሥታት እንድንገዛ የሚሠሩ ብዙዎች፤ በዓሉ እንዳይከበር ፈልገው ነበር። እንደእኔ ላሉ እና ታሪኩን በትክክል ለሚያውቁ ሰዎች ይሄ አይዋጥም። ከእናት እና ከአባቱ የተወለደ ሰው ከእነርሱ አልተወለድኩም ብሎ ታሪኩን መመለስ አይችልም። ሆኖም አሁን ሃውልቱ ሳይነካ የበለጠ እንዲከበር ተደርጎ እንደውም የንጉሡ ሃውልት ያለበት ቦታ እንደዜሮ ዜሮ ተወሰደ።
አሁን እንደቀድሞ ወታደራዊ መንግሥት መስመር ለቆ ሳይሆን ንግግሩ እንሻሻል፤ ሥራ እንከፋፈል፤ ሃሳብ እናዋጣ፤ ያለንን ዕውቀት አንዳችን ለአንዳችን እያካፈልን ሀገሪቷን እናሻግር የሚል ነው። ያንን ለማድረግ በተጠራንበት ሁሉ እየተሳተፍን ትንሽ እና ትልቅ ነው ሳንል በየመገናኛ ብዙሃኑ እየቀረብን የሁሉንም አድማጭ እና አንባቢ ለማዳረስ እየሞከርን ነው። መፅሔትም እያሳተምን ነው። ማህበሩ በዓሉን እያስከበረ፤ መንግሥትም እየረዳን ነው።
የዓድዋ በዓል ራሱ በዚህ መልኩ መከበር መጀመሩ አስደሳች ነው። ምክንያቱም የዓድዋ በዓል የጥቁር ሕዝብ በዓል ነው። በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበረውን በሙሉ የሚያካትት ነው። ጥቁሮች መሥራት እና መዋጋት እንደምንችል፤ መብታችንን ማስጠበቅ እንደምንችል ያሳየንበት ነው። የራሳችን ቀን መቁጠሪያ ያለን፤ የራሳችን ባህል እና ሃይማኖት ያለን መሆናችንን አሳይተንበታል። አሁን መንግሥት ይህንን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ሲያስከብር ታይቷል።
አሁንም አንዳንድ የተመረዙ ሰዎች አይጠፉም። የተመረዙት ባስተማሯቸው ፕሮፌሰሮች ምክንያት ነው። በደርግ ጊዜ በአርበኞች ጥላቻ ስለተበከሉ ተማሪዎችንም መረዙ፤ በዛ ጊዜ ተማሪ የነበረ ከዛ ጭቅጭቅ መውጣት አቃተው። ድሉ የዛ ወቅት መንግሥት ጉዳይ አይደለም። የሀገር ጉዳይ ነው። አሁን ብዙዎቹ ገብቷቸዋል፤ አምነዋል። ሆኖም የሀገር ጉዳይ መሆኑን ቢያውቁም ካፈርኩ አይመልሰኝ እንደሚባለው ማመን አይፈልጉም። በፊት የተናገሩትን ለማጠፍ ተቸግረዋል። ውስጣቸው ቢያምንም መፅሐፍ ለመፃፍ ሲጠየቁ፤ ጊዜ የለንም ይላሉ። መፅሐፍ ተችታችሁ ተናገሩ ሲባሉ ፈቃደኞች አይደሉም። ይህ ሲታይ አሁንም ገና ውስጣችን ንፁህ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ማህበሩ ያለው አዲስ አበባ ብቻ ነው ?
ልጅ ዳንኤል፡- አይደለም። አስራ አራት ዞኖች አሉ። ባለፈው ጅማ ሔደን በደንቡ መሠረት ምርጫ አካሂደናል። ትግራይ ትንሽ አስቸጋሪ ቢሆንም በጣም የበሰሉ ሰዎችን በመላክ ሰሞኑን ምርጫ እየተካሄደ ነው። ማህበሩን ያቃኑታል የተባሉ ሰዎች እየተመረጡ ነው። ከዛ አርሲ፣ ባህርዳር እና ዳውሮም ይቀጥላሉ። ይሄ እየተሠራ ነው። ተረክበን የነበረው ቢናጋም ሳይፈርስ እየጠገንን አስቀጥለናል። ሁሉም እንዲመቸው አዲስ ደንብ አዘጋጅተን በየቦታው ያሉትን በደሞዝ የሚሠሩትም ሆኑ የሚደጎሙትን ትንሽ ከኢኮኖሚው ጋር እንዲጣጣምላቸው የሚያገኙትን ከፍ አድርገን እየሠራን ነው። እንደሚታወቀው ቤታችን ፈርሷል።
አዲስ ዘመን፡- አዎ! ግን የአርበኞች ሕንፃ ሲፈርስ አካሔዱ እንዴት ነበር?
ልጅ ዳንኤል:– በንግግር ነው። ‹‹እንዴት ይሻላል?›› ተብለን ነው። መንግሥት አለማለሁ ሲል አታለማም ካልን እኛ ኢትዮጵውያኖች አይደለንም ማለት ነው። ከታች ሰው ተኝቶ ከላይ ሽንት እየፈሰሰ ይፅዳ ሲባል እምቢ ማለት ሃጢያት ነው። ይህ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የሆነ አይደለም። ስንጠየቅ ፍቃደኞች ሆንን። እነርሱም ቢሮ ተከራይተው፤ ዕቃችንን ለማጓጓዝ ገንዘብ ሰጡ። ከሃውልቱ ብዙም ሳይርቅ አራት ኪሎ ብርሃንና ሠላም አካባቢ መሬት ሠጥተውናል። አንዳንዶች ‹‹ ታሪካዊው ሕንፃ ለምን ፈረሰ?›› ይላሉ።
ዋናዎቹ የአራት ኪሎ አርበኞች ሃውልት፣ ስድስት ኪሎ የሰማዕታቱ ሃውልት እና ጊዮርጊስ የምኒሊክ ሃውልት እንጂ ይሔ ከጦርነቱ በኋላ የተሠራ ሕንፃ አይደለም። ለአዲሱ ሕንፃም አፈሩ ተመርምሮ ግንባታው ተጀምሯል። መንግሥት ከተማውን በሙሉ እየሠራ በመሆኑ፤ የእኛ መሠራቱ አያጠራጥርም። የእኛን ጉዳይ ከንቲባዋም ሌሎችም በደንብ እየተከታተሉልን ነው። አርበኛውን እና የአርበኛውን ባህል ይሔ መንግሥት ካሰብነው በላይ ይጠብቀዋል።
አዲስ ዘመን፡- እናንተስ አሁን ምን እየሠራችሁ ነው?
ልጅ ዳንኤል፡-በየትምህርት ቤት እየሔድን ስለኢትዮጵያዊነት እና ስለባህላችን ስለአብሮነት እና ስለሰላም እንዲሁም ማደግ ያለብን መሆኑን በተመለከተ ለወጣቶች ንግግር እናደርጋለን። ዓለም መሬት ላይ መነጋገር ትቶ ጨረቃ ላይ ደርሷል። እኛ ገና ከድህነት እና ከጭቃ ቤት አልወጣንም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስለትናንትናው ማሰብ አለበት። የነበረበትን የማያውቅ ትውልድ ዛሬ ላይ ቆሞ ነገውን ሊያስብ አይችልም። ያለበለዚያ ዝም ብሎ ከእንቅልፉ እንደባነነ ይሆናል።
እኛ ትልቅ ታሪክ ያለን አገር ነን። ፈረንጆች ጫካ እና ጉድጓድ ውስጥ ሲኖሩ እኛ ቤተመንግሥት ነበረን። አክሱምን፣ ላሊበላን እና የፋሲል ግንብን የሠራን ነን፤ ይህንን ትውልዱ ማወቅ አለበት። ከማንም በፊት ሕዝብ የምናስተዳድርበት ሥነሥርዓት ነበረን። የገዳ ሥርዓት እና በአማራ አካባቢ የነበረው የአስተዳደር ሥርዓትን መጥቀስ ይቻላል። ይህንን በተመለከተ እያስተማርን ነው።
አባቶቻችን ከጫካ በወጡ በአምስት ዓመት ውስጥ ስንወለድ የአባቶቻችን ተስፋ ‹‹ ነፃነታችንን አስጠብቀናል፤ ለኑሮ የኢትዮጵያ ሀብት በቂ ነው። ልጆቻችንን እናሳድጋለን፤ ሀገራችን ታድጋለች፤ ከሌላው ጋር መፎካከር እንችላለን።›› ብለው ነበር። ሆኖም ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር እየተባለ የተማረው አለቀ። ከዛ በኋላ የመጣው እንደባዶ በርሜል ሲንኳኳ የሚጮህ እንጂ ከውስጡ ማር እና ወተት የሚያወጣ አልሆነም። በዛ ጊዜ ስድስተኛ ክፍል የደረሰ ተማሪ በእንግሊዝኛ ድርሰት መፃፍ ይችል ነበር። አሁን ያ የለም። በርዳታ መኖር ተለመደ።
አንድ ከፊት ሆኖ የሚመራ መምህር፤ ራሱን ከማንም በታች አድርጎ ሕብረተሰቡን ከእርሱ በላይ እንደሆነ ማሰብ እና ማገልገል ይገባዋል። ባህል እና ታሪክን ይዞ የማይሄድ ከሆነ ከላይ ቁጭ ብሎ የሚናገረው ሁሉ አጥፊ መሆኑ አይቀርም። ነገ ልጅ ተወልዶ በርዳታ የሚኖር ከሆነ ባይፈጠር ይሻላል። ለውጥ ያስፈልጋል። ከድህነት መውጣት የግድ ነው። ሁልጊዜ በርዳታ የምንኖር ከሆነ ዋጋ የለውም።
በትንንሽ እና በማይረቡ ጉዳዮች እርስ በእርስ እየተጋጨን፤ እኔ ከአንተ እበልጣለሁ በሚል አስተሳሰብ ሀገሪቱን አዳክመናል። ለነፃነቱ የተሞተለት ሕዝብ ከድህነት መውጣት አለበት። መንግሥት አለ፤ ሕገ መንግሥት እና ሥርዓት አለ። የተወሰነ ሰላም አለ። በእርግጥ ችግሮች መኖራቸው አይካድም፤ ሰሜን ላይ ችግር አለ። በሌሎችም አካባቢዎች ችግሮች አሉ። ሆኖም ይሄ የሚቀረፈው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ከተነሳ፤ በጠመንጃ አይሆንም። ጠመንጃ ያመጣውን አይተናል።
አዲስ ዘመን፡- አርበኞች በአንድ ዓላማ ለሀገራቸው ነፃነት ተዋግተው ተሳክቶላቸዋል። ይህንን ህብረት የውስጥ ሠላምን ለማረጋገጥ መጠቀም የሚቻለው እንዴት ነው?
ልጅ ዳንኤል፡– ሳይሞከር አልቀረም። ለምሳሌ አንድ ግንበኛ ሸክላ እያነሳ ሲገነባ፤ መልሶ ከስር አንደኛው ሸክላ ከተመዘዘ ከላይ የተገነባው ይናዳል። ይህ እየሆነ ሀገራችንን የሚፈለገው ቦታ ላይ ለማድረስ ብዙ አቅም፣ ጉልበት እና ሀብት እየፈሰሰ ነው።
አሁን ብዙ ቀጣፊዎች አሉ፤ አንዳንዱ በአንድ በኩል እየጎዳ በሌላ በኩል ያመሰግናል። አንዳንዱ እግሩን ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ያስቀምጣል። የእኛ አባቶች ጦርነቱን ያሸነፉት ‹‹ማንም ይምጣ ማንም ሀገራችን ተወራለች፤ ስለዚህ ልንታደጋት ይገባል›› ብለው በሙሉ ልብ የአውሮፕላን ጭስ ውስጥ እንገባለን ብለው ነው። ከተሸነፍን እንማረካለን ለጣሊያን እንገዛለን አላሉም፤ አልወላወሉም። ከተሸነፍን እንሞታለን ብለው ዘምተዋል። ከእባብ እና ከጊንጥ ጋር ተካፍለው እንደሚተኙ ሁሉ ያውቃሉ። ያ ሁሉ ለዓላማ የነበራቸው ፅናት ነው። የእነርሱ ዓላማ ለሀገር መስዋት መሆን ብቻ ነበር።
አንዳንዶች ንጉሠ ነገሥቱም እዋጋለሁ ሲሉ ቆይተው ሸሽተው ሄዱ አሉ። ሆኖም ንጉሡ ተዋግተው ቢገደሉ እንግሊዞች ሕንድ ላይ 300 ዓመት እንደገዙት እኛንም ጣሊያኖች ይገዙን ነበር። በመሔዳቸው እና በመትረፋቸው በተለያየ መንገድ ሲታገሉ ነበር። ሊጎፍኔሽን ላይ ያደረጉት ንግግር የሚዘነጋ አይደለም።
ስለዚህ ዘመን ስንነጋገር የአርበኞችን ዓይነት ሕብረት ለመፍጠር የተማረ እና ሀገሩን የሚወድ፤ ሃይማኖቱን የሚያከብር፤ በሥነምግባር ያደገ እና ራስ ወዳድ ያልሆነ ሰው መብዛት አለበት። በእርግጥ አሁን የኑሮ ውድነት አለ። ሰዎች የሚበሉትን ካጡ ስርቆት ውስጥ ይገባሉ፤ ወይም ማጅራት መተው ይዘርፋሉ። በየትኛውም አካባቢ የሚነሱ ግጭቶች አንድም ከዚሁ እና ከጥቅም ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሆነዋል። እዚህ ላይ ሕዝቡ ምስጉን ነው። ሌላ ሀገር ቢሆን በትንሽ ነገር ሕዝቡ ይተራመሳል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ ለሃይማኖቱ ይገዛል። የግድ ካልሆነበት ወደ ጥፋት አይሔድም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከንጉሡ በኋላ ያለው እየሞተ የሚኖር ሕዝብ ነው። መኖር ያለበት እየሞተ የሚኖር ሕዝብ ሳይሆን እየኖረ የሚሞት ሕዝብ ነው። አሁን እየበላ፣ እየታከመ፣ ልጆቹን እያስተማረ ከችግር ነፃ የሆነ ሕዝብ እንፍጠር እየተባለ ነው። ልጆቹን ለማስተማር ተሰቃይቶ፤ ለሁሉ ነገር ተጨንቆ መኖር ተለምዷል። ይህ እየሞቱ መኖር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰነ የመካከለኛ ደረጃ ነዋሪ እየተፈጠረ ነው።
በሌላ በኩል እንደድሮ በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ሕዝብ ሳይሆን ከ130 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መኖሩ መታወቅ አለበት። ይህንን ያህል ሕዝብ ይዞ የተወሰነ ሰላም መገኘቱም እንደቀላል መታየት የለበትም። አዲሱ ትውልድ ደግሞ ከሃይማኖቱ ሸሸት እያለ ነው። ይህንን መኮትኮት እና ወደ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ማስገባት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ መንግሥት ሆደሰፊ መሆን አለበት። ዋነኛ የመወያያ መድረክ መፍጠር የግድ ነው። በተጨማሪ ችግሩ የመጣው ከየት ነው? የሚለው መታወቅ አለበት። የተወሰኑ ሰዎች ተመካክረው የጣሊያኖች ማፍያ እንደሚረብሹት እየረበሹ ነው? ወይስ ሌላ ጉዳይ አለ? የሚለው ታውቆ ጠንከር ብሎ በጥንቃቄ ሕብረተሰቡ ሳይናጋ ልክ እንደሰንጠረዥ ጨዋታ ለሀገሪቷ መርዝ የሆኑትን ፈልጎ ለማውጣት ጥበብ እና ትዕግስትን መጠቀም ያስፈልጋል።
አሁንም ሰላም ለማስፈን እየተሠራ ነው። ነገር ግን እየተሠራ ያለውን ማጠናከር እና መጠንቀቅ ያሻል። ይህንን ለማጠናከር ደግሞ በከተሞች አካባቢም መንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች በትክክል በሥነምግባር የታነፁ መሆን ይኖርባቸዋል።
አሁን ያለው መንግሥት ከመቼውም የበለጠ በርካታ ሥራ ሠርቷል። ከንቲባዋ ለሊት ሳይቀር ይሠራሉ፤ በእጅጉ ይለፋሉ። እርሳቸው ለሊት እና ቀን እየሠሩ ቢሆንም እስከ ታች ማየት ይጠበቅባቸዋል። ህብረተሰቡ ዶክመንቴ ጠፋብኝ ይላል። ግብር የከፈለበት ካርታ ይሸጥበታል፤ ይለወጥበታል። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ የሚወቅሰው መንግሥትን ነው። መንግሥት ለምኖም ሆነ ተጨቃጭቆ ይሠራል፤ ነገር ግን ከታች ያሉት ሕዝቡን በአግባቡ አያገለግሉትም። ይሄን ማስተካከል የግድ ነው። ለማስተካከል በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፤ የማይቻል ነገር የለም። ትዕግስት ካለ ይቻላል። ባቡሩን ሃዲዱ ላይ መመለስ ያስፈልጋል።
የተማሩ ሰዎችን ደሞዛቸውን ከፍ ማድረግ፤ የመንግሥት ሠራተኞች ቤት የሚያገኙበት ወይም ለቤት የሚደጎሙበትን ሁኔታ መፍጠር የግድ ነው። ይህ ሁሉ ካለ ወደ ጉቦ እና ወደ ሌላ የሚሄዱበት ሁኔታ ይቀንሳል። ኢንዱስትሪያችንን ከፍ ካደረግን የእርሻ ግብዓቱን ተቀብለን ወደ ማኑፋክቸሪንግ የምናደርስ ከሆነ ለውጥ መገኘቱ አይቀርም።
መረሳት የሌለበት ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ጠላት ይኖራታል። እዚህ ላይ ማንም ጥርጣሬ ሊኖረው አይገባም። የመጀመሪያዎቹ ጠላቶቿ አካባቢው ላይ ያሉት ሀገሮች ናቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ብዙ ችግሮች ቢኖሩብንም እናድጋለን። ታች ሆነን አልቀረንም። ፈረንጆች ደግሞ ኢትዮጵያ የተነሳች ጊዜ ቀደም ሲልም ኢትዮጵያ የፊት ለፊት መሪ ስለነበረች መላው አፍሪካ እንደሚነሳ ያውቃሉ። ለእነርሱም መጥፎ እንደሚሆን ያስባሉ። ስለዚህ የውጪ ጠላትን በጥንቃቄ ማየት እና መከታተል ያስፈልጋል።
ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጣ አስተማሪዎች እንደማር ነጥረው ለሕብረተሰቡ የሚያስተምሩ መሆን አለባቸው። እንደሚሰማው መምህር ከተማሪ ጋር አብሮ ጫት ከቃመ፣ ሲጋራ ካጨሰ እና ቆንጆ ሴት ከሆነች አብረሽኝ ካልተኛሽ ውጤትሽን አበላሻለሁ ማለቱን ከቀጠለ ሀገር ችግር ላይ ትወድቃለች። ለአንድ ዓላማ መነሳት ብርቅ እንደሆነ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- የወቅቱን የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል:- የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰብን ሲሸጡበት ምንም አላለም። ጦር ሲወረወርብህ ጎንበስ ብለህ አሳልፍ ይባላል። አሁን ደግሞ የተወሰደብንን የባሕር በር በተመለከተ የሚጠይቅ መጣ። ይሄ ትልቅ እድል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሃሳቡ መነሳቱ በራሱ ምን ያህል ተገቢ ነው?
ልጅ ዳንኤል:- ሃሳቡ መነሳቱ መቶ በመቶ ተገቢነት ያለው ነው። በፊት የጠፋውን ለማስተካከል መነሳት ፍፁም የሚደገፍ ነው። ሁላችንም የውስጥ ስምምነቶችን አናውቅም። የድሮዎቹ መንግሥታት እነአጼ ምኒልክ የውጪ ተንኮል ይገባቸው ነበር። የሚመጣባቸውን ቀድመው ስለሚረዱ፤ ፈረንጆችን አማካሪ ሲያደርጉ ሰላይ እንደሆኑ እየጠረጠሩ ነበር። አሁን በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ብዙ ዕውቀት ያላቸው አሉ። እነርሱን መጠቀም ያስፈልጋል።
ደም ሳይፋሰስ የባሕር በር የሚገኝበትን መንገድ በተመለከተ መሥራት እንደሚገባ ምንም አያጠራጥርም። የሕዳሴ ግድብ ቅድሚያ የታሰበው በአጼ ኃ/ሥላሤ ዘመን ነው። ንጉሱ ሲሞክሩ ግብፅ ከኢትዮጵያ የበለጠ ከዓለም ጋር ግንኙነት ስለነበራት አልቻሉም። ንጉሡ በዕድሜም በአስተሳሰብም ክብር ስለነበራቸው ተቋቋሙ እንጂ በዛ ሃሳባቸው ያጠፏቸው ነበር። በእርግጥ በኋላም አጥፍተዋቸዋል። እርሳቸውን ያገለለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። ምናልባት በውጪ ጠላቶች አማካኝነት ወታደሩ ውስጥ የነበሩ ሀገሪቷ እንዳትሻሻል የሚፈልጉ ሰዎች ውስጥ በመግባት ሀገር ችግር ውስጥ የምትወድቅበት ሁኔታ ተፈጠረ። የሆነው ይኸው ነው። የዓባይን ግድብ ለመገደብ ጉሊት ቁጭ የሚሉ እናቶች ሳይቀሩ ከአንድ ብር ጀምረው አዋጥተው ማሠራት ተችሏል። ወደቡም ቢሆን መንግሥት ሃሳቡን ማንሳቱም ሆነ በሰላማዊ መንገድ እንቅስቃሴ ማድረጉ ትክክል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ እንዲገነባ ከተዋጣው መዋጮ በተጨማሪ ምሁራኖች ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር በመወያየት ሰፊ ተሳትፎ ነበራቸው። የባሕር በርን በተመለከተ ማን ምን ይሥራ?
ልጅ ዳንኤል:- ሁሉ ነገር የሚነሳው ከመሪ ነው። መሪ ሰነፍ ከሆነ ሕብረተሰቡም ሰነፍ ይሆናል። መሪው ትጉህ እና የነገን አርቆ የሚያይ እና የሚተነብይ ከሆነ፤ ሕብረተሰቡም ያግዛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ሀብታችንን የሠራነውን የምንሸጥበት የፈለግነውን የምናስገባበት በር ከሌለን ሞተናል።›› ብለው በየጊዜው ይናገራሉ። በፊት ጭራሽ ሃሳቡ አይነገርም ነበር። አሁን የከተማውም ሆነ የገጠሩ ሕዝብ ውስጥ ይህ ሃሳብ ገብቷል። የገጠሩም ከተማረው የበለጠ ስለሀገሩ ያውቃል። ስለሀገሩ ይጨነቃል።
አሁን ዓለም በእጅ ስልክ ላይ ነው። መረጃ ማግኘት ይቻላል። ይህንን መጠቀም ያስፈልጋል። በየትምህርት ቤቱ እየሔዱ የታወቁ የተማሩ የውጪ ጉዳይም ሆነ ሌሎች ሰዎች ንግግር ማድረግ አለባቸው። ድሮ ጉድጓድ ሲቆፈር ለተማሪው ይነገራል፤ ተማሪው ለምን እንደሚቆፈር ስለሚያውቅ ራሱም ይረዳል፤ ለቤተሰቡም ያሳውቃል። አሁን ማህበራዊ ሚዲያዎችን መጠቀም ይገባል። ሕዝቡ የሚነገረውን እያጣራ ማዳመጥ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። ነገሮችን ማዳመጥ የጠላትን አካሔድ ለማወቅ ይረዳል። አትስሙ አይባልም፤ የሚሰማውን ማጣራት ግን የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዓሉን አስመልክቶ የሚያስተ ላልፉት መልዕክት ካለ እነሆ
ልጅ ዳንኤል፡– በትንሹም በትልቁም ጉዳይ መደናቆር እና ፀጉር መሰንጠቅ አያስፈልግም። መቻቻልን እና ባህልን መጠበቅ፤ ለሀገር ሉዓዋላዊነት ሁል ጊዜ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። በምንም ዓይነት ማንም መሃከላችን ሠርስሮ ገብቶ እንዳይከፋፍለን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሕዝቡ ከሁሉም የበለጠ ሰላም ላይ ሊያተኩር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሠግናለሁ።
ልጅ ዳንኤል፡- እኔም አመሠግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም