የሥራ ላይ ጫና እና አድሎ

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሴቶች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል:: ከፍተኛ ምርታማነት፣ ዝቅተኛ ደመወዝ፣ ሰፊ የሰው ጉልበት፣ ጤናማ ያልሆነ የሥራ ሁኔታ፣ ዝቅተኛ ጥራት ያለው የሥራ ስምሪት የሚታየውም በእነዚሁ ሀገራት በሚገኙ ፋብሪካዎች ውስጥ ነው::

በኢትዮጵያም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ በፓርኮች የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው ያሉ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ነው:: ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ከ10 በሥራ ላይ ካሉ ፓርኮች ውስጥ ዘጠኙ በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት እና ጫማ ማምረቻ ላይ የተሠማሩ ናቸው:: እነዚህ ዘጠኙ ፓርኮችም 75 በመቶ ድርሻ የያዙ ሴት ሠራተኞች ናቸው።

በ2013 በተቋቋመው የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ ፈረንጆቹ 2020 ለመቶ ሺህ ዜጎች ከተፈጠረው የሥራ ዕድል የሴቶች ድርሻ ከ75 በመቶ በላይ ነው:: በዚህም በርካታ ሴቶች የራሳቸው ሥራና ገቢ አግኝተው ከጥገኝነት መላቀቅ ችለዋል:: ወርሃዊ ፍጆታቸውን መሸፈን እና ቤተሰባቸውን መደገፍና ራሳቸውም ከፊቱ በተሻለ ሁኔታ ለማኖር በቅተዋል::

ይሁንና በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ ጥናት ሲደረግበት የቆየው እና በታኅሣሥ 2024 የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው ሰነድ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚሠሩ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሴቶች አሁንም ቢሆን የአስተዋጽኦቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ያመላክታል:: ሴቶቹ በማምረቻ ቦታዎች ከወንዶች ይልቅ ተመራጭ የሆኑት የአንዳንዶቹ የትምህርት ዝግጅት አነስተኛ ቢሆንም የሥራው ፀባይ የሚፈልገውን ትኩረት የያዙ፣ ታዛዥ፣ በተፈጥሮ ተሰጥኦ ያላቸው፣ ከሙስና የራቁ፣ ፈጣን በመሆናቸው መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

ጥናቱ ዓለም አቀፉን የሥራ ድርጅት ሪፖርት ዋቢ በማድረግም ሴቶች ለተመሳሳይ ሥራ የሚከፈላቸው ደመወዝም ከወንድ አቻዎቻቸው ያነሰ እንደሆነም ጠቅሷል::በዚሁ በኢንስቲትዩቱ ከክርስቲያን ሚሼልሰን ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ባካሄደው ጥናት የደመወዝ ልዩነቱ ለረጅም ጊዜ አስተማማኝ እና ዋስትና የሚሆን የኢኮኖሚ አቅም እንዳይኖራቸው ስለማድረጉም ተመልክቷል:: በመስኩ እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ እውቅና ሲሰጣቸው አለመታየቱን አንስቷል:: በፋብሪካዎች ያለው የሥራ ሁኔታ አደገኛ ከመሆኑ አኳያ ብዙውን ጊዜ ደህንነት አይሰማቸውም፣ ይጨነቃሉ፣ በዚህም ሳቢያ አእምሯዊና አካላዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል:: የጤና አገልግሎት ተደራሽነታቸውም ቢሆን ውሱን ነው:: የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን በሥራ ቦታው መተግበር አስመልክቶም ሴት ሠራተኞች የእድገት ደረጃቸውን እና የሥልጠና ዕድሎችን የሚያደናቅፉ፣ ለእንግልት የሚዳርጉ አድሏዊ ድርጊቶች እንደሚገጥሟቸውም ተጠቅሷል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ፀጋ ሁሉም ተግዳሮቶች በሴት የፋብሪካ ሠራተኞች ላይ በተጨባጭ እየገጠሙ ያሉ መሆናቸውን በፈረንጆቹ 2024 ኢንስቲትዩቱ ይፋ ባደረገው በዚሁ ጥናት መረጋገጡን ይናገራሉ::

ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ሴቶች በስፋት በተሠማሩባቸው የፋብሪካ የሥራ ቦታዎች የሚታየው የሥርዓተ ጾታ አለመመጣጠን በሴት ሠራተኞች ላይ ብዙ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑም ታይቷል::‹‹የሴቶችን አቅም ይገድባል፣ የሥራ ደህንነት ይጎዳል›› በማለት ዋና ዳይሬክተሩ በጥናቱ ከተዘረዘሩት መካከል ፈታኝ ያሏቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ::

‹‹በኢትዮጵያ ሴቶች ለቤተሰቦቻቸው የመጀመሪያ ደረጃ ተንከባካቢ ሆነው ያገለግላሉ›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ በዚህም የተነሳ ሴቶች ላይ የሚደረሰው የሥራ ጫና ከሥራ ቦታ ባሻገር እስከ ቤታቸው ዘልቆ በጤናቸው፣ በቤተሰባቸውና በማህበራዊ ግንኙነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል:: ተጽዕኖው ከፍ እያለ ሲሄድ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ተሳትፏቸው በኩል የሚያሳድረው ጫና መኖሩን ይናገራሉ ፡፡

እነዚህን በዋና ዳይሬክተሩ የተነሱትን ሃሳቦችም በየፋብሪካዎች የሚሠሩ ሴቶችም እንደሚጋሩት ነግረውናል:: በክልል ከሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአንዱ ተሰማርተው እንደሚሠሩ የገለፁልን ወይዘሮ ሕይወት ተወልደ በሴቶች ላይ የሥራ ጫና መኖሩን እና በዛ ላይ ከክፍያ ጋር ተያይዞ አድሎም እንዳለ ይጠቅሳሉ።

እንደ ወይዘሮ ሕይወት በተለይ ሴቶች የመጀመሪያ ደረጃ የቤተሰብ ኃላፊና ተንከባካቢዎች መሆናቸው እና በሥራ ቦታ ላይ የሚፈፀም አድሏዊ አሠራር በሴቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ሳይታለም የተፈታ ነው:: በተመሳሳይ ሥራ ለእሳቸው የሚከፈላቸው ክፍያ ለወንዱ ከሚከፈለው ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑ አንዱ የአድሏዊነት ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ::

ወይዘሮ ሕይወት ሴቶች በቤት ውስጥም ተደራራቢ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገልጻሉ። ለዚህም በምሳሌነት ያነሱት የራሳቸውን ተሞክሮ ነው። «በሥራ ቦታ አምሽቼ ወደቤት ብመለስና ቢደክመኝም የሚጠብቀኝ የቤት ውስጥ ሥራ አይቀርልኝም:: ባለቤቴም እኔም ከምናገኛት ጥቂት ደመወዝ ላይ እንደ አቅማችን ሠራተኛ ብንቀጥርም ሁለት መንቲያ ሕፃናትን ብቻ ስትንከባከብ ስለምትውል ምንም ሰርታ አትጠብቀንም:: እንጀራ ከመጋገር፣ ወጥ ከመሥራት፣ ቤት ከማጽዳት ጀምሮ ሙሉ የቤት ሥራው የኔ የሥራ ድርሻ ነው:: ባለቤቴ አብሮኝ ቢሆንም ሕፃናቱ ሲያለቅሱ ከማባበል ውጭ የሚያግዘኝ ነገር የለም» ይላሉ::

ከሳምንቱ አብዛኞቹን ቀናቶች ከሥራ መልስ በዚህ በቤት ውስጥ ሥራ ተጠምደው ሌሊቱን የሚያጋምሱበት፤ ጠዋትም ማልደው በመነሳት ለባለቤታቸው ምሳ ቋጥረው የሚሄዱበት መደበኛ የየዕለት ሥራቸው በመሆኑ በቂ እረፍትም ሆነ እንቅልፍ አለኝ ብለው አያምኑም::በመሆኑም አንዳንድ ቀን ሥራ ቦታ ላይ እንቅልፍ ከድካም ጋር ተደማምሮ እንደሚፈታተናቸው ያነሳሉ::

ወጣት አሚና ኑሩ ሌላዋ በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥራ ልምድ ስታካብት የቆየች ነች:: አሁንም በአንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ እየሠራች ብትገኝም ሥራው እንዳልተመቻት ታነሳለች:: ከዚህ ቀደም ትሠራባቸው የነበሩትን ፋብሪካዎች የለቀቀችውም በሥራ ላይ አለመመቸት ምክንያት ስለመሆኑም ታስታውሳለች:: ከንጋቱ 12 ሰዓት ገብታ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ያለ ምንም እረፍት በሥራ ያሳለፈችበት ጊዜ እንዳለም ታነሳለች:: ሆኖም ለዚህ ሥራ ምንም ዓይነት የትርፍ ሰዓት ክፍያም ሆነ እውቅና እንዳልተሰጣት ትገልፃለች:: ብዙ ሥራ የመሥራት ፍላጎትና የሥራ ፍቅር ቢኖራትም ሴቶችን የሚያበረታታ ሁኔታ ባለመኖሩ አሁን ላይ ከመደበኛው የሥራ ሰዓቷ ውጭ ተጨማሪ ሥራ መሥራቷን ማቆሟንም ታነሳለች:: ከችግሮቹ መካከል አንዱ በፓርኮችና በሌሎች ፋብሪካዎች ለተመሳሳይ ሥራ የሚከፈለው ደመወዝ የተመጣጠነ አለመሆኑ ነው፡፡

ወጣቷ የደመወዝ ልዩነት ያስፈልጋል እንኳን ቢባል እኩል ሥራ በሁለቱም ጾታዎች ሰርቶ ማበረታቻ ለሴቷ መደረግ ነበረበት:: ምክንያቱም ቀደም ባሉት ጊዜያት ሴቶች እንጂ ወንዶች በደል አልደረሰባቸውም::የሥራ ዕድል ተሳትፏቸውም ቢሆን ከበቂ በላይ የሴቶችን ድርሻ ጭምር የያዘ መሆኑ ይታወቃል::በመሆኑም የደመወዝ ልዩነት መኖር አለበት ከተባለ ከዚህ አንፃር ሴቷን ለማበረታታት የሚደረግ መሆን ነበረበት ትላለች::

ሴቶች እክል አጋጥሟቸው ከሥራ ገበታቸው ሲዘገዩም ሆነ ሲቀሩ የመጀመሪያ ደረጃ የቤተሰብ ኃላፊነታቸውም ሆነ ለዚህ ያስገደዳቸው ሁኔታ ከግምት ገብቶ አይታይም ብላ ታምናለች:: እንደ እሷ ሃሳብ ይሄ ከቅርብ አለቆቻቸው አልፎም ከሌሎች በፋብሪካ ውስጥ ከሚሠሩ አመራሮች ጋር ያጋጫቸዋል፡፡

ወጣት አሚና ‹‹ይሄን ሃሳብ ማቅረቤ ለአሰሪዎቼ ወይም የቅርብ አለቃዬ ለሆኑት አልተመቻቸውም::እንደ ነገረኛም የሚቆጥሩኝ ነበሩ:: በዚሁ ሳቢያ ጭራሽ ከዚህ ቀደም አድርገው የማያውቁት የተለያየ ጫና ሲያደርሱብኝ ለቀቅኩ:: አሁን የምሠራበትም ተቋም ቢሆን ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የማገኝበት አይደለም:: አማራጭ ስላጣሁ ብሠራውም የራሴን ሥራ ለመፍጠርና ሥራውን እስካቋርጥ ይረዳኛል›› በማለት አስተያየቷን ሰጥታናለች::

እንደ ወጣት አሚና ገለፃ ከተግዳሮቶቹ መካከል ሴት ሠራተኞች ከሚሠሩት ሙያ ጋር ተያያዥ የሆነ የሥራ ላይ ሥልጠና ዕድል ካለማግኘታቸው ጋር ተያይዞ የሚደረገባቸው ጥብቅ ቁጥጥር መኖሩን ትገልፃለች:: በሥራ ቦታዎቹ የሚደረገው ምደባ በዘፈቀደ መሆኑን፣ ሲሳሳቱ የሚሰደቡበት፣ ብሎም የኃይል ርምጃ ሊወሰድባቸው ስለመቻሉም ታወሳለች፡፡

በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 27 ትላልቅ የጫማ እና የአልባሳት ፋብሪካዎች ላይ ተመስርቶ በቅንጅት የተካሄደው ጥናትም ምደባው በዘፈቀደ ስለመደረጉ ያነሳል::

በሴት ሠራተኞቹ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለውም ይጠቅሳል::ሥራውን ለመልቀቅ የሚያስገድዱ ምክንያቶች ስለመኖራቸው ይገልፃል::በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ተመራማሪና የጥናቱ ተሳታፊ ጥጋቡ ደጉ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት በጥናቱ ጉዳዩ ተቃኝቷል:: በፋብሪካ በሕክምና ቡድን 63 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ነበር::ከእነዚህ ሴቶች መካከል 22 በመቶው በስድስት ወራት ውስጥ ሥራቸውን አቋርጠዋል::በጥናቱ የ30 ወራት ክትትል ከነዚህ ሴቶች ውስጥ በፋብሪካ ተቀጥረው የቀሩት 15 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር፣ ዋና ተመራማሪ እና የጥናቱ ተሳታፊ ቆንጅት ኃይሉ(ዶ/ር) ሥራው የሴቶቹን አካላዊ ደህንነት፤ አሁን እና የወደፊት ሁኔታ ላይ ያለው አሉታዊ እና በጎ ተጽዕኖ መቃኘቱን ያነሳሉ:: በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሥራ ልምድ ያላቸው ሴት ሠራተኞች አጠቃላይ ሁኔታም ዳስሷል ይላሉ:: በተለይ በአበባ ልማት ድጎማ በሚደረግላቸው የምግብ እቃዎች እና የእድገት እድሎች ድጋፍ ማግኘታቸው እንደ በጎ ተጽዕኖ ተወስዷል:: በሥራ ገበታ ላይ ሱፐርቫይዘሮች (ተቆጣጣሪዎች) እና የቡድን መሪዎች የሚያደርጉላቸው ድጋፍም አወንታዊ ልምዶችን የሚያጎለብት መሆኑ ታይቷል::

ሥራ አስኪያጆች ከእውነታው የራቁ ተስፋዎች፣ ዘለፋዎች እና አልፎ ተርፎም ትንኮሳ የሚፈጥሩ አንዳንድ ሥራ አስኪያጆች ሊኖሩ መቻላቸው ደግሞ ሴቶቹ በሥራ ቦታቸው እንዲጨነቁ፣ ደስተኛ እንዳይሆኑና ሥራቸውን እንዲለቁ መገደዳቸውን ያወሳሉ:: ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት መሰደድን፣ ቤተሰቦቻቸውን ከመደገፍ ጨምሮ በሥራ ሁኔታ ርካታ ማጣት፤ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠርም ይመኛሉ:: ብዙ ሴት ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ እና ተስፋ ማጣት ወይም የመሻሻል እምቅ ተስፋ ማጣት ስለወደፊቱ እርግጠኛ አለመሆንም ይስተዋልባቸዋል፡፡

ቆንጅት (ዶ/ር) ጥናቱ በኢትዮጵያ ፋብሪካዎቹ የሚሠሩባቸው ሴቶች ገቢያቸውን፣ ፍጆታቸውን እና ቁጠባቸውን በማሳደግ ከድህነት እንዲወጡ በጥቂቱም ቢሆን መርዳታቸውን ስለመቃኘቱ ይናገራሉ:: ከዚሁ ጎን ለጎንም በመስኩ የሚስተዋሉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በብርቱ ስለመፈተሹ ያነሳሉ::ዓላማው እነዚሁ ህፀጾች በሚቀረጽ ፖሊሲ ታርመው ፋብሪካዎቹ የበለጠ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲያደርጓቸው መሰነቁንም ያወሳሉ:: ውጤታማ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ በመስኩ የሚገጥሟቸውን ውስብስብ ችግሮች መረዳት የግድ የሚል ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ::

‹‹ሴት ፋብሪካ ሠራተኞች ላይ ያለው የሥራ ጫና አስቸኳይ ትኩረትም ይሻል›› የሚሉት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ፀጋ (ዶ/ር) ጥናቱን መሠረት አድርጎ በሥራ ቦታ ላይ እኩል አያያዝን የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች መቅረጽ አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃሉ:: በተጨማሪም ፍትሃዊ ደመወዝ እንዲኖር ማድረግ፣ የሥራ ሁኔታን ማሻሻል፣ የሠራተኛ መብትን ለማስጠበቅ የሠራተኛ ሕግን ማስከበር ያሻል:: ለሴቶች ሥልጠና እና የልማት እድሎችን መስጠት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል::

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You