‹ሁለቱ የአፅዋማት ወቅቶች መግጠም ለኢትዮጵያ ትልቅ በረከት እና ጸጋ ነው›› – ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሀፊ

አዲስ አበባ፡– የዐብይ ፆምና የረመዳን ፆም ወቅቶች መግጠማቸው ለኢትዮጵያ ትልቅ በረከት እና ጸጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሀፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለፁ። ለእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውንም አስተላለፉ።

ዋና ፀሀፊው ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ የአማኞች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የእነዚህ አፅዋማት ወቅት መግጠም እንደሀገር ትልቅ በረከትና ፀጋ ነው። በነዚህ ወቅቶች በጎ ሥራ ይበዛል፣ ክፉ ሥራ ይጠፋል፤ ሁሉም ቅን ያስባል።

መስጠት፣ ማካፈል፣ ማብላት ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ በኢፍጣርና በመሳሰሉት ማዕድ ማጋራት የሚ በዛበት ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል። የሚፆሙት የማይ ጾሙትን ሳይተቹ፣ የማይጾሙትም የሚፆሙትን ሳይተቹ ቢቻል በጋራ እየጾሙ ለፈጣሪ ራሳቸውን ቢያስገዙ መልካም መሆኑን አመልክተዋል።

አሁን ያለንበትን ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግር ራስን ለፈጣሪ በማስገዛት እንደሚፈታ አስረድተዋል። አማኞች የየእምነታቸውን አስተምህሮ በመጠበቅና በመተግበር መጾም እንዳለባቸው ገልፀው፤ በጎ ነገርን ሁሉ በማድረግ ወቅቱን በጋራ መሻገር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

መፆም ከምግብና ከውሃ ብቻ ሳይሆን ከክፉ ነገር መቆጠብን እንደሚጨምር አመልክተዋል። ወቅቱ የማይስማሙ የሚስማሙበት፣ ጦርነት ውስጥ የገቡ ሰላም የሚፈጥሩበት፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት የምንች ልበት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነቶች በተለይ ረመዳን ጾምን በማስመልከት እንደሚቆሙ አስታውሰውዋል። የጾም ወቅት የጥይት ድምፅ ሊሰማበት እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡

የዐብይ ፆም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቁ ፆም የሆነበት ምክንያት ራሱ እየሱስ ክርስቶስ ለአርባ ቀንና ለአርባ ሌሊት በመጾሙና ዲያብሎስን በማሸነፉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከሰባት ዓመት ህፃን ጀምሮ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች እንደሚጾሙ፤ ክርስቶስ አርባ ቀኑን ከጾመ በኋላ ታመመ፤ አባቶቻችንም እርሱ እየታመመ እኛ ልንበላ አይገባም በሚል ህማማቱን ጨምሮ በአጠቃላይ 55 ቀናት እንዲጾም አደረጉ ብለዋል።

ታላቁ የረመዳን ጾምም በተመሳሳይ በእስልምና እምነት አስተምህሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመው ፤ መላው የእስልምና እምነት ተከታይ ከትንሽ እስከ ትልቅ እንደሚጾመው ገልፀዋል።

የታላቁ ረመዳን ወር ቅዱስ ቁርዐን የወረደበት፣ ሰይጣን የሚታሰርበት፣ መልካም ነገር የሚደረግበት፣ ዘካ የሚወጣበት፣ የእምነቱ ተከታይ ሁሉ በጎ ነገር የሚያደርግበት የራህመት ወር መሆኑንም ጠቁመዋል። ለሁለቱ እምነት ተከታዮችም ለዐብይ ጾም እንዲሁም ለታላቁ ረመዳን ጾም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You