ካራማራ የአይበገሬነት ተምሳሌት

‹‹ያለ ውል ከሄደች ቆሎዬ በውል የሄደች በቅሎዬ›› የሚለው አባባል የሀገሬን ሰው የነፃነት እና የፍትህ ትርጉም የሚያሳይ ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በየዘመኑ የመጣባትን ወራሪ ስትከላከል የኖረችው። አንድም ባርነት ውርደት ነውና ባሪያ ላለመሆን…!። ሁለትም ባለቤቱን ካልናቁ… እንደሚባለው ንቀትን ስለማይወድ አጥሩን ላለማስደፈር በርካታ ተጋድሎ ተደርጎ ለዛሬ ነፃነት ለመድረስ በቅተናል፡፡

ባርነት አንገትን ያስደፋል ነፃነትንም ያሳጣል። ባሪያ የጌታው ነውና የባሪያው የሆነ ነገር ሁሉ የጌታው ነው። ማለትም አንተ ባሪያ ከሆንክ ልጅህም የጌታህ ባሪያ ነው። ነፃነቱን የተገፈፈ ሰው የኔ የሚለው ነገር የሌለው በጌታው ፈቃድ አዳሪ ነው።

ለነፃነት የሚደረግ ትግል እና የቅኝ ግዛት ፍላጎት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የኖሩ ሃሳቦች ናቸው። ዛሬ ላይ በቀኝ ግዛት ስር የነበሩ ሀገራት በአብዛኛው የእኔ የሚሉት ባሕል፤ ወግ ሥርዓት እና ሃይማኖት የላቸውም። ቢኖራቸውም ተበርዟል። ሀብት፤ ንብረት እና እውቀታቸው ሁሉ ተዘርፏል።

ከአሰሳ ዘመን (ኤጅ ኦፍ ኤክስፕሎሬሽን) ጀምሮ እስከ ዘመናዊው ዓለም (ሞደርን ኢራ) ድረስ ቅኝ ገዥ ኃያላን ሀገራት ግዛቶቻቸውን ለማስፋፋት ሲጥሩ ቆይተዋል። ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ እንደ ብሪታንያ፣ ፈረንሣይ፣ ፖርቹጋል እና ቤልጂየም ያሉ የአውሮፓ ኃያላን ቀኝ ገዥዎች በአፍሪካ ፣ በእስያ እና በአሜሪካ አህጉር ሰፊ ግዛቶችን ያዙ።

የቀኝ ገዥዎች ፍላጎት የሀብት፣ የመሬት እና የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ነበርና እርስ በእርሳቸው ሳይቀር ሽኩቻ ውስጥ ገቡ። ቀኝ ገዢዎች ብዙውን ጊዜ በያዟቸው አካባቢዎች ሕዝብ መበዝበዝ፣ የሀገሬው ተወላጆች ባሕሎችን ማጥፋት እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን መንፈግን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

በ19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ሀገራት ለነፃነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ታዩ። በቅኝ ግዛት ስር ያሉ ሕዝቦች የመብት የማንነት ግንዛቤያቸው እያደገ በመምጣቱ ምሁራንና እና አንቂዎች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እና የብሔራዊ ሉዓላዊነት የማስከበር እንቅስቃሴን ጀመሩ።

ትግሉ ከትጥቅ ትግል እስከ ሰላማዊ ተቃውሞ ድረስ ብዙ መልክ ነበረው። እንደ ህንዱ ማህተመ ጋንዲ እና በጋና ክዋሜ ንክሩማህ ያሉ መሪዎች በሀገራቸው ቅኝ ገዥዎች ላይ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ሲያደርጉ ቆዩ።

ከቅኝ አገዛዝ ጋር በተደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና ካላቸው ክንውኖች አንዱ የሆነው በኢትዮጵያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የተከሰተው ክስተት ነው። የካቲት 23 ቀን 1889 የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር እና የቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት በሚፈልጉ የጣሊያን ወራሪ ጦር መካከል የተካሄደው ጦርነት ለነፃነት ፋና ወጊ ሆነ።

ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክ በዚህ አጭር ጽሑፍ ላይ መዘርዘር ውቅያኖስን በጭልፋ ለማጉደል መሞከር ቢሆንም በወፍ በረር እንመልከተው፡፡

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር፤ በአፍሪካ ቀንድ፤ በኤደን ባሕረ ሰላጤና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ባላት ጅኦ ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ምክንያት በርካታ ጠላቶች አፍርታለች። ዓባይን ጨምሮ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ለወራሪ የሚያጓጓ እና የኔ በሆነች የሚያስብል ነው።

በ16ኛው ክፍለ ዘመን የወቅቱ ገናናዎቹ የኦቶማን ቱርኮች፣ በኋላ ግብጾችም በቱርኮቹ ተልከው መጥተው የምጽዋን ወደብ ለመያዝ ሞክረዋል።

በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያውያን ተከፋፍለው ተዳክመው ሳለ ግብፆች በድጋሚ በ1868 ዓ.ም በሶስት አቅጣጫ በአውሳ፤ በጉንደትና በጉራ ተዋግተውናል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በታሪኳ የሰው ሀገር ወራ እና አሸብራ ባታውቅም ግን በየዘመናቱ ወራሪ አያጣትም።

ከበርሊኑ አፍሪካን በቅኝ ግዛት የመቀራመት ጉባኤ በኋላ ኢጣሊያ ቀድማ አሰብን፤ ቀጥላ በ1877 ዓ.ም የምጽዋን ወደብ በጦር ኃይሏ ወራ ይዛብናለች። የመረብ ምላሹ ገዥ ራስ አሉላ አይቀጥጡ ቅጣት ቀጥተው እና አሳፍረው መለሷቸው።

ከአጼ ዮሐንስ ህልፈት በኋላ ኢጣሊያኖች ከአጼ ምኒልክ ጋር የውጫሌን ውል ተፈራረሙ። የውሉ አንቀጽ 17 ሲጋለጥባቸው መረብን ተሻግረው ይፋ ወረራ ፈጸሙብን። የአጼ ምኒልክም ሕዝቡ በወቅቱ በነበረው በሽታ ተዳክሟል ብለው ዝም ቢሏቸውም እንደ ፍልፈል መሬት እየማሱ ዓድዋ ላይ ደረሱ። ከዚህ በኋላ ነበር እንግዲህ አጼው የክተት አዋጅ ያወጁት።

በዚህም ንቀትን የማይወደው ኢትዮጵያዊ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአንድነት ቆመ። ድር ቢያብር ነውና ነገሩ የካቲት 23 ቀን 1888 የዓድዋ ድል ተበሰረ። በቀኝ ገዥዎች ሲጨቆኑ ለኖሩ አፍሪካውያንም ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ኩራት የድል አርማ ሆነች፡፡

የኢጣሊያ ፋሽስት መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ አባቶቹ ድል ተመተው ተዋርደዋልና ለበቀል ከዓድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ በ1928 እንደገና በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጸመ። ሞሶሎኒ የያዘው በቀል ነውና የማይጨው ውጊያ ላይ በተወገዙ የመርዝ ጋዝ ፈንጂዎች ታግዞ አሸነፈ። አዲስ አበባን እና ዋና ዋና ከተሞችን ተቆጣጠረ። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ለአምስት ዓመት በነጮች ቀኝ ግዛት ተገዝታለች የሚሉ ዛሬም ላይ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማኮሰስ የሚጥሩ ባንዳዎች አሉ። ጣሊያን በአምስት ዓመታት ቆይታው በኢትዮጵያ ውስጥ ከከተሞች ውጭ አንድም የገጠር መንደር ውስጥ አልገባም። በዋና ከተሞችም ቢሆን አርበኞች ለሰላቶ ጣሊያኖች በጀ ብለው እጅ አልሰጡም።

ለዚህም ማሳያው የካቲት 12/ 1929 ዓ.ም አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም በግራዚኒ ላይ ቦንብ ወርውረው አቆሰሉት። ጣሊያኖች በብቅላ 30ሺ የሚደርሱ ዜጎችን ጨፈጨፉ። ይሄንን ያየ ባንዳ ኢትዮጵያዊ ሳይቀር ወገኑ ጋር በአንድ ጎራ እንዲሰለፍ እና ጠላት ላይ የተጠናከረ ርምጃ እንዲወስድ የየካቲት 12 ጥቃት ጠላት ላይ የተጠናከረ ርምጃ ለመውሰድ መነሻ ሆኗል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢትዮጵያ በታላቅ ተጋድሎ ነፃ ወጣች።

በዚህ ፀረ ፋሽስት ትግል ያገዙን እንግሊዞች አንድ ክፉ ጥንስስ በምስራቅ አፍሪካ ጥለውብን ሄዱ፤ “ታላቋ ሶማሊያ” ሲሉ መርዛቸውን ተከሉ። በ1952 የእንግሊዝን ቅዥት ሶማሊያ ይዛ የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩበትን መሬት በሙሉ በኃይል ለመጠቅለል ሞከረች። ያቀደችው እቅድ አልተሳካላትም። በ1956 ደገመው መጡ አሁንም አልሆነም ተመለሱ፡፡

በ1961 ግን መንግሥት ፈንቅሎ መንግሥት የሆነው ሞሀመድ ዚያድባሬ አዋሽ ወንዝ ዘልቆ ግዛት ሊያስፋፋ በርዕዮተ ዓለም አንድ ከሆነው ከሶቭየት ህብረት መጠነ ሰፊ የሠራዊት ግንባታና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ተደረገለት፡፡

ሶቪየት ህብረትም በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ቁጥር የምትበልጠው ኢትዮጵያ የሶሻሊስት ሀገር ስትሆን ሱማሊያን ዓይንሽ ላፈር ብሎ ተዋት። በዚህን ጊዜ ዚያድ ባሬን ከአሜሪካን ጉያ ገብቶ ተሸጎጠ። ወቅቱ ለኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ ጊዜ ሆነ፡፡

ርዕዮተ ዓለም ቀይራለች እና ለ25 ዓመታት ይሰጥ የነበረ የአሜሪካ ወታደራዊ ርዳታ ተቋረጠ። በኤርትራ የገንጣዮች ጦርነት ተጠናክሮ ቀጠለ። በሰሜን ምዕራብ፣ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚደገፉ ታጣቂዎች ጥቃት ከፈቱ። በመሀል ሀገር ቀይ ሽብር ታወጀ። የደርግ መንግሥትም ተከፈለ።

ዚያድባሬ ሐምሌ 3 ቀን 1969 ሀገራችን በደቡብ 300 ኪ.ሜ በደቡብ ምስራቅ ደግሞ 700 ኪ.ሜ ዘልቆ በአሜሪካ እየተደገፈ ወረራውን አስፋፋ። በገላዲን፤ በሙስታሂል፤ በጎዴ፤ በዋርዴር፤ በአዋሬ፤ በቀብሪደሀርና በደገሃቡር የነበሩ የኢትዮጵያ የጦር ክፍሎች በጠላት ላይ ጉዳት ቢያደርሱም እስከ አፍንጫው ታጥቆ የነበረውን ወራሪ ኃይል ማቆም አልቻሉም። በዚህም የጠላት ጦር ወደ ጅጅጋ፤ ሐረርና ድሬዳዋ ለመጠጋት ቻለ። በድሬዳዋ ግንባር በከፍተኛ ትንቅንቅ ከተማዋን ከጠላት መንጋጋ ማትረፍ ተቻለ፡፡

በዚህ ቀውጢ ሰዓት ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የተላለፈውን የእናት ሀገር ጥሪ በመቀበል ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለማዳን ተረባረቡ። በታጠቅ ጦር ሰፈር አጭር ሥልጠና የወሰዱ የሚሊሽያ አባላት ተሰናዱ። ከሶቭየት ህብረት፤ ከኪዩባ፤ ከደቡብ የመንና ከሌሎች ወዳጅ ሀገሮች በተገኘ ድጋፍ ሠራዊታችን ለከፍተኛ መልሶ ማጥቃት ተዘጋጀ። ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በ5 ምዕራፎች የተከፋፈለ የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ነደፉ።

በእናት ሀገር ጥሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ በእድሮች፣ በሴቶችና እናቶች የተቀናጀ እንቅስቃሴ ስንቁን አሟልቶ በጥር ወር 1970 ዓ.ም ከገጠሩ ገበሬ እስከ ከተማው ፖሊስ ሠራዊት፣ ከሕክምና ባለሙያው እስከ መንግሥት ሠራተኛው፣ ከመምህሩ እስከ ተማሪው ለግዙፍ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተሰናዳን። በወቅቱም የአዲስ አበባ ሕዝብ የእድር ድንኳኖቹን እያወጣ ስንቅ በቻለው አቅም እያቀረበ የሀገር ተወራለችና ድንበር ሊያስከብር የአቅሙን አዋጣ።

ሶማሊያም ጥር 14 ቀን የከፋውን ማጥቃት ሰነዘረች። ጠላት የወገንን ዝግጅት በማጨናገፍ ከባቢሌ፣ አወዳይ፣ ፈዲስና ኮምቦልቻ አቅጣጫዎች በማጥቃት የሐረርን ከተማ ለመያዝ ዘመተ። እቅዳቸው ወደ አወዳይና አማሬሳ በመገስገስ የሐረር እና ድሬዳዋን መስመር መቁረጥ ነበር።

ነገር ግን በለስ አልቀናውም ከጥር 14 እስከ 16 በተደረጉ ውጊያዎች በመቶ የሚቆጠሩ ወታደሮችን፤ በርካታ ታንኮችንና መድፎችን ጠላታችን አጣ። በዚህ ውጊያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች በ86 የአየር በረራ ምልልስ የሶማሊያን ታንኮች፣ ብረት ለበሶችንና መድፎችን አወደሙ። በአወዳይና አማሬሳ የሚመጣ ጠላት ስጋት መሆኑ አበቃለት፡፡

ድል አድራጊው ሠራዊት ወደ ፈዲስ ተዛውሮ ጥር 17 ቀን 1970 ዓ.ም አዲስ መልሶ ማጥቃት ከፈተ። በአየር ኃይል እየታገዘ እግረኛው ሠራዊት በርካታ የጠላት ከባድ መሣሪያዎችንና ጥይቶችን ማረከ። ሠራዊቱ ፈዲስንና አካባቢዋን ካፀዳ በኋላ ወደ ድሬዳዋ ግንባር ዞረ። ጥር 24 ቀን ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ላይ የኪዩባና የኢትዮጵያ ወታደሮች ሀረር በነበረው የሶማሊያ ጦር ላይ ድንገተኛ ማጥቃት ፈጸሙ፡፡

ባልጠበቁት ሰዓት ጥቃት የደረሰባቸው የሶማሊያ ወታደሮች ያበሰሉትን ምግብ እንኳ ሳይበሉ በርካታ ታንኮችን፣ ብረት ለበሶችን፤ መድፎችን፣ መትረየሶችንና ብዙ ስንቅ ጥለው ሸሹ። ያፈገፈጉ በርካታ ብረት ለበሶች ደግሞ በተዋጊ አውሮፕላኖች እየተመቱ ወደሙ። በገደል እየተንከባለሉ ከጥቅም ውጭ ሆኑ፡፡

የኢትዮጵያ ወታደሮች እና የኪዩባ ወታደሮች ከሰሜን በኩል ወደ ጅጅጋ አመሩ፣ በኮምቦልቻ ግንባር የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሐረር ያመራ የነበረውን የሶማሊያ ጦር መክቶ መለሰው። ሌላኛው የኢትዮጵያ ጦር የደንገጐ-ድሬዳዋን መንገድ ለመቁረጥ የመጣውን የሶማሊያ ጦር የማጥቃት ርምጃ ካከሸፈ በኋላ መልሶ ማጥቃቱን የካቲት 1 ቀን 1970 ዓ.ም ጀመረ፡፡

ከኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይሎች ጋር የተጣመረው ሚሊሺያ ብርጌድ በጣምራ ጃርሶን ነፃ አወጡ። የካቲት 2 ቀን የኮምቦልቻ-ጃርሶ መንገድን በመቆጣጠር በርካታ የጦር መሣሪያ ተማረከ። የካቲት 21 ቀን አጥቂ የወገን ጦር ክፍል ግሪቆጨርን ከጠላት ወረራ ነፃ አወጣ፡፡

የሶማሊያ ጦር ዋናው የመልሶ ማጥቃት በቆሬ ጅጅጋ መንገድ እንደሚሆን ስለተገመተ በዚህ መስመር ጠንካራ ምሽጐች ተዘጋጁ። ጠላትን በምሽግ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከቆሬ-ጅጅጋ መንገድ በስተሰሜን ተነስቶ ወደ ምስራቅ በጐን የሚያልፍ የወገን ሠራዊት ዚያድባሬን ባልጠበቀው አቅጣጫ ቢያጠቃ ዘመቻውን ቀላልና ፈጣን እንደሚያደርገው ታመነ፡፡

በዚህ መልክ በተቀናጀ መልሶ ማጥቃትና ከፍተኛ ወኔ ሀገርን ከዚያድባሬ ጦር ነፃ አወጡ። የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ከወራሪው አስለቅቀው ባንዲራዋን በካራማራ ተራራ በድል ብስራት ዜና ታጅቦ ለመውለብለብ ቻለ። ዛሬም የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም የምሥራቁ ድላችን የካራማራ የወገን ጦር ጀግንነት 47ኛ ዓመት ታስቦ ለመዋል በቅቷል።

የአሁኑም ትውልድ ሀገር እና ባንዲራ ለሚባለው ነገር ትኩረት እና ክብር ሊሰጥ ይገባል። ኢትዮጵያ ከሌላው ሀገር የሚለያት ለዘመናት ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር በርካቶች አጥንቶቻቸውን ከስክሰውላታል። ደማቸውንም አፍስሰውላታል። ስለዚህ ሕይወታቸውን ሰጥተው በነፃነት ላኖሩን ጀግኖች ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል እና ክብር ለእነሱ ባለውለታዎቻችን ይሁን፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You