‹‹የሕዳሴ ግድባችን መጠናቀቅ ለኢንዱስትሪዎቻችን ትልቅ ብሥራት ነው›› – አቶ ታረቀ ቡሉልታ

– አቶ ታረቀ ቡሉልታ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ

ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ካላት እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ሰፊ የሰው ኃይል አኳያ ዘርፍ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ያለው አበርክቶ አመርቂ እንዳልነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ለዚህም በዋናነት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በቂ ስላልነበር ይነሳል፤ ሀገሪቱ የምታመርታቸው የግብርና ምርቶች ዕሴት የማይጨመርባቸው በመሆኑ ከዘርፉ የላቀ ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርጓት ቆይቷል። ይሁንና የዛሬ ሰባት ዓመት የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ ይገኛሉ።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ዋነኛው ነው። አሁን ላይ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ባሻገር የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ወደ ዘርፍ በመሳብ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። እኛም ባለፉት ሰባት ዓመታት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በሚመለከት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታን አናግሯል። እንደሚከተለው ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት የአምራች ኢንዱስትሪው ገፅታ ምን ይመስል ነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን ብንጀምር?

አቶ ታረቀኝ፡– ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ሴክተሮች አንዱ ነው። እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት የተሰጠው ትኩረት እምብዛም አልነበረም፤ ምክንያቱም እንደሀገር ስንመራበት የነበረው ፖሊሲ ግብርና መር በመሆኑና በቅድሚያ ግብርናውን የማሳደግና ከሚገኘው ካፒታል ኢንዱስትሪውን እናሳድጋለን የሚል እሳቤ ስለነበር ነው። በዚህም ኢንዱስትሪው የትኩረት ማዕከል አልነበረም።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ግን ይህ እይታ ተቀይሮ ሁሉንም ሀገራዊ አቅሞቻችንን መጠቀም አለብን በሚል ወደ ብዝኃ-ዘርፍ ነው የተሄደው። በተለይም አምስት ዘርፎች መንግሥት ልዩ ትኩረት የሰጣቸው ሲሆን የአምራች ኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የማዕድን፣ ቱሪዝምና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዋነኞቹ ናቸው።

እነዚህን የትኩረት ዘርፎች እንዲሳኩ የለውጡ መንግሥት በእቅድ ነው ሥራውን የጀመረው። ለምሳሌ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በተለይ የአፍሪካ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ግልፅ ራዕይ አስቀምጦ ነው ወደ ሥራ የገባው። የዓመታዊ የእድገት ምጣኔ ድርሻው (ጂዲፒ) እያደገ መሄድ አለበት የሚል እሳቤም አለው። በነገራችን ላይ አሁን ኢንዱስትሪው የጂዲፒ ድርሻ 6 ነጥብ 8 በመቶ ሆኗል። የወደፊት ዓላማችንም ይኸው እያደገ ሄዶ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ የሚጠጋ ድርሻ እንዲኖረው ማስቻል ነው።

ሌላው የዘርፉ ራዕይ ትኩረት የሚያደርገው፤ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል እያደገ መሄድ አለበት የሚል ነው። በመሠረቱ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የምንፈልገው ለሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። በሚቀጥሉት አስር ዓመታት መጨረሻ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል።

የዘርፉ ራዕይ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማሳደግ ዓላማ አለው። አሁን ላይ ወደ 12 ሺ የሚጠጉ ኢንተርፕራይዞች ይቋቋማሉ ተብሎ የታቀደ ሲሆን ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ውጤታማ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ዘርፉ በገበያ ውስጥ ያለውን ድርሻ ማሳደግ የሚል ትልቅ አጀንዳ ተይዞም እየተሠራ ነው።

በዚህ ረገድ ሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በመጠቀም ያለንን የገበያ ድርሻ ለማሳደግ በስፋት እየተንቀሳቀስን ነው። ይሄ እቅዳችን ስንጀምር 30 በመቶ ነበር፤ ይህም በአስር ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 60 በመቶ የሚጠጋ የገበያ ድርሻ እንዲኖረው የማስቻል ነው። በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ከፍተኛ የሚባል እድገት ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፤ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምጣኔ ሃብት እመርታም እያሳደረ ያለው አዎንታዊ አስተዋፅዖ ጎልብቷል።

አዲስ ዘመን፡- በእነዚህ ዓመታት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተመዘገበው ውጤት ዐቢይ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ታረቀኝ፡- ባለፉት ሰባት ዓመታት ለመጡት ውጤቶች ዐቢይ ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው ነገር በመንግሥት የተሰጠው ትኩረት ነው። ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በሙሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተለየ ትኩረት በመስጠታቸው ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡት።

በሌላ በኩል ትልቅ እመርታ እንዲመዘገብ ያደረገው ፖሊሲና የሕግ ማሕቀፎች ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ እንዲሻሻሉ በመደረጋቸው ነው። እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት የነበረው ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርገን አልነበረም። ነገር ግን ለውጡን ተከትሎ ዘርፍን በመሠረታዊነት ለማሳደግ በማለም ወቅቱን የዋጀ፤ ወቅታዊ የሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርገን የሚችል አዲስ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዲቀረፅ ተደርጓል።

ሌላው በዘርፍ የነበረው ችግር የአደረጃጀት ጉዳይ ነው፤ እንደሚታወሰው ከለውጡ በፊት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ተዋቅሮ በተደራቢነት ነው ሲሠራ የቆየ ነው። በተለይ ከንግድ ጋር አንዳንዴ ሲገናኝ አንዳንዴ ሲፋታ ኖሯል። ይህም እንደሀገር አብዛኛው ትኩረታችንን ኢንዱስትሪው ላይ እንዳናሳርፍ አድርጎናል።

ይህንን የተረዳው የለውጡ መንግሥት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 1263 እንደአዲስ እንዲቋቋም አድርጓል። ስለዚህ በዚህ በአጭር ጊዜ የተሠሩ ሥራዎች ባለፉት በርካታ ዓመታት ከተሠሩት ሥራዎች የተሻለ ትኩረት አግኝቶ የተሠራ ነው። ይህም በመሆኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት እየጨመረ ነው።

ለምሳሌ በ2014ዓ.ም አምራች ኢንዱስትሪው ማደግ የቻለው 4 ነጥብ 8 የነበረ ሲሆን፤ በ2015ዓ.ም 7 በመቶ፣ 2016ዓ.ም 10 ነጥብ 01 በመቶ ከፍ ብሏል። አሁን ላይ ያለውን የኢንዱስትሪ እድገት ስናይ ከጊዜ ወደ ጊዜ አመርቂ የሆነ እድገት እያስመዘገበ ነው። ከዚህ በመነሳትም በ2017ም በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሻለ እድገት እየተመዘገበ ይቀጥላል ተብሎ ነው እየተሠራ ያለው።

ሌላው እንደትልቅ እመርታ የሚታየው የማምረት አቅም ነው፤ ከለውጡ በፊት የነበረው ትልቁ ችግር የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለመሻሻሉ ነው። ይህንን ሥራ ስንጀምር የኢንዱስትሪው የማምረት አቅም ከ45 በመቶ ያልዘለለ ነበር። አሁን ላይ ግን ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 ነጥብ 08 በመቶ ደርሷል። ይህም ማለት የኢንዱስትሪዎች ችግር እየተቀረፈ፤ ምርታማነታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያመለክት ነው።

በነገራችን ላይ የኢንዱስትሪዎቻችንን ምርታማነት የሚቀንሱ ብዙ ነገሮች አሉ፤ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር፤ የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የፋይናንስ አቅርቦት በሙሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ምርታማነት የሚቀንሱ ናቸው። ነገር ግን በለውጡ ዘመን በተሠሩ ሥራዎች በተለይ ከፋይናንስ አኳያ ወሳኝ የሚባል ሥራ ተሠርቷል።

የፋይናንስ ፖሊሲያችንን ስንመለከት ከለውጡ በፊት አብዛኛው ተበዳሪ መንግሥት የሆነበትና ይህንንም የሚፈቅድ አሠራር ነበር የተዘረጋው። መንግሥት ተበዳሪ በሆነበት ሁኔታ የግሉ ዘርፍ ብድር አያገኝም ነበር። አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ በዋናነት ሊያሳድገው የሚችለው ደግሞ የግሉ ዘርፍ ነው።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ ተሳትፎ፤ ፋይናንስ አግኝቶ፤ ኢንቨስት አድርጎ ዘርፉን ሊያሳድገው የሚችለው ከ80 በመቶ በላይ ተበዳሪ የግሉ ዘርፍ ነው። በመሆኑም የፋይናንስ እይታውና ፖሊሲው ስለተቀየረ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚቀርበው ፋይናንስ መጠን አድጓል። ይህም የኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተሻሻለ እንዲሄድ በማድረግ ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው።

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ምርትን ከመጠቀም አኳያ ከዚህ በፊት የትኩረት አቅጣጫ አልነበረም። ድጎማ በመስጠት በመደገፍ አኳያ የሀገር ውስጥ ምርት ድጋፍ አልነበራቸውም። እድገታቸውም የሚለካ አልነበረም። አሁን ላይ ከውጭ የሚገቡትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል።

ስትራቴጂ ወደ 96 የሚጠጉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የለየ ነው። ይህንን በአስር ዓመት የምናሳካው ነው። አንዳንዶቹን በአምስት ዓመት፤ ረዘም ካለም በአስር ዓመት ውስጥ እንድናሳካው ታስቦ የተዘጋጀ ስትራቴጂ ሲሆን የሚጠቀሙት ግብዓት ከሀገር ውስጥ ወይም ከውጭ እንደሆነ በተጨባጭ ተለይቶ ተቀምጧል።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የተሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል?

አቶ ታረቀኝ፡- በነገራችን ላይ የሀገር ውስጥ ምርቶች ከዚህ በፊት በገበያ ላይ የነበራቸው ድርሻ 30 በመቶ ነበር፤ አሁን ወደ 41 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ውጤት ሊመጣ የቻለው ለሀገር ውስጥ ምርቶች ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ነው። አሁን ላይ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅማችን እያደገ በመምጣቱና ከውጭ የሚመጣውን ምርት እየተተካ ከመሆኑም አኳያ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን ያመላክታል።

መንግሥት ትልቁን ቁርጠኝነት በመውሰዱ፤ አቅጣጫም አስቀምጦ በመንቀሳቀሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚታይ እመርታ ተመዝግቧል። በተለይም ሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ግዢ እንዲፈፅሙ ከማድረግ አኳያ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ለዘርፉ እንደወሳኝ ለውጥ የሚታይ ነው። ለዚህ አብነት አድርገን ብንጠቅስ ከዚህ ቀደም ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገባ የነበረው የፀጥታ አካላት ልብስ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ነው የሚመረተው። ይህም 2014 ሲጀመር የማይሳካ የሚመስል ነበር።

ምክንያቱም ከጥራት፤ ከብዛት አኳያ ሀገር ውስጥ ልምዱ ያልነበረን በመሆኑ ነው። ነገር ግን አቅጣጫ ከተቀመጠ ወዲህ በጣም የተሳካ ልምድም ተገኝቶበታል፤ ወደ ሌሎች ምርትም እንድንሸጋገር መነሻ አድርገን የምንወስደው ነው። አሁን ላይ ከፌዴራል እስከ ክልል የፌዴራል ፖሊሶች፤ ሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ የሚሊሻ አካላት በሙሉ ሀገር ውስጥ የተመረተውን ልብስ ነው የሚጠቀሙት።

ጫማ እንዳውም ረዘም ያለ ልምድ ያለበት ነው። ስለዚህ ያጫማ ምርቱም የተሻለ ጥራት ያለው ተወዳዳሪነት ባለው መልኩ የቀጠለ ነው። በተጨማሪም ምግብና መጠጥን ብንወስድ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ቢራ ገብስ፣ የሕፃናት ምግቦች በብዛት ከውጭ ይመጡ እንደነበር ይታወቃል፤ አሁን ግን በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎቻችን በብዛት እየተመረቱ ነው።

በተመሳሳይ የከተማ ልማትንም ውበት እንዲሰጠው ከማድረግ አኳያ ዛሬ መንገድ ላይ የምናየቸው ፖሎች የሀገር ውስጥ ምርት ናቸው። ይህም ገዢው ራሱ መንግሥት ሆኖ ነው። ስለዚህ ገበያም አለ፤ ኢንዱስትሪውም የማደግ፤ የመስፋት ዕድሉ በመኖሩ አምራቹ እየተበረታታ ነው።

በተመሳሳይ ሀገር ውስጥ የሚመረቱ መኪኖች እየጨመሩ የመጡበት ሁኔታ አለ፤ በልዩ ዲዛይን ከቱሪዝም ጋር ተያይዞ የቱሪስት መኪኖች ሀገር ውስጥ እየተመረቱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ ትልቅ አቅም ነው የፈጠረልን። ከተኪ ምርት አኳያም እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የምናነሳው።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በባለሀብቶች በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የተደረገውን ጥረት ቢያብራሩልን?

አቶ ታረቀኝ፡– ለኢንዱስትሪው የሚቀርቡ መሠረተ ልማቶችን ስንመለከት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ከማጠናቀቅ፤ ታዳሽ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ከማስቻል አኳያ በተነፃፃሪ አነስተኛ ዋጋ የሚከፈልበት ታዳሽ ኃይል ነው። ይህም ለኢንዱስትሪ ቅድሚያ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

በተለይ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለምሳሌ ሥራ የጀመሩትን የይርጋለም፣ ቡልቡላ፣ ቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ መውሰድ እንችላለን፤ እነዚህ ፓርኮች በልዩ ሁኔታ ኃይል እንዲቀርብላቸው እየተደረገ ነው። ይሄ የሚያሳየው መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረትና ያሳየውን ቁርጠኝነት ነው። በአጠቃላይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ያገኛናቸው ውጤቶች አመርቂ ናቸው ማለት ይቻላል።

የተለያዩ የድጋፍ ካውንስሎችን በማቋቋም ችግሮቻቸው በአጭር ጊዜ እንዲፈቱ ጥረት ተደርጓል። ይህም ካውንስል ሁሉም ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ያሉበት ካውንስል ነው፤ በ15 ቀን እየተገናኙ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ችግር በመለየት አቅጣጫ በማስቀመጥ ችግሮች እንዲፈቱ እየተደረገ ነው። በዚህም ትልቅ ውጤት አግኝተናል። ምክንያቱም እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በተናጠል ችግር እየተለየ፤ አቅጣጫ እየተቀመጠ፤ ባለቤት እየተሰጠው ችግሮች እንዲፈቱ እየተደረገ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› እንደሀገር መጀመሩ ያስገኘው ውጤት ምንድን ነው?

አቶ ታረቀኝ፡– በንቅናቄ ወይም በኢኒሼቲቭ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንደኛው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› ነው። የዚህ ንቅናቄ እሳቤ ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሀገር የማድረግ ጉዞን ማፋጠን ነው። በተለየ ትኩረት፣ በተለየ ንቅናቄ የማሳካት ሥራ ነው የሚሠራው። ይህንን ንቅናቄ በ2014 ዓ.ም ስንጀምር ለኢንዱስትሪ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው ምቹ አልነበረም።

በተለይ ከኮቪድ 19 መከሰት፣ ግብዓት ከሚገኝበት ከራሺያና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ፤ ሀገር ውስጥ ከነበረው ግጭት በመነሳት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ተፈልጎ ነው ንቅናቄው የተጀመረው። ስለዚህ ይህ ንቅናቄ ታላሚ ያደረገው የኢትዮጵያ ኢንዱስትራላይዜሽን የማፋጠን ነው። በዚህም ትልልቅ ውጤቶችን አግኝተናል። የመጀመሪያውና እንደትልቅ ውጤት የምናነሳው አደረጃጀት ነው። ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና እስከ ክልል ከተማ መስተዳደር ያሉ አደረጃጀቶች ተናባቢ እንዲሆኑ በማድረግ ነው ሲሠራ የቆየው። ከፌዴራሉ አደረጃጀት ጋር ተመሳሳይ እንዲሆኑ የተደረገበት ትልቅ ውጤት ነው።

በነገራችን ላይ በዚህ ንቅናቄ ነው አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ያገኘነው። ከዚህ ፖሊሲ በመነሳት 14 አዳዲስ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ ተደርገዋል። በዚህም ውስጥ ፍኖተ ካርታና ሰባት የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎች ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህ ውስጥ እንደምሳሌ ማንሳት የምንችለው የተኪ ምርት ስትራቴጂ፣ የቆዳ፣ የአቅም ግንባታ፣ የኮሙዩኒኬሽን፣ የኢንዱስትሪ ትስስር ስትራቴጂዎች እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪ ምርምር ቴክኖሎጂ ልማት ሽግግር ፍኖተ ካርታ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ልማት ፍኖተ ካርታ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ድጋፍና ክትትል መመሪያ፤ የግብዓት ምርት ጥምርታ መመሪያዎች ናቸው። ይህም ኢንዱስትሪውን የምንደግፍበት በስትራቴጂ ተገማች የሆኑት፤ በእቅድ የሚሰፍር እንዲሆን አድርጎታል። ስለዚህ ሁልጊዜ ከስትራቴጂ አኳያ እናየዋለን።

ሌላው የድጋፍ፤ የክትትልና በተለይ የኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥር ከማድረግ አኳያ በንቅናቄው ከፌደራል እስከ ክልል ሰፋፊ ውይይቶች ይደረጋሉ። በዚህም ከውሳኔ ሰጪው ጨምሮ እስከ ዘርፍ ተዋናይ ባለሀብቶች ደጋፊ የሆኑ ተቋማት፤ ድረስ ሰፊ የሆነ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ተደርጓል። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲኖር አስችሏል።

ከዚህ በፊት ይጓተት የነበረው የመሠረተ ልማት አቅርቦት፤ ከመብራት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲቀረፉ ከማድረግ አኳያ የንቅናቄው መጀመር አዎንታዊ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በተለይ በዘርፉ ሰፊ ችግር የነበረበት የመሬት አቅርቦት እንዲፈታ ለማድረግ አስችሏል። ለምሳሌ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የማምረቻና መሸጫ ቦታ የማቅረብ፤ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መሬት የማቅረብ ችግር ነበር፤ ይሄ ንቅናቄ ከተጀመረ 60 ሺ የሚጠጋ ሄክታር መሬት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲቀርብ ተ ደርጓል።

ኢንዱስትሪዎች ገበያ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አለ፤ ይህም ኤክስፖ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓመት አንድ ጊዜ፤ በክልሎችና እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ ይካሄዳል። ይሄ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ነው። ስለዚህ ኅብረተሰቡ በሀገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን እንዲገዛና እንዲጠቀምባቸው ማድረግ እየተቻለ ነው። ይህም በንቅናቄው ከተሰጠው ትኩረት የመጣ ነው።

የፋይናንስ አቅርቦትን በተመለከተ፤ አስቀድሜ እንዳነሳሁት ከዚህ በፊት ለአምራች ኢንዱስትሪው ይቀርብ የነበረው ፋይናንስ መጠን አነስተኛ ነበር። የንቅናቄው መጀመር ለዘርፉ አንቀሳቃሾች የሚቀርበው ፋይናንስ እንዲሻሻል አድርጓል። ይህም ሲባል የሥራ ማስኬጂያ፣ የፕሮጀክት ወይም የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ሊሆን ይችላል፤ ከነበረበት 12 በመቶ ወደ 16 በመቶ በላይ ከፍ ማድረግ ተችሏል። ይህ ግን በቂ ነው ማለት አይደለም በሂደት እያደገ መሄድ ይኖርበታል። ስለዚህ እንደልዩ ንቅናቄ ያስገኘው ውጤት ነው ማለት እንችላለን።

በንቅናቄው ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ከተጀመረ ወዲህ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እያደገ መጥቷል። ከዚህ አኳያ የአራት ዓመታትን ሁኔታ ብናነሳ 2013 ዓ.ም የነበረው 343 ሚሊዮን ዶላር ነበር፤ ነገር ግን ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ከጀመረበት ከ2014 ጀምሮ 2 ነጥብ 098 ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት ተችሏል። 2016 ዓ.ም ላይ 2 ነጥብ 844 ቢሊዮን ዶላር ነው ሀገር ውስጥ እንዲቀር የተደረገው።

2017 ዓ.ም በስምንት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ79 ቢሊዮን ዶላር ማስቀረት ተችሏል። ይህም በሀገር ውስጥ የሚተካው ምርት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል። የገበያ ድርሻውም ከ 30 በመቶ እያደገ መጥቶ ወደ 41 በመቶ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም ትልቅ ፋይዳ የተገኘበት አድርገን መውሰድ እንችላለን።

ሌላው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚጠበቅበት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ነው። ይህ ሥራ በቀጣይም በልዩ ትኩረት መሠራት ያለበት ነው። አሁን ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያገኘን ያለነው የውጭ ምንዛሪ ግኝት በቂ ነው ተብሎ አይወሰድም፤ በተለይ እድገቱ የሚፈለገው ከዚያ አኳያ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።

ነገር ግን ካለፉት ዓመታት አንፃር ሲታይ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን ነው የምናየው። ለምሳሌ ዘንድሮ የ2017 ዓ.ም ስምንት ወር አፈፃፀም ሲታይ ወደ 204 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ስምንት ወራት ጋር ሲነፃፃር 21 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወይም 12 በመቶ እድገት ነው ያስመዘገብነው። ነገር ግን እንደታላቅ ሀገር የምንልከውም ሆነ እያገኘን ያለነው የውጭ ምንዛሪ በቂ ነው ተብሎ አይወሰድም። ወደፊት ልዩ ትኩረት ሰጥተን ወደ ውጭ የምንልከው የኢንዱስትሪ ምርቱን ማሳደግ ይኖርብናል።

አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ በዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

አቶ ታረቀኝ፡- መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሳደግ በማለም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ሆነ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ምቹ ምኅዳሮችን ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ምክንያቱም አምራች ኢንዱሰትሪ ዘርፍ ኢንቨስትመንቱ እያደገና ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ በሄደ ቁጥር የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ነው የሚሆነው። ባለፉት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶችን በቁጥር እየጨመረ ነው።

ለአብነት ያህል ብንጠቅስ፤ በ2014 ዓ.ም 94 የሚጠጉ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ብቻ የነበሩ ሲሆኑ በ2015 ዓ.ም ወደ 136፣ 2016 ዓ.ም ወደ 220 ማሳደግ ተችሏል። ይህም በብርም ሆነ በካፒታል ሲታይ በጣም ትልቅ ነው። ከዚህ አንፃር ለምሳሌ 2017 ዓ.ም የግማሽ ዓመት 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ከውጭ ወደ ሀገር ፈሷል። ይህ ማለት ኢንቨስትመንት በቁጥርም፤ በካፒታልም እየጨመረ ነው።

በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ስንመለከት በቁጥርም፤ በካፒታልም እያደገ የመጣ ኢንቨስትመንት ነው ያለው። በተለይ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ አስተማማኝ አቅም የሚሆነው የሀገር ውስጥ ባለሀብት ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሲገባ ነው። ይህም በቁጥር ሲታይ ከ2014 ዓ.ም 240 የሚጠጉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሀገር ውስጥ ተስበዋል፤ 2015 ዓ.ም ላይ 808 የሚጠጉ ገብተዋል።

2016 ዓ.ም ላይ 899 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተቀላቀሉ ሲሆን ይህም በተለይ አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ኢኒሼቲቮች እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።

በነገራችን ላይ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከዚህ በፊት ይገባ የነበረው የውጭ ባለሀብት ነበር፤ ለሀገር ውስጥ ባለሀብት የተከለከለ ነበር። በተለይ አሁን ላይ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የሀገር ውስጥ ባለሀብት ነው። ይህም የሆነው አስቀድሜ እንዳልኩት የመሬት አቅርቦቱ በመጨመሩ፤ የፋይናንስ ያላቸው ምቹ ሁኔታ በመኖሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ትልቅ ድርሻ እያበረከተ ነው።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ 2014 ላይ በዘርፉ ፈሰስ ያደረገው 18 ነጥብ 8 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን ይህም በ2015 ዓ.ም ላይ ወደ 60 ነጥብ 8 ቢሊዮን፣ 2016 ዓ.ም ወደ 136 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል። ስለዚህ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ሲታይ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚያመለክተው።

አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የተሠራው ሥራ ምን ያህል ውጤታማ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ታረቀኝ፡- አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ አንዱ የሚጠበቅበት የሥራ ዕድል ለዜጎች መፍጠር ነው። ከ2014 ዓ.ም እስከ 2017 ድረስ ያለውን ብናይ 855 ሺ 375 የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ይህ ወደፊት ትልቅ ሥራ እንፈጥራለን ካልን ሥራው የሚፈጠረው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ነው። ምክንያቱም አንድ ሄክታር ላይ ከሁለት እስከ አራት ሺ ሰው ማሰማራት እንችላለን።

ይሄ የሰው ኃይል ምርታማ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲያድግ ከተፈለገ የሥራ ዕድል ሆኖ የሚመጣው በዚህ ዘርፍ ነው። እንደአጠቃላይ ሲታይ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይ ከቅኝት አኳያ ሀገር በቀል እሳቤዎች በመምጣታቸው፤ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች፤ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀቱ፤ የአሠራር ሥርዓቱ በመሻሻሉ፤ በተለይ ከዚህ ቀደም አስቸጋሪ የነበረው የተቋማት ችግር በመፈታቱ የመጣ ነው።

በኢትዮጵያ ታምርት በተፈጠረው የፋይናንስ ክላስተር አንድ ላይ እየመጡ እያቀዱ ሥራዎችን እየገመገሙ ነው የሚሄዱት፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ክላስተር አለ፤ እየገመገሙ እያሻሻሉ ነው የሚሄዱት። የግሉ ዘርፍና ኢንቨስትመንት ጋር በጋራ ተቀናጅተን በመሥራታችን፤ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ ትኩረት ስለተሰጠው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ ተስፋ በመጣል ላይ ያለ ዘርፍ ነው ማለት እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ምንም እንኳን በርካታ ሥራ አጥ ዜጎች ቢኖሩም በዚሁ ልክ ኢንዱስትሪው የሚፈልገው የሰው ኃይል እጥረት እንዳለበት፤ የትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪ ተናበው እንደማይሠሩ ይነሳል። እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎችን በማጣጣም ረገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ ታረቀኝ፡– የሰው ኃይሉ ም ርታማነት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ምርታማነት በማሳደግ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው። የኢትዮጵያ የሰው ኃይል ልማቱ በጣም ሰፊ ነው፤ በተለይ በርካታ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ ይመረቃሉ፤ በየዓመቱ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የሠለጠነ ኃይል ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ይወጣል። ነገር ግን በዚህ ኃይል ወደ ኢንዱስትሪ ከማሰማራት አኳያ ሁለት ነገሮች ይፈለጋሉ፤ ከትምህርት ተቋማት የሚያገኘውን እውቀት በኢንዱስትሪው ባሕሪና አቅም ዳግም ማጎልበት ይጠይቃል።

ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ክህሎት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ተቋማቱ ኢንዱስትሪው የሚፈልገው የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲያመርቱ ለማስቻል ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር የግንኙነት አግባብ ፈጥረን አብረን እየሠራን ነው ያለነው። በዚህ ረገድ የሰው ኃይሉን ከማቅረብ አኳያ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ናቸው። ይህንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።

በሁለተኛ ደረጃ ኢንዱስትሪዎች ራሳቸው የሚፈልጉትን የሰው ኃይል ወስደው በሚፈልጉት መልኩ ዳግም በክህሎት የማሳደግ ሥራ ይሠራሉ። ይህ ዘርፍ በንድፈ ሃሳብ የሚሠራ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ ስለሆነ እየወሰዱ ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። አሁን ላይ የራሳቸውን የሰው ኃይል በሚፈልጉት መንገድ እየሠለጠኑ ወደ ሥራ የሚያስገቡ የተወሰኑ ኢንዱስትሪዎች አሉ፤ በአብዛኞቹ ግን ከመንግሥት የሚጠብቁ ናቸው። እነሱ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። በጋራ ተቀናጅተን መሥራታችንን እንቀጥላለን።

ይህም ሆኖ ግን የሠለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ ቀርቧል ማለት አንችልም። የመጀመሪያው የክህሎት ክፍተት አለ፤ በቀጥታ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሁልጊዜ ችግር አድርገን የምናነሳው የሠለጠነ የሰው ኃይል ለኢንዱስትሪው በቂ አለመሆኑን ነው። ስለዚህ እሱን የማብቃት፤ የማሳደግ ኢንዱስትሪው የሚፈልገው የሰው ኃይል ከማቅረብ አኳያ ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት ይኖርብናል።

ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ስትራቴጂ አዘጋጅተናል፤ አዋጁም ፀድቋል፤ ትምህርት ሚኒስቴር በበላይነት፤ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደግሞ ምክትል ሆነው ነው እየመሩት ያሉት። የጋራ የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ምክር ቤት አለ፤ በዚያ ምክር ቤት እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው። ይሄ ነገር ግን ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።

ከዚያ ውጪ የኢንዱስትሪ አመራር ሥርዓታችን ነው። አሁን ኢንዱስትሪውን እየመራ ያለው የሰው ኃይል፤ ኢንዱስትሪውን በማወቅ፤ ያንን ችግር በሚፈታ መልኩ በቂ አመራር ተፈጥሯል ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ እንደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአመራር ክህሎት በተለይ ከአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ጋር በጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን እየሠራን ነው።

በከፍተኛ አመራር ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ተጠሪ ተቋማት፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር አመራር ራሱን የቻለ የኢንዱስትሪ ሥልጠና እንዲያገኙ፤ በሁለተኛ ደረጃ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና መሪዎች ሆነው የሚመሩ እንዲሠለጥኑ ይደረጋል። በሦስተኛ ደረጃ በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች እውቀቱን አግኝተው ኢንዱስትሪ በእውቀት የሚመራበትን ሥርዓት ለመፍጠር ስትራቴጂ ነድፈን በጋራ እየሠራን ነው። በመሠረቱ የክህሎት ሥራ አንዴ ሠርተን የምንጨርሰው አይደለም፤ በቀጣይነት የሚሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር ሲባል በተቀረፁ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች ታቅደው ነበር፤ ሆኖም እንደታሰበው ሽግግሩን ማምጣት አልተቻለም፤ አሁንስ ወደ ሽግግሩን ለማሳለጥ ሀገራዊ ሁኔታው ምን ያሳያል ይላሉ?

አቶ ታረቀኝ፡- በሁለቱም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች የተሠሩ ሥራዎች አሉ፤ ነገር ግን አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተለይቶ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ አልነበረም። ምክንያቱም ለመንግሥት ኢንዱስትሪው ቅድሚያ የሚሰጠው ዘርፍ አልነበረም። አሁን ላይ ግን ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንደኛው ነው።

ካለፉት ዓመታት አሁን ላይ ልዩ የሚያደርገው ኢንዱስትሪው በልዩ ትኩረት እየተመራ በመሆኑ ነው። በሁለተኛ ደረጃ የእድገት ምጣኔውም እየጨመረ መምጣቱ ነው። ከለውጡ በፊት ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የነበረው ድርሻ 4 ነጥብ 8 ነበር፤ በ2016 ዓ.ም 10 ነጥብ 01 በመቶ እድገት አምጥቷል፤ ዘንድሮ 12 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ያመጣል ተብሎ ነው የሚታሰበው። አሁን ላይ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈጣን የሆነ እድገት እየተመዘገበ ነው።

ያለፈው ሥርዓት የውጭ ምርትን ነው የሚያበረታታው፤ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን ያበረታታል። ይሄኛው ፖሊሲ ግን ዜጋ ተኮር ነው። የግል መሪ የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾችን ነው የሚፈልገው። ከዚህ ቀደም መንግሥት ራሱ ምርት ላይ ይገባ ነበር፤ ለምሳሌ በወቅቱ መንግሥት የገባባቸውን ፕሮጀክቶች መጥቀስ ይቻላል፤ ይህም የመንግሥትን በጀት የመውሰድና ያንን በጀት የማባከን ሂደት ነው የነበረው።

አሁን የምንከተለው ከእይታ አኳያ ዜጋውን በግንባር ቀደምትነት የሚያበረታታ ነው። ከዚህ ቀደም መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት ሥርዓት ነው የነበረው። በተቃራኒው ግን የዓለም ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ኢንዱስትራላይዜሽን ሊሳካ የሚችለው ዜጋው ባለቤት መሆን ሲችል ነው። ከዚህ በመነሳት የለውጡ መንግሥት በዘርፉ ያለውን እይታ ስርነቀል በሚባል ደረጃ ለውጦ ነው ወደ ሥራ የገባው።

እይታው በመስተካከሉ ከመጡ አንኳር ለውጦች መካከል በተለይ ተኪ ምርቶችን የሚያበረታታ ሥርዓት መፈጠሩ ነው። ከዚህ ቀደም እንደሀገር ተኪ ምርት ትኩረት አልተሰጠውም ነበር። የሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ አያገኝም፤ የነበረውም ምልከታ ጤናማ አልነበረም። አሁን ላይ የተኪ ምርት ስትራቴጂ እንዲወጣ ተደርጓል፤ ይህ በመሆኑ የሀገር ውስጥ ምርት በልዩ ትኩረት ግዢያቸውን ይፈፅማል።

ከዚህ በፊት ሀገር ውስጥ ምርት እያለ ከውጭ ነው የሚመጣ የነበረው። ይህ በመሆኑ ሀገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የሚሞቱበት አጋጣሚ ነበር። ምክንያቱም ሀገሪቱ የተሻለ ድጋፍ ያለው፤ የተሻለ የማምረት አቅም ያለው ሀገር ሸቀጥ ማራገፊያና መጣያ የሆነችበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

አሁን ግን ዜጋ የራሱን ምርት በሀገር ውስጥ አምርቶ፤ መንግሥት ራሱ ገዢ ሆኖ ሽያጭም እንዲበረታታ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህም በፖሊሲ የሚደገፍ ነው። ለምሳሌ አሁን ያለው ፖሊሲ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚጠቀሙበትን በተነፃፃሪ ታሪፉ አነስተኛ ነው። በተለይ አምራች ከሆነ እስከ ዜሮ ታሪፍ ነው። ይህም አምራቾች እንዲያመርቱ ያበረታታል። ትልቅ ታሪፍ ሲጫንበት ተስፋ ያስቆርጠዋል።

ከመዋቅራዊ ሽግግር አኳያ የምንፈልገው ወደፊት ኢኮኖሚያችን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ እንዲይዝ ተደርጎ ነው እየተሠራ ያለው።

ስለዚህ አሁን የተሸከመን ያለው፤ በሚቀጥሉትም ሊሸከመን የሚችለው ግብርና ነው። ግን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት አምራች ኢንቨስትመንት አምራች ኢንዱስትሪው ላይ ማድረግ ከቻልን፤ አሁን የተሰጠው ትኩረት ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ በእርግጠኝነት የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ የኢኮኖሚያችን ማዕከል ሆኖ የሚቀጥለው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው። ስለዚህ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፤ እነሱን ካስቀጠልን ካሰብንበት የማንደርስበት ሁኔታ አይኖርም።

አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ዓመት የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምን አበርክቶ ነበረው በተለይ በዘርፉ ይነሱ የነበሩ ችግሮች በማስቀረት ረገድ የነበረውን አስተዋፅዖ ያብራሩልን?

አቶ ታረቀኝ፡- ይሄ በአብዛኛው የተደረጉ ሪፎርሞች የአምራች ኢንዱስትሪውን ማዕከል ያደረጉ ናቸው። የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥያቄዎች ናቸው እንዲመለሱ የተደረጉት። በተለይ ዋና ማነቆ የነበረው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ነበር፤ አሁን በተደረገው ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በገበያ የሚመራ ከተደረገ በኋላ አንድም ኢንዱስትሪ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር አያነሳም።

ምክንያቱም በገበያ ነው የሚመራው፤ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱም መንግሥት ከሚመራው ፖሊሲ የተነሳ ጨምሯል፤ ስለዚህ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሪ ጨምሯል። ነገር ግን የሚነሳው ጥያቄ የፋይናንስ አቅርቦት ነው። አሁንም እየቀረበ ያለው የተሻሻለ የፋይናንስ አቅርቦት ቢኖርም በቂ አይደለም።

በተለይ ከዋጋ ንረት የተነሳ መንግሥት የሚከተለው የሚሊተሪ፤ ፊዚካል ፖሊሲ የመንግሥትን ወጪ የመቀነስ ሂደት አለ። የብድር አቅርቦትን የመቀነስ ሁኔታ አለ። ከዚያ አኳያ ሰፊ የፋይናንስ ፍላጎት በመኖሩ በሂደት እየተስተካከለ የሚመጣ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ የግሉ ዘርፍ ለማሳተፍ ምን ታስቧል?

አቶ ታረቀኝ፡- አሁን ያለው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአብዛኛው የግሉ ዘርፍ እንዲገባበት ነው የሚበረታታው። በተለይ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ወደ ኢንዱስትሪዎች እንዲገባ ይበረታታል። አንዳንድ በግሉ ዘርፍ የማይቻሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ደግሞ መንግሥት የሚገባበት ሁኔታ ይኖራሉ።

በተለይ ከሀገራዊ ፋይዳቸው በመነሳት። አንቺ ያነሳሽው አንዱ የማዳበሪያ አቅርቦት ነው። ይህም ለማዳበሪያ አንዱ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግለው የነዳጅ ቅሪት ነው፤ ሀገር ውስጥ ነዳጅ ባለመኖሩ ፋብሪካው ቢገነባም የተወሰነ ግብዓቱን ከውጭ ማምጣት የግድ ይላል። ስለዚህ በመንግሥትም ሆነ በሽርክና ወደፊት የማዳበሪያ ፋብሪካ የምንገነባ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ሥርዓት በእንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የነበረው አተያይ የተለየ ነበር። በተለይ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳዮችን መለየት ላይ ክፍተት አለ። ለዚህ አብነት አድርገን የምናነሳው ያዩ ላይ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ታስቦ የተሄደበትን ርቀት ነው።

ይህ ቦታ በምን እይታ እንደተመረጠ ግልፅ አልነበረም። የተሳሳተ የመንግሥት ፖሊሲ ያመጣው ነው። አንደኛ ነዳጅ ወይም የነዳጅ ተረፈ ምርት በሌለበት ሁኔታ አብዛኛው ግብዓት ከውጭ እያመጣን እዚያ ድረስ እያመላለስን ማዳበሪያ ለማምረት መታቀዱ በራሱ ኪሳራ ነው። ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ ማዳበሪያ አምርተን ከምንጠቀመው ይልቅ ከውጭ የምናመጣበት ወጪ የሚቀንስበት ሁኔታ ነው የነበረው።

አሁን በአዲስ እይታ ለመገንባት ታስቧል፤ በተለይ ከሞሮኮ ጋር በሽርክና ሀገር ውስጥ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ቦታዎች ተለይተዋል። በተለይ ድሬዳዋ አካባቢ ለመገንባት የታሰበው ፋብሪካ ሱማሌ ክልል ላይ የተጀመረው ነዳጅ ልማት ሥራ ከቀጠለ የግብዓት ጥያቄያችን ይፈታል የሚል እምነት ነው የተያዘው። ከውጭ የሚመጣው ግብዓትም ቢሆን ድሬዳዋ ለወደብ ቅርብ በመሆኑ አዋጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በመንግሥት የተያዘ እቅድ ነው፤ ካለው በጀትም ሆነ በሽርክና ሊሠራው የሚችል ነው።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ከኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ለመውጣት ማሰቡ ወደ ዘርፍ ለመቀላቀል ያሰቡ ባለሀብቶችን ወደኋላ ይጎትታል የሚል ሃሳብ ይነሳል፤ በዚህ ላይ ያለዎት ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ታረቀኝ፡– በነገራችን ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ራሱን የቻለ የመንግሥት ልማት ድርጅት ነው። እስከአሁን በግልም በመንግሥትም 30 የሚጠጉ ፓርኮች ለምተዋል። ለምሳሌ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ በግል የለማ ሲሆን 100 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረበት ነው። ጆርጅ ሹ የተባለው ኢንዱስትሪ ፓርክ በግል የለማ ነው።

አሁን ላይ እንደመንግሥት የታሰበው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በብዛት መገንባት ሳይሆን ወደ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን የመቀየር ሥራ ነው የሚሠራው። ይህ ሲሆን ኢንዱስትሪው የተሻለ ማበረታቻ ያገኛል። ድሮ ከነበረው ቢያንስ 15 ዓመት የሚቆይ ማበረታቻ ነው የሚያገኘው። በተጨማሪም የሎጅስቲክስና ከስተም አገልግሎታቸው እዚያው ነው የሚያልቀው። ይህ በመሆኑ ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ለማስገባት ረዘም ያለ ጊዜ የነበረው እንዲያጥር ያደርገዋል። በተሳለጠና በአጭር ጊዜ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቻችን መንግሥታዊ አገልግሎት ይቀርብላቸዋል።

ሌላው ከአፍሪካ ነፃ ቀጣና ገበያ ጋር በተያያዘ ያመረትነው ምርት በቀጥታ ማቅረብ የሚችሉበትን ሰፊ ዕድል የሚፈጥርላቸው። ይህም በፊት ከነበረው የተሻለ፤ የተሳለጠ የአሠራር ሥርዓት እንዲኖራቸው ነው እየተደረገ ያለው። ይህም ሲባል መንግሥት ጥሎ ይወጣል ማለት አይደለም። ሆኖም እንደሚታወቀው ኢንዱስትሪ ፓርኮች የለሙት በብድር በመሆኑ ያንን ኪራይ እየከፈሉ ሌላ የሚያለሙበት ሁኔታ በአዋጅ ጭምር የተቀመጠ ነው። አዋጁ እስካልተቀየረ ድረስ ፓርኮቹን የማልማት ሥራ አይቀርም፤ ግን ውጤታማነታቸውን የመጨመር ሥራ ይሠራል።

አዲስ ዘመን፡- የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚኖረው ጠቀሜታ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ታረቀኝ፡- የሕዳሴ ግድባችን መጠናቀቅ ለኢንዱስትሪዎቻችንን ትልቅ ብሥራት ነው። አንዳንድ ጊዜ የሚታየውና ለኢንዱስትሪዎቻችን ፈተና ሆኖ የቆየው የኃይል መቆራረጥ፤ የአቅርቦት ችግር ነው። እስከአሁን ድረስ ኢንዱስትሪዎቻችን ተገማች የሆነ ኃይል የማያገኙ ናቸው። ከተማ ውስጥ ያለውን ኃይል ነው የሚጋሩት። ይህም በመሆኑ የኃይል መቆራረጥ ዕድሉ የሰፋ ነበር ።

በተለይ አሁን ላይ ኢንዱስትሪዎቻችን እያደጉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የማይቆራረጥ ኃይል እንዲያገኙ እንደመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው። ሕዳሴ ግድብ ደግሞ የሚያመነጨው ኃይል ከፍተኛ በመሆኑ ለዘርፍ አንቀሳቃሶች ትልቅ የምሥራች ነው። ከዚህም ባለፈ የግድቡ መጠናቀቅ ወደፊት በአነስተኛ ዋጋ ኃይል የሚያገኙበትን ዕድል ያሰፋዋል፤ የማምረቻ ወጪያቸውን እንዲቀንሱና የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያጐለብቱ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። በነገራችን ላይ የግድቡ መጠናቀቅ አሁን ላይ ሥራ ላይ ላሉት ኢንዱስትሪዎች ብቻ ሳይሆን አዳዲስና ሰፊ ኢንቨስትመንትንም ይዞ የሚመጣ ነው የሚሆነው። በመሆኑም ቀጣይ ሥራዎችንን ይህኑኑ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚከናወኑ ይሆናሉ ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ ታረቀኝ፡– እኔም አመሰግናለሁ።

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You