
ዓድዋ የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የነፃነት ታጋዮች የድል ታሪክ ነው:: የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ መላው አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲተጉና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ መሠረት የሆነ ታላቅ ድል ስለመሆኑም ብዙሃን ይመሰክራሉ::
በተመሳሳይም የዓባይ ግድብ የአልሸነፍ ባይነት መገለጫ ነው:: የኢትዮጵያውያንን አልበገርነት እና ጀግንነት ባህሪ ያስቀጠለ እና የዘመኑ ትውልድም የተጋድሎ መገለጫ ተደርጎም ይወሰዳል:: በአጠቃላይ ዓድዋ እና የዓባይ ግድብ ጎልቶ መሰማት ጀምሯል:: ይህንኑ ጉዳይ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ እና ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል እንደሚከተለው ያብራሩታል::
ኢንጂነር ሃብታሙ እንደሚሉት የዓድዋ ድልና ሕዳሴ የአንድነት ተምሳሌት ናቸው፤ ሁለቱም የኢትዮጵያውያን አንድነት የተረጋገጠባቸው ናቸው:: ዓድዋ የአልሸነፍ ባይነት መገለጫ ነው:: ወራሪው ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ለማንበርከክ የነበረው ምኞት የከሸፈበት እና የጥቁር የበላይነት የነገሰበት አኩሪ ድል ነው::
በተመሳሳይም የዓባይ ግድብ የአልሸነፍ ባይነት ተምሳሌት ነው:: ኢትዮጵያ የማንንም ተጽዕኖ ተቀብላ መኖር እንደማትችል እና መብቷንም ለማስከበር ሊከፈል የሚገባውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀች ሀገር መሆኗን ያስመሰከረችበት የልማት ሥራ ነው::
ሕዝቡ ዓድዋ ላይ እራሱ አሊያም ልጆቹን ወደ ግንባር እንደላከ ሁሉ ለዓባይ ግድብም እንዲሁ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በሀብቱ ተሳትፏል:: ስለዚህ ዓድዋና ሕዳሴ የአንድነት ማሳያ ናቸው:: የዓድዋ ድልና የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ማሰሪያ እና ምልክት ናቸው ሲሉ ይገልጿቸዋል::
ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚልም ተመሳሳይ ሃሳብ ያነሳሉ:: የሕዳሴ ግድብና ዓድዋ በብዙ መንገድ ይመሳሰላሉ:: የዓድዋ ድል እና የሕዳሴ ግድብ የአልበገርነት ተምሳሌቶች ናቸው:: ሁለቱም የኢትዮጵያውያን ቆራጥነትና አንድነት ማሳያዎች ናቸው::
ዓድዋ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታላላቅ የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ ነው:: ከዓድዋ ጦርነት በፊት በነጮችና ጥቁሮች መካከል የነበረው ተፈጥሯዊ ግንኙነት የተዛባ ነበር። ነጮቹ ራሳቸውን እንደ ገዢ ሲቆጥሩ፣ ጥቁሮቹን ደግሞ እንደ ተገዢ ሕዝብ ይቆጥሩ ነበር። ዓድዋ ግን ይህንን የተዛባ አስተሳሰብ ያስተካከለ የድል በዓል ነው::
በተመሳሳይም በቅኝ ግዛት ውሎች ምክንያት የመልማት ዕድል ተነፍጓቸው የቆዩ ሀገራት በራሳቸው አቅም መልማት እንደሚችሉ የዓባይ ግድብ ምስክር ሆኖ ብቅ ብሏል:: የዓባይ ግድብ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ የዘመኑ ትውልድ የድል አክሊል ነው ሲሉ ገልጸውታል::
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የዓድዋ እና የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያ ተፈትና ማለፍ እንደምትችል ማሳያ የሆኑ ድሎች ናቸው ሲሉ ያብራራሉ:: የዓድዋ ድልና የዓባይ ግድብ የውጭ ጫና የፈተናቸውና የኢትዮጵያውያን አሸናፊነት የተረጋገጠባቸው ታላላቅ ስኬቶች ናቸው:: ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የተዋጋችው አንድን ሀገር ብቻ አይደለም:: በወቅቱ ከጣሊያን ጋር ኅብረት ከፈጠሩትና የቅኝ ግዛትን ማስፋፋት ከሚፈልጉት ጋር ሁሉ ነበር:: ኢትዮጵያ በወቅቱ ያሸነፈችው የተነሱባትን ኃይሎች ሁሉ ነው::
ስለዚህ ይህ ትልቅ ስኬት ነው:: የዓባይ ግድብን በተመለከተ ደግሞ እኛን ስትገዳደረን የነበረችው ግብጽ ብቻ አይደለችም:: ኢትዮጵያ በድህነቷ እንድትዘልቅ የሚፈልጉ ኃይሎች ጭምር ናቸው:: ይሁንና ኢትዮጵያ ማሸነፍ የቻለችው ሁሉንም ነው:: ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ምክንያት በጸጥታው ምክር ቤት ስትወሰድ ዓላማው ኢትዮጵያን በዚያ ደረጃ ማብጠልጠል ነበር:: ስለዚህ በኢትዮጵያ ጥንካሬ እሱን ወደ አፍሪካ ኅብረት መመለስ መቻል ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው:: ዓድዋ የቅኝ ገዢዎችን የመስፋፋት ሕልም ያጨናገፈ ሲሆን የዓባይ ግድብ ደግሞ በቅኝ ግዛት ውሎች ምክንያት ተገድቦ የቆየው የመልማት ፍላጎት ነፃ የወጣበት ነው::
ዓድዋ እና ዓባይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ የተሳተፉባቸው የወል ድሎቻቸው ናቸው ሲሉ ረ/ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ያስረዳሉ:: ሁለቱም ድል የተገኙት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፈውባቸው ነው:: በዓድዋ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍስሰውና ሕይወታቸውን ገብረው በከፈሉት መስዋዕትነት ነው:: ድሉ ለሁሉም ጥቁር ሕዝቦች እኩልነት የተከፈለ የደም ዋጋ ነው። ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን የዓድዋ ድል በሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት የሚያምን ማንኛውም የሰው ዘር ሊያከብረውና ሊዘክረው የሚገባ ክስተት ነው::
በተመሳሳይ መጋቢት 24 ቀን በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳክቶ ከመገባደጃው ጫፍ ደርሷል። ተማሪዎች ከዕለት ጉርሳቸው፣ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው፣ የጉሊት ተዳዳሪዎች ከመቀነታቸው፤ የጉልበት ሠራተኞች ከዕለት ምንዳቸው፣ የፀጥታ ኃይሎች ከሬሽናቸው፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከፍሬያቸው እየቀነሱ ግድቡን ከማጠናቀቂያ ምዕራፉ አድርሰውታል:: በዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ይገባዋል::
የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዘመኗ ከሰራቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አቻ አይገኝለትም:: በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሰባተኛ የሆነው ይህ ግዙፍ ግድብ ያለ ማንም የፋይናንስ ድጋፍ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነፍስ ወከፍ ባዋጣው ገንዘብ የተሠራ ነው::
ይህን ሃሳብ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ይሰማሙበታል:: ዓድዋ እና ዓባይ ግድብ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ:: ዓድዋ ላይ ሰው የዘመተው ባለው አቅም ነው:: ይህም ሲባል በጦር፣ በጎራዴና በእጁ ላይ በሚገኘው መሳሪያ ጭምር ነው:: በተመሳሳይ ሕዳሴንም ኢትዮጵያዊ የገነባው ከተረፈው ነገር ላይ አይደለም:: የትኛውም አካል ኢትዮጵያን ሳያግዛትና ድጋፍ ሳያደርግላት በመንግስቷና በዜጎቿ የተሠራ ግድብ ነው:: ይህ ትልቅ ስኬት ነው::
በጣም ወሳኙ ጉዳይ በኢትዮጵያ የውሃ ልማት ታሪክ ዛሬ ያመጣነውን ስኬት በአንድ ጀምበር ያመጣነው ጉዳይ አለመሆኑ ነው:: ስኬቱ የመጣው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው:: በዚህ ስኬት ውስጥ የመሪዎች ቅብብሎሽ አለ:: ንጉሡ አጼ ኃይለሥላሴ አንድ የአሜሪካ ኩባንያ ቀጥረው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ ግድቦችን ካስጠኑ በኋላ ለዓለም ባንክ ብድር እንዲሰጣቸው ቢያቀርቡም ‹‹እኛ ብድር ሰጥተናችሁ ግድቡን ከምትገነቡ እናንተን በስንዴ ብናግዝ ይሻላል፤ ምክንያቱም እኛ ግብጾችን ማስቀየም አንፈልግም::›› የሚል ዓይነት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል::
በወቅቱ ደግሞ በዓለም ባንክም በአፍሪካ ባንክም በጥቅሉ አበዳሪ በሚባሉት ደረጃ ባሉ ውስጥ ግብጾች ተሳትፎ ያደርጋሉ:: አጼ ኃይለሥላሴም ‹‹አንድ ቀን ኢትዮጵያውያን ይገነቡታል›› በሚል ጽናት አልፈውታል፤ ምክንያቱም ቦታው ቢጠናም አቅም ባለመኖሩ የጀመሩትን ማሳካት አልቻሉም:: ሊያሳካ የሚችል ትውልድ እንደሚመጣ ግን ርግጠኛ ነበሩ::
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአዎንታዊም በአሉታዊም የሠሯቸው ነገሮች አሉ፤ ከሠሯቸው ሥራዎች ውስጥ ግን አንድ መደነቅ የሚገባው ነገር ቢኖር “እኛ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረንም እቅም ሳይኖረን መጠቀም ያስቸግራልና የሰው ኃይል ላይ መሥራት ይጠበቅብናል::” በሚል በአርባ ምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂን አቋቁመዋል:: ይህ ደግሞ ወሳኝ ነው::
የውሃ ሀብት ስላለ ብቻ ሥራ ሊሠራ አይችልም በሚል የውሃ መሃንዲስ፣ የመስኖ መሃንዲስ፣ የመጠጥ ውሃ ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርግ መሃንዲስ አምስት ዓመት ውሃ ላይ ብቻ በማተኮር መማር እንዲቻል ተፈልጎ የአርባ ምንጩ ከፍተኛ ተቋም ተከፈተ፤ ከዚህ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሰልጣኞች ዛሬ የሀገሪቱን ውሃ ሀብት እያጠኑና እየተመራመሩ ወደ ጥቅም እየለወጡት ይገኛሉ::
በኢህአዴግ ዘመንም በተመሳሳይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ሕዝቡን በማስተባበር የዓባይ ግድብ እንዲጀመር ማድረግ በመቻላቸው ትልቅ ስኬት ነው:: የጋራ ስምምነቱን ተፈጻሚ ማድረግ የተቻለው ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሠሩት ሥራ ነው፤ ሶስቱ ሀገራት ለስምምነት የተጨባበጡት በእርሳቸው ጊዜ ነው:: ሶስቱ ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ ተፈራርመው ሕዳሴን ሕዳሴ እንድናደርግ የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል::
ሕዳሴ በመሃል የራሱ ችግር ነበረበት፤ በመሃል ላይ ተስተጓጉሎ ነበር:: እሱ ችግር ተፈትቶ ሕዳሴ ሕዳሴ እንዲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በየቀኑ የሚያደርጉት ክትትል እንደ አንድ ፕሮጀክት ብቻ የሚታይ አይደለም፤ በየዕለቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ክትትል የሚደረግበት ፕሮጀክት ነው:: የተበላሸን አስተካክሎ ማስፈጸም መቻል በመሪ ቅብብሎሽ የመጣ ሥራ ነው:: ይህ ትልቅ ትምህርት የሚሰጠን አሠራር ነው::
ዓድዋም እንዲሁ ነው:: በሁሉም ነገር ላይ ከተባበርን ብዙ ማድረግ ይቻላል፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህን ፈጽመውታል፤ ዛሬም ማድረግ ይቻላል:: ስለዚህ ሕዳሴና ዓድዋ የአንድነት ማሰሪያ ናቸው፤ የቁጭትም ማሳያ ናቸው:: ሁለቱም የውጭው ኃይል በኢትዮጵያ ላይ ያለውን አመለካከት ያኮላሹ ናቸው:: በዓድዋ ላይ የተገኘው ስኬት የቅኝ ገዥዎችን አስተሳሰብ ያመከነ ነው፤ ሕዳሴ ላይ ግብጽና ግብራበሮቿ ጭምር የተሸነፉበት ስኬት ተመዝግቧል:: ስለዚህ ሁለቱም በብቃት የተጫወትንባቸው ሜዳዎች ሲሆን፣ ጠላትን በዝረራ ከጨዋታ ውጭ ያደረግንበትን ስኬት ያስመዘገብንባቸው መለያችን ናቸው ሲሉ ያብራራሉ::
ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል አክለው እንደጠቀሱትም የዓድዋ ድል ከመበሰሩ በፊት ጥቁሮቹ ራሳቸውን የማስተዳደር አቅምና ችሎታ እንደሌላቸው ሲቆጥሩ ነጮች ደግሞ ጥቁሮችን የመግዛት ሙሉ መብት እንዳላቸው ያምኑ ነበር:: በተጨማሪም ጥቁሮች ባሕልና ታሪክ አልባ፤ እንዲሁም በተፈጥሯቸው ያልተሟሉ የሰው ዘሮች እንደሆኑ ተደርጎ ይነገር ነበር። ዓድዋ ይህን ሁሉ ቀይሯል:: በአውሮፓውያን በኩል፣ ነጮች ይከተሉት የነበረው የተዛባ ትርክት “የነጭ ዘር የበላይነት” መንኮታኮትና እርቃኑን መቅረት የጀመረው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። ከዚህ ድል በኋላ ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካ ላይ የነበራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች ተናግተዋል። የጭቆና መረባቸው ስጋት ውስጥ ወድቋል:: የአሁኑን ትውልድ አይበገሬነትም በዓባይ ግድብ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም