አዲስ አበባ፡- ነባሩ የፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድኃኒት ቫይረሱን በመላመዱ አዲስ መድኃኒት ማሰራጨት መጀመሩን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በኤጀንሲው በኤች አይቪ ቲቢና ወባ ግብዓቶች የግዢ ትምበያ ቡድን መሪ ወይዘሪት ፅዮን ፀጋዬ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን በመስጠት ላይ የነበረው የፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድኃኒት ቫይረሱን መለማመዱን በጥናት አረጋግጧል፡፡
ድርጅቱ 2018 ባወጣው የጤና መመሪያ “Nevirapine based Regimen” መሠረት ያደረጉ የፀረ ኤች.አይ.ቪ. መድኃኒቶች ወደ ‹‹Dolutegravin (50mg)›› መድኃኒቶች መቀየር እንዳለባቸው እንዲሁም “Efavirenz based Regimen” መሠረት ያደረጉ የፀረ ኤች. አይ. ቪ. መድኃኒቶች የታካሚውን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንዲቀየሩና የመጀመሪያ ምርጫ መድኃኒት እንዲሆኑ አቅጣጫ በማስቀመጡ፤ መመሪያውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አዲስ የፀረ ኤች. አይ. ቪ. መድኃኒት በማስመጣት ከሠኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለጤና ተቋማት በቀጥታ ማሠራጨት መጀመሩን የቡድን መሪዋ አስታውቀዋል፡፡
ወይዘሪት ፅዮን የተሻሻለው መድኃኒት በሠውነት ውስጥ ያለውን የቫይረስ መጠን እንደሚቀንስ ፤ቫይረሱን የመከላከል አቅምን (ሲዲ 4) እንደሚጨምር ፤ ከተለያዩ መድኃኒቶች ጋር ቢወሠድ ተቃርኖ እንደሌለውና የጎንዮሽ ጉዳቱ ከቀድሞው መድኃኒት የቀነሠ መሆኑን ገልፀው፤ከዚህ ቀደም ይሠጥ የነበረው መድኃኒት በሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ምክንያት ብዙ ታካሚዎች ያቋርጡ እንደነበርና የተሻሻለው መድኃኒት ይህንን ችግር እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ አሁን የቀረበውን ባለ 50 ሚሊ ግራም መድኃኒት አዋቂዎችና ከ20 ኪሎ በላይ የሆኑ ሕፃናት መውሠድ ይችላሉ፡፡ ከ20 ኪሎ በታች ለሚመዝኑ ህጻናት ከ50 ሚሊ ግራም በታች የሆኑ መድኃኒቶችን ለማቅረብ የአለም የጤና ድርጅት ከአምራቾቹ ጋር በመነጋገር ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም የተወሰኑ እናቶች በእርግዝና ወቅት በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት በጽንሱ ላይ የሚፈጠር የጤና ዕክል ስላጋጠማቸው በቂ ጥናት ተደርጎ እስኪረጋገጥ ድረስ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ስለሚታመን ከ1 እስከ 3 ወር የሚገኙ ነፍሰጡሮችና መውለድ የሚፈልጉ ሴቶች የተሻሻለውን መድኃኒት ፈጽሞ መጠቀም አይኖርባቸውም፡፡
መድኃኒቱ አዲስ በመሆኑ ህክምናውን ለማስጀመር እያንዳንዱ የጤና ተቋም ያለውን የታካሚ ብዛት መሰረት በማድረግ ከአንድ ወር በፊት አገልግሎቱን እየሰጡ ለሚገኙት 1400 የጤና ተቋማት መሰራጨቱን የገለጹት ወይዘሪት ፅዮን፤ ከዚህ በኋላ ግን ተቋማቱ አጠቃቀማቸውን እያዩ ጥያቄ ሲያቀርቡ በተለመደው መንገድ እንደሚሰራጭ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
የትናየት ፈሩ