አዲስ አበባ ፦ ብሔራዊ የሥራ እድል ፈጠራ ስትራቴጂው የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ለይቶ እንደሚያግዝ ተገለጸ፡፡
ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት የንግድ የልማት አማካሪ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ብሔራዊ የሥራ ፈጠራ ስትራቴጂ ሰነድ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደገለጹት፣ ስትራቴጂው የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ለይቶ ለመደገፍ የሚያግዝ ነው ፡፡
የአገሪቱ ትልቁ ጥያቄ የሥራ እድል መፍጠር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ አንጻር ስትራቴጂው የሚኖረው ሚና ብዙ ጊዜ በማህበር ሥራ እድል በመፍጠር ላይ ያጠነጠነውን አካሄድ በተለየ መልኩ የሚያስኬድና የፈጠራ ሃሳብ ያለውን ሰው ጠንካራ ድጋፍ በማድረግና የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት በሥሩ በርካቶችን እንዲያቅፍ የሚያደርግ፤ በዚህም ዘላቂነት ያለው የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በብሔራዊ ደረጃ የተዘጋጀው የሥራ ፈጠራ ስትራቴጂ በተለያየ መንገድ ሲከናወን የቆየውን ሥራ የተጠናና ውጤታማ ለማድረግ ከየት ተነስቶ የት ይድረስ የሚለውን ለመለየት እንዲሁም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ያቀናጀ በመሆኑ ውጤታማነቱ ከወዲሁ ያስታውቃል ፤በአሁኑ ወቅትም ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ትግበራ በሚገባበት ደረጃ ላይ ይገኛል እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
ሀብት የሚባለው መሬት፣ ውሃ፣ የሰው ጉልበትና ሌሎችም ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ግን እነዚህ ነገሮች በሙሉ ወይም በከፊል የሌላቸው አገራት የሥራ ፈጣሪ ሰዎቻቸውን በመጠቀምና በመደገፍ ከዜሮ ተነስተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ ኢትዮጵያንም በዚህ አካሄድ ተጠቃሚ ለማድረግ ስትራቴጂው ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሥራ እድል መፍጠር አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜያዊ ነው፤ ዘላቂ የሚሆነው ሥራ ፈጣሪ የሆኑ ወጣቶችን ለይቶ መደገፍ ሲቻል መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የብሔራዊ ፕሮግራም ኦፊሰር ና የተቋሙ ተወካይ አቶ አሰግድ አዳነ እንዳሉት አገሪቱ ላይ ያለው የሥራ እድል ፈጠራ በየዓመቱ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡትን ሥራ ፈላጊዎች የማዳረስ አቅም የለውም፤ በመሆኑም የሥራ ፈጠራ ሁኔታው የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ሌሎችንም በማስፋፋት መሸፈን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
እፀገነት አክሊሉ