
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች አባቶቻችን ሉዓላዊነቷ እና የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ የቆየች ሀገር ስለመሆኗ በርካታ የድል ምስክሮች አሉን። አርበኞቻችን በተለያየ ጊዜ ሊወራቸው የመጣን የጠላት ጦር በመመከት ሉዓላዊነታቸውን ሲያስከብሩ መቆየታቸው እንዲሁ በዝክረ ታሪካችን በኩራት ሲወሳ የሚኖር ገድላችን ነው። ከዚህ የድል አብራክ አንዱ ደግሞ የካራማራ ድል ነው፡፡
ካራማራ የኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የወንድማማችነት ህብር የታየበት፣ ድልና አርበኝነት በአንድ ላይ የጎመሩበት እንደ ዓድዋና እንደተቀሩት ሉዓላዊነታችንን እንዳስከበርንባቸው የድል ታሪኮቻችን ደምቆ የሚወሳ ታሪክ ነው።
የካቲት 26/1970 ከዛሬ አርባ ሰባት ዓመት በፊት በአብዛኛው ሚሊሻ የሆነው የኢትዮጵያ ጦር እብሪተኛውን የዚያድ ባሬ ጦር ካራ ማራ ላይ ድባቅ መትቷል።
ሽንፈት የማይወደው የኢትዮጵያ ሕዝብ የታላቁ ዓድዋ ድል በተከበረበት ወርሀ የካቲት ሌላኛውን ታሪክ ጽፏል። ስለሉዓላዊነታቸው ቀልድ የማያውቁት አባቶቻችን በ‹‹አትንኩኝ›› ባይነትና በታላቅ የሀገር ፍቅር መንፈስ የዚያድ ባሬን ተስፋፊ ጦር አሳፍረው በመመለስ የሀገርን ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል።
ሶማሊያ በ1952 ዓ.ም ከጣሊያን እና ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ነፃነቷን ባገኘች ማግሥት የሀገሪቱ መሪዎች ‹ታላቋን ሶማሊያ እንገነባለን› በሚል ቅዥት መለከፋቸው፤ ‹‹አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ›› እንዲሉ ሆኖ ገና በቅጡ ደርጅተው ራሳቸውን ማስተዳደር ሳይጀምሩ በአጉል ተስፋ ከማይወጡት የታሪክ ሽንፈት ውስጥ ገብተዋል።
ሰርጎ ገቦችን አስታጥቆ በመላክ፣ በፈንጂ አደጋ፣ ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃቶችን በመፈጸም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመረው የሀገሪቱ መሪዎች የጠባጫሪነት ተግባር፤ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ወደ ግልጽ ጦርነት ተቀይሯል።
በእብሪት የሰከረው እና ታላቋን ሶማሊያ እገነባለሁ በሚል የህልም ቅናት የተነሳው የዚያድ ባሬ ጦር በምስራቅ በኩል ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ በኩል እንደዚሁ ሶስት መቶ ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ጥሶ በመግባት ወረራ ፈጽሟል። ‹‹አላርፍ ያለች ጣት›› እንዲሉ በዚህ የነገር ቁስቆሳ የጀመረው ጦርነት ሶማሊያን አሳፍሮ ኢትዮጵያን የሚስከብር ሆኖ ተቋጭቷል።
የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት፤ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር በርካታ ቅድመ ዝግጅቶችን ስታደርግ ቆይታለች። የስንቅ፣ የትጥቅ፣ የሥነ ልቦና፣ የቅንጅት፣ የወታደር ምልመላ እና የመሳሰሉ ለአሸናፊነት ያበቁኛል ያለቻቸውን ሁሉ ስታደርግ ቆይታለች። በተቃራኒው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጥሩ ቁመና ላይ አልነበረም። በውስጣዊ ችግር ከመወጠሯ በተጨማሪ በወቅቱ የነበራት ሠራዊት ቁጥር፤ የትጥቅ እና የስንቅ አቅርቦቱ እጅግ አናሳ ነበር፡፡
የካራማራ የድል ብስራት ሲነሳ አሸናፊነታችን ከሀገር ፍቅር እና ከሉዓላዊነት መታፈር የመነጨ እንደሆነ ነጋሪ አያሻም። ለዚህ ምስክር የሚሆነን ደግሞ የሁለቱ ሀገራት የሠራዊት ዝግጁነት፣ የሥነ ልቦና ንቃት፣ የትጥቅ እና የስንቅ ዝግጁነት ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት በቁጥር አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ሶስት መቶ ሺህ የሚሆን ሕዝባዊ ሠራዊት በአጭር ጊዜ ሥልጠና ለውጊያ የተሰለፈበት ሁኔታ ነበር። ባልሰፋና ባልደረጀ የጦር አሰላለፍ በትጥቅ እና በሥነ ልቦና ተገንብቶ የመጣን ወራሪ መክቶ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ መቻል በእጅጉ የሚያስገርም ድል ነው።
በተጋድሎ እና በብርቱ የአንድነት መንፈስ ጸንታ የቆመችው ሀገራችን ለጠላት በማይመቹ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ታጥራ ትኖራለች። ድል ቁርሱ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት የካቲት 26/1970 ዓ.ም ካራ ማራ ተራራ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በድል አድራጊነት ለማውለብለብ ችሏል። ይህን ሁለንተናዊ ትርጉም ያለውን ድል ብዙ ምሁራን በአድናቆት ጽፈውለታል። እውቁ ኢትዮጵያዊ የታሪክ አዋቂ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳም ‹ካራማራ ከዓድዋ በኋላ የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ውህደት በድል የተገለጸበት ታሪክ ነው› ሲሉ አሞካሽተውታል።
አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ሀገር የሰጡን ባለውለታዎቻችን ለዚህ ትውልድ የሚነግሩት ብዙ ቁም ነገር አለ። በኢትዮጵያ የድል ታሪክ ውስጥ ተሰንደው የሚገኙ ጀብዶች ለሀገር ቅድሚያ በሰጠ፣ ለሉዓላዊነት እና ለዳር ድንበር መታፈር ራሱን ለጥይት ባሰናዳ ኢትዮጵያዊነት የተገኙ ናቸው። ትውልዱ ከዓድዋ አንድነትን ከካራማራ ወንድማማችነትን ተምሮ ኢትዮጵያዊነትን የማስቀጠል እዳ አለበት፡፡
በየዓመቱ የሚዘከሩ የድል ታሪኮች ከሻማ ማብራት ባለፈ ትውልዱ ላይ ጥላ አጥልተው ሊያልፉ ይገባል። የገጠሙን የፖለቲካ እና የውስጥ ለውስጥ አለመግባባቶች ኢትዮጵያዊነትን አስበልጠን ከተወያየንባቸው የኢምንት ያክል አንሰው የሚታዩ ናቸው። ችግሮቻችን ልቀውና በልጠው ለአላስፈላጊ ችግር እየዳረጉን ያሉት ኢትዮጵያዊነት ባልቀደመበት የአንድ ወገን የበላይነት ነው።
በዓድዋ ድል ማግሥት ካራማራን ማክበር በእውነት በየትኛውም ዓለም ያልታየ ጀግንነት ነው። ብዙ የጠላት ኃይሎች ክንዳችንን ቀምሰው ወደኋላ አፈግፍገዋል። አሁን ባለው የጀብድ ታሪክ የትኛውም ሀገር እንዳይደፍረን ሆነን የበረታን ነን። ግን እኛው በእኛ ተሸንፈናል። አሸናፊ በሌለው የእርስ በርስ መጠፋፋት ውስጥ ነን። ዓለምን ስንረታ ራሳችንን መርታት አልቻልንም፡፡
ከጠላት በላይ በራስ እንደ መደፈር የሚያስቆጭ የለም። እርስ በርስ እየተደፋፈርን ነው። እርስ በርስ እንደ ጠላት እየተያየን ነው። የሚቀረን ቢኖር ግን የእርስ በርስ እርቅ ነው። የሚቀረን የእርስ በርስ ትቅቅፍ አለ። የጋራ ታሪኮቻችንን አስተቃቅፈውና አስተሳስረው ለሌላ ድል እንዲያበቁን የተከፈለልንን የሕይወት ውለታ ማሰብ ያስፈልጋል። የዛሬ ነፃነት ዝም ብሎ አልተገኘም። የደም ዋጋ፣ የሞት ግብር ተከፍሎበታል።
ካራማራ ከዓድዋ የወረስነው ሌላኛው የነፃነት ሀውልታችን ነው። ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተረዱ ቆራጥ አባቶቻችን የተገኘ የደም ሀውልት ነው። ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ እስከዛሬዋ እለት ድረስ ኢትዮጵያውያን በማንም ላይ የጦርነት አዋጅ አውጀው አያውቁም። በታሪክ የምናውቃቸው ጦርነቶች በጠላት ሴራ የተጠነሰሱ፣ በእብሪት እና በማንአለብኝነት ድንበር በመግፋት፣ ሉዓላዊነት በመድፈር በኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱ ናቸው።
ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊነት ተረትቶ እና እጅ ሰጥቶ አያውቅም። ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀው እና በአውሮፓ ስልጣኔ ማዕከል ፈር ቀዳጅ ከሆነው የቫራቶኒ ጦር እስከ ዚያድ ባሬ ድረስ ጠላትን እምሽክ ሲያደርግ የመጣ ነው። የድል ታሪኮቻችን ስለኢትዮጵያ እና ዳር ድንበር የተከፈሉ ናቸው።
በአትንኩኝ ባይነት የሚታወቀው ሕዝባችን ትዕግስቱን ጨርሶ በአንድ የተነሳ እለት ጠላትን መግቢያ የሚያሳጣ ነው። ‹ከአንበሳ መንጋጋ ማን ያወጣል ሥጋ› የሚባልለት ሠራዊታችን በሠራዊት ብዛት እና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ተማምነው ለግዞት የተጠጉንን ሲያሽመደምድ አይተናል፡፡
ሠራዊታችን አንበሳ ነው። በፍቅር ካልሆነ በጠላትነት ማንም ደፍሮ ፊቱ እንዳይቆም በኢትዮጵያ የማለ ነው። በዓድዋ፣ በአንባላጌ፣ በካራማራ እና በኡጋዴን የተደረጉ የጀብድ ታሪኮች ከየትም የመጡ ሳይሆን ሀገሬን አትንኩ በሚል ቆራጥነት ለኢትዮጵያዊነት የተከፈሉ ናቸው። እንደ ካራማራ የድል ብስራት ሁሉ አሁን ያለንበትም ጊዜ ስለሰላም የትውልዱን ውለታ የሚጠይቅ ነው። ሰላም እና አብሮነት ከመቼውም ጊዜ ግድ በሚለን ጊዜ ላይ ነን፡፡
ድል ያለው ጦር ሜዳ ብቻ አይደለም። ድል ስለ ሰላም በሚከፈል የእርቅ እና የተግባቦት መንፈስ ውስጥም አለ። ይሄ ትውልድ መሳሪያ ታጥቆ ጦር ሜዳ በመሄድ ድልን መዘከር አይገባውም። ባለበት እና በተሠማራበት ቦታ ሁሉ ስለሀገሩ አንድነት እና ዘላቂ ሰላም የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ የድል ባለቤት መሆን ይችላል፡፡
ጊዜው መሳሪያ አውርደን በሰላም ስለሰላም በአሸናፊ ሃሳብ የምንዋጋበት ነው። አሁን ያለው ትውልድ ችግሮቹን በመሳሪያ አፈሙዝ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ የሚገደድበት ዘመን ላይ ነው። ሀገራችን ከትውልዱ ብዙ ውለታን ትፈልጋለች። እርቅና ተግባቦት በዚህ ዘመን ላይ ለድል የሚያበቁን ብቸኛ ማሸነፊያዎቻችን ናቸው፡፡
ሁሉም ትውልድ የራሱ የዘመን እውነት አለው። ይሄኛው ትውልድ ሰላም እና እርቅን በውይይት እንዲያመጣ በሚገደድበት ጊዜ ላይ ተገኝቷል። የሚነሱ የሰላም ጥያቄዎችን፣ የልማት እና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በዋናነት በሰላም ለመፍታት እንገደዳለን። ዛሬ ላይ የምናከብራቸው የዛኛው ትውልድ የድል ታሪኮች በአንድነት እና በህብረት የመጡ መሆናቸውን እናምናለን አምነን ከእምነታቸው ጥላ ስር ተጠልለን አሁናዊ ችግሮቻችንን በአንድነት እና በህብረት ስንፈታ ግን አንታይም።
ሉዓላዊነት የሚለው ስም ከጋራ ሸንተረር ባለፈ ከሰው መሆን የክብር እና የነፃነት አብራክ ስር የተገኘ የማንነት ቀለም ነው። ይህ የማንነት ቀለም ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም ያለው ሆኖ ከጥንት ወደዛሬ መጥቷል። የተቀዳጀናቸው የድል ታሪኮች በሉዓላዊነት ስም የሚጠራውን ሰውኛ ክብራችንን ለማስጠበቅ መሆኑ ይታወቃል።
ከታሪክ ተዋረድ ተነስተንም ኢትዮጵ ያዊነትን ገና ሲነኳቸው በሚቆጡ አናብስት ልንሰይማቸው እንችላለን። አናብስት የጫካው አውራ ናቸው። ኢትዮጵያም የአፍሪካ አውራ ናት። ልክ እንደ ቤርሙዳ ግዛቷ በድል የታጠረ፣ የፍትህ እና የእኩልነት ሚዛን። የማይደፈሩ፣ የማይሞከሩ፣ የማይነኩ..፣ የሚያከብሩ የተከበሩ ሕዝቦች መገኛ ናት። ካራማራም የነዚህ ሕዝቦች ህብር ወለድ ዘመን ተሻጋሪ የድል ችቦ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም