በኢትዮጵያ በተለያዩ አደጋዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ለእዚህ የከፋ አደጋ ከሚዳረጉት መካከልም አፋጣኝ የመጀመሪያ ርዳታ ማግኘት ሲገባቸው ባለማግኘታቸው የሚሞቱትና ለከፋ ጉዳት የሚዳረጉት ቁጥር ቀላል የሚባል አለመሆኑም ይገለጻል::
ለእዚህ ችግር መፍትሔ ለማፍለቅ በተለያዩ አካላት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ መፍትሔ በአብዛኛው እየፈለቀ ያለው ችግሩን በቅርበት ከሚያውቁ ባለሙያዎች አካባቢ ነው:: ባለሙያዎቹ ከብዙ ጥረት በኋላ ልፋታቸው ፍሬያማ እየሆነ የመፍትሔ ሃሳብ ይዘው ቀርበዋል:: ከ‹‹ብሉ ኸልዝ ኢትዮጵያ›› መሥራቾቹ ዶክተር ኤልያስ ታደሰና ሦስት ጓደኞቹ ሥራ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው::
‹‹ብሉ ኸልዝ ኢትዮጵያ›› የመጀመሪያ ርዳታ ለመስጠት ታልሞ የተቋቋመ ድርጅት ነው:: ከድርጅቱ መሥራቾች መካከል ሦስቱ የሕክምና ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ አንደኛው የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ባለሙያ ነው:: ለ12 ቋሚና ለ20 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል፣ ሥራዎቹን እያሰፋ ሲሄድ ደግሞ ለተጨማሪ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዷል::
ዶክተር ኤልያስና ሁለቱ ጓደኞቹ የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪዎች ሳሉ ነው በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች የመጀመሪያ ርዳታ መስጠት የሚለው ሃሳብ በውስጣቸው ማደር የጀመረው:: የሥራውን ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉትም ከአዲስ አበባ ከተማ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት በምትገኘው ሐረር ከተማ አንድ ሆስፒታል ነው:: በወቅቱ በተለያዩ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎች ቀጥታ እነርሱ ወደሚሠሩበት ሆስፒታል ይመጡ ነበር::
እነ ዶክተር ኤልያስ በቀላል አደጋ የተጎዱ ሰዎች ጭምር ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ይመለከታሉ:: አደጋው በደረሰበት አካባቢ ላይ ተጎጂዎቹ የሚረዳቸው ሰው ስለሌለና የሚሰጣቸው የመጀመሪያ ርዳታም ትክክል ባለመሆኑ የተነሳ በትንሽ አደጋ የሰዎች ሕይወት እንደዋዛ ሲያልፍ መመልከት የዘወትር ገጠመኛቸው ነበር::
የብሉ ኸልዝ ኢትዮጵያ መሥራችና ከፍተኛ ኦፕሬሽን ኦፊሰር ዶክተር ኤልያስ ታደሰ እንደሚለው፤ የሰዎችን ሕይወት በቀላሉ ማትረፍ ሲቻል በአካባቢው ላይ የመጀመሪያ የሕክምና ርዳታ የሚሰጥ ሰው ባለመኖሩ ሳቢያ ሆስፒታል ሳይደርሱ የብዙዎች ሕይወት የሚያልፈባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም::
በተለይ በአንድ አጋጣሚ አንዲት ነፍሰጡር በመኪና ተገጭታ ወደ ሆስፒታል ሲያመጧት በአያያዛቸው ትክክል አለመሆን ሳቢያ አከርካሪ አጥንቷ ላይ ክፉኛ ጉዳት በመድረሱ ሆስፒታል እንደ ደረሰች ሕይወቷ ማለፉን ያስታውሳል:: ይህን አጋጣሚ ከአእምሯቸው ቶሎ ማውጣትና መርሳት አልተቻላቸውምና ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ መወያየትና መመካከር መጀመራቸውን ዶክተር ኤልያስ ይገልጻል::
እነ ዶክተር ኤልያስ ችግሩን የሚቀለብሱበትን መንገድ ፍለጋ ሲሉም የተለያዩ ጽሑፎችና ጥናታዊ ሥራዎችን አነበቡ:: በዚህም ታዳጊ የሚባሉ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ሰዎች በአደጋ የሚሞቱበት ሁኔታ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ተረዱ:: የመጀመሪያ ርዳታ ለመስጠት የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል ባለመኖሩ አደጋ ሲከሰት መጀመሪያ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ በቂ ግንዛቤ እንደሌለ ተረዱ::
ይህ መነሻ አድርገው ባካሄዱት ጥናትም አደጋዎች ሲደርሱ ሰዎች የመጀመሪያ ርዳታ ለመስጠት ይቅርና ወዲያውኑ የሌሎችን እገዛ ማግኘት የሚያስችሏቸው ስልክ ቁጥሮችን እንኳ እንደማያወቁ መረዳት መቻላቸውን ያብራራል::
ዶክተር ኤልያስ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ እንዳብራራውም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በትራፊክ አደጋ ብቻ በየቀኑ አስር ሰዎች ይሞታሉ:: አንድ በማንቸር ዩኒቨርሲቲ ላይ የተሠራው ጥናት ደግሞ ተጎጂዎች የመጀመሪያ ርዳታ የሚሰጣቸው ሰው ቢያገኙ በአደጋው የሚሞተውን ሰው ብዛት በ60 በመቶ ያህል ማስቀረት እንደሚቻል ያመለክታል:: ይህም በአደጋ በየቀኑ ሊሞቱ ከሚችሉ አስር ሰዎች መካከል የስድስቱን ሕይወት ማትረፍ እንደሚቻል ያስገነዘባል::
ይህን ጥናት መነሻ በማድረግም በአደጋ ምክንያት ሊሞት የሚችለውን ሰው በመታደግ የሚከሰተውን የሞት መጠን ለመቀነስ በማሰብ ወደ ሥራ እንደገቡም ይገልጻል:: ይህን ውጥናቸውን ለማሳካትም የመፍትሔ ሃሳብ ያሉትን ይዘው መምጣታቸውን ይናገራል::
ከአራት ዓመታት በፊት ይህን ሃሳብ ይዘው ወደ ሥራ ሲገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት የመጀመሪያ ርዳታን የተመለከቱ ሥልጠናዎች መስጠትና ‹‹ደራሽ›› የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ መሥራት ነበር:: ከዚያም ብሉ ኸልዝ ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት አቋቁመው መሥራት ጀመሩ::
ድንገተኛ አደጋ በሚያጋጥም ጊዜ ደራሽ በተሰኘው መተግበሪያ በመመራት ርዳታውን መስጠት ይቻላል:: መተግበሪያው በአደጋ ጊዜ ወደ ማን መደወል እንዳለበት፣ አምቡላንስ እስከሚመጣ ምን ማድረግ እንደሚገባ ወይም ደግሞ በአቅራቢያው በምን ያህል ርቀት ላይ ሆስፒታል እንደሚገኝ የሚጠቁሙ መረጃዎችን ይዟል:: የመጀመሪያ ርዳታ ሥልጠናዎች ለጤና ባለሙያዎች፣ ለተቋማት ሠራተኞች እና ለኅብረተሰቡ ለመስጠት በሚያስችሉ ሁኔታዎችም ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል::
ዶክተር ኤልያስ እንዳለው፤ የሞባይል መተግበሪያው አራት ዋና ዋና ጉዳዮችን ይዟል:: የመጀመሪያው ባካሄዱት የዳሰሳ ጥናት አደጋ ቢያጋጥም ለጥናቱ የተመረጡ ሰዎች የሚያውቁትን የአምቡላንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ስልክ ቁጥር እንዲጠቁሙ ማድረግ ነበር፤ ለእዚህም ስልክ ቁጥር ከተጠየቁ ከሶስት ሺ ሰዎች መካከል ትክክለኛውን የስልክ ቁጥር የሰጡት ስድስት ያህሉ ብቻ ነበሩ:: ይህም አደጋ ሲያጋጥም የሚደወልለትን የአምቡላንስ ስልክ ቁጥር የማያውቁ ብዙ ሰዎች እንዳሉ አመላክቷል::
ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ መተግበሪያው የሀገሪቱ የመንግሥትም ሆኑ የግል አምቡላንሶችን ስልክ ቁጥሮች በአንድ ላይ በማቀናጀት ሰዎች በቀላሉ እንዲያውቋቸውና ማግኘት የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲይዝ ተደርጓል::
ሁለተኛው ደግሞ አምቡላንሱ አደጋ የደረሰበት ቦታ እስኪደርስ እንዲሁም ተጎጂው (እየደማ ያለ ሰው ሊሆን ይችላል፤ ትንታ ያጋጠመው ሊሆን ይችላል) ሆስፒታል እስኪወሰድ ድረስ ምን መደረግ እንዳለበት እና እንደሌለበት የሚያመላክቱ 25 የሚጠጉ የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ችግሮችን በመመረጥ በሦስት ቋንቋዎች (በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዘኛ) በመተግበሪያ እንዲጠቆሙ ተደርጓል:: በጽሑፍ፣ በቪዲዮና በኦዲዮ ጨምር አማራጮች የቀረቡበትና ኅብረተሰቡ በቀላሉ እንዲያውቃቸውና እንዲማርባቸው የሚያስችል ሁኔታ የተፈጠረበት ነው::
በተጨማሪ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ‹‹ቻት›› የተገጠመለት በመሆኑም፣ አደጋ ሲያጋጥም ‹‹ቻቱ›› ላይ በመግባት መልዕክት የሚልኩበትና ምን ማድረግ እንዳለባቸው መረጃ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቷል:: ይህን በመጠቀም አደጋ ለደረሰበት ሰው ርዳታ መስጠት እንደሚቻልም ዶክተር ኤልያስ አመልክተዋል::
ሦስተኛው አንድ ሰው በአጋጣሚ ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች አካባቢዎች እያለ ድንገተኛ አደጋው ከደረሰ ወይም ሕመም ቢያጋጥመው ያለበትን አካባቢ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ክሊኒኮችና ፋርማሲዎች ሙሉ አድራሻ ማግኘት የሚችልበትን መረጃ ይጠቁማል::
ዶክተር ኤልያስ እንዳብራሩት፤ የመጀመሪያው የ‹‹ደራሽ መተግበሪያ›› ከሦስት ዓመት በፊት የተለቀቀ ቢሆንም፣ ሁለተኛው ደግሞ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርጎለት በአዲስ መልኩ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ተደርጓል:: በመጀመሪያው መተግበሪያ ላይ የማስተዋወቁ ሥራ በደንብ ስላልተሠራ ያሉት አንድ ሺ ያህል ተጠቃሚ ብቻ ናቸው ያለው ዶክተር ኤልያስ.፣ ሁለተኛው ከተጠቃሚዎች የተለያዩ ግብረ መልሶችን በመሰብሰብ ተስተካከሎ የተሠራ በመሆኑ አሁን ላይ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው:: ይህም ለብዙ ሰዎች ተደራሽ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል ብሏል::
ሥራው ሲጀምር ሃሳቡ አዲስ እንደመሆኑ በአንድ ጊዜ በቀላሉ ኅብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ ለመሆን ችግር ተፈጥሮ እንደነበርም ዶክተር ኤልያስ አስታውሷል:: ‹‹የመጀመሪያ ርዳታ ማማር ለኔ ምን ይጠቅማኛል፤ ከአደጋ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንጂ›› የሚሉና የመሳሰሉት አስተያየቶች ይሰጡ እንደነበር አስታውሶ፣ አሁን ላይ ግን ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን አመልክቷል:: ኅብረተሰቡ ስለመጀመሪያ ርዳታ እንዲያወቅ በማድረግ ተደራሽነት ለማስፋፋት ትኩረት አድርገን እያስተዋወቅን እንገኛለን›› ሲልም ተናግሯል::
‹‹ደራሽ እንሁን›› የሚል የስድስት ሰዓት ዘመቻ በመገናኛ ፣ ሜክስኮ፣ አራት ኪሎ፣ አያት፣ የካ አባዶ አካባቢዎች የመንገድ ላይ ትምህርት መስጠቱንም አስታውቋል:: ይህን ሥልጠና የሚሰጡትም ሥልጠናውን አስቀድሞ የተከታተሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በመንገድ ዳር ትምህርቱ ‹‹ኅብረተሰቡ በጣም ጓጉቶ ይከታተል እንደነበርም አስታውሷል:: በዚህም ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን ማወቅ ስጀምሩ በደንብ እየጠየቁ ብዙ ለመረዳት ሲሞክሩ መመልከት መቻሉንም አስታውቋል:: አቅልለው ሲመለከቱት በነበረው ላይ በተሰጣቸው ሥልጠና ድንገተኛ አደጋ የገጠመውን ሰው ሕይወት ያተረፉ ሰዎች እንዳሉም ዶክተር ኤልያስ ጠቅሷል:: እነዚህ ሰዎች ከዚያን ጊዜ አንስቶም ለጉዳዩ የበለጠ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸውልናል ሲልም አመልክቷል:: ኅብረተሰቡ ለጉዳዩ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን አስመልክቶ፣ ይህም በጉዳዩ ላይ ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራትን እንደሚጠይቅ ተናግሯል::
የድርጅቱ ከፍተኛ ኦፕሬሽን ኦፊሰር ዶክተር ኤልያስ እንደገለጸው፤ ድርጅቱ ከበርካታ ሆስፒታሎችና ሌሎች የጤና ተቋማት ጋር በትብብር ሥልጠናዎችን ይሰጣል:: እስካሁን ለ15ሺ የጤና ባለሙያዎች፣ ከኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ ማዕድን ላይ ለሚሠሩ ድርጅቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ከሌሎችም ብዙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሠራተኞቻቸው ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል:: ለሰልጣኞች ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርተፊኬትም ይሰጣል::
ድርጅቱ ከጤና ሚኒስቴር ፈቃድ ያገኘ ሲሆን ከ‹‹አሜሪካ ኸርት አሶሴሽን›› ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ፍቃድ ማግኘቱን አግኝቷል:: በተለይ በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርተፊኬት እንደሚፈልጉ ጠቅሶ፣ ድርጅቱም ይህንንም ታሳቢ አድርጎ እንደሚሠራ ይገልጻሉ:: ለአብነትም በቴሌኮም ተቋማት ሳፋሪካምና ሕዋዌ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ሠራተኞችም እንዳሉ በመጥቀስ፣ ሠራተኞቹ ሥልጠናውን ካገኙ በኋላ ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት እንደተሰጣቸው አመላክቷል::
ድርጅቱ ገቢን የሚያመነጨው በሚሰጣቸው ሥልጠናዎችና በሚሠራቸው ጥናታዊ ጽሑፎች መሆኑን የገለጸው ዶክተር ኤልያስ፤ ‹‹ከደራሽ መተግበሪያ›› ምንም ዓይነት ገቢ እንደማያገኝና የመተግበሪያው ዋና አላማ ሰዎች ስለመጀመሪያ ርዳታ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ መሆኑን ያስረዳል::
ለሥልጠናው ክፍያም እንደየሥልጠናው ዓይነት ልዩነት እንዳለው ጠቅሶ፤ ለተማሪዎች የሚሰጠው ሥልጠናና ለድርጅት ሠራተኞች የሚሰጠው ሥልጠና ተመሳሳይ እንዳልሆነ ይገልጻል:: ለሁሉም ግን ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ሥልጠና እንደሚሰጥ ያመላክታል::
‹‹ወደዚህ ሥራ ስንገባ ሃሳቡን ወደ አንድ በማምጣት በተግባር ለመተርጎም ብዙ አልተቸገርንም›› የሚለው ዶክተር ኤልያስ፤ ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ያለው ቢሮክራሲ ግን በጣም ፈታኝ እንደነበር አጫውቶናል:: ተግዳሮቶቹን ለመፍታት ብዙ ጥረቶች አድርገው አሁን ላሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ተናግሯል::
ድርጅቱ እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስተግራም፣ ቴሌግራም፣ ቲክ ቶክ፣ ሊንክዲን እና ዩቲዩብ በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ጠቃሚ መረጃዎችንና አስተማሪ ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ኅብረተሰቡ እንዲማር ያደርጋል:: በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው ዘጠነኛው የኢትዮ ኸልዝ አውደ ርዕይ ላይም በመገኘት ሥራውን አስተዋውቋል::
አውደ ርዕዩ የድርጅቱን ሥራዎች በደንብ በማስተዋወቅ መለያ (ብራንድ) ለመፍጠር የተቻለበት መሆኑን ዶክተር ኤልያስ አስታውቋል:: ለጤና ባለሙያዎች የሚሰጣቸውን የሥልጠና ዓይነቶች ተመልክተው አብረው ለመሥራት ከሚፈለጉ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉንም አስታውቋል::
በተመሳሳይ ‹‹ደራሽ›› የተሰኘውን ተሻሽሎ የተሠራ መተግበሪያ ለማስተዋወቅ አውደ ርዕዩ እንደጠቀማቸው ተናግሮ፣ አውደ ርዕዩን ከጎበኙ ብዙ ሰዎችና ድርጅቶች ገንቢ አስተያየቶች ማግኘት መቻሉንም ይገልጻል::
ዶክተር ኤልያስ እንዳስታወቀው፤ ድርጅቱ በቀጣይ ‹‹ደራሽ 3ፖይንት ዜሮ›› በሚል በማሻሻል ሦስተኛውን መተግበሪያ ለመሥራት እየሠራ ነው:: ይህም ተጠቃሚ ግብረ መልሶችን በመሰብስብ ኅብረተሰቡ በቀላሉ እንዲጠቀምበት በሚያስችል መልኩ ይዘጋጃል:: ድርጅቱ በባህር ዳር፣ ሸኪሶ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሳና አዳማ ከተሞች ላይ እየሠራ ሲሆን፣ ይህን ተደራሽነቱን ወደ ሌሎች ቦታዎች ለማስፋት ይሠራል::
‹‹ሃሳብ ኖራቸው ገና ወደ ሥራው ለመግባት እየተንደረደሩ ያሉ በርካታ ጀማሪዎች እኛን የገጠመን ተግዳሮት ሊገጥማቸው ይችል ይሆናል›› የሚለው ዶክተር ኤልያስ፤ ይህንን አውቀው በመታገል እጅ ሳይሰጡ ዓላማቸውን ከግብ ማድረስ እንዳለባቸው መክሯል::
የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ጀማሪዎች በተገኘው አጋጣሚ ይህን ሃሳባቸውን ለማውጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲል አስገንዝቦ፣ ተግዳሮቶችን ወደኋላ የሚመልሷቸው ብቻ አርገው መመልከት እንደሌለባቸው፣ የሚማሩባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መረዳት እንዳለባቸው ጠቁሟል:: ባይሳካላቸው እንኳ ተስፋ ሳይቆርጡ የተሻለ ነገር ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግሯል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም