
ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው። በቀላሉ ሊለቅ የማይችል የህብር አንድነት። ነብር ዥንጉርጉርነቱን ሊፍቅ እንደማይችል የማይፋቅ አብሮነት። በደም የተገመደ ጥብቅ ትስስር።
ኢትዮጵያውያን አንድ የሀገር ማንነት ያላቸው ባለቡዙ ባህል ባለቤቶች ናቸው። ብዛሃነታቸው ለአንድነታቸው እንቅፋት ያልሆነባቸው ተከባብረው እና ተዋልደው የሚኖሩ ድንቅ ሕዝቦች።
ዛሬ ደግሞ አንዳቸው የአንዳቸውን ባህል እና ወግ ሊጋሩ ከያሉበት ተጠራርተው በጊዮን ሆቴል 16ኛ የባህል ሳምንት ‹‹ባህሎቻችን የወል ትርክት አምባ›› በሚል መሪ ቃል ሊያከብሩ ማልደው ተገኝተዋል።
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን ባህላዊ አልባሳቶቻቸውን ለብሰው፣ ምግቦቻቸውን ይዘው አጠቃላይ መገልገያ እቃዎቻቸውን እና ባህላዊ የቤት አሠራራቸውን ሸክፈው በጊዮን በክብር ተሰይመዋል።
የጋምቤላ አኝዋክ ቤሄረሰብ ባህላዊ እቃዎች፣ ምግብ እና አልባሳቶችን ይዛ በፌስቲቫሉ ላይ ያገኘናት ወጣት አባንግ ኢጂራ በልደታ ክፍለ ከተማ ተጋብዛ ከነጓደኞቿ መገኘቷን ትናገራለች።
የመጡበት አካባቢ በሞቃታማነቱ ነውና የሚታወቀው ወንዶቹ ከወገባቸው በላይ ልብስ አለበሱም ሴቶቹም እንዲሁ ቀለል ያለ ለሙቀት የሚሆን ደማቅ ቀለም ያለው ቀሚስ መሳይ ሽርጥ ለብሰዋል።አንገታቸውንም በውብ ጨሌዎች አድምቀዋል።
በአካባቢያቸው ተዘውትሮ የሚበላው ባህላዊ ምግብ ገንፎ ወይም በአካባቢው አጠራር ‹‹ፑን›› የሚባል መሆኑን ወጣት አባንግ ትናገራለች።ገንፎው (ፑን) በአዘገጃጀት ልዩነቱ በሶስት ይከፈላል።አንደኛው ፑን ከነጭ በቆሎ፤ ሌላኛው ከቢጫ በቆሎ እና ከማሽላ እንደሚዘጋጅ ትገልጻለች።
የገንፎዎቹ ማባያዎች ውስጥም ‹‹ዲቶንጎ›› የሚባለው ለየት ያለ እና የክብር ምግብ ነው።አሳ፤ ጎመን በስጋ እና ቦርዴ እንዲሁ በአካባቢው የሚዘወተሩ ባህላዊ የምግብ አይነቶች ናቸው።
ሉል እና አሮድ የሚባሉ ከጨሌ የሚሠሩ የቤት ውስጥ መገልገያዎች እና የተለያየ ቅርጽ ያላቸው የገንፎ ማገንፊያ እንጨቶችንም ለማስተዋወቅ በቦታው ይዘው መገኘታቸውንም ትናገራለች።አውደርዕዩ የሌሎች ብሄሮችን እና ብሄረሰብ አባላቶችን ለመተዋወቅ ረድቷታል።
ወጣት ሚላን ከበደ ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የኦሮሚያን ባህላዊ አልባሳት ለብሳ፤ ምግቦቹንም ይዛ እና ባህላዊ የቤት አሠራሩንም ከጓደኞቿ ጋር ገንብታ በጊዮን የባህል ሳምንት አውደርዕይ ላይ ተሰይመዋል።
ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተለያዩ ብሄሮችን አልባሳት፤ የአመጋገብ ሥርዓት፤ የመገልገያ ቁሳቁሶች ፤ መጠጥ እና ባህላዊ የቤት አሠራር ዘዴን እንዲያሳዩ እድል እንደተሰጣቸው ወጣት ሚላን ትናገራለች።
በዚህም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የኦሮሚያ ባህላዊ አኗኗርን የሚያሳዩ እቃዎችን፤ የአረቄ አወጣጥ ሥርዓት ፤ ባህላዊ የመንደር ግንባታ እና የቀንድ ከብቶችን ይዞ መገኘቷን ትገልጻለች።
ሌሎች ክፍለ ከተሞችም እንዲሁ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ለማስተዋወቅ እንደመጡ እና ይህም ከተማ ላይ የተወለዱ ልጆች ትንሿን ኢትዮጵያ እንዲያዩ እድልን የፈጠረ መሆኑንም አብራርታለች፡፡
ኢስቲፋኖስ ግሪንስቲት (ዶ/ር) በአውደርዕዩ የተገኙ የስዊድን ሀገር ጎብኚ ናቸው።የመጡትም ስለ ኢትዮጵያ የሚያወራ መጽሀፍ ለመጻፍ ይረዳቸው ዘንድ ሀገሪቷን ለመጎብኘት ነው።
በቀጣይም በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ እና ይሄም 16ተኛ የባህል ሳምንት አውደርዕይ ምን ሊያዩ እንደሚችሉ በጥቂቱ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም