የዓድዋ እና የጉባ ድል

አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት፣ ሀብቷን ለመመዝበርና በሕዝቦቿ ጫንቃ ላይ የባርነት ቀንበርን ጭነው ያሻቸውን ለማድረግ በማሰብ ያላቸውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያና የሠለጠነ የሰው ኃይል ይዘው ወረዋታል:: አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራትም በወቅቱ የመጣባቸውን ወራሪ ኃይል መቋቋም የሚያስችል አቅም ስላልነበራቸው ሳይወዱ በግድ የቅኝ ገዢዎች ሰለባ ሆነዋል::

የባርነት ቀንበር በጫንቃቸው ላይ ወድቆ በገዛ ሀገራቸው ምንም አይነት መብት እንዳይኖራቸው ተደርገዋል:: ከሚመዘበረው ሀብታቸውና ከሚደርስባቸው መከራ ባሻገርም ወደ ሌሎች ሀገራት ሳይቀር በባርነት ተግዘዋል፤ የራሳቸውን ማንነት ትተው የየገዢዎቻቸውን ቋንቋና ባሕል የማወቅ ግዴታም ተጥሎባቸዋል::

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር በዋሉበት በዚያን ወቅት አባቶቻችን ክብራቸውን እና የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አሳልፈው ላለመስጠት ከመጣባቸው ወራሪ ጋር ተጋፍጠው በብርቱ ትግልና በታላቅ ድል ነፃነታቸውን አስከብረዋል:: ድፍን አፍሪካውያንን ያኮራና ያደመቀ ድልንም ተቀዳጅተዋል:: ዛሬ ላይ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡበትን ቀን ሲያከብሩ ኢትዮጵያ በአንጻሩ የድል ቀኗን የምታከብር ብቸኛ ሀገር ለመሆን በቅታለች::

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ባስመዘገበችው ድል የራሷንም የጥቁር ሕዝቦችንም ዓርማ ከፍ አድርጋ ያውለበለበችበት እለት ነው:: ይህ ቀን አባቶቻችን ብዙ ማይልስ ተጉዞ፤ ውቅያኖስ አቋርጦ፤ የመጣውን ፋሺስት በዓድዋ ተራሮች አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ዓለምን ያስደመመ ታሪክ የጻፉበት ነው::

ድሉ ለአፍሪካ ሕዝቦች በሙሉ ታላቅ የምሥራች የፈጠረ ሲሆን በሌላ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች በነጮች የተሸነፉበት በመሆኑ አውሮፓውያንን ያስደነገጠ ነበር:: ያውም ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀ እና የሠለጠነ ተዋጊ ያለውን ኃይል:: ድሉ ጥቁሮች ለነጮች ተንበርክከው መኖር እንደማይችሉ ያሳየና ያስተማረም ተደርጎ ይታያል::

ምንም እንኳን የሌሎች የአፍሪካውያን ቁስል የእኛም ቁስል ሆኖ ቢያመንም እድሜ ለአባቶቻችን ተጋድሎና ለዓድዋ ድል ይሁንና፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ነፃነታችንን ያረጋገጥንበትን፤ ታዋቂነትን ያተረፍንበትን ታላቅ ድል አግኝተናል፤ የድላችን ወጋገንም በመላው አፍሪካ፣ በካሪቢያን ደሴቶች እና ጥቁር ሕዝቦች በሚኖሩበት የዓለም ዳርቻ ሁሉ አብርቷል::

የዓድዋ ድሉ ለአፍሪካውያን ወጋገን ከመሆንም አልፎ ነፃ ያልወጡ ሀገራት አዲስ ንቅናቄ እንዲያደርጉና የይቻላል መንፈስን እንዲሰንቁ መነሳሳትን ፈጥሯል፤ ለፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ መጀመርም መንስዔ ሆኗል:: ምዕራባውያን ለበርካታ ዓመታት በጥቁሮችና በሌሎች ጭቁን ሕዝቦች ላይ የገነቡት የበላይነት አስተሳሰብም እንዲሸረሸር አድርጓል:: በአውሮፓውያን ወረራ አንገታቸውን ሰብረውና ተሸማቀው የነበሩ ሌሎች አፍሪካውያንም ተስፋና ክብር እንዲሰማቸው ሆኗል:: ያም ብቻ ሳይሆን የተጫነባቸውን የባርነት ቀንበር ከትከሻቸው ላይ ለመጣል እንዲያምጹ በር ከፍቶላቸዋል::

የዓድዋ ድል አባቶቻችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ላለማስደፈር፤ ነፃነታቸውን ለማስከበር፣ እኩልነትን ለማስፈን እና ሰላምና ደኅንነት የሰፈነባትን ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ሲሉ በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ ደማቅ ድል ነው፤ ኢትዮጵያ በከፍታ ማማ ላይ እንድትቀመጥና የአፍሪካ ምሳሌ እንደትሆንም አድርጓታል::

ኢትዮጵያ ወሰኗን ማስከበሯን ተከትሎ ሦስት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በቅኝ ግዛት ያስተዳድሩ የነበሩ የአውሮፓ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በሚጋሯቸው ድንበሮች የወሰን ስምምነት ለመፈራረም ተገድደዋል:: ከነዚህ ውስጥ አንዷ ራሷ ጣሊያን መሆኗ ደግሞ እንደተጨማሪ ድል የሚታወስ ነው:: ጣሊያን ኢትዮጵያን ልትወር ሞክራ በዓድዋ ጦርነት ከባድ ሽንፈት ካጋጠማት በኋላ በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትንም የምታስመልሳት ስለመሰላት ከኢትዮጵያ ጋር የወሰን ማስከበር ሥራን በፍጥነት ለማከናወን ተገድዳለች::

ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ባገኘችው ሞገስ የአፍሪካ ሀገሮች ብቻ ሳይሆኑ አውሮፓውያን ራሳቸው ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነትን ለመመሥረት የቀደማቸው አልነበረም:: እንደ ፈረንሳይ፣ ራሺያ፣ አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገራት ኤምባሲያቸውን ከፍተዋል፤ የንግድ ትብብርም ፈጥረዋል::

ይህን ተከትሎም በአውሮፓ መታየት የጀመሩ የዘመኑ ሥልጣኔዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል:: እንደ መኪና ስልክ ባቡርን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩትም በዓድዋ ድል ማግሥት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ:: ከድሉ በኋላ አንድ ዓመት ሳይሞላ ፈረንሳይ የኢትዮ – ጂቡቲን የባቡር መንገድ ገንብታለች::

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ግርማ ሞገስ እንዲኖራትና ተሰሚነትን እንድታገኝ ካደረጋት በኋላ በብዙ የአፍሪካ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ተዋናይ እንድትሆን አስችሏታል:: በዚህም የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሠረት የመሪነት ሚናን ተጫውታለች፤ የኅብረቱ መቀመጫ እስከመሆንም በቅታለች:: ቀደም ሲል በኮሪያ፣ በኮንጎ ኋላም በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን፣ በቡሩንዲ እና በሶማሊያ በተባበሩት መንግሥታት ሥር ታቅፋ ስለሰው ልጆች ሰላምና እኩልነት ስትል ጦሯን አዝምታለች::

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን የአፍሪካ ፈር-ቀዳጅ እንዳደረጋት ሁሉ እነሆ ዛሬም ይህ ትውልድ በህዳሴው ግድብ ያስመዘገበው ድል ኢትዮጵያን የልማትና የኢኮኖሚ አርበኛ በማድረግ በአፍሪካ ምሳሌ እያደረጋት ይገኛል:: የዚህ ዘመን ትውልዶችም በራሳችን አቅም ተዓምር የሚባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ገንብተን በማጠናቀቅ ለኢኮኖሚ እድገታችን ለማዋል እየታተርን እንገኛለን::

የዓድዋ ድል ለጥቁርና ለተጨቆኑ ሕዝቦች የትግል ተስፋ እና አቅም እንደነበረ ሁሉ አሁንም በዓባይ ወንዝ ላይ የሠራነው ግድብ ለተፋሰሱ ሀገራትና የውሃ ሀብታቸውን በአግባቡ ላልተጠቀሙበት የአፍሪካ ሀገራት በሙሉ በምሳሌነት የሚጠቀስ ታላቅ ድል ነው:: የህዳሴው ግድብ ድል ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብቷን ያረጋገጠችበትና እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራትም አርዓያ የሆነችበት የዚህ ዘመን ትውልድ ያስመዘገበው እንቁ ድል ነው::

ጣሊያን ኢትዮጵያን የመውረር ሙከራ ስታደርግ ዓፄ ምኒልክ አማላጅ እየላኩ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ብዙ ጥረዋል:: ግን ሰሚ አላገኙም ፤ አውሮፓውያን በበርሊኑ ጉባኤያቸው የአፍሪካን ካርታ ዘርግተው አሕጉሪቱን በተቀራመቷት ጊዜ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በጣሊያን እጅ እንዲወድቅና ጉዳይዋ በሙሉ በጣሊያን እንዲወሰን የተስማሙት በመተማመን ነበር:: ለምን ትወረራለች ብሎ ከኢትዮጵያ ወገን የቆመ አንድም የአውሮፓ ሀገር አለመኖሩ የዚህ ማረጋገጫ ነው::

ኢትዮጵያ የጣሊያንን ጦር መክታ ትመልሳለች የሚል ግምት ቢኖራቸው ኖሮ ጣሊያኖች ያን ያህል ማይልስ ተጉዘውና ባሕር አቋርጠው ባልሞከሩንም ነበር:: ግን የሀገር ወዳድ ሕዝቦቿን አይደፈሬነትና ጀግንነት በዓድዋ ድል አረጋግጣለች:: የዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ያንቀሳቀሰ ነበር፤ ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በጦርነቱ ሰዓት ሀገሬው ጠላቱን አሳፍሮ ወደ መጣበት ለመመለስ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል::

አቅም ያለውና መዋጋት የሚችለው ሀገር ወዳድ ዜጋ ጥቂት የሚባሉ ኋላ ቀር መሣሪያዎችንና እንደ ጎራዴና ጦር የመሳሰሉ ባሕላዊ መሣሪያዎችን ይዞ ግንባር ለግንባር ገጥሟል፤ የጦር አመራሮች በእቅድና በተናበበና መልኩ ጦሩን መርተዋል፤ ሴቶች ከተዋጊው ስር ስር እየሄዱ ምግብ በማዘጋጀትና ስንቅ በማቀበል አገልግለዋል፤ ቁስለኛ ሲያነሱ የነበሩት፣ ቀለብ ሲያጓጉዙ የነበሩት፤ በዘፈንና በቀረርቶ ሞራል ሲሰጡ የነበሩ አዝማሪዎች፤ ሌላው ቀርቶ ቀለብ የጫንባቸው የነበሩ እንስሳት ሳይቀሩ ለተገኘው ድል የየራሳቸውን አስተዋፅዖ ስላበረከቱ ሁሉም የድሉ ባለቤቶች ናቸው:: የዓድዋ ድል የብዙዎች ተሳትፎና ርብርብ የታየበት፤ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚለው የአባቶቻችን ብሂል በትክክል የተተረጎመበት ነው::

ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት በጉባ ተራሮች ግርጌ የመሠረት ድንጋይ ስታስቀምጥና በራሷ የገንዘብ አቅም ጀምራ እንደምትጨርሰው ይፋ ስታደርግ፤ ብዙዎች ትወጣዋለች የሚል ሀሳብ አልነበራቸውም:: ይህ ደግሞ ከንቀት የመነጨ አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት አይከብድም::

የአሁኑ ትውልድም አባቶቹ በዓድዋ ጦርነት ያሳዩትን ትብብርና አንድነት በአግባቡ ተጠቅሞ በጉባ ተራሮች ግርጌ ሌላ ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ዳግማዊ ድል አስመዝግቧል:: የዓድዋ ድል ለእኩልነት ለነፃነት ለፍትሕ፣ ለሰላምና ለሉዓላዊነት በተሰባሰቡ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውን ተጋድሎ የተገኘ ድል ሲሆን በጉባ ተራሮች ግርጌ የተመዘገበው የህዳሴው ግድብ ድል ደግሞ የኢኮኖሚ እድገትን አረጋግጠው ከድህነት ለመውጣት በሚሹ ትውልዶች ክንድ የተገነባ ነው::

የዓድዋ ድል ጥቁሮችን አስደስቶ ነጮችን እንዳስኮረፈ ሁሉ የህዳሴው ግድብም አፍሪካውያንን ያስደሰተና ተስፋ የሰጠ፤ የኢትዮጵያን እድገትና መለወጥ የማይፈልጉትን ያስኮረፈና ያስደነገጠ ነው:: ለዚህም ከሰሞኑ የአፍሪካ የውሃ ሚኒስትሮች የህዳሴውን ግድብ እንዲጎበኙና የኢትዮጵያን እውነታ እንዲያረጋግጡ የተደረገላቸውን ግብዣ ግብፅ ማውገዟ ኩርፊያዋንና ድንጋጤዋን የሚያሳይ ነው:: ልክ እንደግብፅ ሁሉ ሌሎች ደስ የማይላቸው አካላት መኖራቸውም የማይቀር ነው:: በአንጻሩ አፍሪካውያን የውሃ ሚኒስትሮች የህዳሴውን ግድብ ካዩ በኋላ ደስታቸውን ገልጸዋል፤ የራሳቸውን የቤት ሥራም ይዘው ሄደዋል::

በህዳሴው ግድብ ላይ ልክ እንደ ዓድዋ ጦርነት ሁሉ የሀገሪቱ ዜጎች ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተሳትፎ አድርገዋል፤ ተማሪዎች ከደብተር መግዣቸው፣ ሠራተኞች ከደመወዛቸው፣ ነጋዴዎች ከወረታቸው፣ አርሶ አደሮች ከበረከታቸው፣ እናቶች ከመቀነታቸው ያላቸውን በመስጠት ግድቡ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ብርቱ ርብርብ አድርገው የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ አድርሰውታል::

የዓድዋ ድል በመላው አፍሪካ ብርሃን እንደፈነጠቀ ሁሉ የዓባይ ግድብም እንዲሁ ከሀገር ያለፈ ተስፋን ፈንጥቋል:: ኢትዮጵያ ታላላቅ ወንዞቿን ገንብታ ለልማትና ለኢኮኖሚ እድገት ማዋሏ ለሌሎች አፍሪካውያን ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ አንድ ነገር ነው:: የዓድዋ ድል የአፍሪካ ሀገራትን አንድነትና ትብብር እንዳጠናከረ ሁሉ ከህዳሴው ግድብ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይልም በኢነርጂ ዘርፍ የተጀመረውን ቀጣናዊ ትስስር የበለጠ በማጠናከርና በማስፋፋት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው::

ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ እንደመኪና፣ ባቡር፣ ስልክ፣ መብራት የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ሀገሯ እያስገባች ለሕዝቦቿ አስተዋውቃለች፤ ዘመናዊ ትምህርትም አስጀምራለች:: በዚህም የሥልጣኔ ሽግግር አድርጋለች:: አሁንም ከህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት የኢኮኖሚ አቅሟን የምታሳድገበት ዕድል ፈጥራለች::

በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን ለማረጋገጥ ከውጭ ጣልቃ ገቦችና ፍትሕን ከማያውቁ ምዕራባውያን እንዲሁም ወንዙን በብቸኝነት እንጠቀም ከሚሉ ሀገራት ጋር እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አድረገናል:: ፍትሕን፣ እውነትን፣ ርትዕን እና ኅብረትን ይዘን አሸንፈናቸዋል:: ከዓድዋ ድል በቀሰምነው ልምድ መሠረት የህዳሴ ግድባችን ድልም እነዚህን መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች እንዲመልስ አድርገናል::

ጦርነት የኋላ ቀርነት መገለጫ ነው፤ ዓለም እንደ አሁኑ ባልሠለጠነበት ዘመን ችግሮችን ለመፍታት የመጀመሪያው አማራጭ ተደርጎ የሚታየው ጦርነት ነው:: አቅም ያለው አቅም የሌለውን በጉልበት ተጭኖ የፈለገውን የሚያደርግበት አሠራር ዛሬ ላይ ተቀባይነት የለውም:: በይበልጥም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም፤ እንኳን ዛሬ ድሮም ቢሆን የማይሠራ መሆኑን የዓድዋ ጦርነት ያረጋገጠው ሐቅ ነው::

ዛሬ ከጦርነት ይልቅ ውይይትና ንግግር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው:: የራስን መብት ለማስከበር የሰውን መብት ማክበር እንደሚያስፈልግ ዓለም እየተረዳው የመጣ እውነታ ነው:: የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም ሰጥቶ የመቀበል መርሕን መከተል እንደሚስፈልግ በጽኑ ይታመንበታል:: ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የባሕር በር ጥያቄዋ መልስ እንዲያገኝ እየተከተለች ያለው ፖሊሲዋም ይሄው ነው::

አፍሪካውያን የአውሮፓ ተገዢ የሚሆኑበትና አሁንም በምዕራባውያን ዘንድ አንሰው የሚታዩበት አንዱ ምክንያት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ አለመቻላቸውና የእርዳታ ስንዴን ጠባቂ መሆናቸው ነው:: ዛሬ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ በተለይም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ለማስቀረት የበጋ ግብርናን አዲስ የሥራ ባሕሏ አድርጋ ምርታማነቷን በማሳደግ ላይ ትገኛለች:: አልፋ ተርፋም የስንዴ ምርቷን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀምራለች::

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ዐሻራ ልማቷ እያስመዘገበች ያለችው ውጤትም ይሁን ነባር ከተሞችን የማዘመን ተግባሯ እንደ አሕጉር ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው:: እነዚህ ተግባሮቿ ከህዳሴው ግድብ ድል በተጨማሪ ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሆኑና ሌሎቹም ሊከተሏቸው የሚገቡ የዚህ ትውልድ ተጨማሪ ድሎች ናቸው::

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You