
-ኢንጂነር አበራ ተስፋዬ የውሃ መሀንዲስ
በውሃ ሀብት ምህንድስና ከቀድሞ አርባ ምንጭ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከአሁኑ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ወደ ሀገረ ግብጽ አቅንተው ድህረ ምረቃ ዲፕሎማ በሃይድሮሎጂና በሃይድሮሊክስ ተምረው ያጠናቀቁ ናቸው ። በኔዘርላንድ በሚገኘውና በዩኔስኮ- አይ.ኤች.ኢ የውሃ ትምህርት ኢንስቲትዩት በሃይድሮኒክስ ኢንጅነሪንግ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል ።
የተለያዩ ሀገራት ላይ በመዘዋወርም ዘላቂ የልማት ግቦችን በሚመለከትና በውሃ ዘርፍ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል። በሥራቸውም ዓባይን ከምንጩ እስከ ፍጻሜው (መዳረሻው) የሚያውቁና በምርምር ሥራቸው ውስጥ ያካተቱ ናቸው ። ከውሃ ጋር በተያያዘ በቀድሞ የሸለቆዎች ልማት ጥናት ባለሥልጣን በሃይድሎጂስትነት ሠርተዋል። አስዋን ግድብ ድረስም በመዝለቅ የተለያዩ ትምህርታዊ ጉብኝቶችን አድርገዋል የዛሬው የልዩ እትም እንግዳችን ኢንጂነር አበራ ተስፋዬ ። እኛም በዓባይ እና ከዓባይ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ ሲባል ወደ አዕምሮዎ ቀድሞ የሚመጣው ምንድነው?
ኢ/ር አበራ፡- እንዲህ አይነት አጋጣሚዎችን አግኝቶ ስለ ውሃ ምህንድስናው ማውራት በእጅጉ መታደል ነው። ለእኛ ለውሃ ባለሙያዎች እንድንተነፍስበት እድል ይሰጠናል ። ከዚህ አንጻርም እኔ ስለዓባይ ሳነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው የቀድሞ የሸለቆዎች ልማት ጥናት ባለሥልጣን ውስጥ የተሠራው ጥልቅ ሥራ ነው። ሃይድሮሎጂስት ሆኜ እሠራ ነበርና አሁን ግድቡ የሚሠራበት ቦታ ላይ ጥልቅ ጥናት ተደርጓል። በዚህም ብዙዎቻችን ድካማችን መቼ ፍሬ ያፈራ ይሆን እንል ነበር። ወንዞቻችንን መጠቀም አለመቻላችንም ቁጭት ይፈጥርብን ነበር ።
አይነኬ የሚመስል፤ ብዙ ጫና የነበረበትና የሚሳካ የማይመስለው ነገር ግን ዛሬ እውን ሆኖ ስመለከተው እጅጉን ያስደስተኛል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉዳዩ በጣም ደስተኛ ቢሆንም ለውሃ ባለሙያዎች ግን ደስታው የተለየ ነው። የእኛ ደስታ እጥፍ ድርብ ትርጉም ያለው ነው ። ምክንያቱም በውስጣችን ያመቅነውን የመልማት ጉጉት እውን እንድናደርገው እድል የሰጠን ነው ። ሌሎች ወንዞቻችንንም እንዲለሙ አቅጣጫ እንድናመላክት በር የከፈተልን ነው። የመናገር ነጻነታችንንም ያረጋገጠልን። በምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ውጤታማና ደስተኛ እንድንሆንም መደላድል የሚፈጥርልን ነው ።
በወኔ ተናግረን፣ ሰዎች አድምጠውን ሀገራችንን በሁሉም ዘርፍ ስኬታማ እንድናደርግም ያግዘናል። በአጠቃላይ ዓባይን ሳነሳ በቃላት ዘርዝሬ የማልጨርሰው ስሜት ይሰማኛል። ለእኛ የውሃ መሀንዲሶችም በርካታ ጥቅሞችን የሚያጎናጽፈን ነውና ስሜቱ ቀላል አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ወንዞቻቸውን ለመጠቀም በየዘመናቱ ለፍተዋል ። የውጪ ጫናና መንግሥታት የተመቻቸ ሁኔታ ስላልተፈጠረላት ግን እውን ሊያደርጉት አልቻሉም። አሁን ግን ግንባታው ተጀምሮ እድገት አሳይቶ በሚቀጥለው ስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ሰምተናል ። አሁን ያ የቀደመው ሁኔታ አክትሟል።
ግንባታው እንደ ሀገር ትልቅ አቅም የሚፈጥር፤ እድገትን የሚያፋጥን እንደሆነ ጥርጥር የለውም ። ኃይል ማመንጨትና ለብዙዎች መትረፍ እየቻለ ነው። መጠናቀቁ ላይ በመቃረቡም ከዚያም ያለፈ ተግባር እንደሚኖረው እሙን ነው። የመጠናቀቁ ዜና ለሁሉም ልዩ ስሜት የሚጭር ነው።
በሀገራችን ያለው የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ወደ 44 በመቶ ብቻ ነው። የገጠሩ ሕዝብ አሁንም ከጨለማ አልተላቀቀም። በኩራዝና ማገዶ እየተጠቀመ ይገኛል። ይህንን ሕዝብ ከዚህ ችግሩ ለማላቀቅ ደግሞ ያለውን ሀብት ማሳየትና እንዲጠቀመው መሥራት ያስፈልጋል። ለዚህ የዓባይ ግድብ ያለው አበርክቶ ትልቅ ነው።
ከግድቡ በሚመነጭ ኤሌክትሪክ ጭለማ ውስጥ የነበሩ ዜጎች ብርሃን ያገኛሉ ። ኑሯቸውን አሻሽለው ከዘመኑ ጋር ይዋሃዳሉ ። ዜጎች ከሥራ አጥነት እንዲላቀቁ ያግዛቸዋል። ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የገቢ ምንጭ እንድታገኝ ያደርጋታል። ከጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት፣ ትስስርና ትብብር ለመፍጠርም ይጠቅማታል ። ታዲያ ይህ ሁሉ ጥቅም ደስታ በሚሉ ሦስት ቃላት ብቻ ጠቅልሎ ማቅረብ ይቻላል? እንደ እኔ ግን አይቻልም ። ስለዚህም ስሜቱ በየአቅጣጫው ሲታይ ከደስታ በላይ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ለመጠናቀቅ ጥቂት ሥራዎች የቀረው የዓባይ ግድብ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ምን ማለት ነው? ከዓድዋ ጋር ሲነጻጸርስ እንዴት ይገለጻል?
ኢ/ር አበራ፡- እንደሚታወቀው ዓድዋ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔር፤ ሃይማኖት፤ ጾታ፤ እድሜ ሳይገድበው የተሳተፈበትና በኃይሉ ነጻነቱን ያረጋገጠበት፣ ክብሩን የጠበቀበትና ሌሎች ክብርና ሞገስ እንዲሰጡት ያደረገበት ልዩ የድል በዓል ነው። ዓድዋ ነጭ ጥቁርን እንዳይንቅ ያደረግንበት ድል ነው። በተለይም ኢትዮጵያውያን የትም ሀገር ብንሄድ ያለምንም መሸማቀቅ በኩራት እንድንናገር እድል የሰጠን ነው።
በዓለም ላይ ዓባይን የመሰለ ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ፤ በራስ ባለሙያ፤ በራስ ወጪ ተሠርቶ አያውቅም። ከዚህ አንጻር ይህንን አደርጋለሁ ብሎ መነሳት ከምንም የመነጨ አይደለም። ኢትዮጵያውያን የተሠሩበት ማንነት አልችልምን የሰበረ በመሆኑ ነው ። ይህ ደግሞ የመጣው ከዓድዋ ድል በኋላ ነው ። ዛሬም ያንን ነው እያደረግን ያለነው።
ትናንት በገነባነው ማንነት ዛሬን እየኖርን ነው። ለሌሎች አፍሪካ ሀገሮችም ነጻነትን እያላበስን ነው። በዓባይ ግድብ ዓለምን ጭምር እያስደመምንና ለእርሷም ምሳሌ እየሆንን ነው። እንዴት ከተባለ በዓባይ ግድብ አረንጓዴ የኃይል አማራጭን እየገነባን እንገኛለን። ይህ ደግሞ ዓለምን በአየር ብክለት ከሚመጣ አደጋ መጠበቅ ያስችለናል ።
ዓባይን በቴክኒካል ሥራዎች ልቀን የምንታይበት፤ በኢኮኖሚያችን ከፍ የምንልበትን ነጻነት ያገኘንበት ዳግማዊ ዓድዋ ነው። በእርሱ እውን መሆን አይችሉምን ወደ ይችላሉ ቀይረናል። እንመታቸዋለን የሚሉ አካላትንም አደብ አስገዝተናል። እንደ ግብጽ አይነት ሀገራትንም ሃሳብ ማስቀየር ችለናል። የኢትዮጵያ ሃሳብ እንዲያሸንፍም አድርገንበታል።
ለዚህ መሠረቱ ደግሞ ማንነታችን በነጻነት የተገነባ መሆኑ ነው። በነጻነት የተሠራ ሰው መቼም ቢሆን አይወድቅም፤ አይሸማቀቅምም ። የጀመረውን ሳይጨርስም ወደ ኋላ አያፈገፍግም። ሁልጊዜ ለስኬቱ ይዋደቃል ። የፊቱንና እድገቱን ይመለከታልም። ሁሌ ብልፅግናውን ያስባል። አሁን በዓባይ ግድብ እየሆነ ያለውም ይህ ነው ። ቀጣይ ከዚህ የተለየ ነገር ይመጣል ብዬ አላስብም ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ግድቡን ስትጀምር ጀምሮ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን አብሮ ማደግን መርህ አድርጋ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ይሄንን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለችም። እርስዎ ከዚህ አንጻር እስካሁን የተሄደበትን ጉዞ እንዴት ያብራሩታል፤ ውጤቱስ እንዴት ይታያል?
ኢ/ር አበራ፡– በዓለማችን ላይ 276 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና 592 ድንበር ተሻጋሪ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳሏት ጥናቶች ያመላክታሉ። 40 በመቶ የዓለም ሕዝብም የሚኖረው በእነዚህ ድንበር ተሻጋሪና ሃይቆች ተጋሪ ሀገራት ውስጥ ነው። 90 በመቶ ሀገሮች እነዚህን የወንዞችና ተፋሰሶች ሃይቆች ይጋራሉ። ከዚህ አንጻርም የዓባይ ወንዝን የሚጋሩ ሀገራት አሉ ።
የወንዙ መነሻ ኢትዮጵያ ብቻ ነች ። 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ ታጋራለች ። ይህ በሆነበት። እውነታ ውስጥ አንዳንዶች ዛሬም ቢሆንም በዚህ ሀብቷ እንዳትጠቀም ይፈልጋሉ። ተጠቃሚዎቹ እኛ ብቻ ነንና መሰል ነገሮች ሲሉም ከርመዋል።
ኢትዮጵያውያን መብቱ ቢኖራቸውም ይህንን ማድረግ አልፈለጉም። ልምዳቸው፤ ባህላቸው መጋራትና አብሮ ማደግ በመሆኑ ማንም ሳይደግፋቸው ያለሙትን አብረን እንጠቀመው ሲሉ ጋበዟቸው። እነርሱ ግን ዛሬም ድረስ አልተኙም። ፍራቻ በደማቸው ውስጥ የሌለው ኢትዮጵያውያን ሴራቸውን እያከሸፉ ዛሬም ማልማታቸውን ቀጥለዋል። የራሳቸውንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ደፋ ቀና እያሉ ናቸው። አሁን ደግሞ ማብቂያው ላይ እየደረሱ ይገኛሉ።
እስከዛሬ የታችኛው ሀገራት የተለያዩ ግድቦችን ማንንም ሳያስፈቅዱ በራሳቸው ስምምነት ገንብተዋል ። በዓባይ ዙሪያ ሲሆን ግን እኛ ካልነው ውጪ አይሆንም ወደማለቱ ገብተው የተለያዩ ጫናዎችንም እያደረጉ ነው። ያለምንም ማስረጃ ዲዛይኑ ጭምር ትክክል አይደለም፤ እኛን ይጎዳናል ሲሉም ከርመዋል ። የተለያዩ ውዥንብሮችን እየፈጠሩም ሲከሱ ቆይተዋል ።
የውሃው ባለንብረት የሆነችው ኢትዮጵያ ያልገባችበት ስምምነት ሊገዛት እንደማይችል የተረዱ አይመስሉም፤ ቢረዱም አምነው ለመቀበል ፈቃደኝነት አጥተዋል። ያንን ማስረዳት የሚቻለው ሠርቶ በማሳየትና ፤ የአቅም ልካችን የት ድረስ እንደሚዘልቅ በማረጋገጥ ስለሆነ በዓባይ ግድቡ ይህንን አሳክተን አሳይተናል። በዚህ ድርጊት ደግሞ ብዙዎችን አፋቸውን አሲዘናል። ወደምምንፈልገው መስመርም እንዲመጡ አድርገናል ።
እስከ ዛሬ ባለው አካሂድ የታችኛው የወንዙ ተጋሪ ሀገራት የላይኛውን ሲጫኑ ታይቶም፣ ተሰምቶም አያውቅም። ይልቁንም በላይኞቹ ሀገራት መልካም ፈቃድ ነው ተግባራት የሚከናወኑት ። እኛ ሀገር ላይ ግን ሲሆን ተቃራኒ ትርጉም ተሰጥቶት የጫና ናዳ ሲፈስብን ከርሟል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ ። አንዱ የእድገት ደረጃችን ነው ።
ለምሳሌ፡- ግብጽ ሦስት እጥፍ የኢትዮጵያን የነፍስ ወከፍ ገቢ አላት ። ሌላው ያደጉት ሀገራት ጋር ያለን የትስስር ሁኔታና ተፈላጊነታችን ነው ። እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት ከእኛ የተሻለ እድገት ላይ መኖራቸውና የሌሎች አውሮፓና አረብ ሀገራት ድጋፍ ያላቸው መሆናቸው ጫናን እንዲፈጥሩ እድሉን ሰጥቷቸዋል ። ሆኖም ውጤቱ የተጠናቀቀው በኢትዮጵያ አሸናፊነት ነው ።
ኢትዮጵያ ልማቷን በማፋጠን ለመፍትሄው ሠርታለች። ተቀራራቢ የውሃ ተጠቃሚነት እንዲኖርም እያደረገች ትገኛለች። የዓለም ሀገራት በራሳቸው ሕግ እንዲመሩ ለማስቻልም በተለያየ መልኩ እያስገነዘበች ነው። ለአብነት ዘላቂ የልማት ግቦች ከሚባሉት መካከል አንዱ ሁሉንም ሀገራት ፍትሃዊ፤ ምክንያታዊና ሚዛናዊ የሆነ ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ማስቻል ነው። ይህ እውን እንዲሆን በምትደራደርባቸው ጊዜዎች ሁሉ አሳውቃለች ።
ያንን አልፎ የሚመጣ ካለም ለማንም እጅ ሳንሰጥ ተቋቁማ እንደምትቀጥል እያሳየች ነው። አሁንም ቢሆን መልካም ትስስራችንን በማይነካ መልኩ ዛሬ ላይ ያደረስነውን ግድብ እስከ መጨረሻው ልንደግፍና ስኬቱን ልናከብር ከምንም በላይ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የተለያዩ አካላት በተለይ ግብጽ ሰፊ ስም የማጥፋት፣ በጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ጊዜ የመክሰስ ዘመቻ ስታደርግ ቆይታለች። ያንን ሁሉ በዲፕሎማሲ ማሸነፍ ማለት ምን ማለት ነው?
ኢ/ር አበራ፡- በዓለም ላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሀይቆችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ስምምነቶች በተለያዩ ሀገሮች መካከል ተደርጓል። ከፍ ሲልም በዓለም አቀፍ ሕግ አጠቃላይ ማሕቀፍ ለመጓጓዣ ላልሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሃይቆች ለመጠቀም የሚያስችል የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ተፋሰስ ስምምነቶች በግንቦት 21 ቀን 1997 እ.ኤ.አ ተፈርሞ በነሐሴ 17 ቀን 2014 እ.ኤ.አ ወደ ሥራ የተገባበት ሁኔታ አለ። ዲፕሎማሲ ማለትም እነዚህን ሕጎች አክብሮ በእኩል ደረጃ መፈጸም መቻል ነው ።
ዲፕሎማሲ ሁሉም በእኩል ደረጃ አሸናፊ እንዲሆን ማስቻል ነው ። ከዚህ አንጻር እኩል የሚለውን በውሃ ሳይንስ መተንተንና የውሃ ዲፕሎማሲው ምን ይላል የሚለውን ማወቅ ይፈልጋል ። ከትርጓሜው በመነሳትም ወደ ተግባር መለወጥ የግድ ይላል ። በተለይም ውሃ ምህንድስናው ከሳይንስ ባሻገር በጂኦ ፖለቲክስ ዙሪያ ጥልቅ እውቀትን የሚሻ ነው፤ ያንን እያዩ መተርጎም ይገባል። ከዚህ አንጻር የነበሩን ተደራዳሪዎች እጅግ ጠንካራና የተመረጡ እንደነበሩ ማየት ተችሏል ።
በሁሉም ዘርፍ የበቁና የነቁ ምሁራንም እንደሆኑም እስከአሁን በነበሩት የዲፕሎማሲ ሥራዎች መመልከት ችለናል። ሁሌ ሳይንሱን ይዘው መተማመን ላይ ለመድረስ ተሟግተዋል። አሸንፈዋል የሚያስብሉ ውጤቶችንም አሳይተዋል። ለአብነት እንደ ግብጽ አይነት ሀገራት በየጊዜው ተለዋዋጭ ሃሳቦችን ይዘው ቢመጡም ሁሌም ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ስትቀጥል ታይቷል ። ድርድሩ መልካም ጎኖችን እንዲያሳይ መደላደሎችን ፈጥሯልም። የሀገራቱ ጥያቄዎች ሳይቀሩ ደጋፊ ሃሳብን የያዘ ሆኗል።
አሁን ድረስ ያሉ የክርክር መንፈሶች ወደ ጥሩ ምላሽ እየመጡ ያሉ ናቸው ። ሆኖም ዲፕሎማሲውን መተማመን ላይ እንዳይደርስ ያደረጉት ነገሮችን ለይቶ በማውጣት አሁንም መሥራት ይገባል ። ለአብነት የእስከአሁን ጉዞውን ሲያደናቅፉና እንቅፋት ሲሆኑ የቆዩት በእኔ እምነት የውሃ መሀንዲሶች ናቸው ለማለት እቸገራለሁ ።
እነርሱ ኢትዮጵያ በምታደርገው ነገር ሁሉ ምንም አይነት ጥርጣሬ የላቸውም ። ከዲዛይኑም፤ ከአሠራሩም፤ ከመጠቀም መብት ጋርም ቢሆን ልዩነታቸው የሰፋ አይደለም። ይህንን እንዲሆን የሚያደርጉት ፖለቲከኞች ናቸው። ሥልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ ብዙ ነገሮችን እየፈጠሩ ሕዝቡን ለመያዝ ይሞክራሉ። ስለዚህም እነርሱን ማስቆም ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
ሀገራቱ ዓባይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ጥቅም ላይ ሊያውሏቸው የሚችሉ የውሃ ሀብት አሏቸው። በከርሰ ምድር ውሃቸውም ቢሆኑ ለምሳሌ ግብጽ 500 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውሃ አላት። ለምዕተ ዓመትም እንደምትጠቀመው ይገለጻል። ሆኖም ያንን ትታ እኛ ላይ ብቻ ማተኮሯ ለምን እንደሆነ ለዓለሙ ማህበረሰብ ማሳወቅም ይገባል።
ሚዛናዊ፤ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ማስቻል ላይም አሳማኝ በሆነ መልኩ ማቅረብና ወደ እራስ ሃሳብ ማምጣትም ይገባል ። ያን ጊዜ ደጋፊያችንን እናበረታለን። ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንድንሠራ እንሆናለን ።
አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ግድብ መሠራቱ ለሌሎች ሀገራት ምን ምን ነገሮችን ያስገኛል?
ኢ/ር አበራ፡- በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። አንዱ ከአስዋን ግድብ ውስጥ በስርገትና በትነት የሚባክነውን ውሃ እንዳይባክን ማድረጉ ነው ። ይህም በመጠን ሲገለጽ የአስዋን ግድብ 160 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ይይዛል። ከዚያ ውስጥ ከ10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የሚሆነው በትነትና በስርገት የሚባክን ነው ። ከዚህ አንጻር የእኛ ግድብ መሠራቱ የስርገትና የትነቱን መጠን በብዙ መልኩ ይቀንሰዋል።
ኢትዮጵያ ወደታችኛው ሀገራት የሚሄደውን የደለል መጠን ከመቀነስም አንጻር ፋይዳው የላቀ ነው ። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ግድቦቻቸውን በደለል መሞላት ይታደገዋል። ግድቡ አግባብ ያለው ውሃ እንዲይዝም መደላድልን ይፈጥርለታል ። እንዲሁም የጎርፍ አደጋን ከመከላከል አንፃር በጣም ጠቀሜታ አለው ።
ግብጾች የአስዋን ግድብ ሲሠሩ 500 ዓመታትን እንዲያገለግላቸው አድርገው ነው። ይህንን በታቀደው አግባብ እውን ለማድረግ ደግሞ በየጊዜው የሚመጣውን ደለል ማስወገድ ግድ ይላቸዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ ይህንን ችግራቸውን ጭምር በአማከለ መልኩ እየሠራች በመሆኑ የሚያደናቅፉ ነገሮች ሊደረጉባት አይገባም ።
ሱዳኖችም ቢሆኑ ግድባቸው ደለሉ ሲቀር በቂ የውሃ ክምችት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል ። ከዚያም አልፎ በየጊዜው ከሚደርስባቸው የጎርፍ አደጋ ይታደጋቸዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የእርሻ ሥራቸውን እንዲያሰፉና ንብረታቸው እንዳይጠፋ ያግዛቸዋል ። ተመጥኖ ውሃ ስለሚለቀቅላቸውም ያላቸውን የውሃ ሀብት ጨምረውበት መስኗቸውን እንዲያሰፉና መሰል የልማት ሥራዎችን እንዲያከናውኑም እድል ይፈጥርላቸዋል ።
የእኛ ሥራ የሀገሪቱን ዜጎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገሮችንም የኤሌክትሪክ ችግር የሚፈታ ይሆናል። ምክንያቱም በቂ ኃይል ሲመረት ሌሎችንም ማሰብ ይቻላል። ከዚያ ባለፈ ከእኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ገዝተው የከርሰምድርና መሰል የኃይል ምንጫቸውን ለሌሎች ሥራዎቻቸው እንዲጠቀሙትም እድል ይሰጣቸዋል።
ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ ማለት ደግሞ ኢኮኖሚያቸውን ከማሳደግ አንጻርም ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። የውሃ ኃይል አረንጓዴ ታዳሽ ኃይል በመሆኑ የአካባቢ ደህንነትን ከመጠበቅ አንጻርም ከፍተኛ ፋይዳ አለው። አረንጓዴ የአየር ንብረትን በመፍጠር በዓለም ላይ ጭምር ያለውን የአየር ብክለት ከማስቀረት አንጻርም የማይተካ ሚና አለው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውሃ ማማ እንደሆነች የሚነሳበት አግባብ አለ ። ማማነት በተጨባጭ ከፍ ያለ የውሃ ሀብት አላት የሚለውን የሚገልጽ ነውን ፤ ወይስ ሌላ ትርጉም አለው?
ኢ/ር አበራ፡– ኢትዮጵያ 12 የወንዝ ተፋሰሶች አሉዋት። ከዚህ ውስጥ የተወሰኑት ደረቅ ተብለው ይፈረጃሉ ። ሀገር አቋራጭ የሆኑት ላይ እንደ ሀገር ጊዜ ተወስዶ ማስተር ፕላን ተሠርቷል ። በእያንዳንዱ የወንዝ ተፋሰስ ውስጥ የውሃ ፍሰቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነም ተለይቷል ። በዙሪያቸው ያሉ የእርሻ መሬቶችና ለመስኖ ምን ያህሉ አገልግሎት እንደሚሰጥ ሳይቀር በዝርዝር ታይቷል። ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያ 122 ነጥብ 6 ቢሊዮን ኪዩብ ሜትር የገጸ ምድር ውሃ አላት ተብሎ ይገመታል። የውሃ ማማነት የሚለው ስያሜም የመጣው ከዚህ አኳያ ነው። እውነት የውሃ ማማ ነች ወይ ለሚለው ግን ምላሹ ሁለት ነው።
አንደኛው ውሃ አላት ወይ የሚለው ከሆነ አላት የሚለውን ይገልጻል። የውሃ ባለሀብት መሆኗ ከተጠቃሚነት አንጻር ከሆነ የውሃ ማማ አደለችም ብሎ መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ከፍ ያለ የውሃ ሀብት ቢኖራትም ዛሬ ድረስ በስፋት የምትጠቀመው በአብዛኛውን ጊዜ የከርሰ ምድር ውሃን ነው። ይህ ደግሞ አላቂ የሚሆንበት እድል አለው ። ማማ ያስባላትን የውሃ ሀብት መጠቀም እስካልቻለች ድረስ የውሃ ማማ ልንላት አንችልም።
የውሃ ሀብቷ በተለይም በወንዝ የሚመጣው ውሃ ነዳጅን ሊተካ የሚችል አቅም ያለው ነው። ሁለትና ሦስት ጊዜ በመስኖ የእርሻ ማምረት እንድትችል ፤ የሥራ እድል እንድትፈጥር ያግዛት ነበር። ሆኖም ይህንን እድሏን በሙሉ ለሌሎች ሀገራት አሳልፋ ሰጥታለች ። በእርሷ ሀብት የሚበለጽገው ሌላ ሀገር ነው ።
ካሉዋት የገጸ ምድር ውሃ ውስጥ በተለይም ከወንዞች በአግባቡ ተጠቅማበታለች የሚባለው አዋሽ ብቻ ነው። ሌላው የውጪ ሀገራት ገባርና የገቢ ምንጭ ሲሆን ነው የሚታየው። እናም ማማ የሚለውን ስያሜ ለማግኘት ወንዞቻችንን መጠቀም የግድ ይለናል። አሁን ደግሞ በሃይድሮፓወርና የመስኖ ሥራዎች ጅምሮች እየታዩ ናቸው፤ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በሚገባው ልክ ተጠቅማበታለች ማለት ይቻላል፤ ካልተቻለስ በቀጣይ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
ኢ/ር አበራ፡- አልተጠቀምንበትም ። ብንጠቀምበት ብዙ እናተርፋለን ። በጥቂቱ ሥራ አጥ ወጣት በሀገሪቱ እንዳይኖር ማድረግ እንችላለን ። ውሃን ተጠቅመን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት እንችላለን፤ አምራችና ሥራ ወዳድ ዜጋን እንፈጥራለን ። ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የኑሮ ደረጃችንን እናሻሽላለን። በገቢ ጭምር የላቅን ሆነን ከአደጉት ሀገራት ተርታ እንሰለፋለን ።
ጥናቶች እንደሚያመለከቱት በውሃ ሀብት ብቻ ዓለም ላይ ሦስት አራተኛ የሚሆነው ሥራ ተፈጥሯል ። ስለዚህም ውሃ ኃይል፤ ውሃ ምግብ፤ ውሃ የሥራ ፈጠራ፣ በአጠቃላይ ውሃ ሕይወት መሆኑን ተገንዝበን ያለንን የውሃ ሀብት በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ። ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ቆራጥነት ከምንም በላይ ያስፈልጋል ።
ከሌሎች ሀብታት ይልቅ የውሃ ልማት ሥራ ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል ። ምንም እንኳን ሕዝቡ ለሀገሩ መስጠትን ባይቦዝንም ከሕዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ብቻ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በቀጣይ ማከናወን ቀላል አይሆንም። ስለሆነም በብድርና መሰል ያጋርነት ሥራዎችን በማከናወን ልማቱን ለለውጥና ብልፅግና መምጣት መጠቀም ያስፈልጋል ። ከዚያ ባሻገር የሕዝቡን ተሳትፎና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ማሳለጥና ዜጎች የበለጠ ባላቸው አቅም ልክ እንዲሠሩ ማበረታታት ይገባል።
እኛ ተፈጥሮ ያደለችን ሕዝቦች ነን ስንል ዝም ብለን አይደለም ። ውሃ፤ መሬት፤ በቂ የሰው ኃይልና ጉልበት በበቂ ሁኔታ አለን ። ነገር ግን ከአለን አንጻር ምንም አልሠራንም፤ አልተጠቀምንም ። ያለንን ሀብት አጣጥሞ የመጠቀም ችግርም የገጠመን ነን ። ሌሎች ሀገራት የሌላቸውን ፈልገው በማምጣት ሀገራቸው ወደ ብልፅግና ጎዳና እንድትሻገር ሲያደርጉ እኛ ግን ያለንን እንኳን አንመለከተውም።
መለወጥ ከአሰብን እነዚህ ነገሮች በአግባቡ መጠቀም ይገባናል ። የሥራ ባህላችንን መቀየር ያስፈልገናልም ። ያለንን ሀብት ለይተን ጥናታዊና ስኬታዊ በሆነ መልኩ በእቅድ ለመሥራት መታተር አለብን ። አሁን ላይ ያሉ ነገሮች ደግሞ ይበል የሚያሰኙ ናቸው ። ሠርቶ የመጨረስ ባህል በእጅጉ እየሰፋ ነው።
የሥራ አጥ ቁጥሩን መቀነስ፤ ልማቶችን ማስፋት የሚቻለውም ይህንን ማጠናከር ሲቻል ነው ። እሴት መጨመር ላይም በስፋት መሥራት ስንችል ነው ። ምክንያቱም ጥሬውን ከላክን አላቂ የሚሆኑ ሀብቶች ይኖራሉና እጃችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥ ያደርጉናል። በዚያ ላይ ትርፋማ መሆንም አንችልም ። ስለሆነም ይህንን እያሰቡ መንቀሳቀስም ግድ ይለናል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክት የሆነው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ እንደሚጀመር አስረድተዋል ። የዚህ ፕሮጀክት ስትራቴጂክ ጠቀሜታን እንዴት ያብራሩታል?
ኢ/ር አበራ፡- በሀገር ደረጃ አሁን ላይ ተጀምሮ ቀረ የሚለው አስተሳሰብ እየጠፋ ነው ። ለዚህም ማሳያው ብዙ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ሆነዋል፤ በአጭር ጊዜ ተገንብተው ታይተዋል ። የአፈር ማዳበሪያውም ከዚህ አንጻር የሚታይ ነው ። በእርግጥ ባለፈው ጊዜ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ጅምሮች ነበሩ ። ሆኖም መቀጠል አልቻለም ። አሁን ያለው መንግሥት ደግሞ ይህንን ሲያነሳ ላያሳካው ነው የሚል እሳቤ የለኝም። በአጭር ጊዜ ጨርሶት በተለይ በማዳበሪያ እጦት የሚሰቃየውን አርሶ አደር እፎይ ያሰኘዋል።
እንደሚታወቀው ማዳበሪያ ከፍተኛ ወጪም ድጎማም የሚደረግበት ነው ። በሀገር ውስጥ ይህንን ማምረት ደግሞ የተለየ ትርጉም አለው ። አንደኛው ሀገሪቱ ከከፍተኛ ወጪ እንድትድን እድል ይፈጥርላታል ። ማዳበሪያውን ለማምረት የሚያስችላትን ግብዓት በአብዛኛው ከተፈጥሮ ሀብቷ ታገኛለች። ከዚያ ባሻገር ደግሞ በአሲድና መሰል ጎጂ ነገሮች እየተጎዳ ያለውን መሬቷን በራሱ ተፈጥሮ እንድታክም ትሆናለች። ይህ ሲሆን ደግሞ ከፍተኛ ምርት እንዲገኝ መደላድልን ይፈጥራል ። ከምንም በላይ ደግሞ አርሶ አደሩ ያለምንም ጭንቀት በቀላሉና በወቅቱ ማዳበሪያ አግኝቶ እንዲያመርት ይሆናል ። በዚህም የኑሮ ውድነቱ ይቀንሳል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ያሳዩበት ዐሻራቸውን ያኖሩበት የሁሉም የዓይን ብሌን መሆኑ ይታወቃል። ይሄ ብቻ በቂ አይደለም። የዚህን ተሞክሮ በሌሎች የልማት ሥራዎች መድገም ያስፈልጋል ። ከዚህ አንጻር ምን አስተያየት አለዎት?
ኢ/ር አበራ፡- ማንኛውም ልማት ካለወጣቱ የሚሳካ አይደለም ። ስለዚህም በማንኛውም ዘርፍ ላይ ወጣቱን ተሳታፊ በማድረግ የራሱን ዐሻራ እንዲያሳርፍ መፍቀድ ይገባል ። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል በሥራ አሳትፈን ሥራ አጥነትን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን እናሰፋለን። ለዚህ ደግሞ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉን።
አንዱ ያለን ሰፊና ለም መሬት ነው ። እርሱን በመጠቀም ምርታማነታችንን መጨመር ይገባናል። ከትልልቅ ወንዞቻችን መካከል የተወሰኑት ላይ ነው የሠራንበት። ስለዚህ ካሉን ሀብቶች ጋር በማስተሳሰር ገቢያችንንም፤ የኑሮ ደረጃችንንም ከፍ ማድረግ ይኖርብናል ። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ቁርጠኛ መሆን አለበት ። ሕዝቡም ቢሆን ተባባሪነቱን ከምንጊዜም በላይ ማሳየት ይገባዋል ።
አዲስ ዘመን፡- ከዓባይ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት
ኢ/ር አበራ፡- ኢትዮጵያ አሁን ላይ የውሃ ሀብቷን በተለያየ መልክ እያስተዋወቀች እንደሆነ ይሰማኛል። አንዱ የውሃ ቀን በሚል ትምህርት ቤቶች አካባቢ እየሠራች ያለችው ተግባር ነው። ነገር ግን ይህንን ማስፋት ያስፈልጋል። ዓለም ጭምር እየተጠቀመችባቸው ያሉ ምሁሮች ቢኖሯትም ምሁሮቿን ስለ ኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ምንነትና ቀጣይ ተጠቃሚነት እንዲናገሩ እድል ስትፈጥር አይታይም። ትልልቅ የምርምር ሥራዎችና ውጤታማ ተግባራት እንደ ተሞክሮ እየወጡ አይደለም ።
ዓባይ አሁን ባለበት ሁኔታ ኃይል ማመንጨት ብቻ አይደለም ዋና ተግባሩ ። ከ250 ኪሎ ሜትር በላይ ሄዶ ሰፊ የሥራ እድልን የምንፈጥርበት ነው ። ስለዚህም የዓሳ ሀብትን ማልማት፣ የቱሪዝም ቦታ ማድረግ፤ የውሃ ትራንስፖርቶችን መፍጠር፤ ሰፋፊ መስኖዎችን በዙሪያው በመፍጠር ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶችን በስፋት ማምረት ላይ መሥራት ይገባል።
ለዚህ ደግሞ በዓባይ ግድብ ዙሪያ ሥራው እስኪጠናቀቅም ሆነ ከተጠናቀቀ በኋላ ምንም አይነት ግጭቶች ከጎረቤት ሀገራት ጋር እንዳይኖር መተማመን ላይ በስፋት መሥራት ያስፈልጋል ። የመረጃ መለዋወጥም ማድረግ ይገባል ።
እኛ ዋና ፍላጎታችን በራሳችን ሀብት መልማትና መበልጸግ ነው ። ስለዚህም ያንን የሚያረጋግጥ አሠራር መዘርጋትና ትክክለኛ መረጃዎችን መስጠትም ከምንም በላይ ከምሁራን ይጠበቃል ። ሁሉም ሀገራት እንዲረዱን ማድረግ መቻል አለብን ። ይህንን ደግሞ መንግሥት በሚገባ አስቦበታል እንደሚሠራው እምነት አለኝ።
ሌላው በየጊዜው የታችኛው ሀገራት አዳዲስ አጀንዳዎችን ሲሰጡን መቀበል የለብንም ። ከዚያ ይልቅ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አግባብ ያለው መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርብናል። አጀንዳ ተቀባይ ሳይሆን ሰጪዎችም መሆን ይገባናል ። እኛ እውነትን፣ ሳይንስን፣ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት አድርገን ልንፈጥራቸው የምንችላቸው አዳዲስ አጀንዳዎች አሉን ። ስለዚህም ልማታችንን እያፋጠንን ዘወትር አዲስ ነገር አፍላቂና ተቀባይነትን አምጪ መሆንም ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን ።
ኢ/ር አበራ፡– እኔም አመሰግናለሁ ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም