
ከአምስት ዓመታት በፊት (በ2012 ዓ.ም) አሜሪካዊቷ ሞዴልና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂ አሽሊ ግርሃም ለልጇ ‹‹ምኒልክ›› የሚል ስም አወጣች፡፡ ምክንያት ስትባል ደግሞ በኢትዮጵያ ጥበባዊ ሥራዎች ስለተገረመች፣ ምኒልክ የጠቢቡ ስለሞን ልጅ ስለሆነ እና የእዚች ጥበበኛ ሀገር ንጉሥ ስለሆነ ነው አለች፡፡
ወዲያውኑ ግን አንድ አሳፋሪ ክርክር ተጀመረ። ክርክሩ፤ ቀዳማዊ ምኒልክን ነው ያለችው ወይስ ዳግማዊ ምኒልክን ነው ያለችው? የሚል ክርክር ነበር፡፡ ምናልባትም መረጃው ካልደረሳት ይሄን ጉዳችንን እንኳን ያልሰማች!
‹‹የትኛው ምኒልክ?›› የተባለበት ምክንያት ቅጥ ያጣ የብሔር ፖለቲካችን የፈጠረው ጣጣ ነው። ይሄኛው የእነ እገሌ ነው፤ ይሄኛው የእነ እገሌ ነው፤ የእኛ ይሄኛው ነው፣ እሱ የእነ እንትና ነው…. የሚል ኋላቀር አመለካከት ሥር ስለሰደደብን ነው። እነርሱ ‹‹ኢትዮጵያ›› ሲሉን እኛ ከፋፈልነው ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ ዓለም ‹‹ኢትዮጵያ የዓለም ሃያል ሀገር ናት›› ብሎ ቢመዘግብልንም እኮ አንስማማም ማለት ነው፡፡ ኃያል የተባለችው በአክሱም ነው፤ አይ አይደለም በላሊበላ ነው፤ በዳሽን ተራራ ነው፤ ኧረ ዳሎል ነው፤ በኮንሶ እርከን ነው፤ በሶፍ ዑመር ዋሻ ነው…. እያልን ልንከራከር እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ውበት የእነዚህ ድምር መሆኑን እየካድን ነው፡፡
ከዓመት በፊት በኬንያ አንድ የፍጥነት መንገድ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ስም ተሰይሞ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ የማስታውሰው በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ የነበረውን የአገዛዝ ሁኔታ በመጥቀስ ‹‹አይገባቸውም›› አይነት ይዘት ያለው ብሽሽቅ የሚያነሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ አፍሪካውያን የአፍሪካ አባት የሚሏቸውን እኛ ምንም አልመሰለንም ማለት ነው።
በዚህ አጋጣሚ ሰሞኑን የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ወደ ቀድሞ ስሙ ተፈሪ መኮንን መመለሱ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እንዲህ አይነት ሥራዎችንም ልናደንቅና ልናመሰግን ይገባልና ይበል ብለናል፡፡
እዚህ ላይ እንደ ሕዝብ ብልጥ መሆን አለብን። መሪዎቻችን ብዙ ችግሮች ሊኖሩባቸው ይችላሉ። ዳሩ ግን በውጭ የሚታወቁት በዓለም አቀፍ ሥራዎቻቸው ነው፡፡ እኛ ሀገር ውስጥ ያለውን ጉዳይ እያነሳን ካጣጣልን ብልጦች አይደለንም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የበፊቶቹ እንዲህ ነበሩ እያልን ከወቀስን ዓለም የሚታዘበን እኛን አሁን ያለነውን ትውልድ ነው፡፡ ሊታዘቡን ይችላሉ። በውጭ የሚከበሩ መሪዎቻችንን በውስጥም ማክበር ራሱን የቻለ የዲፕሎማሲ ብልጠት ነው፡፡
እንግዲህ ዓድዋ የዚህ ውጤት ነው፡፡ ዓድዋ ላይ ትልቅ ትርክት ልንገነባ ይገባል፡፡ እነሆ ላለፉት 129 ዓመታት ዓድዋ ሳይረሳ ገናና ሆኖ እየተከበረ ነው፡፡ የበለጠ ለማክበር ወኔ ይሆነን ዘንድ አንድ የተጨመረ ነገር ልብ እንበል፡፡
ዓድዋ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ አለፍ ሲልም የአፍሪካ ኩራት እየተባለ ይገለጽ ነበር፡፡ አሁን ግን የዓለም መሆኑ ጎላ ብሎ እየተነገረ ነው፡፡ ሰፋ አደረግነው ተብሎ ‹‹የጥቁር ሕዝቦች ኩራት›› ይባል ነበር፤ አሁን ግን ‹‹የሰው ልጆች›› ኩራት እየተባለ ነው የሚገለጸው፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያም፣ ከአፍሪካም፣ ከጥቁርነትም አልፎ የሰው ልጅን መብት ያስከበረ ድል ነው፡፡ በእርግጥ ነጮች ለጥቁር ንቀትና ጥላቻ ስለነበራቸው የጥቁሮችን ድል አድራጊነት በተለየ ሁኔታ ያስመሰከረ ነው፤ ያም ሆኖ ግን ዓድዋ የሰው ልጆችን ሁሉ መብት ያስከበረ የድል በዓል ነው፡፡ ለዚህም ነው ዓለም በገናናነቱ የሚያውቀው፡፡
በዚህ ዓመት በተደረገው 38ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞተሊ ስለዓድዋ ኃያልነት ተናግረዋል፡፡ ዓለም እዚህ ድረስ ያከበረው በዓል ነው ማለት ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም የተደረገውን 6ኛው ዙር ምርጫ አሸናፊው ብልፅግና ፓርቲ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም መንግሥት ሆኖ መመስረቱን ይፋ ሲያደርግ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበርና ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው መሪዎች ‹‹እናት ሀገራችን›› እያሉ ነበር ኢትዮጵያን የሚገልጿት፡፡ ‹‹እናት›› ማለት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚማሩት ከኢትዮጵያ ነው እያሉ ነው፤ ቀድማ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ናት እያሉ ነው፤ ችግር ቢያጋጥመን መሸሻ እና መጠጊያችን ኢትዮጵያ ናት እያሉ ነው፡፡
በቅርቡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተሠሩ ትንታኔዎችና ዜናዎች ነበሩ፡፡ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች ነው፡፡ ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ አብዛኞቹ ከጎረቤት ሀገራት የመጡ ናቸው፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታ ‹‹ኢትዮጵያ እናት ናት›› የሚለውን የመሪዎች ንግግር ከፖለቲካ ትክክለኝነት(Political Correctness) ያለፈ ሀቅ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከመሪዎች ንግግር በላይ በተግባር ታይቷል ማለት ነው፡፡
ለመሆኑ ዓለም እንዲህ ሲያከብረን እኛ ምን ላይ ነን? የሚለውን ማለት አለብን፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ብዙ ነገሮችን የምንታዘበው፡፡
‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ እኩል ነው›› እንደሚባለው ይህን ገናና አኩሪ ታሪክ በሚገባው ልክ እያሰረጽነው አይደለም፡፡ እስኪ አንድ ኃያል የሆነች የዓለምን ሀገር አስቡ! ይቺን ሀገር እንዴት ነው የምናያት? እንቀናባታለን፣ እንመኛታለን አይደል? ቅኝ የተገዙ ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ እዚያ ነው የሚያዩዋት! ስሜቱ ለእኛ አይገባን ይሆናል፤ እንዲያውም ይባስ ብሎ ‹‹ቅኝ ባለመገዛታችን ምን ተጠቀምን?›› የሚል ተሟጋችም ሊኖር ይችላል። ይህ ተሟጋች ይህ ስሜት የተፈጠረበት ከስጋዊ ጥቅም አንፃር ነው፤ የዚህ ደግሞ ምክንያቱ ድህነት ነው፡፡
ለአሁኑ ድህነት ተጠያቂው የአሁኑ ትውልድ ራሱ ነው፡፡ ቅኝ የተገዙ አገራት ከእኛ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው (ካላቸው) ቅኝ ስለተገዙ ሳይሆን ጠንክረው ስለሰሩ ነው፤ ኋላቀር የሥራ ባህላቸውን ስላሻሻሉ ነው፣ ከብሽሽቅና ንትርክ ወጥተው ሰላም ስለፈጠሩ ነው፡፡ በጦርነት ሀገራቸውን ከማውደም ይልቅ የሥራ ባህል አብዮት ስለፈጠሩ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር መዘርጋት ስለቻሉ ነው፡፡
በታታሪ የሥራ ባህልና በእርስ በእርስ መከባበር ብንይዘው፤ የዓድዋ ታሪክ ኢትዮጵያን የዓለም ልዕለ ኃያል የሚያደርግ የድል ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ላይ በጦር ኃይል ገናና ናቸው እያልን የምናሞካሻቸውን ሀገራት የሚበልጥ የድል ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ያህል ከዓለም ጋር ተዋግታ ያሸነፈች ሀገር(ለዚያውም በዚያን ዘመን) የለችም፡፡ በብዙ ዓመት ትግል ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጡ እንጂ መሬታችንን አናስረግጥም ብለው ገና ከጅምሩ ድል ያደረጉ የሉም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ የምታከብረው የነፃነት ቀን ሳይሆን የድል ቀን ነው!
የዓለም ሀገራት ሕዝቦችና መሪዎች እንደ ዓድዋ ባሉ ታሪኮቻችን እያከበሩን ነውና እኛም እርስ በእርሳችን እንከባበር!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም